ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ገበያው እንዴት ተጠቃሚ መሆን ይቻላል?

ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት ብቻ በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ መድረኮችን አዘጋጅታለች። በእነዚህ መድረኮች አያሌ ድርጅቶች፣ ሀገሮች፣ መሪዎች፣ ተዋቂ ሰዎች እንዲሁም ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች ወዘተ. ተሳትፈዋል። በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ብቻ ከ17 ሺ ሰዎች በላይ መሳተፋቸውን መረጃዎች አመላክተዋል።

እነዚህና ሌሎች ኮንፈረንሶች ለኢትዮጵያ በርካታ ፋይዳዎች አሏቸው፤ ከእነዚህ ፋይዳዎች መካከል ሀገሪቱ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

ኮንፈረንሶቹ በሀገሪቱ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታዎች ይፈጥራሉ ተብለው ታምኖባቸውም በስፋት እየተሠራ ነው። ኮንፈረንስ ቱሪዝም አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ ንዑስ ዘርፍ ሲሆን፣ በርካታ ሀገሮችም ከዘርፉ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም በእዚህ በኩል ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በስፋት እየሠራች ትገኛለች፡፡

በቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ የማይስ ዴስክ ኃላፊ አቶ ብዙዓለም ጌቱ ይህ ዓይነቱ የቱሪዝም ኮንፈረንስ ቱሪዝም ሲባል መቆየቱን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ማይስ ቱሪዝም እየተባለ እንደሚጠራ ይናገራሉ፤ የቢዝነስ ሁነት ኢንዱስትሪ ሲሉ የኢንዱስትሪው ሰዎች የሚጠሩበት ሁኔታ እንዳለም ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ማይስ ወይም የኮንፈረንስ ኢንዱስትሪ በአብዛኛው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ኮንፈረንሶች፣ የማበረታቻ ጉዞዎችን ፣ ኢግዚቢሽኖችን/ አውደ ርዕዮችን/ ያካትታል፡፡

በአብዛኛውም በኢኮኖሚ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ወይም ተጽእኖ ፈጣሪዎችን የማሳተፍ ባሕሪ አለው። ከግለሰቦች ይልቅ ቡድኖች በስፋት ይሳተፉበታል። ፉክክሩም አንድን ቡድን ማምጣት ሲሆን፣ በአብዛኛው የመንግሥታዊና በየነ መንግሥታት ስብስባዎች እንዲሁም የሙያ ማህበራት ስብሰባዎች ይካሄዱበታል። ኮርፓሬት ኩባንያዎችም እንዲሁ የኮንፈረስ ቱሪዝም ኢላማዎች ናቸው።

በዚህ ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፊት ለፊት ከሚጠቀሱት ሀገሮች መካከል ጀርመን አንዷ መሆኗን ኃላፊው ጠቅሰው፣ አሜሪካም በጣም ብዙ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ ትታወቃለች ይላሉ። ከኢሲያም ማሌዢያ ሲንጋፓር፣ ቻይና በእዚህ በኩል ወጣ ብለው ይገኛሉ ይላሉ። በሙያ ማህበርም እንዲሁ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካና ርዋንዳ እንደሚጠቀሱ አመልክተው፣ ሞሮኮም ግብጽም ኬንያም የእኛ ቅርብ ተፎካካሪዎች ናቸው ሲሉ ያብራራሉ።

በኮንፈረንስ ቱሪዝሙ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የመጀመሪያዎቹ አስፈላጊ ነገሮች የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ ከዚያ ደግሞ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መሠረተ ልማቶች እንደሚያስፈልጉም አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሌላው ኮኔክቲቪቲ ነው፤ ይህም ከብዙ አቅጣጫ ይታያል፤ አንዱ ለትራንስፖርት አገልግሎት ያለው ምቹነት ይሆናል። ይህም ከአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡር ትራንስፖርትና ከመሳሰሉት ጋር ይያያዛል፤ ሀገሪቱ የምትገኝበት ሥፍራም ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

ለዚህ ኢንዱስትሪ የመንግሥት ሚና ቁልፍ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። የኮንፈረሱ ተሳታፊዎች በቡድን ነው የሚመጡት፤ በሙያ ማህበራት፣ በሀገር ደረጃ የሚመጡ የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የደህንነት ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጠዋል፤ ይህን ለመጠበቅ የመንግሥት ሚና ከፍተኛ ይሆናል። በኮንፈረንሱ የሚሳተፉ አካላትን አግባብቶ በማምጣት በኩልም የመንግሥት ሚና በጣም ከፍተኛ ነው።

የርዋንዳ ተሞክሮ ይህንን ያመለክታል፤ በአፍሪካ እስከ እአአ 2014 ድረስ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ስሟ ያልተጠራ ርዋንዳ አሁን ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ የሙያ ማህበራትን ኮንፈረንስ በማስተናገድ ሁለተኛዋ ሀገር ለመሆን ችላለች። ይህን መድረክ በተከታታይ እያስተናገደችም ትገኛለች።

አንደ ኃላፊው ገለጻ፤ እነሱን የሚቀበሉ የሙያ ማህበራት ያስፈልጋሉ። ኮንፈረንሶቹን በማዘጋጀቱ ላይ የሀገራት የኢንዱስትሪ ልማት እድገትም ዋጋ አለው፤ የኢኮኖሚ አቅም ማሳያም ጭምር ነው። አሜሪካ የኮንቬንሽን ቢዝነስን የጀመረችው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። አሁን እኛ የኮንቬንሽን ቢሮ የምንለውን መጀመሪያ መጠቀም የጀመሩት አሜሪካኖች ናቸው።

ቱሪዝሙ ከዚያ በመቀጠል ወደ ኢሲያ ሄዷል፤ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ወደ ምስራቅ ሲያመዝን እነቻይና ማሌዢያ ሲንጋፓርና ኢንዲያ ቱርክ ወደ እዚህ ዘርፍ መሳተፍ ገብተዋል።

የኮንቬንሺን ሴነተር ቢዝነስን እንደ አጠቃላይ ካየነው ኢኮኖሚውን ጭምር ያሳያል፤ በተለይ ኢግዚቢሽን ቢዝነስ ከሆነ የሀገር ውስጥ ምርቶችንና ኢኖቬሽኖች የሚታዩበት ጭምር ተደርጎ ይወሰዳል።

ሌላው የማረፊያ ስፍራ ነው፤ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲሁም መዝናኛዎች በጣም ያስፈልጋሉ፤ አሁን በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው በጣም ያስፈልጋሉ ሲሉም ይገልጻሉ።

የኮንቬሽን ተሳታፊዎች ቀኑን ሙሉ ከስብሰባው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ነው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ያሉት ኃላፊው፣ ኢግዚቢሽን የሚያሳዩ ከሆኑም ኢግዚቢሽን ሲያስጎበኙ ይውላሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ ከዚያ ማምሻ ላይ መዝናናት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። በመሆኑም የመዝናኛ ወይም የማምሻ ስፍራዎች ለኮንቬሸን ማዕከል ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በኮንፈረስ ቱሪዝም የማበረታቻ ጉዞ የሚባል ነገር እንዳለ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በታሪካዊና በአድቬንቸር ቱሪዝም ላይ ነበር አተኩራ ትሠራ እንደነበር ጠቅሰው፤ ለማበረታቻ ጉዞ የሚያስፈልጉ ደረጃቸውን የጠበቁ በኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ የተገነቡት ዓይነት መሠረተ ልማቶች/ የሀይ ኢንድ ቱሪዝም ፕሮጀክቶች/ አልነበሯትም ሲሉ ያብራራሉ።

የትኛውም የቱሪዝም ምርት ከተፈጥሮ ጋር ተቃኝቶ ከተሠራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት አለው ሲሉም አመልክተው፣ የተጠቀሱት ቦታዎች አንደኛ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተገነቡ ናቸው፤ ሁለተኛ የትኛውም ሰው ከከባድ ከባቢ ወጥቶ የሚዝናናባቸው ቦታዎች ናቸው ይላሉ። ድርጅቶች ሠራተኞች እንዲዝናኑ ሲፈቅዱላቸው ወጪውን ችለው እንዲህ ዓይነት ቦታዎች ይልኳቸዋል ሲሉ ያብራራሉ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ሁሉ አንጻር ስትታይ እንደ ሀገር ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም፤ እንደ አዲስ አበባ ግን ለኮንፈረንስ ቱሪዝሙ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ሙሉ ለሙሉ እናሟለለን ብዩ አስባለሁ ሲሉ ኃላፊው አስታውቀዋል። የአፍሪካ ግንባር ቀደሙ፣ ከዓለም የመጀመሪያ ሃያዎቹ አየር መንገዶች መካከል ስንጠራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን ከፍተኛ ስፍራ ጠቅሰው፣ የምንገኝበት ጆግራፊካል ስፍራ ሌላው ብዙ ፋይዳው ያሉት ግብዓት ነው። የቪዛ ፖሊሲው በጣም መሻሻሉን፣ የኦን አራይቫል ቪዛ አገልግሎት መኖሩን፤ ለአፍሪካ ሀገሮች የተፈጠሩ ያለ ቪዛ መግባት የሚችሉበት ሁኔታም ለእዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከመሠረተ ልማት አኳያም አቅሙ ተገንብቷል። አፍሪካ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት ኮንፈረንሶች ከ500 አይበልጡም፤ በአማካይ ሲታይ ከ500 እስከ 1000 ይሆናሉ።

ኢትዮጵያ እነዚህ ማስተናገድ የሚችሉ የኮንፈረንስ ማዕከላት አሏት። ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኮንፈረንስ ማዕከል/ ኢሲኤ/ የአፍሪካ ሕብረት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እንዲሁም የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል አዳራሾችን ተሰብሳቢ የመያዝ አቅም ጠቅሰዋል። በኮንቬንሽን ማዕከል ደረጃ እነዚህ ይጠቀሱ እንጂ ሌሎች ትላልቅ ሆቴሎች እንዳሉም አመልክተዋል።

ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው ምን መጎብኘት ይችላሉ ብለን ካልን ደግሞ ለእዚህም የሚሆን አቅም አለ፤ ተፈጥሯል ሲሉ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ተሳታፊዎቹ ከስብሰባ በፊትና በኋላ የሚደረግ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፤ ወደ አንደ ሀገር ሲሄዱ የሀገሪቱን ማህበረሰብ ባሕል ለማወቅ ይፈልጋሉ፤ ልምድ ለመጋራት ይሻሉ። ለእዚህ ደግሞ አዲስ አበባ ብዙ አማራጮች አሏት፡፡

ገበያዎቿን፤ ባሕላዊ አልባሳትና ቁሳቁስ የመሸጫ ቦታዎችን መጎብኘት ይችላሉ። በቅርቡም ትንሿን ኢትዮጵያን የሚያመላክተው አንድነት ፓርክ ተፈጥሯል። የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎች ናቸው ሲሉም አመልክተዋል። የኮሪደር ልማቱ የፈጠራቸው ምቹ ሁኔታዎችንም ጠቅሰዋል፤ ተሳታፊዎች ስካይላይት አርፈው ከሆነ ከስብሰባ ውጭ በእግራቸው እስከ መስቀል አደባባይ ቢፈልጉ እስከ አራት ኪሎ ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም አመልክተዋል።

አገልግሎት በሚሰጡ ድርጅቶች በኩልም እንዲሁ የተመቻቸ ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፣ በሀገሪቱ ከኢትዮጵያ አልፎም ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገድ የሚችሉ ድርጅቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳመለከቱት፤ ሌላው የሚያስፈልገው የሆቴል አገልግሎት ነው። በዚህ በኩልም በቂ አቅም አለ። ስካይላትን ብቻ ብንወሰድ ከ1000 በላይ የመኝታ ክፍሎች አሉት፤ በዚህም አንድ ኮንፈረንስ ራሱ ጀምሮ ራሱ ሊጨርስ ይችላል።

በሀገሪቱ የሆቴል ችግር የለም፤ በርካታ ጥራታቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አሉ። በአዲስ አበባ ብቻ ከ20 ሺ በላይ አልጋዎች ስለመኖራቸው ጥናቶች ያመለክታሉ። እናም በሆቴል አልጋዎች በኩልም ኮንፈረንሶችን ለማዘጋጀት አቅሙ አሉ።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንደ ሌላው የቱሪዝም ዘርፍ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ዜጎችንና ሀገርን እንደሚጠቅምም ኃላፊው አስታውቀዋል። ተጠቃሚነቱ በተለያየ መልኩ እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶቹ ኮንፈረንሶች ለተሰብሳቢዎች ጎን ለጎን ጉብኝት ያመቻቻሉ፣ ከዚህ በተጨማሪ እውቀት ይዘው መጥተዋል፤ በመሆኑም እንደ ኢኮኖሚ መሳሪያ ይታያሉ፤፡ መንግሥትም እዚህ ላይ ያተኩራል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የውሃ አቅርቦትን ለአብነት ወስዶ ማየት ቢቻል በእነዚህ ጉባኤዎች ወቅት በፊት ያስፈልግ ከነበረው በላይ ውሃ ያስፈልጋል። ይህን ፍላጎት ለማሟላት ይሠራል፤ በእዚህም በቀጥታ ገንዘብ ሊገኝ ይችላል። ሰዎች ግን በተለያዩ ደረጃዎች በተዘዋዋሪ መልኩ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በእዚህ ወቅት እንግዶችን የመቀበልና የመሸኘት ሥራ ተጨማሪ ሥራ ይዞ ይመጣል። በቲፕ፣ በአገልግሎት ክፍያና በመሳሰሉት ሠራተኞች ይበልጥ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። እነሱ የተለያዩ ነገሮችን ሲሸምቱ ደግሞ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከዚህ ባሻገር ደግሞ የእነዚህ ሁነቶች ትልቁ ጥቅም ሀገርን ማስተዋወቅ፣ ገጽታን መገንባት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቱሪዝም ይበልጥ ለመጠቀም ምን መሠራት አለበት የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊው በሰጡት ምላሽ ‹‹የሁነቶች የተጽእኖ /የኢምፓክት/ ትንተና ሊሠራ ይገባል›› ሲሉ አስገንዝበዋል።

ኃላፊው እንዳብራሩት፤ ሁነቶቹ በፍጹም ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን ማረጋገጥም ይገባል። ሆቴሉ በአግባቡ አገልግሎት መስጠት አለበት፤ የቴክኖሎጂው ትእይንት ከሆነም ቴክኖሎጂውን እንዲታደሙ የምንፈልጋቸው የነገው ትውልድ ተረካቢዎች እንዲታደሙ ማድረግ ይገባል። ኢኖቬሽንም ከሆነ እንደዛው ነው። ከትምህርቱም አኳያ ኢንጂነሪግ ላይ የሚካሄድ ከሆነ እውቀትን በአግባቡ መያዝ ያስፈልጋል።

ሁነቶቹን በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበው፣ መሰል ሁነቶችን በውጭው ዓለም ከፍለን ነው ማግኘት የምንችለው፤ በእኛ ሀገር ግን ይህ ምቹ ሁኔታ እንደ ስብሰባ ይታያልና በእዚህ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

ሴሚናሮችን በሚገባ ማዘጋጀት /ዴቨሎፕ/ ማድረግ ላይ መለማመድ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ ያሉት አቶ ብዙዓለም፣ ከዚያ ውጪ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የሚፈልጓቸውን ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ጎን ለጎን መካሄድ ያለባቸው ሁነቶች ላይም በጥንቃቄ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ተሰብሳቢዎቹ ወይም ተሳታፊዎቹ ቀኑን ሙሉ ባተሌ ሆነው ይውላሉ። ትርፍ ጊዜ የሚያገኙት ምሽት ላይ ብቻ ነው። ስለዚህ ምሽት ላይ ጉዞዎችንና ጉብኝቶችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። ብሄራዊ ሙዚየም በምሽት መጎብኘት የሚችልበት እድል መፈጠር ይኖርበታል፤ ምርጥ የተባሉትን የሀገሪቱ የቱሪስት መስህቦች የሚጎበኙበት ሁኔታም እንዲሁ መመቻቸት ይኖርበታል።

የሙዚየም የሥራ ሰዓት ትንሽ ገፋ ተደርጎ ከስብሰባ ሲወጡ እንዲጎበኙት ቢደረግ ጥሩ መሆኑን አመልክተዋል። አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በምሽት በጣም ጥሩ ሆናለች ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህን የከተማዋን ገጽታ እንዲያዩ በቅድሚያ ከአስጎብኚዎች ወይም አገልግሎቱን ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር ትስስር ፈጥሮ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም አስታውቀዋል።

አንድነት ፓርክን ጨምሮ ሌሎች መዳረሻዎች በምሽት የሚጎበኙበት ሁኔታ ቢፈጠር ሰዎቹ ከስብሰባ እንደወጡ ሊጎበኟቸው ይችላሉ፤ አቶ ብዙዓለም በእነዚህ ላይ መሠራት አለበት ብለው ያስባሉ። ሆቴሎችም ቆይታቸውን ውብ በሚያደርግ ሥራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ ተሳታፊዎቹ ደግመው እንዲመጡ ማድረግ የሚያስችል አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት።

በግሌ ቱሪስቱ ወይም ተሳታፊው የያዘውን ዶላር ሁሉ መቀበል ይገባል ብዬ አላምንም ሲሉም ጠቅሰው፤ ከዚህ ይልቅ በተደጋጋሚ እንዲመጡ ማድረግ ላይ መሠራት ይኖርበታል ይላሉ። ኢስያ ላይ የሆቴል አገልግሎታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ በመስጠት ተመላልሰው እንዲገለገሉባቸው ያደርጋሉ፤ የጎብኚው በተደጋጋሚ ወደ ሆቴሎቹ መሄድ ትልቅ ዋጋ አለው፤ ቋሚ ደንበኛ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

ለእዚህ ሥራ የሚያስፈልጉ ተቋማት ተቀናጅቶ መሥራትም ሌላው ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ብዙዓለም፣ ከቪዛ ጀምሮ ከአውሮፕላን ማረፊያ ከጸጥታ አካላት፣ ከማህበረሰቡና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የሚደረገው የተቀናጀ ሥራ ይበልጥ መጠናከር አለበት ሲሉም መክረዋል።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You