
አዲስ አበባ፡- የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችል የራሱን ሶፍትዌር አልምቶ በሙከራ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የባለሥልጣኑ የብቃት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግስት በዳዳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የአዲስም ሆነ የነባር የጤና ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ በኦላይን ብቻ ለመስጠት ከጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ የማላመድ ሥራ እየሠራ ነው፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በኦንላይን የሚሰጠው አገልግሎት በቀላሉ ሊሞላ የሚችል ከመሆኑ በተጨማሪ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ውድ የሆነውን የጤና ባለሙያዎች ጊዜ የሚቆጥብ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሙከራ ትግበራው መስተካከል የሚገባው ተስተካክሎና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ከተሻሻሉ በኋላ ሶፍት ዌሩን ካለማው አካል ጋር ርክክብ በማድረግ ወደ ሙሉ ትግበራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመግባት በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ትዕግስት የኦንላይ አገልግሎት መስጫው በሙከራ ደረጃ የተስተዋሉበትን ተግዳሮትች ሲጠቅሱ፤ የጤና ሚኒስቴር እና የባለሥልጣኑ የአይቲ ባለሙያዎች ተናቦ የመሥራት ክፍተት አንዱ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ችግሩን ለማስወገድና የተሳለጠ የትብብር ሥራ እንዲኖር በሥራ ኃላፊዎች ደረጃ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በተገቢው ሁኔታ የሚፈታ ይሆናል ብለዋል፡፡
የነባር የጤና ባለሙያዎች ፋይል ሙሉ ለሙሉ እስካን ሆኖ አለመጠናቀቁም ባለጉዳዮች በአዲሱ ሲስተም ወዲያው አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ አድርጓል ብለዋል፡፡ ይህን ተግዳሮት ቀደም ሲል ሲሠራበት በነበረው መንገድ በከፊል ኦንላይን ሲስተም እንዲስተናገዱ በማድረግ መፍታት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ተግዳሮት ሊሆን ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ አዲስ የለማውን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ባለሥልጣኑ እየተጠቀመባቸው ባሉት የአይቲ መገልገያ ግብዓቶች በሚገባው ልክ ማስቀጠል አለመቻሉ ተገምግሟል። ለዚህም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለፋይናንስ ቢሮ በልዩ ሁኔታ ተገቢው ብቃት ያላቸው ግብዓቶች ግዢ እንዲከናወን ተጠይቋል፤ ወደ ሙሉ ትግበራ ሲገባ እንደአስፈላጊነቱ እየታየ ግብዓቶቹን የመቀየር ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
የተጀመረው የኦንላይን ሲስተም ስማርት ስልክ ያለው ተገልጋይ በቀላሉ ራሱ አገልግሎቱን ሊያገኝ በሚችልበት መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፤ አገልግሎቱ ሙሉ ለሙሉ መተግበር ሲጀምር ደንበኞች አገልግሎቱ በኦንላይን ብቻ License.aafda.gov.et በሚለው ፖርታል የሚሰጥ መሆኑን በመረዳት ባሉበት ስፍራ ሆነው ለመስተናገድ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል፡፡
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም