“የወል ትርክት በሌለበት በነጠላ ትርክት ሀገር ለመገንባት መሞከር ውጤቱ መበታተን ነው” – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

ሁለተኛው የብልፅግና ጉባዔ መጠናቀቅን ተከትሎ ክልሎችም በየደረጃው ውይይቶችን በማካሔድ ላይ ናቸው። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተሠራውን ሥራ በማስመልከት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዶ የወቅታዊ እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- ከሳምንታት በፊት ብልፅግና ፓርቲ ጉባኤውን ማካሄዱ ይታወቃል፤ ፓርቲው እንደ ሀገር ያመጣው ለውጥ ምን ይመስላል?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- ሁለተኛው የብልፅግና መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ተከናውኗል። በዚያ ጉባኤ ላይ የታዩት ሶስት ዋና ዋና ነገሮች ናቸው፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ባለፍንበት ስድስት ዓመት የነበረው የለውጥ ሂደት ከምን ተነስቶ ምን ደርሷል? የሚለው ጉዳይ በጥንካሬም በጉድለትም የፈተሸ ሲሆን፣ ለወደፊትም መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮችንም አይቷል። በአንደኛው የብልፅግና መደበኛ ጉባኤ ያስቀመጣቸው ውሳኔዎችና ሃሳቦች መፈጸም አለመፈጸማቸውን ገምግሟል። የሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ምንድን ናቸው? የሚለውን ጠቁሟል። በመሆኑም ሁሉን ነገር ማየት የምንችለው በዚህ ውስጥ ነው።

ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት የሠራናቸው ሥራዎች አሉ። በሠራናቸው ሥራዎች ውስጥ የታዩ ጉድለቶች አሉ። ለወደፊት ደግሞ መድረስ የምንፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ። ማሕቀፉ የሚያርፈው በዚህ ውስጥ ነው።

ባለፍንባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁልጊዜም መነሳት ያለባቸው ሶስት ዋና ነገሮች ናቸው። ሁሌም ቢሆን በየአጀንዳዎቻችን ሳንረሳ እያስታወስን መሥራት ያለብን ነገር ቢኖር አንደኛው ሰላም ነው። ሁለተኛው ደግሞ ልማት ሲሆን፣ ሶስተኛው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ነው።

ከሰላም አኳያ እንደሚታወቀው መንግሥት ለውጡን ተከትሎ ሁሉም አካል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርጓል፤ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶች የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሲሆኑ፣ አንዳንዶች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ እድሜ ልካቸውን መግባት የማይችሉ ናቸው፤ እንደዚያ ሆኖ ሳለ እንኳ ሁሉም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ በተደረገላቸው መሠረት ገብተውም በሰላም እንዲኖሩ መደረጉ የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖረን የሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ የብሔረ መንግሥት ግንባታ እና የተቋም ግንባታ ውስጥ እኩል አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ ተደርጓል። ይህ የተደረገው ሁሉንም ሰው ለማሳተፍ የተደረገ ነው። አንዱ እና መሠረታዊ ለውጥ የሚባለው ምኅዳሩን ማስፋትና ሁሉም ሰው ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን፣ ይህ በየትኛውም ጊዜያት ያላየነው ጉዳይ ነው። ሁለተኛው ደግሞ መንግሥታችን የሚከተለው ሪፎርም ስለሆነ አጠቃላይ ሁሉን ነገር ከስር መሠረቱ አልናደም። ሶስተኛውና ዐብይ የሚባለው ከነበሩ ነገሮች የሚጠቅሙ ነገሮች መውሰድ መቻሉ ነው። መንግሥት ሁሉንም በዜሮ አላጣፋም።

በአጼ ኃይለሥላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ ከተሠሩ ሥራዎች መልካም የሆኑትን ወስደናል፤ አሁን ደግሞ አዳዲስ ሃሳቦች ለመጨመር ጥረት ተደርጓል። ወደፊት ሊወስደን የሚችለውን ሃሳብ በጥናት እና የዓለም አቀፍ ሁኔታን በመተንተን የምንጨምርበት ይሆናል። ከዚህ መካከል አንደኛው ምኅዳርን ማስፋት ነው። የዓለም አቀፍ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ የሚገባ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በልማትም ትልቅ ለውጥ መጥቷል።

እንደሚታወቀው አንዳንድ ቦታ ላይ ችግር አጋጥሞናል፤ አንደኛው የህልውና ጦርነት ነበር፤ ይሁንና በአንድ እጃችን ጦርነቱን እያካሔድን በሌላኛው እጃችን ደግሞ ልማቱን እያካሔድን ያንን ጊዜ ማለፍ ችለናል። በዚህ የተነሳ በጦርነትም ውስጥ ሆነን የሀገሪቷ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ከስድስት ነጥብ ሁለት፣ እስከ ስድስት ነጥብ ሰባት በመቶ የተጓዘ ነው። ይህን የምንመሰክረው እኛ ብቻ አይደለንም፤ በዘርፉ ዙሪያ ያሉ ዓለም አቀፍ አጥኚዎች የመሰከሩት ጭምር ነው።

ጦርነት ውስጥ ባንሆንና በአሁኑ ወቅት በአማራ፤ በተመሳሳይ ኦሮሚያ ላይ የነበረው ችግርም ባያጋጥመን እንዲሁም በአንዳንድ ክልሎች ኪስ ቦታዎቻቸው ላይ የተፈጠሩ ችግሮች ባያጋጥመን ኖሮ የት እንደርስ ነበር የሚለውን ደግሞ በቀላሉ መገመት የሚያዳግት አይሆንም።

ስለዚህ በዚህ ውስጥ ሆነን የሰራናቸው የልማት ሥራዎች በጣም ሰፊ ለውጥ አላቸው፤ ይህ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ኢንሼቲቮች አስገብተናል። ለአብነት ያህል የስንዴ፣ የሩዝ፤ የሌማት ትሩፋት፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለሸገር፣ አረንጓዴ ዐሻራ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች በጣም ብዙ ናቸው።

በኋላ ላይ ውጤቱን የምንጠቀመው እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለንም፤ በተለይ ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር ተያይዞ አፍሪካውያንም ጭምር ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥራ ነው። ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ደን ነው የሚባለው በደቡብ አሜሪካ ውስጥ የሚገኘው አማዞን ነው። አማዞን ለረጅም ጊዜ እንክብካቤ ስለተደረገለትና ስለተጠበቀ የዓለምን የአየር ጸባይ በማስተካከል በኩል የራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከልነው ችግኝ ወደ ስምንት ቢሊዮን ነው። ስምንት ቢሊዮን ማለት የዓለም ሕዝብ ቁጥር ነው። ይህ ማለት ደግሞ የዓለም ሕዝብ እያንዳንዱ አንዳንድ ችግኝ ተክሏል እንደ ማለት ነው። እነዚህ ኢትዮጵያ የተከለቻቸው ችግኞች የመጽደቅ ምጣኔያቸው እንደየቦታው ይለያይ እንጂ በአማካይ ሲወሰድ 94 በመቶ ነው። ይህን ተንከባክበን ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ካደረስነው የአየር ጸባያችንን በማስተካከል፣ ለቱሪዝም የሚሆኑ ቦታዎችን በመለየት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ሌላው ትልቅ ለውጥ ያለው ትርክታችንን ማስተካከል መጀመራችን ላይ ነው። ትርክት ማስተካከል ሲባል እንደሚታወቀው በኢትዮጵያዊነትና በብሔር መካከል የነበረው ትርክት ወደ ብሔር አድልቶ ነበር። እናም ምንም ነገር ሲያጋጥም ሰው ሮጦ የሚሸጎጠው ወደ ብሔሩ ጉያ እና ወደ ሃይማኖቱ ነበር። መነጋገር ይሉትን ነገር አይሻም፤ በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የማድረግ ፍቃደኝነት የለውም። ብሔሩንና ሃይማኖቱን ምሽግ አድርጎ ጸብ ይፈጥራል፡ ማኅበረሰብ ከማኅበረስ ጋር መቀባበል እንዳይኖርና ይታትራል።

ወደ አንዱ ብቻ እንዳያመዝን ሁለቱም ሚዛናቸውን በጠበቀ መንገድ እንዲሔዱ ማድረግ ይቻላል። እንዲያም ሆነ የመጨረሻው ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር ነው። እኛ ወደ ሌላ ሀገር ስንሄድ በብሔር ማንም አያውቀንም። የሚያውቁን በኢትዮጵያዊነታችን ነው። ከዚህ ሀገር የመጣ ዜጋ እንባላለን እንጂ ጉራጌ ነው፤ አማራ ነው፤ ኦሮሞ ነው፤ ወይም ትግሬ ነው በሚል ደረጃ አያውቁንም።

ስለዚህ ይህ ሁኔታ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ለማድረግ የብልፅግና መንግሥት አይደፈሬ የሆነውንና ለበርካታ ዓመት በልምምድ ደረጃ ያደገውን ይህን አጀንዳ ለማስተካከል የተሠራው ሥራ ጥሩ ነው።

ሌላው ትልቁ ለውጥ የመሀል መንገድ መምረጥ ነው፤ እንዲህም ሲባል ወደ ወደዚህ አሊያም ወደዚያ መወጠር አያስፈልግም። መሃል መንገድ በመያዝ ማዕከላዊ መሆን ወሳኝ ነው። የምንም ነገር አክራሪነት አይጠቅመንም። የሃይማኖትም፤ የብሔርም አክራሪነት አይጠቅመንም። ሁሉን የሚያስተናግድና ሁሉን የሚያማክል ሃሳብ ኖሮበት፤ ነገር ግን መሃል መንገድ ከወዲህም ከወዲያም ያለ ሃሳብ ካለ የሚወስደውን ሃሳብ ለመያዝ ተሞክሯል። ይህ በፖለቲካው መስክ ትልቅ ለውጥ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ነገር በአምስት ዓመትና በስድስት ዓመት ውስጥ አይመጣም።

ሌላው የተደረገ ጥረት ሀገሪቱን የምንመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ በአጭር ጊዜ መቀመጡ ነው። ብልፅግና ካለው ማኒፌስቶ ተነስቶ ከማኒፌስቶው የሚቀዱ ስትራቴጂክ ፖሊሲዎች አሉ። ከበፊቱ የወሰድናቸው አሉ፤ አሁን ደግሞ አዳዲስ ነገሮችንም ለማስገባት ተሞክሯል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችለው ከ1983 እስከ 1987 ዓ.ም ኅዳር ወር ድረስ የሽግግር መንግሥት ነበር። በዚህ ወቅት ሀገር የተመራው ስትራቴጂ ሳይኖር ነው። ከዚያም በኋላ የመጀመሪያው ተሃድሶ እስከሚከናወን እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ ይህች ሀገር ፖሊሲና ስትራቴጂ አልነበራትም። ሀገር ይመራ የነበረው በተቋማትና በቢሮ እቅድ ነበር።

ይህን በማሰብ በአሁኑ ወቅት ብልፅግና በሁለት፣ በሶስትና አራት ዓመት ትልልቅና ሀገርን ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ቀርጿል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው ብሎ መውሰድና ማጎልበት መልካም ነው።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ነገር ሲታይ የተገላቢጦሽ እንዳይመስል፤ ለምሳሌ ከሰላም አኳያ አንዳንድ ቦታ ችግር አለ። ችግር ያለብን ሁሉን ቦታ ማስጠበቅ ስላልቻልን አይደለም። ሁሉንም ቦታ ያለውን ነገር ክፍት ስላደረግን ነው። ሰው በነፃነት እንዲሳተፍ ስላደረግን እንጂ ከመጀመሪያ ጀምሮ እነዚህን ነገሮች ዝግት አድርጎ በመሳሪያና በሕግ የሚሠሩ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል፤ ነገር ግን በትንሹም ቢሆን የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ ውስጥ ሲገባ የሚተው ክፍተቶች አሉ። በዚህ መካከል ደግሞ የምንከፍላቸው መስዋዕትነቶችም አሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ መንግሥትም ሕዝብም የሚከፍላቸው መስዋዕትነቶች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- ብልፅግና ፓርቲ በመልካም አስተዳደር ላይ እንደማይደራደር በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤው ማጠናቀቂያ ባወጣው የአቋም መግለጫ ጠቁሟል፤ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ምን ታስቧል?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- ትክክል ነው፤ መልካም አስተዳደር የሁሉ ነገር መቋጫ ነው። መልካም አስተዳደር በውስጡ አገልግሎት አሰጣጥ አለው፤ ሌብነትን ለመከላከል የሚደረግ ትግል አለ፤ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት በሚያከናውናቸው ነገሮች ግልጽኝነትና ፍትሐዊነት አለ። ከዚህ የተነሳ መልካም አስተዳደር ሲባል በጣም ሰፊ የሆነ ሃሳብ ነው።

ነገር ግን አንዱ የመልካም አስተዳደር መገለጫ የሆነውን የአገልግሎት አሰጣጥን ብናነሳ የአገልግሎት አሰጣጡ በጣም ጥሩ ነው ብሎ ኅብረተሰቡ አላነሳም። የሚናገረው መንገላታቱን ነው። የሚገልጽልን በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚቀራችሁ ነገር አለ በሚል ነው።

የብልፅግና መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተለያየ ጥናት አድርጎ በእያንዳንዱ ክልል የተለያዩ ሴክተሮች ላይ የሚታይ ችግር መኖሩን አጢኗል። ለምሳሌ ያህል እንደ መሬት አስተዳደር፣ የግዥ ሥርዓትና መሰል የሰው ምልልስ የሚበዛባቸው ተቋማት ሙስና የሚስተዋልባቸው ቦታዎች ናቸው። እነዚህ ላይ ጥናት ተደርጎ ሥራ እየተሠራ ነው።

ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሌሎች ሀገሮችን ልምድ ስናጤን ችግሩ የሚዘጋው በሥርዓት ነው። መዋቅራዊ ለውጥ እስካላመጣን ድረስ እና ተቋም እስካልገነባን ድረስ እነዚህ ነገሮች አይስተካከሉም። ለምሳሌ እንደ አሜሪካ ዓይነት ሀገሮችን ብንወስድ ሥርዓት ገንብተዋል። አንድ ሰው አንድ አገልግሎት ሲፈልግ ከባለሙያው ጋር አይገናኝም። በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት አገልግሎቱን ያገኛል፤ ላገኘው አገልግሎት ደግሞ ክፍያውን በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት ይከፍላል።

እኛ ዘንድ ግን በአሁኑ ወቅት እንደ እሱ ዓይነት ሥርዓት አልተገነባም፤ ዛሬም የእጅ ንክኪ አለ፤ በመሆኑም ሰው ከሰው ይገናኛል። ሕጋዊ የሆነ መብቱን ለማግኘት ክፍያ ተጠይቆ የሚስተናገድበት ዘርፍ አለ። ይህ መታረምና መስተካከል አለበት። ከሕዝብ የሚለየን ይህ ዓይነቱ አሠራር ነው። ይህን ችግር ለማረም የአንድ ወገን አሠራር ብቻ በቂ ባለመሆኑ ሠራተኛውም አመራሩም ሆነ ሕዝቡ በጋራ ሲተጋገዝ የሚፈታ ይሆናል። የሁሉም ትብብር ችግሩን እንዲቀንስ ያደርገዋል። በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚታየውን ችግር ለመቀነስም እየተሠራ ነው። መንግሥት ዘንድ ሆነ ማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው አቋም ጥብቅ ነው። ሁለተኛው የብልፅግና መደበኛ ጉባኤም ካስቀመጣቸው ጉዳዮች አንዱ በመልካም አስተዳደር እጦት የሚፈጠሩ ችግሮችን እናስተካክል የሚል ነው።

የፌዴራል መንግሥት የሚያስቀምጣቸውን አቅጣጫዎች የክልል መንግሥታትም የሚተገብሩት ነው፤ እንዲያውም መሬቱም ሆነ አገልግሎቱም ያለው ክልል ላይ እንደመሆኑ አብዛኛው ችግር ያለው ክልል ላይ ነው። ይህን ለማስተካከል በየደረጃው ያለው አመራር የጉባኤው አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እያደረገ ነው። እንደ ክልልም ከአባሎቻችን ጋር ተወያይተናል። እሱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሕዝብ ጋር ውይይት እንካሂዳለን። የጉባኤውን አቅጣጫ ሁሉ ሰው በግልጽ ካወቀው በኋላ በጋራ የምንተገብረው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የወል ትርክትን እንደ ሀገር የመገንባቱ ጅማሮ እንዳለ ይታወቃል፤ በእስካሁኑ ሂደት እያመጣ ያለው ውጤት እንዴት ይገለጻል?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- የወል ትርክት ሁሉ ሰው የሚግባባበት ጉዳይ ነው። የወል ትርክት ማለት የሁሉም ሰው የሆኑ አጀንዳዎች እንደ ማለት ነው። እነዚህ አጀንዳዎች ሲነሱ የሁላችንንም ስሜት መኮርኮር የሚችሉ ዓይነት የሆኑ ናቸው። በአሁኑ ወቅት እያሰቃየን ያለው ነጠላ ትርክት ነው። ነጠላ ትርክት ደግሞ አንድን አካባቢ የሚያገዝፍ ነው። ለሌላው እምብዛም ትኩረት የሚሰጥ አይደለም። በርግጥ የሚያስፈልጉ ነጠላ ትርክቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ዋናውና ሊያስተሳስር በሚችለው በገዥ ትርክት ዙሪያ ትኩረት መስጠቱ አስፈላጊ ነው።

አሜሪካውያኑ “አሜሪካ ፈርስት” እንደሚሉ ሁሉ እኛም ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ነገር ላይ መሥራት ይኖርብናል። እንደሚታወቀው በአሜሪካ የተለያዩ ፕሬዚዳንቶች በየወቅታቸው ሀገሪቱን ሲያስተዳድሩ፤ ሁሉም በወል ትርክታቸው ውስጥ አይነኬ የሚባሉ ጉዳዮች አሏቸው። እነዚያን የወል ትርክቶች በፍጹም አሳልፈው የሚሰጧቸው አይደሉም። ልክ እንደ አሜሪካ ተመሳሳይ ነገርን ለመገንባት ሂደት ያስፈልጋል።

በእኛ በኢትዮጵያውያን እስካዛሬ ድረስ በውስጣችን ያሉ በርካታ ነጠላ ትርክቶች አሉ። ይህን ማስተካከል ይፈልጋል። በትውልዱ አዕምሮ፤ በትምህርቱም መስክ የገቡ ነጣጣይ ትርክቶችን ማስተካከል ያሻል። በሃይማኖቱም ውስጥ የገቡ ደባል ነገሮችን ማስተካከል ያስፈልጋል።

ይህን ካደረግን በኋላ የወል ትርክቶችን በአግባቡ የሚስተናገዱባቸው ቦታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የትምህርት ተቋም፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ እና የሲቪክ ማኅበራት ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ አደረጃጀቶች የወል ትርክት በፍጥነት ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ የራሱን ሚና እንዲጫወት ማድረግ ይችላሉ።

የወል ትርክት አለን? የለንም? የሚል ነገር ሊነሳ ይችላል። በርካታ የወል ትርክቶች አሉን። እነርሱን ልቅም አድርጎ ማውጣት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በየቦታው የሰበሰባቸው አጀንዳዎች አሉ። እነዚያም መጨረሻ ላይ ሲጠናቀቁ የተስማማንባቸው ጉዳዮች የወል ትርክት ሆነው ይቀጥላሉ።

የወል ትርክት ሆነው ከቀጠሉ በኋላ በሕገ መንግሥት አሊያም በአንዳች ነገር ካስቀመጥናቸው በኋላ ሁሉም ለዚያ አጀንዳ መሳካት ይሮጣል። ይህ ሲሆን በየአካባቢው የሚስቡን ነገሮች በራሳቸው ጊዜ የሚንጠባጠቡና የሚከስሙ ይሆናሉ። የወል ትርክት በሌለበት ሀገር፤ በነጠላ ትርክት ሀገር ለመገንባት መሞከር የመጨረሻ ውጤት የሚሆነው መበታተን ነው። ስለዚህ የያዝነው የሚያዋጣንን አጀንዳ ነው። በዚህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ ሥራ ይሠራል። አድካሚና አልፊ ነው። ነገር ግን ሌላ ምንም አማራጭ የለንም። በመሥራት በሂደት የወል ትርክትን እየገነቡ መሔድ ያስፈልጋል። የሀገረ መንግሥት ግንባታም ከወል ትርክት ውጭ አይሆንም።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ኢትዮጵያን ከተረጂነት በማላቀቁ ረገድ ምን እየተሠራ ነው?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- በመጀመሪያ የተረጂነትን ትርጓሜ መረዳቱ ተገቢ ነው። ተረጂነት ማለት ሉዓላዊነትን የሚያሳጣ እንዲሁም የሀገር ደኅንነትን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ ነው። በእስካሁኑ ሂደት በተለያየ መንገድ ስንረዳ መጥተናል። ሀብት ለመፍጠር አልሞከርንም። የፈጠርነውም ሀብት ቢሆን በተለያየ ጊዜ ባጋጠመን ጦርነት ወድሟል። ስለዚህ የተወሰነው የማኅበረሰባችን ክፍል ተረጂነትን ሲለማመደው ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ለምሳሌ የእኛን ክልል ብጠቅስ 65 በመቶ ተረጂነት የነበረባቸውን አካባቢዎች ነፃ አድርገናል። ምንም የፈጠርነው ነገር የለም፤ ነገር ግን ሰዎቹ ያላቸውን መሬት በአግባቡ እንዲያርሱና “አምስት፣ አስራ አምስት፣ ሃያ አምስት” የሚል የዶሮ መርሃ ግብርን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማድረግ ነው። እንዲህም ሲባል አምስት ዶሮ በመጀመሪያው ዓመት፤ አስር ዶሮ በቀጣዩ ዓመትና ሃያ አምስት ዶሮ በቀጣዩ ዓመት አርብተው እንቁላሉን በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

በሌላ በኩል “ሰላሳ፣ አርባ፣ ሰላሳ” የምንለው የአትክልት መርሃ ግብር አለን። እንዲህም ሲባል በመጀመሪያው ዓመት ሰላሳ፣ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ አርባ፣ በቀጣዩ ዓመት ሰላሳ ይተክላሉ። በሶስት ዓመት ውስጥ አንድ መቶ ይኖራቸዋል ማለት ነው። ይህ ካላቸው ሸጠው ለሚፈልጉት አገልግሎት ማዋል ይችላሉ። ከእዚህ በተጨማሪ ከብት ማደለብና ወተት ማዘጋጀትንም ከእርሻው ጎን ለጎን ይሠራሉና በሴፍትኔት የሚመጣው ጉዳይ ይህንን የሚያዳክም ነው።

እንዲህ ሲባል ግን የትኛውም ሰው ከተረጂነት ነፃ ይወጣል ማለት አይደለም። ሌላ ሀገርም ተረጂ አለ። እንደሚታወቀው አሜሪካ ያደገ ሀገር ነው፤ ነገር ግን “ፉድ ባንክ” አለ። በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ ሰዎች ምግባቸውን ተመላልሰው የሚወስዱት ከምግብ ባንኩ ነው። እዚያም ተረጂነት ቢኖርም የእኛ ይብሳል።

ስለሆነም ይህንን ለማስተካከል የግብርና ሥራችንን፣ የሥራ እድል ፈጠራውን፣ የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩን ማጠናከር፣ ሰዎች ከተረጂነት አስተሳሰብ እንዲወጡ ማድረግ፣ ምንም የሌላቸውን በተቻለ መጠን ወጪያቸውን መሸፈን ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው የምገባ መርሃ ግብር ላይ ድጋፍ ማድረግ፣ አረጋውያንን በመሰብሰብ ምግብና መጠለያ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማበጀት ወሳኝ ነው። እነዚህን ነገሮች ስናደርግ ካለንበት የተረጂነት አረንቋ መውጣት እንችላለን።

ለምሳሌ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት፣ መንበራቸውን እንደተቆናጠጡ በርካታ ውሳኔዎችን የወሰኑ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አንዱ የርዳታን ጉዳይ ማስቆም ተጠቃሽ ነው። እኛ ባንዘጋጅ በተወሰደው ርምጃ ምክንያት ርዳታው ስለሚያቆም እንቸገራለን። ኢትዮጵያ ግን ቀድማ በቂ ዝግጅት አድርጋለች። ርዳታ ቢቀር ምን እንሆናለን ማለቱ በቂ ስለማይሆን የእርሻ ሥራችንን ማጠናከር ይኖርብናል። ይህን እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ማጠናከርን ይጠይቀናል። ኅብረተሰቡም በሥነ ልቦናው በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። መንግሥትም ከዚህ አኳያ ዝግጅት እያደረገ ነው።

የዜጎችን የሥራ እድል ፈጠራን በሚመለከት ለምሳሌ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለዘጠኝ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል በሚል በሀገር ደረጃ እቅድ ተይዟል። በእኛ ክልል በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሥራ እድል እንፈጥራለን። ይህ ማለት በዓመት እስከ 350 ሺ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ እድል እንፈጥራለን ማለት ነው። ማኅበረሰቡ የሥራ እድል አገኝቶ ካፒታል መፍጠር ከቻለ የሚመጣው ትልቅ ለውጥ ነው። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የተቀመጡ ምሩቃን አሉ፤ እነርሱን ሥራ ማስያዝ ይኖርብናል። በተመሳሳይ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁትንም ሥራ ማስያዝ አለብን። ሥራ ማስያዝ ሲባል የሚያዘው የመንግሥት ሥራ አይደለም። በሥራ እድል ፈጠራ ውስጥ አልፈው የራሳቸውን ካፒታል እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው።

በቅርቡ የኬንያው ፕሬዚዳንት ንግግር አድርገው እንደነበር ይታወሳል። ‹‹የአሜሪካ ርዳታ ቆመ ብለን የምናለቅሰው ለምንድን ነው? የአሜሪካን መንግሥት ለእኛ ገንዘብ የሚመድብበት ምንም ምክንያት የለውም፤ ምክንያቱም እኛ የአሜሪካ ዜጎች አይደለንም ብለዋል። ›› ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውንም የራሳችንን ሀብት አውጥተን በአግባቡ መጠቀም አለብን። ኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህ አኳያ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ነች።

በኢትዮጵያ ካሉን ክልሎች እንደ እነጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ሶማሌ ያለው መሬት በአግባቡ ቢታረስ ኢትዮጵያን ይመግባል፤ ከዚህ በተጨማሪ ሊታረስ የሚያስችለን ሁሉ መሬት ቢታረስ ሙሉ ኢትዮጵያን ከመመገብ አልፎ ለሌሎች ይተርፋል። ለዚህ ደግሞ ጽናት የግድ ይላል።

ሰብሰብ ብለን የተሻለ እንዳናስብና እንዳንተባበር ከዚህና ከዚያ የሚረብሹን ጉዳዮች አሉ። የሚወረወሩብንን አጀንዳዎች ሰብሰብ አድርገን መጨረስ አለብን። እነዚህ የሚረብሹንን አጀንዳዎች በሁለት መልኩ መጨረስ አለብን ብለን እናስባለን፤ አንደኛ በምክክር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሽግግር ፍትህ ለአንዴ እና ለመጨረሻ የሚዘጉ ጉዳዮች መኖር አለባቸው ብሎ መንግሥት እየሠራ ይገኛል። ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሁሉም ነገር የሚያያዝ ነው፤ ኢኮኖሚ ከሰላም ጋር አይነጣጠልም።

አዲስ ዘመን፡- በክልል ደረጃ በግብርናው ዘርፍ እየተሠራ ያለው እንቅስቃሴ በመልካምነቱ እየተነገረለት ይገኛል፤ ይህ ውጤት የመጣው እንዴት ነው?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንም፤ ገና ነን። በሁሉም የሥራ መስክ መስመር እያስያዝን ነን፤ ገና የሚቀረን ነገር አለ። በርግጥ የተሠሩ አንዳንድ ሥራዎች አሉ፤ ነገር ግን መዘናጋት የለብንም። ምክንያቱም ምንም ነገር የሚለካው በሕዝብ ፍላጎት ነው። ሕዝቡ የሆነ ጥያቄ እያለው እኛ የሆነ ደረጃ ደርሰናል ካልን እንቆማለን። ብልፅግና፣ መንግሥትም እኔ የምመራው ክልልም የጀመርናቸው መልካም ነገሮች እንዳሉ እናምናለን። ነገር ግን የሚቀሩን ነገሮች እንደሚበልጡም እናውቃለን። ምክንያቱም የሚታመሙ እናቶች አሉ። ስለዚህም ክሊኒክ ሰርተን አልጨረስንም። ትምህርት ቤት ያልገቡ ተማሪዎች አሉ። ትምህርት ቤት ገንብተን አላጠናቀቅንም። የሚራቡና የሚታረዙ ሰዎች አሉ፤ መግበንና አልብሰን ገና አልጨረስንም። ይህን ባልጨረስንበት ሁኔታ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሰናል ማለት አንችልም።

ግብርናው ላይ የተጀማመሩ የተለያዩ ኢንሼቲቮች አሉ። እነሱ መልካም የሚባሉ ናቸው። ግብርና በሶስት የተለያዩ ወቅቶች የሚሠራበት መስክ ነው። በእኛ ክልል ይህንን ወቅት ወደ አራት ለውጠነዋል። ጸደይን በመሃል እንጠቀማለን። መስኖ ስላለ እሱን እንጠቀማለን። ሁለተኛው የማምረት አቅማችን ጨምሯል። በአነስተኛ መሬት ብዙ ማምረት ጀምረናል። ግብዓትን እናቀርባለን፤ አርሶ አደሩን ደግሞ እናስተምራለን።

ሌላው አርሶ አደሩን ከልማት የሚነቅሉት ጉዳዮች ላይ አንደራደርም። አርሶ አደሩን ከልማት የሚነቅለው ነገር ወሬና ሱስ ነው። ለምሳሌ ጫት፣ አረቄ ከመሳሰሉት እንዲላቀቅ እያስተማርን እንገኛለን። ይህ ዓይነቱ አጠቃቀም ከሥራ በኋላ ባላቸው ጊዜ እንጂ በዋና የሥራ ጊዜ የሚደረግ አለመሆኑን ግንዛቤ እየሰጠናቸው ነው።

የግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በሙሉ ሰዓት እገዛ እንዲያደርጉላቸውም እያደረግን ነው። በየደረጃው ያለው አመራር የግብርና ሥራ ዋና መውጫችን ነው ብሎ እንዲሠራ በማድረግ የተመዘገቡ ትንንሽ ውጤቶች አሉ። እነሱ ገና በመሆናቸው ማስፋት ይጠበቅብናል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገርም እንደ ክልልም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እየተሠራ እንደሆነ ይታወቃል፤ እንቅስቃሴው እንዴት ይገለጻል? አዋጭነቱስ የት ድረስ ነው?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ በዘርፉ የተያያዘችው ጉዞ አዋጭ ነው፤ መለኪያው ደግሞ የያዝናቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የውጭ ጉዳይ መርሃ ግብር ነው። እነዚህ አንኳር ጉዳዮች ሲተነተኑ ያስቀምጥናቸውን የብልፅግና ዓላማዎች በሙሉ የሚያሳኩ ናቸው። እንደዚያ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ መንግሥታትም በተለይ በመደመር እሳቤ የሕዝብ ተጠቃሚነትን መሠረት አድርገን እየሠራን ነው።

እኛ በዓለም ደረጃ የተለየ ወዳጅ የለንም፤ የምንጠላውም ሀገር የለንም፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር አይነኬ ጉዳዮች ናቸው የተባሉትን ጭምር እየነካን ነን፤ ለምሳሌ የባሕር በር ጥያቄ የማይነካ ሆኖ የተከደነ በር። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ወደ 133 ሚሊዮን ደርሷል። ይህን ያህል የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ የምትኖረው ያለ ወደብ ነው። የባሕር በር ይገባኛል ብሎ ያነሳው ይህ መንግሥት ነው፤ ከዚህ ቀደም የምንኖረው ያለ ወደብ ነው፤ ይሁንና የይገባናል ጥያቄ አንስተን አናውቅም።

ስለዚህ ሀገሪቷን ለመለወጥ የያዝናቸው አጠቃላይ መርሃ ግብሮች እጅግ በጣም አዋጭ ናቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ቢቀመሩ ለሌሎች ሀገሮችም የሚጠቅሙ ናቸው። ነብይ በሀገሩ አይከበርም እንዲሉ ሆኖ ነው እንጂ በጣም በርካታ ሥራ እየተሠራ ነው፤ አንዳንዶች አልተረዱትም። አንዳንዱ ደግሞ እስኪ እንመልከት እያለ ነው። አንዳንዱ ደግሞ የመጣውን ለውጥ በተጨባጭ እያስተዋለ ገና አላመነም።

ነገር ግን ጠቅለል አድርገን ስናስቀምጠው እኛ በብዙ አብዮቶች ውስጥ አልፈናል። የኋላውንም ሆነ የፊቱን አይተን ማመዛዘን እንችላለን። ተሰንዶ የተቀመጠ ነገር አንበብን ማመዛዘን እንችላለን። እንዲህ እያደረግን ሚዛናዊ ነገር እየሰጠን መጓዝ ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ የተያያዝነው ጉዞ በትክክለኛው መንገድ ላይ ያለ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በኢንቨስትመንቱ ረገድ ምን እያከናወነ ነው? ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያስ በክልሉ ምን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- በኢንቨስትመንት ረገድ ሲታይ እኛ ገና ጀማሪዎች ነን። ለኢንቨስትመንት በጣም ዝግ የሆኑና ሰዎችን ለማስተናገድን የማይማመቹ የነበሩ አሠራሮችን በሙሉ አስተካክለናል። ከመጣን በኋላም ለኢንቨስትመንት የሚመቹ ቢያንስ ከ250 በላይ የሚሆኑ ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ወስነናል።

በኢንቨስትመንቱ ረገድ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተወላጅንም ሆነ ከክልሉ ውጭ የሆነው የክልሉ ወዳጅ ሊሠራ የሚፈልገውን አካል ሁሉ እናሳትፋለን። ስለዚህ ጅምር ነው፤ ያለን ሀብት ምንድን ነው ብለን ለይተናል፤ በዚህም ልየታ ውስጥ አንዱ ግብርና ነው። ሁለተኛው ደግሞ በከፊል ማዕድን ያለ ሲሆን፣ ሶስተኛው ቱሪዝም ነው። በመሆኑም በእነዚህ ሶስት ነገሮች ላይ እናሳትፋለን። ግብርናው ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ቱሪዝምና ማዕድን ይከታተላሉ። በዚህ በኩል የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። የውጭ ዜጎችም እየገቡ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ የሀገርም ውስጥ ሰዎች እየገቡ ነው። ከዚህ የተነሳ ጅምሩ ጥሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የዜጎችን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምን እየተሠራ ነው?

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- ዜጎች በፍትሃዊነት በሀገራቸው ላይ መስተናገድ ካልቻሉ ችግር ያጋጥማል። ዜጎች በፍትሃዊነት የሚጠቀሙባቸው ሴክተሮች አሉ። አንደኛው ማኅበራዊ ሴክተር ሲሆን፣ ትምህርትም ጤናም ነው። ያለውን ሀብት በቀመር መስጠትና እኩል እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው።

ሌላው ፍትሃዊነትን የሚፈልገው የፖለቲካ ተሳትፎ ነው፤ በዚህ ረገድ በጣም መሻሻል አለ። በኛ ክልል ያለነው አስር ብሔር ብሔረሰቦች ነን። ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በሚኖሩን ሹመት ላይም ሆነ አጠቃላይ ሥራው ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንደ ሕዝብም እንደ አመራርም መልካም ነው ብለን እንወስዳለን።

ሌላው ደግሞ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ነው። በአንዳንዱ ቤተሰብና በማኅበረሰብ የሚመጣው እድገት ተመጣጣኝ መሆን አለበት። አንዱን ቦታ እያለማን ሌላውን ቦታ እየጣልን መሔድ የለብንም። የሚፈለገው ሁሉም ማኅበረሰብ ተቀራራቢ እድገት እንዲኖረው ነው። ለልማት የሚደረገውን ሁሉ እንከታተላለን። እንዲሠራም እንደግፋለን። ምክንያቱም ፍትሃዊነት የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ ነውና።

ሀገር ውስጥ ችግር የሚፈጠር ከሆነ ችግሩ የሚመነጨው ከፍትሃዊነት መጓደል ነው። ፍትሃዊነት በተረጋገጠበት ቦታ ችግሮች በጣም አነስተኛ ይሆናሉ። እያደግን ስንመጣ ድጎማም ይኖራል። አሁን ባለን ሁኔታ ግን እጥረት ያለባት ሀብትም ብትሆን እኩል መድረስ አለባት የሚል አተያይ አለን። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ምንም ችግር የለብንም።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ።

እንዳሻው (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You