
ሰላም እና ልማት የትኛውም ማኅበረሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ትልቁ አጀንዳ ነው ። በተለይም ባለንበት ዘመን የሰው ልጅ ከደረሰበት የአስተሳሰብ ልዕልና አኳያ እነዚህ አጀንዳዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፋዊ ከሆኑ ውለው አድረዋል። ዓለም አሁን ላይ ለደረሰችበት ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያላቸው አበርክቶም መተኪያ የሌለው እንደሆነ ይታመናል።
በቀደሙት ዘመናት ግጭቶች እና ጦርነቶች ዓለምን ብዙ ዋጋ አስከፍለዋታል ፣ በዘመናት መካከል ሊረሱ የማይችሉ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ፈጥረዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ሲታወሱ ለቀደሙት ፣ ላሉት እና ለሚመጡ ትውልዶች የልብ ስብራት የሆኑ አሰቃቂ እና ዘግናኝ ክስተቶች ተፈጥረዋል ፣ ዛሬም ቢሆን እየተፈጠሩ ያሉበት ሁኔታ አላበቃም።
በዘመናት እና ዓመታት መካከል በግጭቶች እና ጦርነቶች ምክንያት እያላቸው የሌላቸው ፣ ብዙ ተስፋ እያደረጉ ተስፋ ቢስ የሆኑ ፣ ለብዙ መትረፍ እየቻሉ ተመጽዋች እና ጠባቂ የሆኑ ፣ ለሌሎች ትናንት ፣ ዛሬ እና ነገ ተስፋ ሆነው ለራሳቸው መሆን ያልቻሉ፣ ሀብት ላይ ተኝተው የድህነት እና የኋላ ቀርነት ተምሳሌት የሆኑ ፣ በዚህም አንገታቸውን ደፍተው ለመኖር የተገደዱ ሕዝቦች እና ሀገራት ጥቂት አይደሉም።
ከነዚህ ሀገራት እና ሕዝቦች መካከል ሀገራችን ተጠቃሽ ነች ፣ በዘመናት መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች እና ጦርነቶች ከፍ ካለ የሥልጣን ማማ ወርዳ ፣ ችግሮቹ በፈጠሩት ውድቀት ውስጥ ዘመናትን ለማስቆጠር ተገዳለች ። በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ለሀገራቸው ካላቸው ቀናኢነት የተነሳ የበለጸገች ሀገር ተፈጥራ ለማየት በብዙ ተስፋ ቢያደርጉም ከግጭት እና ከጦርነት አዙሪት መውጣት ባለመቻሏ ተስፋቸው እውን ሳይሆን ቀርቷል ።
እንደ ሀገር / እንደ ትልቅ ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ የተለያዩ ትላልቅ ሥልጣኔዎች ባለቤቶች ብንሆንም ፣ ከግጭት አዙሪት መውጣት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ስክነት መፍጠር አለመቻላችን ፣ የቀደሙ ገናና ታሪኮቻችንን አደብዝዘውታል ፣ ትውልዶች የየራሳቸውን የለውጥ መሻት እውን ማድረግ እንዳይችሉ ፈተና ሆኖባቸዋል።
በየዘመኑ ለነበሩ ትውልዶች ፈተና የሆነ ይህ ችግር ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደ ሀገር ሳንሻገረው ቀርተን ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው። በችግሩ ዙሪያ መግባባት ፈጥረን ፣ ራሳችን የችግሩ መፍትሄ መሆን ካልቻልን እንደ ሀገር ለራሳችን ሆነ ለልጅ ልጆቻችን የምንመኘውን የተሻለች ፣ ለዜጎች የኩራት ምንጭ የሆነች ሀገር መፍጠር አንችልም።
አሁን ያለው ትውልድ ለዘመኑ ዕውቀት እና ጥበብ ፣ ለመረጃ ያለው ቅርበት ፣ ከቀደሙት ትውልዶች በተሻለ መልኩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎችን ማገናዘብ የሚያስችል ባለ እድል መሆኑ ፣ ከሁሉም በላይ በዘመኑ ካስተናገዳቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች የከፈለው ያልተገባ ዋጋ ቁስሉ እስከዛሬ አለማገገሙ እንደ ሀገር ከዚህ ችግር ለመውጣት ያለበትን ሃላፊነት ከፍ ያደርገዋል።
ይህ ትውልድ በየትኛውም መልኩ የግጭት እና የጦርነት ግጥም እና ዜማ አይመጥነውም ፤ በራሱ ዕጣ ፈንታ፤ ተስፋ ባደረጋቸው ነገዎቹ፤ በልጆች እና በልጅ ልጆች ብሩህ ተስፋ ላይ ተነስ ፤ታጠቅ የሚል ከዘመኑ ጋር የተጣላ የግጭት እና የጦርነት ክተት ለማዳመጥ የተገባ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለትናንት ገናና ማንነቱ ትንሳኤ ለመስጠት ቁጭት እና ቁርጠኝነት ፈጥሮ ሊንቀሳቀስ የተገባ ትውልድ ነው።
ትውልዱ ለትናንት ሆነ ለዛሬ ድህነት እና ኋላ ቀርነቱ ምክንያት የሆነውን ግጭት እና ጦርነት የሚጠየፍ ፤ ልብ እና አእምሮውን ለጦርነት የነጋሪት ጉሸማ ሳይሆን ፤ ለሰላም እና ለእርቅ ክፍት አድርጎ የሚጠብቅ ፤ለዚህ የሚሆን መንፈሳዊ እና አእምሯዊ ዝግጅነት የፈጠረ ፤ ሰላም እና እርቅ የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ሊሆን የተገባ ነው።
ትውልዱ ተስፋ ላደረጋቸው ነገዎቹ ከግጭት እና ጦርነት የሚያተርፈው አንዳች ነገር የለም፤ የራሳችን ያቀፈ ታሪክ ሆነ የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ከጦርነት ተጠቃሚ የሆነ የለም ፤ ይኖራል ብሎ መጠበቅ ፤ የሌሎች ክፋት እና ጥፋት ሰለባ ከመሆን ባለፈ ፋይዳ አይኖረውም። ለዚህ በጊዜ መንቃት እና ፈጥኖ መንቀሳቀስ ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዷ ቀን የራሷ የማንቂያ ደውል አላት!
አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም