የካቲት 12 የድል ቀን ነው!

ደመቅ አድርገን የምናወራለት ዓድዋን ነው፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ድል ስለሆነ ነው! የካቲት 12 ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሰማዕት የሆኑበት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ድል እንጂ ሽንፈት አይደለም፤ ሞተው አሸንፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹በቅኝ ያልተገዙ ሀገራት›› ከሚለው የዓለም መዝገብ ውስጥ እንድትኖር፣ ‹‹በአፍሪካ ብቸኛ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር›› እንድትባል የእነዚህ ሰዎች ሰማዕትነት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ‹‹ቅኝ አልተገዛችም›› የተባለው በዓድዋው ድል ብቻ ሳይሆን በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ፋሽስት ቆይታ አለመሳካት ነው፡፡ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሞክሮ አልሳካለት ሲል የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነት የበለጠ አስደማሚ ሆነ፡፡

ይህ አስደማሚ ታሪክ የተመዘገበው በእነዚህ የየካቲት 12 ሰማዕታት ነው፡፡ በሕዝቡ አልገዛም ባይነት ነው፡፡ ጀግና መስዋዕት ሆኖ ያሸንፋል፡፡ ስለዚህ ይህ የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ሊዘከርና ሊዘመርለት ስለሚገባ እስኪ በጥቂቱ እናስታውስ፡፡

በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ላይ ዓለም አቀፍ ውርደትን የተከናነበው ፋሽስት ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ሲዘጋጅ ቆይቶ፤ ያኔ የደረሰበት ሽንፈት ሲያንገበግበው ከኖረ በኋላ በ1928 ዓ.ም በቀሉን ሊወጣ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

እናም ከ88 ዓመታት በፊት፣ ከጣሊያን የኢትዮጵያ አንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በዛሬዋ ዕለት እንዲህ ሆነ። ከጣሊያን ንጉሣዊ ቤተሰቦች አንድ ልዑል ልጅ በመወለዱ በኢትዮጵያ ድል ያለ ዝግጅት ተዘጋጅቶ እንዲከበር በጀኔራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ ተላለፈ። ዝግጅቱም በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የፋሽስት ጣሊያን ባለሥልጣናት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ሁሉ እንዲገኙ ተደረገ።

በዚህ ዝግጅት ላይ ትልቅ የደስታ ስጦታ መዘጋጀቱን መጀመሪያ አብርሃም ደቦጭ ሰማ። ውሳኔውንም ለበጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ፣ ለብላታ ዳዲ፣ ለቀኝ አዝማች ወልደዮሃንስ፣ ለደጅ አዝማች ወልደ አማኑኤል እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጓደኞቹ ተናገረ። ጥሪው ከተደረገበት ቦታ ማንም ሰው መሄድ እንደሌለበትም አስታወቃቸው። ዳሩ ግን የፋሽስቱ እንዲህ በሀገራቸው ላይ ደጋሽ እና ጋባዥ መሆን ያላንገበገባቸው ሆዳሞች አብርሃም ደቦጭን ‹‹ዞር በል ወዲያ!›› ብለውት ለመሄድ ወሰኑ። አብርሃምም ለቅርብ ጓደኛው ለሞገስ አስገዶም ምን ማድረግ እንዳለባቸው መከሩ። በዚች ታሪከኛ ቀን የካቲት 12 ከማንም ቀድመው ዝግጅቱ ላይ መገኘት እንዳለባቸውም ወሰኑ።

ከመሄዳቸው በፊትም እንዲህ አደረጉ። በአብርሃም ቤት ውስጥ የጣሊያንን ባንዲራ በሳንቃ ወለል ላይ አንጥፈው ሚስማር ገደገዱበት። ጣሊያን ጉዱን አላየምና እዚያ አዳራሽ ውስጥ ሽር ጉድ ይላል። አብርሃም እና ሞገስም የልባቸውን በልባቸው ይዘው ወደ ዝግጅቱ ገቡ።

ግራዚያኒም በአዳራሹ እየፈነጠዘ ብሉልኝ ጠጡልኝ ይል ጀመር። አዳራሹ ውስጥ ታድመው ዝግጅቱን ከሚያደምቁት አድር ባዮች ውስጥ ግን፤ ድግሱ እሬት እሬት ያላቸው፣ አዳራሹ የፋሽስት ሶላቶ መራገጫ መሆኑ ያንገበገባቸው የሀገር ነፃነት የናፈቃቸው ሁለት ወጣቶች ነበሩ። ሞገስ አስገዶም እና አብርሃም ደቦጭ። ገዳይ ሲያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል ነውና ነገሩ ግራዚያኒ ከሚገባው በላይ ቅጡን አጣ። በአዳራሹ የታደመውን ሰው እየዞረ ለተወለደው ልጅ ስም እንዲያወጡ ጠየቀ። አድር ባይ ሁሉ ስም ያወጣ ጀመር። አሁን የአብርሃምና የሞገስ ትዕግስት አልቋል። ለማንም የፋሽስት ‹‹ዲቃላ›› ማነው ስም የሚያወጣ ተባባሉ። በቃ አሁን ጉድ ሊፈላ ነው። በኪሳቸው ደብቀውት የነበረውን ቦንብ መዥረጥ፣ መዥረጥ አደረጉት። ግራዚያኒ ላይ ተወረወረ። ቆስሎም ወደቀ። ለአሸሸ ገዳሜ የታሰበው አዳራሽ ‹‹ዋይ! ዋይ!›› ተባለበት።

ሌሎች የጣሊያን ፋሽስቶችም በእልህ እና በብስጭት ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጰያውያንን በግፍ ጨፈጨፉ። አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምም ወደ ሱዳን እየሄዱ ሳሉ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ። ከዚያ በኋላ እንግዲህ የኢትዮጵያ ቆራጥ አርበኞች ጣሊያንን ከሀገር ለማስወጣት ሴት ወንድ ሳይሉ በዱር በገደሉ መዋጋት ጀመሩ። እነ ሸዋረገድ ገድሌ እና ከበደች ሥዩም ከሴት አርበኞች የሚጠቀሱ ናቸው።

የሞገስ አስገዶምና የአብርሃም ደቦጭ ቁርጠኛ ውሳኔ ብዙ ጀግኖችን ለትግል አነሳሳ። በኋላም ለእናት ሀገራቸው ቆርጠው በተነሱ አርበኞች ትግል የጣሊያን ፋሽስት ጓዙን ጠቅልሎ ከኢትዮጵያ ወጣ። እነዚህ ጀግኖች አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ኢትዮጵያን ብቸኛ አፍሪካዊት ነፃ ሀገር አስብለዋል። የሀገር ፍቅር እስከ መቃብር ይሏል ይህ ነው።

የካቲት 12 የድል ቀን መባል ይችላል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም እንደዚያ ባያንገበግባቸው ኖሮ ምናልባትም ነገርየው እየተለመደ ሊቆይ ይችል ነበር፡፡ ምንም እንኳን ድርጊቱ ብዙ ከ30 ሺህ በላይ ንፁሃንን ያሳጣን ቢሆንም፤ ዳሩ ግን ለበለጠ አርበኝነት አነሳስቷል፡፡ ፋሽስቱ ጣሊያን እንደሆነ አንድ ቀን ባይሆንም 30 ሺህ ንፁሃንን መግደሉ አይቀርም ነበር፡፡ ምናልባት ቆይታውን ሊያራዝም ይችል ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያን ቅኝ መግዛት አይችልም ነበር፤ ስለዚህ በሂደት ብዙ እየገደለ፣ ባሪያ እያደረገ ሀገራዊ ጉዳቱን ያራዝመው ነበር እንጂ ሰላም አይኖርም ነበር፡፡ ያቺ ቀን ግን የጣሊያን የመጨረሻ አውሬነት የታየባት ናትና አርበኞችን አበዛች፡፡ በመጨረሻም ተጠራርጎ እንዲወጣ አስደረገች፡፡

እነዚያ ሰማዕታት በደም እና አጥንታቸው ኢትዮጵያን የዓለም የነፃነትና የጀግንነት ተምሳሌት አስደረጉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በኩራት እንዲኖር አደረጉ፡፡ ‹‹ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን›› ያለችው ባለቅኔዋ እጅጋየሁ ሽባባው ይህንን ነው፡፡ እነዚህ ሰማዕታት በየጊዜው ሊታወሱና ሊዘከሩ ይገባቸዋል፡፡

በዛሬዋ ቀን ከ88 ዓመታት በፊት ነፃ ሀገርና የሚያኮራ ታሪክ ሠርተው ላስረከቡን ክብር ለሰማዕታት ጀግኖቻችን እያልን በተከታዩ የነቢይ መኮንን ግጥም እንሰነባበት።

 

 ሐቁ ኦርጅናሌ

የወል ደቦ ፍቅሩ ያገር አጾለሌ፣

ግን ዝናው ያልጮኸ ስሙ ያልተሰማ፣

ያገር አዋይ ራዕይ ያገሬው ከራማ፣

ራሱ ሳይታይ ሌላውን የሚያሳይ፣

ያልተሻገርንበት የብርሃን ድልድይ፣

ያልተዘመረለት የዕውቀት ፈለግ ፀሐይ፣

አዎ አለ አንዳንድ ሰው፣

ጉቶ የሸፈነው ያገር ግዙፍ ዋርካ፣

መስፈሪያ የሌለው ልቡ የማይለካ፣

ሃሳበ ፅብ እረቂቅ ህልሙ የማይነካ፣

ምናቡ አድማስ ሰበር ቃሉ የማይተካ፣

ላልተዘመረለት እንዘምርለት፣

ላልተነገረለት እንናገርለት፣

ያልተዘመረለት።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You