ሰላምና ልማት- የዚህ ትውልድ አርበኝነት!

ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ ተከብሮ የቆየው ጀግኖች አርበኞች ‹‹እምቢ ለሀገሬ፣ እምቢ ለወገኔ›› ብለው በከፈሉት መሥዋዕትነት ነው። ለኢትዮጵያው ከተከፈሉ የመስዋትነት ታሪኮች አንዱ የተፈፀመውም ከ88 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ እለት ነበር።

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የፋሺስት ጣሊያን የጦር መሪ በነበረው ማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ ትዕዛዝ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በተለይም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተጨፈጨፉበት ዕለት ነው፡፡ በ1888 ዓድዋ ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት የጣሊያንን ጦር በማሸነፍ ድል ማድረጉን ተከትሎ ፣ ጣሊያን የሽንፈት ካባ ተከናንባ የኢትዮጵያን ምድር ለቃ ወጣች። ነገር ግን በዓድዋ ሽንፈት ቂም የያዘችው ጣሊያን ከ35 ዓመታት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን በመውረር ብዙ አትዮጵያውያንን በግፍ ለሞት ዳርጋለች።

በወቅቱ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ሀገርን ላለማስደፈር ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጣሊያንን ድርጊት አዲስ ለተቋቋመው የመንግሥታት ማህበር ለማመልከት ወደ ውጭ ሀገራት ቢሄዱም፣ ሕግና ሉዓላዊነት በወቅቱ ትኩረት ሊሰጣቸው ስላልቻለ ኢትዮጵያውያን በብቸኝነት የነጻነት ተጋድሏቸውን አጠናክረው ቀጠሉ።

ጣሊያን በዓድዋ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስና ኢትዮጵያን ለመውረር ባደረገው ወረራ የተበሳጩት ኢትዮጵያውያኑ አርበኞች አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ፣ ከ88 ዓመታት በፊት (የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም) በኢትዮጵያ የፋሺስት ጣሊያን አስተዳደር ተወካይ (ኃላፊ) የነበረውን ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒን ለመግደል ሙከራ አደረጉ።

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የወረወሯቸው ቦምቦች ግራዚያኒን ጨምሮ ሌሎች በስፍራው የነበሩ ሹማምንትን አቆሰሉ። በዚህም የባሰ ለግድያ የሚያነሳሳ ምክንያት በማግኘት ፋሺስቶች የበቀል ሰይፋቸውን በኢትዮጵያውያን ላይ መዘዙ። በሦስት ቀናት ውስጥም ከ30ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን የፋሺስቶች ሰለባ መሆናቸውን ታሪክ ያስረዳል። የበቀል ርምጃው ከአዲስ አበባ አልፎ ደብረ ሊባኖስ ገዳምም በመድረስ ቀሳውስትና ምዕመናን መገደላቸውንም ታሪክ መዝግቦታል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የካቲት 12 በኢትዮጵያውያን ዘንድ በየዓመቱ ይከበራል። የመታሰቢያው ሥነሥርዓት በተለይም በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የየካቲት 12 ሰማዕታት ሀውልት ስር ይካሄዳል።

የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ እለት የኢትዮጵያውያን የአንድነትና አይበገሬነታቸው አንዱ ማሳያ ነው። እለቱ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሲሉ ከወራሪ ሃይል ጋር የተፋለሙና የተዋደቁ ጀግኖች የሚታወሱበት ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ነው። የአሁኑ ትውልድ ይህን እለት አስቦ ከመዋል በዘለለ ከጀግኖች አርበኞችና ከሰማዕታቱ ታሪክ ብዙ የሚማረው ቁም ነገር አለ።

ከዘመኑ ጀግና ወጣቶች መካከል አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የሀገሬን ሉዓላዊነት አላስደፍርም በሚል በፋሽስት ጣሊያን ወታደራዊ አዛዦች ላይ ርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል። ወራሪውን ኃይል ለማቆም በርካታ አባቶችና እናቶች ተሰውተዋል፤ ንብረትም ወድሟል፡፡ የአርበኞች ጽኑ መስዋዕትነትና ህብረት ግን ለአሁኑ ትውልድ ትምህርት የሚሰጥ ነው። በመሆኑም የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ እለት የኢትዮጵያውያን የአንድነትና አይበገሬነታቸው አንዱ ማሳያ ነው።

የአሁኑ ትውልድም የቀደሙ አያቶች ያስከበሯትን ሀገር ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት። ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን ድል አድራጊነትን በመውረስ የሀገሩን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ ሊቆም ይገባል።

ዛሬ ላይ ተከብራና ታፍራ የምትታወቀው ኢትዮጵያ የጀግኖች አባቶች መሥዋዕትነትና ተጋድሎ ውጤት ናት። ወጣቱ ትውልድ ይህንን የአልደፈርም ወኔ አስጠብቆ ሀገሩን ለአደጋ ከሚያጋልጥ ከፋፋይ አጀንዳ ለመጠበቅ በጋራ ሊቆም ይገባል።

ጀግኖች አባቶች መሥዋዕትነት የከፈሉት ለሀገር ካላቸው የፀና ፍቅርና አንድነት ፤ በከፈሉት መሥዋዕትነትም ያልተደፈረችና ነፃነቷ የተከበረች ኢትዮጵያን አስረክበውናል። የዚህ ዘመን ትውልድም ሰላሟንና አንድነቷን የጠበቀች ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በአንድነትና በህብረት ሆኖ ሊደቀንባት ከሚችል አደጋ ሁሉ መጠበቅ ይገባዋል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ቀጣይ ህልውናዋ የሚረጋገጠው በወጣቱ ትውልድ ቆራጥነት ልክ ነው። የዛሬ 88 ዓመት መሥዋዕትነት ከፍለው የሀገራቸውን ክብር ያስጠበቁትና ዛሬ ጀግኖች በመባል የሚጠሩት የያኔዎቹ ወጣቶች መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል። ወጣቱ ትውልድ የነገ ሀገሩ የምትከበረውና የምትጠራው ዛሬ በሚሠራ መልካም ተግባር እንደሆነ አውቆ ለሀገሩ አንድነትና ሰላም ተባብሮ መሥራት ይኖርበታል።

የዚህ ዘመን ትውልድ የሚጠበቅበት ሰርቶ ድህነትን ማሸነፍና ሀገሩን ወደ ብልፅግና ማሸጋገር በመሆኑ ለዚሁ መትጋት ይገባዋል። ጀግኖች አባቶች የሕይወት መሥዋዕትነት ከፍለው ያቆዩዋትን ኢትዮጵያ ትውልዱ አጽንቶ ሊያስቀጥላት ይገባል።

ለሀገር መሥዋዕት መሆን የጥንት አባቶቻችን ያቆዩት እሴት ከመሆኑም በላይ የነጻነትና የአርበኝነት የተጋድሎ ልዩ ምልክት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረችው በጀግኖች ልጆቿ መሥዋዕትነት ነው። አሁንም ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ትውልዱ የአባቶቹን አኩሪ የተጋድሎ ታሪክ ሰላምን በማስፈንና ሀገሩን በማልማት ሊያስቀጥል ይገባል፡፡

ትውልዱ የቀደምት አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክና እሴቶች አውቆና ጠብቆ ማስቀጠል እንዲችል ጀግኖች አርበኞችም በማስተማርና በማስገንዘብ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው። አሁንም የሀገርን ዳር ድንበር በማስከበር የተከበረች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ወጣቱ ትውልድ ያለውን ሀገራዊ ፍቅርና አክብሮት እንዲሸረሸር መፍቀድ የለበትም።

የአሁኑ ትውልድ ጀግኖች አርበኞች በከፈሉት መሥዋዕትነት ሰላምና ነፃነቷ ተጠብቆ የቆየችውን ሀገር ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነትም አለበት፡፡

ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቡት አኩሪ ድል በጨለማ ውስጥ ብርሃን መፈለግን የሚያስተምር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በወቅቱ የነበረው ህብረትና አንድነት አሁን ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍቻነት ሊውል ይገባል።

ሰላም የሰፈነባትን ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በውይይት መፍታትና በሃሳብ የበላይነት ማመን ይገባል። ጀግኖች አርበኞች ዘመናዊ ጦር መሣሪያ የታጠቀውን ወራሪ ኃይል መክተው ሀገር አቆይተዋል። በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ ሀገርን ለማቆየት የተከፈለውን መሥዋዕትነት በመገንዘብ የኢትዮጵያ ልማት አርበኛ ሊሆን ይገባዋል፡፡

አርበኞች ዘርና ሃይማኖትን ሳይለዩ አንድ ሆነው መዋደቃቸው ለውጤት አብቅቷቸዋል። የአሁኑ ትውልድ የእነሱን አርአያና ፈለግ በመከተል አንድነቱን አጠናክሮ ሀገሩን መጠበቅ አለበት፡፡

ብሌን ከ6 ኪሎ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You