
ኢትዮጵያውያን ለነጻነታችን ውድ ዋጋ የከፈልንበት የየካቲት 12 ሰማዕታት 88ኛው ዓመት መታሰቢያ ዛሬ ታስቦ ይውላል። ይህ ቀን ኢትዮጵያውያን በቅኝ አንገዛም፣ አንበረከክም ፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት አናስደፍርም ብለው ለእኛ በነጻነት መኖር መሥዋዕትነት የከፈሉበት ዕለት ነው። ቀኑን በየዓመቱ እናስታውሰዋለን፤ ታሪኩንም እንዘክረዋለን።
በ1929 ዓ.ም በጀነራል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ትዕዛዝ ሰጪነት በአዲስ አበባ ከሰላሳ ሺህ በላይ ዜጎቻችን ህጻን ፣ ሴት፣ ወጣት፣ አዛውንት ሳይል ጭካኔ በተሞላው መንገድ ተጨፍጭፈዋል። እነዚያ ዜጎቻችን ዘግናኙን መከራ ተቀብለውና ታሪካቸውን በወርቅ መዝገብ ጽፈው ለእኛ ደግሞ ነጻነትን አጎናጽፈውናል ።
ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች፣ ለነጭ ያልተንበረከከች ብቸኛዋ ነጻ አፍሪካ ሀገር ሆና እንድትኖር አድርገዋል። የጀግንነትና የሀገር ፍቅርን አውርሰውናል። እነዚህ ሰማዕታት ታዲያ በየዓመቱ ይታወሳሉ። በስማቸው በተሠራው የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት ስርም ጉንጉን አበባ ይቀመጣል። ለታላቅ ሥራቸው ታላቅ ክብር ይገባዋልና።
ኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌት ሀገር መሆኗን ከሚያሳዩ እና ለነጻነታችን መሠረት የሆነ ታሪካችን በመሆኑ ሁሌም የምንዘክረው እና የምንኮራበት ነው። ይሄ አንዱ ምዕራፍ ነው። አሁን ግን በሌላኛው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይሄኛው ምዕራፍ ያለፉ አባቶችና አያቶቻችን የሠሩትን ታሪክ በማወደስና በመኩራራት ላይ ብቻ ከማተኮር አለፍ ብሎ የራስን የታሪክ ዐሻራ ለማሳረፍ የሚሠራበት ዘመን ነው ። የሚያስብ አእምሮ የሚሠሩ እጆችን ይዞ ለልማት የሚሮጥበት ጊዜ ነው። አሁን ከነጻነት እና ከሉዓላዊነት እኩል ከፍ የሚያደርጉንን የሀገራችንን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን። ተረጂነትና ልመና ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ተግባር መሆኑ ግልጽ ነው። ከተረጂነት ጎን ለጎን ቅኝ ግዛት ፤ ነጻነት ማጣት በዓለም ላይ በተደጋጋሚ ታይቷል። ስለዚህ የሀገራችንን ነጻነት ጠብቀንና አረጋግጠን በአደባባይ የምንቆመው ብልፅግናችንን በኢኮኖሚው ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካው ዘርፍ ማረጋገጥ ስንችል ፤ እንደ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የራስን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ የሚያስችለንን ቁመና በሁሉም ዘርፍ ማረጋገጥ ስንችል አንገትን ቀና ፤ ልብን ሞላ አድርጎ መቆም ይቻላል።
ለዚህም የሀገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይገባል። በሁሉም መልኩ ታሪካችንን ማስቀመጥና ዐሻራችንን ማኖር አለብን ። ይህን ሁሉም ዜጋ ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል። ዛሬ የተጀመረው የስንዴ አብዮት ሀገራችንን በዓለም ላይ ካሉ የስንዴ አምራቾች ተርታ አሰልፏታል ። ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር፤ ከስንዴ ተረጂነት ወደ ስንዴ አምራችነት፤ ስንዴን ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ወደ መላክ አሸጋግሯታል። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ጅምር ቢሆንም ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል። የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ፣ የመስኖ እርሻ ሥራዎች ላይ መረባረብ ይገባል።
ታላቁ የዓባይ ግድብ ይሄ ትውልድ በዕውቀቱ ፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ሠርቶና ደግፎ ዓለምን ድንቅ ያሰኘ ታሪካችን ነው። የኮሪደር ልማት፣ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስዋብ፣ ማስፋፋት እና ማደስ፤ እንዲሁም አዳዲሶቹ የገበታ ለሀገር፤ የትውልድ ለሀገር ፤ ጎርጎራ፣ ወንጪ ፣ ጨበራ ጩርጩራ የመሳሰሉት ድንቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተዋል። አቧራ ለብሰው አቧራ መስለው የተቀመጡት ታሪካዊ ቅርሶቻችን ብሔራዊ ቤተመንግሥት ፣ ላልይበላ፣ አጼ ፋሲል ፣ ጅማ አባጅፋር አድሶና አስውቦ ልዩ የቱሪስት መዳረሻዎች እና ሰፊ የገቢ ምንጭ የማድረግ ሥራዎች የዚህ ዘመን የታሪክ ዐሻራዎች ናቸው።
የኤክስፖርት ምርት አቅማችንን በማሳደግ የቡና፣ የሻይቅጠል፣ የቅመማ ቅመም ፣ ማዕድንና ሌሎችም ላይ የተሠራ ሥራ በዓይናችን የምናየው በአፋችን የምንመሰክርለት ውጤቶቻችን ናቸው። ነጻነት ሙሉ የሚሆነው በሁሉም መልኩ ሙሉ ሆኖ መገኘት ሲቻል ነው። በመሆኑም ይሄ ትውልድ የራሱን የልማት ዐሻራ በጉልህ መጻፍ ፤ ሀገራችንን ወደታላቅነቷ የሚመልሱ ታላላቅ የልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባዋል። ብልጽግናችንን በየአቅጣጫውና በየዓይነቱ ማረጋገጥ ከቻልን ኩሩ ሕዝቦች የሚለውን ስማችንን እናስቀጥላለን።
በቀደመው ታሪካችን መኩራታችን እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገራችንን ብልፅግና በሁለንተናዊ መልኩ ማረጋገጥ ይኖርብናል። የልማት ጀግንነታችንን ነጻነታችንን ባረጋገጥንበት ልክ ወደፊት መምጣት ይገባናል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም