
ስመ ጥሩ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቀንቃኝ አማጺያኑ በተቆጣጠሯት ጎማ በምትባል ከተማ የሙዚቃ ቪዲዮ ቀረጻ እያደረገ ሳለ መገደሉ ተሰማ። በመድረክ ስሙ ዴልካት ኤዴንጎ በመባል የሚጠራው ዴልፊን ካቴምቦ ቪኒዋሲኪ አስከሬን ሀሙስ እለት ጎዳና ላይ መገኘቱ ታውቋል።
ሙዚቀኛው ከመገደሉ ቀደም ብሎ ‹‹ኤም 23›› የተሰኙት የኮንጎ አማጺያን ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ድርጊቱን የሚያወግዝ ሙዚቃ ለቆ እንደነበረ ይታወሳል። በአርቲስቱ ሞት ላይ እየወጡ ያሉ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ግለሰቡ የተገደለው በጥይት ተመትቶ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሙዚቀኛው በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ወገኖች በሥራው በመተቸት ከመታወቁም በላይ የፖለቲካ ይዘት ባላቸው ሙዚቃዎቹ በዴሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት ጥርስ ውስጥ በመግባት በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎ እንደነበርም ይታወቃል። አማጺ ቡድኑ ባሳለፍነው ወር ጎማ ከተማን ሲቆጣጠሩ አርቲስቱ በከተማዋ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ታስሮ ነበር። አማጺያኑ ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሕግ ጥላ ስር የነበሩ እስረኞች ሲያመልጡ ሙዚቀኛውም አብሮ እንደወጣ ተነግሯል።
አርቲስቱ ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ ያሉ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማህበረሰቡ መሣሪያ እንዲይዙ አነሳስቷል በሚል የወንጀላ ክስ ከታሰረ በኋላ የፍርድ ሂደቱን እየጠበቀ እንደነበር ተነግሯል። በተጨማሪም እ.አ.አ በ2021 የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ሺሴኬዲን በመዝለፍና ፕሬዚዳንቱ የገቡትን ቃል አልፈጸሙም በሚል ተቃውሞ ሀሰተኛ ዜናዎችን አሰራጭቷል በሚል ክስ አስር አመት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ግን በነጻ ተለቋል።
በተፈጥሮ ሀብት እና በማዕድን የበለጸገችው ምስራቃዊቷን ኮንጎ ለመቆጣጠር የተለያዩ ሃይሎች እየተፋለሙ ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት በአርቲስቱ ግድያ ማን እንተደሳተፈ እስካሁን ግልጽ የሆነ መረጃ እንደሌለ ተገልጿል። የመንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ የሙዚቀኛውን ግድያ አስመልክተው በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ‹አጸያፊ ተግባር፣ ስለሁሉም ፍትህ ይሰፍናል› ብለዋል። ቃል አቀባዩ አያይዘውም በአርቲስቱ ላይ ለተፈጸመው ግድያ ‹‹ኤም 23›› የሚባለውን አማጺ ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል። ከመንግሥት የደረሰውን ውንጀላ በመቃወም ‹‹ኤም 23›› በበኩሉ ጣቱን ወደ መንግሥት ሃይሎች በመጠቆም መሣሪያ እንዲያስረክቡ መጠየቁ ታውቋል።
በማህበራዊ ድህረ ገጽ ላይ የተለቀቁት የቪዲዮ ምስሎች በሰሜን ጎማ ኪሊጂዌ አካባቢ ባለ ጎዳና ላይ የአርቲስቱን አስከሬን አሳይተዋል። ኤዲንጎ ለቪዲዮው ወታደራዊ መለዮ ለብሶ እየሠራ እንደነበረ የተናገሩት የዓይን አማኞች ጥቃቱ እንደተፈጸመ ወዲያውኑ ሕይወቱ ማለፉን ገልጸዋል። የኮንጎ የሥነ ጥበብ እና ባህል ሚኒስቴር ድርጊቱን ‹ግድያ› ሲል የገለጸው ሲሆን አያይዞም ‹በሙያው ለመላው ትውልድ ምኞት እና ተስፋን የፈነጠቀ ቁርጠኛ ድምጻዊ ነበር› ሲል ገልጿል።
የአርቲስቱን ግድያ በመቃወም እንዲሁም እየሆነ ስላለው ነገር ፍትህ ለመጠየቅ በተወለደበት ሰሜናዊ ኪቩ በምትገኘው ቤኒ ከተማ በርካቶች የአደባባይ ተቃውሞ አድርገዋል። ግድያው የተፈጸመው በሩዋንዳ የሚደገፈው ‹‹ኤም 23›› ታጣቂ በሀገሪቱ በተደረገ ከፍተኛ ጦርነት ጎማ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ በተፈጠረ ከፍተኛ ውጥረት እንደሆነ ተገልጿል።
በቅርቡ በሀገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰዎች ሲገደሉ ወደ ሰባት መቶ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ማስታወቁ አይዘነጋም። ግጭቱን በእርቅ ለመቋጨት የተደረገው የቀጣናው ሀገራት ትብብር ፍሬ አለማፍራቱ ሲገለጽ፣ አማጺያኑ ደግሞ ወደ ደቡባዊ ኪቩ መዲና ቡካቩ እየገሰገሱ እንደሚገኝ ታውቋል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም