አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመንን ወደኋላ በትውስታዎቹ እናስታውስ። በአፍሪካ የነጻነት አጥቢያ መሠረቱን የጣለውን የአፍሪካ ህብረት፣ አዲስ አበባ ላይ የተተከለው ምሰሶ ዛሬም ድረስ ዘልቆ 38ኛውን ይዟል። ከወደኋላ ደግሞ በ1952ዓ.ም እና በ1955ዓ.ም ከነበረው በጨረፍታ እንቃኝ። አዲስ አበባ ላይ የነበሩት የግብጹ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ የግድያ ጥቃት ተቃጥቶባቸዋል። በፕሬዚዳንቱ ላይ የግድያ ሙከራ ስለፈጸሙ ሦስቱ ሰዎች መጨረሻም ይነግረናል። ውሻ ሰው መንከሱ ያለ ነው፣ ሰው ውሻ ቢነክስ ግን፤ ወይ ስምንተኛው ሺህ ያስብለን ይሆናል። ይህንኑ ርዕሰ ጉዳይን ጨምሮ ከጳውሎስ ኞኞ “አንድ ጥያቄ አለኝ” ጋር ያስታውሰናል።

የአፍሪካ ዕድል መሠረቱ በአዲስ አበባ ተጣለ

– ካዛብላንካና ሞኖሮቪያ ተሰርዞ አንድ ቻርተር ተፈረመ

የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ የሌሎቹንም ብሎኮችና ቻርተሮችን ሠርዞ የአፍሪቃን አንድነት የሚመሠርተው “የአፍሪቃና የማላጋሲ ሀገሮች ድርጅት ቻርተር ግንቦት 17 ቀን ለግንቦት 18 ቀን አጥቢያ 1955ዓ.ም ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ከ35 ላይ በአፍሪቃ አዳራሽ ተፈርሟል።

በአማርኛ፣ በዓረብኛ፣ በፈረንሣይኛና በእንግሊዝኛ የተጻፈውን ቻርተር የፈረሙት ሰሞኑን ጉባዔ ሲያደርጉ ከሰነበቱ ሃያ ስምንቱ የሀገራትና የመንግሥታት መሪዎች ሲሆኑ የሩዋንዳና የማዳጋስካር መሪዎች ደግሞ በእንደራሴዎቻቸው በኩል አስፈጽመዋል።

(አዲስ ዘመን ግንቦት 19 ቀን 1955ዓ.ም)

ሁለተኛው የአፍሪካ ነጻ መንግሥታት ጉባዔ

-ከ9 ቀን ስብሰባ በኋላ መፈጸም

አሥራ ሁለት ቀኖች ያህል የግልና የይፋ ስብሰባ በማድረግ ላይ ሰንብቶ የነበረው፤ ሁለተኛው የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት ጉባዔ የሥራ ውጤት በሦስት ምድብ አማካይነት ከሰማና በእያንዳንዱ ድምፅ አንቀጽ ከሰጠ በኋላ በክቡር ፕሬዚዳንቱ አማካይነት ሰኔ 18 ቀን 1952 ዓ.ም ተዘግቷል።

(አዲስ ዘመን ሰኔ 19 ቀን 1952ዓ.ም)

በሦስቱ አሸባሪዎች ላይ የሞት ቀጣት ተበየነ

(ኢ.ዜ.አ) የግብጹን ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን አዲስ አበባ ላይ ለመግደል የሞከሩና ሁለት ኢትዮጵያውያንን ገድለው ሶስቱን ያቆሰሉ አሸባሪዎች በሞት እንዲቀጡ ትናንት ያስቻለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ። የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው ሰውፊት ሃሰን፣ አብዱል ቃኒ፣ አብዱል ከሪም አብዱልናዲና አልአረብ ሳዲቅ ሃፊዝ በተባሉ ግብጻውያን ላይ ቅጣቱ የተበየነው አቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ማስረጃ በዝግ ችሎት ላይ ሲመለከት በነበረው ፍርድ ቤት በመረጋገጡ ነው።

(አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 1989ዓ.ም)

ሰው ውሻ ነክሶ ተቀጣ

ኒውተን ዲስተር የሚባል አንድ የሚዙሪ ተወላጅ ሹሺ የምትባል የጎረቤቱን ሰዎች የውሻ ቡችላ ነክሶ ተከሶ በውሻዋ ላይ ስለፈጸመው የነከሣ ወንጀል 3 መቶ ብር ተቀጥቷል።

በንክሻ ወንጀል ክሱን የመሠረተችው ሉሉ የምትባለዋ የውሻዋ ባለቤት፤ ለፍርድ ቤቱ ስታስረዳ፤ ፎስተር ለብዙ ጊዜ ጨዋ ጎረቤታችን ነበር፤ ከውሻዋም ጋር ይዋደዳሉ። ከጊዜ በኋላ የመጣበት የውሻ መንከስ ጠባይ ለእኛም ስለሚተርፍ ሠፈሩን ለቅቆ ይውጣልኝ በማለት አመለከተች።

(አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 1964ዓ.ም)

የሲውዲን ዜጋን የዘረፉት ይፈለጋሉ

(ኢ.ዜ.አ)- አዲስ አበባ ላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በወረዳ 13 የቀይ መስቀል ተወካይ የሲውዲን ዜጋ ላይ የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው በክትትል ከተያዙት ሌላ ለጊዜው ሃይሌ ግዛው የተባለ የቀድሞ አየር ወለድ ባልደረባና አስናቀ ተስፋዬ ከሚባለው ተባባሪው ጋር የተሰወሩ መሆናቸውን የክልል 11 ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በሲውዲናዊው ዜጋ ላይ በተፈጸመው ዘረፋ ከተካፈሉት መካከል የተወሰኑት ከዘረፏቸው ንብረቶች ጋር በፖሊስ ክትትል የተያዙ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

(አዲስ ዘመን ሰኔ 13 ቀን 1986ዓ.ም)

አንድ ጥያቄ አለኝ

-አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

*ከጓደኞቼ ጋር ተቀምጠን ስንጫወት የጂማ ታርጋ ያላቸው 2 መኪናዎች ከፊት ለፊታችን ቆመው አየን። የስሙ አጻጻፍ አንዱ ጂማ ሲል ሌላው ደግሞ ጅማ ይላል። ትክክለኛው የስሙ አጻጻፍ እንዴት ነው?

ይስሐቅ ቀኖ፤ መልኬ ለማ (ከአጋሮ)

-ሁለት ዓይነት ስም የሚጽፈው የጅማ ማዘጋጃ ቤት መልሱን ይስጠን እንጂ፤ እኔ ለራሴ የትኛው ትክክል እንደሆነ አላውቅም።

*በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አራት ኪሎ ስድስት ኪሎ እየተባሉ የሚጠሩት ሥፍራዎች በምን ምክንያት በእንዲህ አይነት ስም ሊጠሩ ቻሉ?

ዘሪሁን ተሰማ

-አራት ኪሎ አራት ማዕዘን መንገድ ስላለውና፤ ስድስት ኪሎም ስድስት ማዕዘን መንገዶች ስላሉት ይመስለኛል።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 1963ዓ.ም)

*ሁሉም በልጅነቱ ያምራል። ነገር ግን እንጀራ በልጅነቱ አያምርም የሚል ትችት አለ። የእንጀራ ልጅ እንጎቻ፣ ወይም ብጥሌ ነው። ታዲያ ይህ አነጋገር ቅዝምዝም ወዲህ፣ ፍየል፣ ወዲያ አልሆነም ወይ፣ ያንተስ አስተያየት እንዴት ነው።

አክባሪህ አየለች ወርዶፍ( ከአርባ ምንጭ)

-እሜትዬ የሚሉት ለኔ አልገባኝም።

(አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 1958ዓ.ም)

*አንዲት ሴት ዕቃ ለመግዛት ከመደብራችን መጥታ ዕቃ ጠየቀች። መልሱ የጅምላ ቤት ነው በማለት ከሥራ ጓደኞቼ ጋር መልስ ሰጠናት። እናንተ በዝባዦች አሁን መብታችን እኩል ነው በማለት ምኑን ልንገርህ ከሰው ልጅ አንደበት በማይወጣ ስድብ ተሳድባ ሔደች። መብት የተሰጠው ለስድብ ያለመሆኑን እባክህን ንገርልኝ?

እድሪስ አህመድ

-እስዋን የሰው ልጅ ላለማድረግ ነው ከሰው ልጅ አንደበት የማይወጣ ስድብ ተሳደበች የምትለው? አንዳንድ መንደር የሚያስቸግሩ ሴቶች ከውጭም ያው ናቸውና መቻል ነው። ንዴታም ደግሞ አለና ይሄንንም አትርሱ። ቆርቋዡም ተናዱአል፤ ተቆርቋዡም ተናደዋል። ይሄም ደግሞ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ስለሚቀር አሁን ዝም እያሉ ማሳለፍ ነው።

(አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 1963 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You