
ወፍ እንደ ሀገሯ ትጮሃለች፣ ጮሃ የማታውቅ ወፍ እለቁ እለቁ ትላለች፣ የሰው ሆዱ የወፍ ወንዱ አይታወቅም፣ የወፍ ዞላ ከቤት ይውላል አሸን ሲፈላ… የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፤ ወፍ ሲንጫጫ፣ ወፍ ሳይቀምሰው፣ ወፍ ነገረችኝ፣ ወፍ ትልቀመው፣ የወፍ እግር፣ በወፍ በረር፣ የአጥር ወፍ አትስማሽ፣ ወፍ ዘራሽ፣ ወፍ አርግፍ… የሚሉ ፈሊጣዊ አነጋገሮች በሀገራችን በስፋት ይነገራሉ:: እነዚህ ምሳሌያዊ እና ፈሊጣዊ አነጋገሮች የሰው ልጅ ከወፍ ጋር ያለውን ቁርኝት የሚገልጹ ናቸው::
ለምሳሌ፤ ወፍ ሲንጫጫ የሚባለው ቀደም ባለው ዘመን ሰዎች እንደ ዛሬው የእጅ ሰዓት እና የእጅ ስልክ ባልነበራቸው ጊዜ የወፎች ድምፅ ንጋትን የሚያውቁበት የማንቂያ ድምፅ ነበር:: ወፎች ንጋትን ያበስራሉ:: የወፍ ዝርያ የሆነው ዶሮ ከወፎች ቀደም ብሎ ንጋትን ያበስራል:: አነጋግ አካባቢ ወፎች በኅብረት ሆነው በመዘመር ንጋትን ያበስራሉ:: ስለዚህ ወፍ ሲንጫጫ የሚባለው ንጋት አካባቢ ያለውን ሰዓት ለመግለጽ ነው:: ወፍ ምሽትንም ትናገራለች:: እየተቀባበሉ የሚዘምሩ ወፎች አሉ:: አንደኛዋ ‹‹መሼ እኮ!›› ስትል፣ ሌላኛዋ ተቀባይ ‹‹ጥቅጥቅ ይበል!›› ትላለች:: ከወፎቹ የሚወጣው ድምፅ እነዚህን ቃላት የሚጠሩ የሚመስል ቃና አለው:: ጥቅጥቅ ይበል የምትለዋ ቦታችንን ይዘናል፣ ቢመሽም ችግር የለውም እንደማለት ነው:: ምንም እንኳን የፀሐይዋ መጥለቅ ቢያስታውቅም ገበሬዎች ይህን የወፎችን ዝማሬ በመስማት እየመሸ መሆኑን ያውቃሉ::
በዚሁ ‹‹የወፍ ቋንቋ›› የሚባለውን እንመልከት:: የወፍ ቋንቋ ማለት ይሄው ነው፤ እየመሸ ወይም እየነጋ መሆኑን ሲናገሩ ማለት ነው:: ይህን የሚያውቀው ታዲያ ሁሉም ሰው አይደለም፤ አባቶች ናቸው:: ወፎች እነዚያን ኅብረ ዝማሬዎች የሚያሰሙት በተለመደው ሰዓት ብቻ ነው፤ ስለዚህ እየመሸ ወይም እየነጋ መሆኑን ማንም ያውቃል:: የወፍ ቋንቋ ችሎታ የሚባለው ግን ከዚህ ያለፈ ነው:: ሰው ሊሞት መሆኑን፣ ወይም የሆነ አደጋ ሊፈጠር መሆኑን፣ ወይም እንግዳ ነገር ሊመጣ መሆኑን ሰዎች ከወፎች ድምፅ በመስማት በልማድ ይናገራሉ:: የወፏን የዜማ ሁኔታ ሰምተው የሚተረጉሙ ሰዎች ናቸው ‹‹እገሌ የወፍ ቋንቋ ይችላል›› የሚባሉት:: ነገርየው ልማዳዊ ስለሆነ ትክክለኛ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል:: ያም ሆኖ ግን የሰው ልጅ ከወፎች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው::
ዛሬ ዓለም አቀፍ የስደተኛ ወፎች ቀን ነው:: ወፎች ከወቅት ወቅት ይሰደዳሉ:: ይህ በሀገራችንም የሚታይ ነው:: ቀኑን ምክንያት በማድረግ በልማዳችን ውስጥ ከወፎች ጋር ያለንን ግንኙነት እናስታውስ::
‹‹ወፍ ነገረችኝ›› የሚባል ፈሊጣዊ ንግግር አለ:: ውስጥ አዋቂ ነገረኝ እንደማለት ነው:: ለምሳሌ፤ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ እንግዶቿን ‹‹ወፍ ነገረችኝ›› እያለች በቀልድ እያዋዛች ስትጠይቅ ሰምቻለሁ:: በጠንካራ የክርክር ቃለ ምልልሶች ውስጥ ‹‹ውስጥ አዋቂ እንደነገረኝ፣ ምንጮቼ እንደነገሩኝ፣ ባገኘሁት መረጃ….›› እየተባለ ይጠየቃል:: በወግና ጨዋታ ውስጥ ደግሞ ‹‹ወፍ ነገረችኝ›› ተብሎ ይጠየቃል:: ወፍ ማንም ስለማያያት እና ምሥጢረኛ ስለሆነች ነው ምሳሌ የተደረገችው::
በማኅበረሰባችን ውስጥ ‹‹የአጥር ወፍ አትስማሽ›› የሚባል ልማድ አለ:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ወደ ከተማ ገብቶ በዘመናዊ መንገድ ወግና ባህል ሆኗል:: የአጥር ወፍ አትስማሽ የሚባለው ለነፍሰ ጡር ሴት ነው:: በድሮው ጊዜ የሕክምና ክትትል ብዙም ስላልነበረ እናቶች የሚወልዱት በልማዳዊ መንገድ ነበር:: በዚህም ምክንያት ምጥ ከጠነከረ ብዙ ስጋትና ጭንቀት ይኖረዋል:: በሚፈጠረው ጭንቀት የአካባቢው ሰው ሁሉ ይሰበሰባል:: ይህ ሳይፈጠር በሰላም ውለጂ ለማለት ነው ‹‹የአጥር ወፍ አትስማሽ›› የሚባለው:: እንኳን የአካባቢው ሰው የግቢው አጥር ላይ ያለችዋ ወፍ ሳትሰማ በሰላም ውለጂ የሚል የመልካም ምኞት መግለጫ ነው::
ይህ ባህልና ልማድ አድጎ (እንበለውና) ዛሬ በከተሞች አካባቢ ፋሽን ሆኗል:: በተለይም ታዋቂ ሴቶችን በድንገት በማስገረም (ሰርፕራይዝ) የተለመደ ሆኗል:: በፈረንጅኛ ቃል ‹‹ቤቢ ሻወር›› የሚሉት ቢበዙም ‹‹የአጥር ወፍ አትስማሽ›› በሚል ተተክቷል:: እንዲያውም በአንድ ትልቅ ፎቶ ቤት እና በሌላ ዲኮር ቤት ውስጥ ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ውስጥ ‹‹ለአጥር ወፍ አትስማሽ›› የሚል ማስታወቂያ አይቼ ሀገርኛ ቃሉን በመጠቀማቸው ደስ ብሎኛል::
‹‹በወፍ በረር›› የሚባለው ፈሊጣዊ አነጋገር በተለይም በጋዜጣ ጽሑፍ ውስጥ የተለመደ ነው:: በወፍ በረር ማለት በፍጥነት ወይም አለፍ አለፍ እያሉ እንደማለት ነው:: በተለይም የዳሰሳ ጽሑፎች ሲጻፉ ‹‹በወፍ በረር›› ማለት የተለመደ ነው::
ወፍ ዘራሽ የሚባል ፈሊጣዊ ንግግርም አለ:: ወፍ ዘራሽ ማለት ሳይዘሩት የሚበቅል ማለት ነው:: ወፎች በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ላይ ያርፋሉ:: ባረፉበት ቅጽበት በአፋቸውም ሆነ በእግራቸው የሰብሉን ወይም ያረፉበትን ተክል ፍሬ ይዘው ይበራሉ:: ፍሬውን በጣሉበት ቦታ ይበቅላል ማለት ነው::
አንድ ሰው ዘፈን ሲዘፍን ለማሾፍ ‹‹ወፎች እረገፉ›› ይባላል:: የድምፅህ ማማር እንኳን ሰው ወፎችን አስደመመ የሚል ምፀት መሆኑ ነው::
በወጣቶች ዘንድ ደግሞ ‹‹ወፍ የለም›› የሚል የአራድኛ ቃል አለ:: ምንም ነገር የለም ለማለት ነው:: ይህ ነገር ልማዳዊ መነሻ አለው:: አንድ ሰው የሆነ ቦታ ሄዶ ሰው ሲያጣ እና አካባቢው ፀጥ ረጭ ሲልበት ‹‹እንኳን ሰው ወፍ አላየኝም›› ይላል:: የሀገር ቤት ሰዎች ምድረ በዳ የሆነን አካባቢ ሲገልጹ ‹‹ወፍ እንኳን የለውም›› ይላሉ:: ከዚያ የተወረሰ ይመስላል በወጣቶች ቋንቋም ‹‹ወፍ የለም›› ሲባል እንሰማለን::
ስለወፎች እና የሰው ልጅ ቁርኝት ይህን ያህል ካልን፤ ዛሬ ዓለም አቀፍ የስደተኛ ወፎች ቀን ነውና ስለ ስደታቸው ደግሞ ጥቂት እንበል::
ወፎች ልክ እንደ ሰው ልጅ ይሰደዳሉ:: የሚሰደዱትም ልክ እንደ ሰው ልጅ ምቹ ሁኔታ በማጣት ነው:: ይህ የወፎች ስደት ወቅትን ጠብቆ የሚደረግ ነው::
አሁን ያለው ወቅት በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓውያኑ (የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ማለት ነው) የክረምት ወቅት አልፎ የመኸር (Spring) ወቅት ያለበት ነው:: በእኛ በኢትዮጵያውያን አቻ ስናደርገው የጥቅምትና የኅዳር ወራት አምሳያ ማለት ነው:: የጥቅምት ወር በኢትዮጵያ አበቦች ፈክተው የሚታዩበት፣ መልክዓ ምድሩ ማራኪ የሚሆንበት ነው:: በዚህ ወቅት ታዲያ አዕዋፋት ይዘምራሉ፤ ይደምቃሉ:: በዚህ ወቅት የወፎችን ቀን ማክበር ነበረብን ማለት ነው:: ይህ ወቅት አልቆ የበጋው ወቅት ሲጀምር ወፎች ይጠፋሉ:: ወድቀው ሲረግፉ ግን አናይም:: ታዲያ የት ሄዱ? ይሰደዳሉ!
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር የዛሬው ቀን የስደተኛ ወፎች ቀን ተብሎ የተከበረው በእነርሱ የመኸር ወቅት አልቆ የበጋ ወቅት ሊገባ ስለሆነ ወፎች መሰደድ ስለሚጀምሩ ነው:: በደቡቡ ንፍቀ ክበብ ደግሞ ክረምት እየመጣ ያለበት ወቅት ነው:: ስለዚህ እነዚህ ወፎች ወደ ደቡብ ንፍቀ ክበብ ይሰደዳሉ:: ባለሙያዎች እንደሚሉት ወፎች አሕጉር አቋርጠው ዓለም አቀፍ ስደት ይሰደዳሉ:: ስለዚህ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ወፎችም ይኖራሉ ማለት ነው:: የኢትዮጵያ ወፎችም ከኅዳር ወር በኋላ ወደ ውጭ ሀገራት ይሰደዳሉ፤ እነሆ በዚህ ወቅት ደግሞ ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ይሆናል:: ለዚህም ነው አንዳንድ ወፎች ድምፃቸውን የምንሰማው በተወሰነ ወቅት ብቻ ነው፤ በሰኔ እና ሐምሌ ድምፃቸውን የምንሰማቸው ወፎች በበጋ ወቅት አንሰማቸውም:: በመስከረምና ጥቅምት የምናያቸው የወፍ ቀለሞች በሌሎች ወራት አናያቸውም:: ይሰደዳሉ ማለት ነው:: ወይም ባለሙያዎች እንደሚሉት አንዳንዶቹ ወፎች ቀለማቸውን ይቀይራሉ:: ሳይንሳዊ ባሕሪዎቻቸውን ለባለሙያ እንተወዋለን!
አዕዋፋት የውበትም፣ የሥነ ምሕዳርም ሚዛን ናቸውና ልንጠብቃቸው ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም