ጉባዔው እንዲሳካ፣ ኢትዮጵያም በከፍታ እንድትገለጥ ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል!

እንግዳ ተቀባይነት፣ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የተሰጠ ልዩ ገጸ በረከት እስኪመስል ድረስ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር ስማቸው ተቆራኝቶ ይገለጻል። እርግጥ ነው፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በዘመን ጅረት ውስጥ በሚነገረው ታሪካቸው እንግዳን ተቀብሎ ማስተናገድ ብቻም ሳይሆን አልምዶ ማኖርን የተካኑ ናቸው።

ዛሬም በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ይሄው ባህልና እሴት አብሮ የዘለቀ፤ የባህሉን ከፍታ ዘመኑ በሚፈልገው አግባብ ገልጦና ዘመኑን መጥኖ መገኘትን ማዕከል አድርጎ ቀጥሏል። ለዚህ አያሌ አብነቶች ቢኖሩም፤ ከሰሞኑ ሲካሄድ የቆየውና ከትናንት በስቲያ መቋጫውን ያገኘው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ እና የኢትዮጵያ ብሎም የኢትዮጵያውያን መስተንግዶ ዛሬም ድባቡ ስላልቀዘቀዘ ማንሳቱ ተገቢ ነው።

ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ መቀመጫነቷ፤ እንደ ሦስተኛ የዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ፤ ለኅብረቱ ጉባዔ መሳካት ቀደም ብላ ነበር ዝግጅቷን ያጠናቀቀችው። ይሄ ዝግጅት ታዲያ ለአፍሪካውያን ሰላምና ደህንነት፣ ምቾትና ተዝናኖት እንዳይለያቸው ከማድረግ ባሻገር፤ በቆይታቸው የኢትዮጵያን መልክ እንዲያዩ እና ልምድና ተሞክሮን እንዲቀምሩ የማድረግ ዓላማም ነበረው።

በተለይ የኅብረቱ ጉባዔ ሰሞን፣ በርካታ አህጉር አቀፍና ዓለምአቀፍ ጉባዔዎች በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ቆይተዋል። በኅብረቱ ጉባዔ የሚሳተፉ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የ46ኛው የኅብረቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባዔ ተሳታፊዎችም ነበሩ። ሌሎች ተሳታፊ እንግዶች፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጭምር በአዲስ አበባ የከተሙበት ነበር።

ለምሳሌ፣ ከኅብረቱ ጉባዔ ጋር በተያያዘ ከ12 ሺህ የሚልቁ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። የሌሎች ጉባዔዎች ተሳታፊዎች ሲታከሉበት ቁጥሩ ከዚህ በእጅጉ ይልቃል። እናም እነዚህ እንግዶች በኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ በአፍሪካ የፖለቲካ መዲና፣ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ ሲከትሙ፤ እንኳን ደህና መጣችሁ ከማለት ባሻገር ቤትን አድምቆ፣ ማጀትን ሞልቶ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አውድን ፈጥሮ ማስተናገድ የግድ ነው።

የነገር ሁሉ መጀመሪያ ፊት እንደመሆኑም፤ እንግዶች የኢትዮጵያን መልክና ፊት የሚመለከቱት አዲስ አበባን እንደረግጡ ነው። ታዲያ አዲስ አበባ ቀደም ብላ መልክና ገጿን አስውባ ነበርና ለዝግጅቱ የተለየ መኳኳል ሳይጠበቅባት ውበቷን አውጥታ መግለጥ ችላለች። በለውቷ እንግዶቿን ማስደመም፤ የኢትዮጵያን የለውጥ ግስጋሴም በምሳሌነት አስመልክታለች።

ይሄ የሆነው ደግሞ እንደ ሀገር በተጀመረው የለውጥ መስመር ተጉዘው አዲስ አበባ የራሷ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መልክ ሆና እንድትገለጽ በሠሯት አመራሮችና ነዋሪዎቿ ነውና፤ አዲስን አስውባችሁ ኢትዮጵያን በከፍታ ለገለጣችሁ ሁሉም የላቀ ምስጋናና ክብር ይገባችኋል። እንደ ዛሬው ሁሉ ለነገውም የተሻለ መልክና ገጿን ገልጣችሁ ኢትዮጵያን ታደምቁ ዘንድም ትጋታችሁ ሊቀጥል ይገባል።

አዲስ አበባ እንግዶቿን የሚማርክ ውበትን ብቻ ሳይሆን፤ በቆይታቸው ሰላምና ደህንነት እንዲሰማቸው የሚያስችል ሙሉ ዝግጅትም ነበር ያደረገችው። በዚህም የደህንነት ተቋማትና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ቀንና ሌሊት ያለ ድካም በልዩ ትጋት ሲሠሩ ቆይተዋል። እንግዶችም ያለ ስጋት እንደ ቤታቸውና ሀገራቸው እንዲሰማቸው ሆነው በነጻነት ወጥተው እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል። እናም ይህ እንዲሆን ላስቻላችሁ የፀጥታ ኃይሎችና ተባባሪ አካላት ሁሉ ክብርም፣ ምስጋናም ይገባችኋል።

ይሄ የፀጥታ ኃይሉ ትጋትና ልፋት ከከተማዋ ሕዝብ መልካም ትብብር፣ ከሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መልካም መስተንግዶ፣ ከከተማዋ ገጽታና የቱሪዝም መዳረሻ ውብ ሥፍራዎች ጋር ሲዳመር፤ እንግዶች ቆይታቸው ያማረ፣ ጉባዔውም ፍሬያማ እንዲሆን አቅም ፈጥሯል። ከዚህም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መልኳ እንዲገለጥ፤ እንደ የነጻነት አርነት በሌላ መልኩ አርዓያ የሆኑ ተግባራትን የምታቋድስ እንድትሆን አድርጓታል።

በጥቅሉ፣ የአፍሪካውያን ዓይንና ጆሮ ከጉባዔው ይጠብቀው የነበረውን ሁሉ በልኩ እንዲያገኝ፤ ለአፍሪካውያን መጻዒ እድል ለመምከር የተገኙ ሁሉ በሙሉ ልባቸው ጉዳያቸው ላይ የሚያተኩሩበት አውድ እንዲፈጠር፤ ጉባዔው ፍሬያማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ ጉባዔያተኞችም በፍጹም ሰላምና ምቾት ውስጥ እንዲቆዩ ከፍ ያለ ሥራ ተሠርቷል። ለዚህ ደግሞ ፖለቲከኞች፣ ዲፕሎማቶች፣ የጸጥታና ደኅንነት ኃይሎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ በጥቅሉም ኢትዮጵያውያን፣ ጉባዔው እንዲሳካ፣ ኢትዮጵያም በከፍታ እንድትገለጥ አድርገዋልና ምስጋና ይገባቸዋል!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You