
በ2014 ዓ.ም በተደረገው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አፍሪካዊ ጉዳዮችን አጉልቶ የሚያሳይ የራሳችን ሚዲያ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን አስታውሳለሁ::
አዎ! ምዕራባውያን ሀገራትን ኃያል ያደረጋቸው መገናኛ ብዙኃን ነው:: እነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሚገኙት በምዕራባውያን እጅ ነው:: ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ‹‹እነ ሲ ኤን ኤንን ‹ዓለም አቀፍ› ያልናቸው እኛ ነን›› ብሎ ነበር:: ዓለም አቀፍ ያደረግንባቸው ምክንያት ግን በመላው ዓለም የሚገኙ ነገሮችን ስለሚዘግቡ እንጂ ይዘቱ ራሳቸውን በሚጠቅም መንገድ ነው::
በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የእርስበርስ ብሽሽቅ ስላለ እነዚህ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ደካማ ጎን እየፈለጉ ሲዘግቡልን እውነተኛነታቸውና የሕዝብ ድምጽነታቸው ይመስለናል:: ነገርየው ግን ሌላ ነው፤ ዋና አጀንዳቸው የራሳቸውን ማግነን እና የየሀገራቸውን ጥቅም ማስጠበቅ መሆኑን ብዙዎቻችን ልብ አንለውም::
ያም ሆነ ይህ ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ለምን የእነርሱ ሚዲያዎች ገናና ሆኑ? ሳይሆን ለምን አፍሪካስ ገናና ሚዲያ አይኖራትም የሚለው ነው መሆን ያለበት::
አፍሪካ ውስጥ እንደነ ቢቢሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ ሮይተርስ፣ አልጀዚራ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒዮርክ ታይምስ፣ ዘ ጋርዲያን… የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸው መገናኛ ብዙኃን የሉም:: በህትመት መገናኛ ዘዴም ሆነ በብሮድካስት ያን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባል የለም:: እነዚህ የምዕራባውያን መገናኛ ዘዴዎች እና አልጀዚራ ናቸው በመላው አፍሪካ እየተዘዋወሩ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ የሚዘግቡልን:: ለዚያም ነው አፍሪካ ችግሮቿ ብቻ የሚዘገቡት::
የመላው አፍሪካን ሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ማወቅ ባይቻል እንኳን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን፤ በአፍሪካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ መፈጠር ያልተቻለበትን ምክንያት መገመት ቀላል ነው፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ የባሱ እንጂ የተሻሉ አይደሉም::
ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ብሽሽቅና የመንግሥታት ፍርርቅ ነበር:: አፍሪካ ውስጥ ደግሞ መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር ነውጥ ይኖራል:: ከገዥው መንግሥት ጎን ለተቃውሞ የተደራጁ አካላት ይኖራሉ:: ይህም ገዥው መንግሥት የተረጋጋ እንዳይሆን ያደርገዋል:: በዚያ ላይ የገዥዎቹ መንግሥታት ባህሪም ነፃነትን የሚፈቅድ አይደለም::
በእነዚህ ምክንያቶች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ልሳን ሲሆኑ፤ የግል መገናኛ ብዙኃን ደግሞ (በተለይ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ) ጭፍን ተቃዋሚና ግጭት አቀጣጣይ ይሆናሉ:: ይባስ ብሎም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የእርስበርስ መወነጃጀል አለ:: ስለዚህ በሀገር ውስጥ ያሉትን መገናኛ ብዙኃን የሀገሬው ሕዝብ አያምናቸውም::
አንድ መገናኛ ብዙኃን ተፅዕኖ ፈጣሪና ተወዳጅ የሚሆነው ደግሞ መጀመሪያ በሀገሩ ሕዝብ ተወዳጅ ሲሆን ነው:: የሀገሩ ሕዝብ ካጣጣለውና ከናቀው ዓለም ለምን ብሎ ይቀበለዋል?
አፍሪካዊ ሚዲያ እንዲኖረን ከማን ምን ይጠበቃል? ከተባለ ሁሉም ነገር ከሁላችንም ነው የሚጠበቀው:: ሁሉም ነገር ከሁላችንም ቢጠበቅም ከመንግሥትና ከሕዝብ ብለን ልንለየው እንችላለን:: ከመንግሥት ነፃነት መስጠት፤ ከሕዝብ ደግሞ በራስ ሀገር ተቋም መኩራትና የራስን ማመን ነው::
እያየነው ያለው ነገር ግን ብሽሽቅ ነው:: አንዳንዱ፤ መንግሥት ምንም እንከን የማይወጣለት አድርጎ ይሠራል፤ አንዳንዱ ደግሞ መንግሥትን የሀገር ጠላት አድርጎ ይሠራል:: ይህ አይነት መካረር የሚያዳክመው የሚዲያ ተቋምን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር ነው፤ ራሱ ፖለቲካውንም ነው::
ሌላው መሰናክል ደግሞ በተለይም የህትመት ሚዲያው ላይ የተጋረጠው የወረቀት ውድነት ነው:: የ2010 ዓ.ም ለውጥ እንደመጣ ብዙ የግል ጋዜጦች ተጀምረው ነበር:: ፖለቲካው ላይ በመንግሥት በኩል የክልከላ ለውጥ ሳይመጣ እነዚህ ጋዜጦች ወዲያውኑ ከሰሙ:: በዚህ ጉዳይ ላይ እኔው ራሴ ዘገባ ሰርቼ ነበር:: የአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው በወቅቱ የሰጠኝ መልስ፤ ጋዜጣዊ የወረቀት ዋጋውን መቋቋም አቅቷት እንደተዘጋች ነው:: ቀጥሎም ሌሎች ጋዜጦች እየተዘጉ ሄዱ:: የቀሩትም መጠናቸውን መቀነስ ጀመሩ፤ አንዳንዶችም በA4 ቅርጽ መታተም ጀመሩ::
ይህ የሆነው እንግዲህ በነፃነት ማጣት ሳይሆን በወረቀት ውድነት ብቻ ተዘጉ ማለት ነው፤ በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ባህል ብዙም ስላልዳበረ አጋር የማግኘት ዕድሉም ጠባብ ነበር::
በወቅቱ የተዘጉት ጋዜጦች አዘጋጆች የሰጡት አስተያየት፤ ነፃነት ቢኖርም በተዘዋዋሪ ግን አሁንም በመንግሥት ቸልተኝነት እንደተቀዛቀዘ ነው:: አንዳንድ ነገሮች ከቀረጥ ነፃ ቢገቡ መንግሥትንም እንደሚያስመሰግኑት ምክረ ሀሳብ አቅርበው ነበር::
እንግዲህ ከሕዝቡም ከመንግሥትም ብዙ ይጠበቃል ስንል መንግሥትም አስቦበት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ፣ ሕዝብም ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ማለት ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ከፈጠርን በአፍሪካ ብሎም በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናል ማለት ነው::
የ“ሲ ጂ ቲ ኤን” ጋዜጠኛ የሆነው ግሩም ጫላ በአንድ ወቅት በ“ሰይፉ በኢ ቢ ኤስ” ፕሮግራም ላይ ቀርቦ አፍሪካዊ ሚዲያ የማቋቋም ዓላማ እንዳለው ገልጾ ነበር:: ምን ላይ እንዳለ ለጊዜው ስላላወቅን የሀሳቡን አስፈላጊነት ብቻ እንውሰድ!
ቀደም ሲል እንዳልኩት አፍሪካዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ለማቋቋም እኛ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ መሆን አለብን:: አባቶቻችን የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ ኢትዮጵያ እንድትሆን ያደረጉትን ጥረት እኛም በዚህኛው መድገም አለብን:: ለዚህ ደግሞ አንዱና ዋናው ሥራ ብሽሽቅና ምቀኝነትን ማቆም ነው:: በፖለቲካው ውስጥ የሚታየውን መጠላለፍ እዚህ ውስጥ አለማስገባት ነው::
ይህን አፍሪካዊ ሚዲያ ለማቋቋም በተለይም ጋዜጠኞች ከፍተኛ ሚና ሊወጡ ይገባል:: የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች እና የቅርቡን የጋዜጠኝነት ሳይንስ የተማሩ ወጣት ጋዜጠኞች በጋራ ሊሠሩ ይገባል:: አንጋፋ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት (እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የቅርቦቹ የግል መገናኛ ብዙኃን) ሙያዊና ቁሳቂ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል:: ምናልባትም የብሮድካስት ሚዲያ ሊሆን ስለሚችል በተለይም የብሮድካስት ሚዲያዎች ትብብር ሊያደርጉ ይገባል::
ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሲሆን፤ ሀገር ውስጥ ካሉን ሚዲያዎች የተሻለ የመሳሪያ ጥራትና አይነት እንደሚያስፈልገው ቢታወቅም ዳሩ ግን በማበረታታትና በማማከር ብዙ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል:: ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን የሚችሉ ጋዜጠኞች፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ልምድ ያላቸው ሰዎች ድጋፍ ቢያደርጉ የታሰበው ነገር በአጭር ጊዜ እውን ይሆናል:: የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ ይሳካ ነበር ማለት ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸው ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ የመፈጸም ልምድ እንዳላቸው በተደጋጋሚ አይተናል፤ ስለዚህ ይህ የሚዲያ ፕሮጀክትም ሊታሰብበት ይገባል:: ይህ ፕሮጀክት ቢጀመር የሀገር ውስጥ ሚዲያዎቻችንም ጠንካራ የመሆን ዕድል ይኖራቸዋልና ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም