
የዛሬዋ የስኬት ዓምድ እንግዳችን ወጣት ሥራ ፈጣሪ ናት:: ላገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ እጅ ሳትሰጥ በተማረችበት የቆዳ ኢንጅነሪግ ዘርፍ ለራሷ ሥራ ፈጥራ ለሌሎችም መትረፍ ችላለች:: በዘርፉ አበረታች ውጤት ካመጡ የትግራይ ክልል ሴት ሥራ ፈጣሪዎች መካከልም በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች::
እንግዳችን ራሕዋ በየነ ትባላለች፤ ተወልዳ ያደገችው ሰቲት ሑመራ ከተማ ሲሆን፣ በትምህርቷ የደረጃ ተማሪ ከሚባሉት መካከል አንዷ ነበረች:: በልጅነቷ ዶክተር የመሆን ሕልም እንደነበራት የምትናገረው ራሕዋ፤ ይኸው ሕልሟ እንዲሳካም ወላጆቿ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉላት እንደነበርም ታስታውሳለች::
ይሁንና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤቷ ሕክምና ለማጥናት የሚያበቃ ባለመሆኑ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ቆዳ ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ገብታ ተማረች:: በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም፣ ለትምህርቷ የተለየ ትኩረት በመስጠትና በርትታ በማጥናት በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀች::
ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላም ዩኒቨርሲቲው እዚያው ቀርታ በመምህርነት እንድታገለግል ዕድል ሰጣት:: ይሁን እንጂ በአንድ በኩል ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ የራሷን ሥራ ፈጥራ ትልቅ ቦታ የመድረስ ራዕይ ስለነበራት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገባች::
ወላጆቿም የፖለቲካው አለመረጋጋት ስላሳሰባቸው አጠገባቸው እንድትሆን ይወተውቷት ያዙ:: በኋላ ሁኔታዎች እየገፉ ሲመጡ ግን ዩኒቨርሲቲው ያቀረበላትን ጥያቄ ‘አሻፈረኝ’ ብላ ወደ ትውልድ ቀዬዋ መመለስን ወደደች:: እናም በትምህርት ላይ የተግባር ሥልጠና ወቅት በሼባ ሌዘር ፋብሪካ የቀሰመችውን ምርጥ ተሞክሮ አቅምም፣ መነሳሳትንም ፈጥሮላት ስለነበር፤ ከቅጥር ይልቅ የራስን ሥራ መሥራት ለሚለው እሳቤዋ መሳካት በአዳዲስና ዘመኑን ከሚዋጁ የፈጠራ ሥራዎች ጋር በማጣመር የቆዳ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት አደረባት::
ይህንን ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የሚያስችሏትን አማራጮች ሁሉ አሰበች:: ከቤተሰቦቿም ጋር ተማከረች፤ በዘርፉ ብዙ ከቆዩ ሰዎች ተሞክሮ ለመቅሰም የራሷን ጥረት አደረገች:: ሆኖም ላሰበችው ሥራ ከሰቲት ሑመራ ይልቅ ሼባ ሌዘር ፋብሪካ ከሚገኝባት ውቅሮ ከተማ ቢሆን የበለጠ አዋጭ እንደሚሆንላት አመነች:: እናም ከቤተሰቦቿ ያገኘቻትን አራት ሺህ ብር ይዛ ውቅሮ ከተማ ቤት ተከራይታ ከተመች::
ወደ ራሷ ሥራ ከመግባቷ በፊት ግን ለሥራዋ የመዳረሻ አቅምና ልምድ ማግኘት እንዳለባት በቅድሚያ ሰፋ ያለ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባት አሰበች:: እናም ለዚህ ትክክለኛው ቦታ በፋብሪካው የቅጠሩኝ ጥያቄ ማቅረብ ነበር:: ሆኖም እንዳሰበችው በፋብሪካው የመቀጠሩ ጉዳይ ቀላል አልነበረም፤ የፋብሪካው ኃላፊዎች በቂ ሠራተኛ እንዳላቸውና ሲፈልጓት እንደሚጠሯት ነግረዋት እያዘነች ወደ ቤትዋ ተመለሰች::
በተለይም ደግሞ በወቅቱ ለቤት ኪራይም ሆነ ለምግብ ፍጆታዋ ሳይቀር እጇ ላይ የነበረው ገንዝብ አልቆ ስለነበር እጅግ ተጨንቃ እንደነበር ታስታውሳለች:: አበው ‘ችግር ብልሃትን ይወልዳል’ እንዲሉ፤ ለችግሯ እጅ ሰጥታና ተጨንቃ እጆቿን አጣጥፋ አልተቀመጠችም፤ ለፍተው ያስተማሯትን ቤተሰቦቿንም ማስጨነቅ አልመረጠችም::
ይልቁንም ገና ተማሪ ሳለች የቆዳ እጅ ሥራ ውጤቶች የማምረት ክህሎት አዳብራ ስለነበር ይህንን ክህሎቷን ለመጠቀምና ጊዜያዊ ችግሯን ለመፍታት ወሰነች:: እናም ቤቷ ሆና የቆዳ እጅ ሥራ ውጤት የሆኑ አነስተኛ የኪስ ቦርሳዎችን እየሠራች ለምታውቃቸው ሰዎች በመሸጥ ኑሮዋን መደጎም ያዘች:: የአካባቢው ኅብረተሰብ የራሕዋን የእጅ ሥራ ውጤት ወደደው:: ግን ደግሞ የማኅበረሰቡ አቅም አነስተኛ በመሆኑና የምትሸጠው በርካሽ ስለነበር ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ለመኖር ተገደደች::
በዚህም ተስፋ አልቆረጠችም፤ ከእጅ ሥራዎቿ ጎን ለጎንም የቆዳ ማኑፋክቸሪንግ ሥራ ለመጀመር የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የማሟላት ሥራ ለአንድ ዓመት ያህል ቀጠለች:: እናም ወደ ሕልሟ ለመድረስ መንገዱን አንድ አለች:: ይሄን ጉዳይ አስመልክታ ራሕዋ ስትናገር፡-
‹‹በ2012 ዓ.ም ፈቃድ ካወጣሁ በኋላ ከቤተሰቦቼ ያገኘሁትን 30 ሺህ ብር ገደማ በመቆጠብ በ150 ሺህ ብር ስድስት የቆዳ ስፌት ማሽኖችን አዘዝኩኝ፤ በተጨማሪም ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ 300 ሺህ ብር ብድር ወሰድኩኝ›› በማለት ከቤት ውስጥ አነስተኛ ሥራ ወደ ቆዳ ኢንዱስትሪው የተቀላቀለችበትን አጋጣሚ ታስታውሳለች:: እንደዕድል ሆኖ ግን ማሽኖቹን በተረከበች በሳምንቱ የሰሜኑ ጦርነት ተነሳ እና የልጅነት ሕልሟን እንዲሁም በዘርፉ የነበራትን የማደግ ተስፋ ሁሉ የሚያጨልም ሁኔታ ተፈጠረ:: ይህ አልበቃ ብሎ በብድር ያስመጣቻቸው ማሽኖች መካከል የተወሰኑት ገና ሥራ ሳትጀምር በጦርነቱ ተወሰዱባት::
በውቅሮም ሆነ በመላው ትግራይ የጦርነቱ ወላፍን የገረፋቸው በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተዘጉበት በዚያ የጭንቅ ወቅት ግን ወጣቷ ራሕዋ ሕልሟ ዳር እስከሚደርስላት ድረስ ተረጋግታ መቀመጥ አልቻለችም:: ጦርነቱን ፈርታ ከመሸሽ ይልቅ የጥይት ድሞፆች እየሰማች፤ በሌላ በኩል ለወራት ድምፃቸውን ያልሰማቻቸው ቤተሰቦቿ ጋር የመጠፋፋቷ ጉዳይ እያስጨነቃት የእጅ ሥራ የሆኑ የቆዳ ውጤቶቿን ከቀጠረቻቸው አምስት ወጣቶች ጋር በመሆን ማምረቷን ቀጠለች:: በተለይም ደግሞ ዘመኑ የሚሻውን የፋሽን ሥራዎችን በአነስተኛ ዋጋ ጥራት ያለው ምርት የማምረት መርሆ ይዛ ለችግሮች ጆሮ ሳትሰጥ ቀን ከሌሊት በማምረት ሥራ ተጠመደች::
ለከፈተችው ፋብሪካ የመጀመሪያ ምርት የሆነውን በዲዛይኑ አዲስ የሆነ በእጅ የተሠራ ጫማዋን ለተጠቃሚዎቿ ‘እንካችሁ!’ አለች:: አዲሱን የራሕዋን ጫማ ጥራት ወደው የሚገዙ ደንበኞች ቁጥር እየተበራከተ መጣ:: አቅሟን እያጎለበተች በመምጣትም ቀበቶ፤ በተለያዩ ዲዛይኖች የተማሪዎች፤ የጉዞ እና የኪስ ቦርሳዎች እንዲሁም የተለያዩ ፋሽን ያላቸው ጫማዎች በማምረት የክልሉን የቆዳ ኢንዱስትሪ ማሳደግ ጀመረች:: የሠራተኞቿን ቁጥርም ወደ 14 ማሳደግ የቻለች ሲሆንም የምትሠራባቸው ማሽኖችና ግብዓቶችን ሳይጨምር ካፒታሏን ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር አሳድጋለች::
‹‹አሁን ላይ በየቀኑ ከ24 ያላነሰ በእጅ የተሠራ ጫማ እና በርካታ ቦርሳዎችን በማምረት ለቸርቻሪ ሱቆች በስፋት አከፋፍላለሁ›› የምትለው ሥራ ፈጣሪዋ፤ የክልሉ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በሚያዘጋጃቸው ኤግዚቢሽን እና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ምርቶቿን ወደ ተጠቃሚዎች የምታደርስ መሆኑን ታስረዳለች:: በክልል ሳትወሰንም በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ላይ የግሏን የመሸጫ ሱቅ ከፍታለች::
በውቅሮ ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት ተካሂዶ በነበረው የሥራ ፈጠራ ውድድር አንደኛ በመውጣት የእውቅና ሰርተፍኬት ማግኘቷን አስታውሳ ‹‹በተጨማሪም አስተዳደሩ ለዘርፍ እድገት እያበረከትኩት ባለው አስተዋፅዖ የመሥሪያና መሸጫ ቦታ እንደሚሰጠኝ ቃል የተገባልኝ ቢሆንም፣ ባለው ቢሮክራሲ ምክንያት እስከአሁን በእጄ አልተረከብኩም›› ትላለች::
አሁን ላይ እያመረተች ያለችበትና በከተማ አስተዳደሩ የተሰጣት የማምረቻ ሼድ ከሥራው ባሕሪ አንፃር ለማምረት ምቹ አለመሆኑን ራሕዋ ታስረዳለች:: መሬቱን እንደተረከበች ግን ፋብሪካዋን ወደ ከፍተኛ የቆዳ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እቅድ መያዟንም ትናገራለች::
‹‹አሁን ላይ በፋይናንስ አቅም ውስንነት ምክንያት የማመርተው ምርት በጣም አነስተኛ የሚባል ነው›› የምትለው ወጣት ራሕዋ፤ ብድር የምታገኝበት ሁኔታ ከተመቻቸላት ግን ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁና አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ፍላጎት ያላት መሆኑንም ነው የገለጸችው::
ይህም ደግሞ በከተማዋ ትምህርታቸውን አጠናቀው ያለሥራ ለተቀመጡ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችላት መሆኑን፤ በተለይም ለሴቶች የተለየ ዕድል ለመፍጠር ያላትን ከፍ ያለ መሻት እንደሚያሳካላትም ነው ወጣት ራሕዋ የምትናገረው:: ይህ ሕልሟ እንዲሳካ ግን የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነ ታሰምርበታለች:: በዋናነት ደግሞ በሽልማት ያገኘችውን የማምረቻና የመሸጫ ቦታ በአፋጣኝ በእጇ ቢያስረክቧት ከከተማዋና ከክልልም አልፎ ለሀገር ጭምር የሚጠቅም ኢንዱስትሪ ለመክፈት ጓጉታለች::
የቆዳ ኢንዱስትሪው ተዋንያዋ ራሕዋ በየነ አሁን ላይ ምንም እንኳን እንዳሰበችው ከፍተኛ አቅም ላይ ባትደርስም፤ ያላትን ለሌላቸው በማካፈልም ሆነ ማኅበራዊ ኃላፊነቷን በመወጣት ረገድም አትታማም:: በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የተቻላትን ያህል በመደጎም በከተማዋ ትታወቃለች:: ካደረገቻቸው ድጋፎች መካከልም ለሴት ተፈናቃዮችና በሕክምና ላይ ላሉ ሕሙማን የሚሆን የንፅሕና መጠበቂያ የሚሆን ድጋፏ ተጠቃሽ ነው::
‹‹እኔ በብዙ ፈተና ውስጥ አልፌ እዚህ ብደርስም፤ በርካታ ሴቶችና ወጣቶች አቅሙም ሆነ መሻቱ እያላቸው ጦርነት ባመጣባቸው ችግር ምክንያት የሌሎችን እጅ ለማየት ተገደው ስመለከት ልቤ ክፉኛ ይነካል:: ለዚህም ነው ከሁሉ በላይ በጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎችን መደገፍ የሚያስደስተኝ›› ትላለች::
አቅመ ደካማና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ለማገዝ የግድ ሀብታም መሆን አይጠበቅብንም የምትለው ራሕዋ፤ ችግረኞችን እያዩ ከማለፍ ይልቅ አቅም በፈቀደ ሁሉ መደገፍ የሕሊና እረፍት እንዳለው ታምናለች:: በተለይም በአሁኑ ወቅት እየቀነሰ የመጣው የመረዳዳት ባሕል እንዲመለስ ማድረግ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ ተግባር ነው ባይ ነች::
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የመንግሥትንና የቀጣሪ ድርጅቶችን በር በማንኳኳት ጊዜያቸውን የሚያባክኑ ወጣቶች ወደ ራሳቸው እንዲመለከቱ ሥራ ፈጣሪዋ ወጣት ራሕዋ ትመክራለች:: ‹‹የትኛውም ስኬት ያለ ሥራ፣ ያለልፋት አይመጣም፤ አልጋ በአልጋ የሆነ መንገድም የለም›› የምትለው ራሕዋ፤ ትንሽ ጥረት አድርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሳካላቸው የሚጠብቁና ቶሎ ተስፋ የሚቆርጡ ወጣቶች የሚሹት ቦታ ለመድረስ ዕለት ዕለት በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ታስገነዝባለች::
ለዚህም ‹‹የእኔ ሕይወት ብዙ አስተማሪ ነው፤ በሥነ-ልቦናም ሆነ በአካልም፣ አልፎም ሕይወት እስከሚያሳጡ ነገሮች ድረስ በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሜ ማለፍ ችያለሁ፤ በመሆኑም የትኛው ወጣት ውጣ ውረዶችን በፅናት በማለፍ ከሠራ ስኬታማ መሆኑ አይቀርም›› በማለት የራሷን የውጣ ውረድ መንገድ እንደ አብነት በማንሳት መክራለች::
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም