አይ ልጅነት ደጉ! ልጅነት እኮ በጣም ደግ ነገር ነው፡፡ ‹‹ለምን›› በሉኝ፤ በልጅነት ሁሉን ነገር የምንረዳው በየዋህነት ነበር፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያት ከራሴ ተነስቼ ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ሬዲዮ በጣም ነበር የምወደው፡፡ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ትኩረት ሰጥቼ ነበር የምከታተል፡፡ በፊት በሬዲዮ የምሰማቸው የማን ብሄር እንደሆነ የማላውቃቸው ደስ የሚሉኝ ሙዚቃዎች ነበሩ፡፡ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ግን ጋዜጠኛው ስለዚያ ዘፋኝ ታሪክና የማንን ብሄር እንደተጫወተ ሲናገር ‹‹ኧሃ ለካ ይሄ ዘፈን የእንትን ብሄር ነበር›› እያልኩ ማወቅ እጀምራለሁ፡፡
ሌላው ደግሞ ስለኢትዮጵያ የማውቀው ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ የእገሌ ዋና ከተማ ማነው? እገሌ ተራራ የት ይገኛል? እገሌ ዋሻ የት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እንጠያየቅ ነበር፤ ፈተናም ይመጡ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህን የምናውቃቸው በእንዲህ አይነት አጋጣሚ ሲነገሩ ነበር፡፡ እንዲያውም እዚህ ላይ እኔ ጎበዝ ነበርኩ፡፡ ግን እኮ የአገርን ታሪክ ማወቅ ማለትም ይሄ ነው፡፡
በተለይም የሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት እያለሁ ደግሞ ከዚህም አለፍ ያሉ ነገሮችን መረዳት ጀመርኩ፡፡ ለምሳሌ የሚቀርቡ ጥናቶችን፣ የሚደረጉ ውይይቶችን፣ ስለ ህገ መንግስት ማወቅ መከታተል ጀመርኩ፡፡
እንግዲህ ከዚህ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ያለው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ እንደነበረው አይደለም፡፡ ሁኔታው እየተቀየረ መጣ፡፡ ለብሔር ብሄረሰቦች ቀን ያለኝ ትኩረት እየቀነሰ ነው የመጣው፤ አለፍ ሲልም የምጠላበት አጋጣሚ ሁሉ ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ መድረኩ ላይ ባለሥልጣናት የሚናገሩት ነገር አሰልቺ በመሆኑ ነው፡፡ የሚያወሩት ስለብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ታሪክ ሳይሆን ስለአለፈ ሥርዓት ሰይጣናዊነትና ስለእነርሱ ቅዱሳዊነት ነው፡፡ ብሄር ብሄረሰቦችን እነርሱ የፈጠሯቸው ይመስል ከዚህ በፊት ያልነበሩ ሁሉ ያስመስሉታል፡፡
ለማንኛውም ከእኔ ግላዊ ሁኔታ እንውጣና እስኪ ስለአጠቃላይ አከባበሩ እናውራ፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበር ከጀመረ እነሆ 13ኛ ዓመቱን አስቆጠረ፡፡ ከ13ቱ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን በቀጥታ ሥርጭት ተከታትያለሁ፡፡ አንደኛውን ደግሞ በአካል የሚከበርበት ስቴዲየም ውስጥ ሆኜ ተከታትያለሁ፡፡ ከዕለተ ቀኑ በተጨማሪም በሰሞኑ የሚዘገቡ ዘገባዎችንና የሚሰሩ ፕሮግራሞችን ተከታትያለሁ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ጥሩ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮችም አሉ፡፡
እንዲያውም ከስሙ እንነሳ፤ ‹‹የብሄር ብሄረሰብ ቀን›› ማለት ምን ማለት ነው? ጠለቅ ያለ ሳይንሳዊ ትንታኔ የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ማለት በቃ ብሄር ብሄረሰቦች ባህላቸውን የሚያሳዩበት ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው በውስጡ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን በዚህ ዕለት እውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ይታያል? ነገሩን ግልጽ እናድርገው፡፡
በብሄር ብሄረሰቦች ቀን የሚታየው ትርዒት ትክክለኛ እዚያ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች የሚያሳዩት ሳይሆን በአማተርም ይሁን በትልልቅ አርቲስቶች ትወና ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ቴአትር ወይም ፊልም እንጂ ትክክለኛው ባህል አይሆንም፡፡ እርግጥ ነው አቅራቢዎቹ እዚያው አካባቢ ተወልደው ያደጉ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን በየባህል ማዕከሉ የሚሰሩ የኪነት ቡድን አባላት ናቸው፡፡ ከኪነት ቡድን አባላቱ በላይ የአካባቢውን ባህል የሚገልጹት ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ይሄም ይሁን ግድየለም፤ ትርዒቱን የሚያሳዩት በየዓመቱ ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው፡፡
የመጀመሪያው ዓመት አዲስ አበባ የሄደው በዓመቱ ሐዋሳ፣ ቀጥሎ ድሬዳዋ፣ ቀጥሎ መቀሌ…. እያለ በሁሉም ቀኖች ላይ የሚገኝ አይጠፋም፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን እንግዲህ ሌሎች አልተሳተፉም ማለት እኮ ነው፡፡ ይሄ እኮ ቱባ(Typical) የሚባለው ባህል ነው፤ ስለዚህ ለምን በከያኒያን ይቀርባል? በየባህል ማዕከሉ የኪነት ቡድን የሚቀርበው እኮ ሁሌም በቴሌቪዥን የምየናው ማለት ነው፡፡
እሺ ይሄም ይሁን ብለን እንለፈው፡፡ በከያኒያኑ የተሰራው ራሱ በአግባቡ ይታያል? ለዚያ ዝግጅት ከስድስት ወር ያላነሰ ጊዜ ባክኖበታል፡፡ ለዝግጅቱ ጊዜና ገንዘብ ባክኗል፡፡ ዝግጅቱን ለማሳየት እስከ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዙም አሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ድካም ተደክሞበት ግን ዝግጅቱ አይታይም፡፡ እርግጥ ነው ማታ በዋዜማ የሚደረግ ዝግጅትም አለ፤ ያ የዋዜማው ዝግጅት ግን የታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሥራ የሚቀርብበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዋዜማው ዝግጅት ላይ ባለሥልጣናትና የተለዩ ሰዎች ብቻ የሚገኙበት ነው፡፡
ዋናው ዝግጅትና ብዛት ያለው ታዳሚ የሚገኘው በዕለቱ ነው፡፡ በዚያን ቀን ግን ያ ሁሉ የተደከመበት ሥራ አይታይም፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን የአለባበስ፣ የአጨፋፈርም ሆነ ሌላ ትዕይንት ለማየት የሚገባ ሰው ማየት አይችልም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው የሚያሳዩበት መድረክ በቂ ስለማይሆን ነው፡፡ ይሄ ማለት ሙሉ በሙሉ አያቀርቡም ማለቴ አይደለም፡፡
መድረክ መሪው ‹‹አሁን የእገሌ ብሔር ባህላዊ ትርዕቱን እያሳየ ያልፋል›› ይላል፡፡ መጀመሪያ ላይ የተጠራው ምናልባት ትንሽ የመታየት ዕድል ያገኝ ይሆናል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ግን እያከታተለ ‹‹ቀጥሎ የእገሌ ብሄር …›› እያለ ሁሉንም ይጠራል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ የሚያልፈው ብሄር የማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ እንዲያውም መድረክ መሪው የሚሰጠው ማብራሪያና በክቡር ትሪቡኑ ሥር የሚያልፈው ብሔር ሌላና ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ እሱ በፍጥነት የትግራይን ጠርቶ ቀጥሎ የአማራን ቀጥሎ የኦሮሚያን ሊጠራ ይችላል፡፡
ስለሱማሌ ብሄር እያወራ የሚያልፈው ግን ገና የኦሮሚያ ወይም የአማራ ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ቀኑ የብሄር ብሄረሰቦች ባህል ታየበት ነው የሚባለው?
ቢያንስ ቢያንስ አንድ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔሮች ብቻ እንኳን በአንድ ጊዜ ቢያልፉ፡፡ እነርሱም ገለጻ እየተደረገ ተራ በተራ፡፡ አንዱን ክልል ጨርሶ ቦታ ከያዘ በኋላ ሌላውን ክልል ደግሞ ማሳለፍ፡፡ ይህ የማይመች ከሆነ መተው እንጂ እያደበላለቁ ማሳለፍ ምንም የሚገልጸው ነገር የለውም፤ ምናልባትም የሚያውቁት የዚያው አካባቢ ሰዎች ናቸው፡፡ ለእነርሱ ከሆነ ደግሞ ያን ያህል ጊዜና ገንዘብ ማባከን ለምን አስፈለገ?
እርግጥ ነው አሁን ባልኩት መንገድ ለማሳካት ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ በጠዋት እንዳይጀመር ደግሞ ወደ ስቴዲየም ሰፊ ህዝብ ስለሚገባ ይህም ያቆያል፡፡ አዘጋጁ አካል ምንም ዘዴ ይጠቀም ምን ብቻ ግን ዋናው ነገር በብሔር ብሔረሰቦች ቀን መታየት ያለበት የብሄር ብሄረሰቦች ባህል ይሁን!
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ዋለልኝ አየለ