
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት መካከል መተባበር እና ውህደት እንዲፈጠር የተለመደውን ግንባር ቀደም ሚና መወጣት አለባት ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ::
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ ግንባር ቀደም ታሪካ ያላት እንደመሆኗ ሁሉ አሁንም በአፍሪካ ሀገራት መካከል መተባበር እና ውህደት እንዲፈጠር የተለመደውን የግንባር ቀደምትነት ሚናዋን መወጣት ይኖርባታል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ አፍሪካ መብትና ጥቅም አጠናክራ መሞገት እንደሚገባትም ገልጸዋል::
እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ጉባኤዎች በመዲናችን አዲስ አበባ መደረጋቸው ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ እንድታጠናክርና ተሰሚ እና በጎ ተጽእኖ ፈጣሪነቷን እንድታስቀጥል እድል ይፈጥርላታል::
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን ተሰሚነት እና በጎ ተጽእኖ ፈጣሪነት አስቀጥላ ለመቆየት ከዚህ በፊት እንደምታደርገው ሁሉ የሁለትዮሽ እና የብዝሃ ሀገራት ግንኙነቷን አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል:: ለዚህም እንደ አፍሪካ ኅብረት ጉባኤ አይነት ታላላቅ መድረኮች በከተማዋ መደረጋቸው ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል::
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ነጻነታቸውን ጠብቀው ከቆዩ ጥቂት ሀገራት አንዷ መሆኗን እና ነጻነቷን ሊገዳደር የመጣ ወራሪ ኃይል መክታ በመመለስ ታሪክ ማስመዝገቧንም አምባሳደሩ አስታውሰዋል:: በዚህም ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት ከመሆን አልፋ፤ የወታደራዊ እና የሥልጠና ድጋፍ በማድረግ ለሌሎች ነጻነት መታገሏንም ጠቁመዋል::
የአፍሪካ ነጻነት እንዲፋጠን፤ እንዲረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲኖር ለማድረግ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ግንባር ቀደም ሚና መወጣቷን ገልጸዋል፤ ይሄንን ታሪካዊ ሀቅ የሚረዱ ሀገራት ሁሌም ምስጋና የሚቸሯት እንደሆነም ጠቅሰዋል:: አሁንም ኢትዮጵያ አፍሪካን ወደ አንድነት በማምጣትና የአፍሪካን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር የመሪነት ሚናዋን መወጣት ይጠበቅባታል ነው ያሉት::
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን የሚገልጹት አምባሳደሩ፤ ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳይ ለማከናወን የሰላም ዋጋ ትልቅ መሆኑን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿንም ሆነ የዓለምን ሰላም እንደራሷ ሰላም በመመልከት በተለያዩ ሀገራት በሰላም ማስከበር ሥራዎች ተሳትፋለች ብለዋል:: በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በቡርንዲ፣ በርዋንዳ፣ በሱዳን እና በሱማሊያ ሀገራት ሰላም ለማስከበር የራሷን አስተዋጽ ማበርከቷንም አመላክተዋል::
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል መሆኗ በሰላም ማስከበር ከፍተኛ ልምድ ያላት ሀገር ስለሆነች ለምክር ቤቱ ትልቅ ልምድ እንድታካፍል እና አሁንም ለአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ ጠንካራ አስተዋጽኦ እንድታደርግ እድል ይፈጥርላታል ብለዋል::
ኢትዮጵያ አንዷ የአፍሪካ ሀገር በመሆኗ የአህጉሪቱ ልማት፣ አንድነት እና ብልፅግና የእሷም ስኬት ነው:: አሁንም የምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና አለው:: ሌሎችም የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያን እንዲረዷትም እድል ይፈጥራል:: ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ እና ለሌሎች ግንኙነትም የራሱን ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል::
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም