ኤልዳ – የአካል ጉዳተኞች ድምጽ

‹‹ችሎቱ መሀል አንዲት መስማት የተሳናት እጆቿን ወደላይ ዘርግታ በፀጥታ ታነባለች፡- ዳኞቹ ግራ ቢገባቸው የምልክት ቋንቋ ተርጓሚ ፈለጉና ሀሳቧን ተቀበሉዋት። መጀመሪያ በተኛሁበት በደረቀ ሌሊት በር ሰብሮ ገብቶ ደፈረኝ፤ኋላ ደግሞ ልጁ የእኔ አይደለም ብሎ ካደና ቀለብ አልሰፍርም አለኝ አለች፡፡ ይህን ስሰማ ልቤ ክፉኛ አዝኖ መላ መታሁ፡፡ የሙያ አጋሮቼን አስተባብሬ ኤልዳ (ኢትዮጵያን ሎየር ዲሲብሊቲ አሶሴሽን/ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማህበርን) አቋቋምን፤ በዚህም ምክንያት ፍትህ ላጡ ለአካል ጉዳተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች ድምጽ መሆን ችለናል›› ሲሉ የኤልዳ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሴ ጥላሁን የማህበሩን ቁመና ሊያስቃኙኝ ገጠመኛቸውን በማስቀደም ሀሳባቸውን ጀመሩ፡፡

ሌሎች የአካል ጉዳተኛ ማህበራት የአገልግሎት ትኩረታቸው ልማት ተኮር ሲሆን አካታች ትምህርት፣ የሥራ ቅጥርና ግንዛቤ ፈጠራ የሚሉ አብይ ጉዳዮችን ከዳር ለማድረስ የሀብት ምንጭ በማፈላለግና ፕሮጀክት በመቅረፅ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይሁን እንጂ ሂደቱ የተሳሳተ ምልከታ አለው፡፡ ይህም የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ እንደ በጐ አድራጐት አድርጐ መውሰድ ከግለሰብ እስከ ተቋማት ድረስ ክፍተቱ ጐልቶ ይታያል፡፡

ኤልዳ ግን የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ሰብአዊ መብት ተኮር መልክ እንዲይዝና መንግሥታዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተዘረጋውን የሕግ ማሕቀፍ ማክበር ግዴታቸው እንደሆነ ለማስገንዘብ ተከታታይ ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ለራሱ ለአካል ጉዳተኛውም ቢሆን የተሰጡትን ሕጋዊ መብቶች አውቆ እንዲጠቀም ለማስቻል የማንቃት ሥራ ይሠራል፡፡ መብትና ግዴታዎች በሕገ ደንብ ሰፍረው የአካል ጉዳተኞች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከመወትወት ባሻገር የማህበሩ አባላት ሙያና ክህሎታቸውን ተጠቅሞ የነፃ ሕግ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በመሥራት ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አንፃር ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ሥራዎች ውስጥ ምን ያህል አካል ጉዳተኞችን አካታች እንደሆነ ይፈትሻል፡፡ በአካልም ሆነ በልዩ ልዩ መገናኛ አውታሮች የምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ስለ ሀገርና ዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎችም የአካል ጉዳተኛውን አቅም ለመገንባት በሀዋሳ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ አዳማ፣ ሰበታና አዲስ አበባ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ማስተማር ችሏል፤ በዚህም አመርቂ ውጤት ታይቷል፡፡ ኤልዳ የነፃ ሕግ ድጋፉን የሚሰጠው ለአካል ጉዳተኛ ቤተሰቦችም ጭምር ሲሆን በዋናነት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥሰት መገለጫው የአድሎአዊነት መኖር ነው።

በዚህም ምክንያት አካል ጉዳተኞች ከብዙ መድረኮች ይገለላሉ። የስልጣን ባለቤት አይደለም። የትምህርት እድል በሚፈለገው ልክ አያገኙም። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተዳምረው አምራችና ውሳኔ መስጠት የሚችል አካል ጉዳተኛ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ይህን ለመቅረፍ ኤልዳ በቀየሰው መንገድ 400 የሚጠጉ አካል ጉዳተኞች የነፃ ሕግ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከተሰሩት ጉዳዮች ውስጥ አብላጫውን የሚይዝ ውርስ ሲሆን፤ በርካታ መስማት የተሳናቸው የነፃ ሕግ ድጋፍ አገልግሎቱን በቀዳሚነት አግኝተዋል፡፡ በመቀሌና አዲስ አበባ የሥራ ቅጥር፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ትምህርትና ጤናን አስመልክቶ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምን እንደሚመስል ሪፖርት ያዘጋጃል፡፡ ምንም እንኳን ኤልዳ ከተቋቋመ አምስት ዓመት ቢሆነውም ከኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ማህበር፣ ከፍቅር የአእምሮ እድገት ውስንነት ማህበር፣ ከኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበርና ከኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ጋር በትብብር መሥራቱ አካል ጉዳተኞችን በቀላሉ ለማግኘት ከመቻሉም በተጨማሪ ሀብታቸውን በጋራ መጠቀሙ ፍሬአማ አድርጐታል፡፡

ከተማችንም እየሄደችበት ካለው ፈጣን የመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ምቹ የመንገድ ሥርዓት እንዲፈጠር በኢትዮጵያ መንገድ ደህንነት ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር ከፌዴራል ትራፊክ ማኔጅመንትና ከተባበሩት መንግሥታት የትራንስፖርት ድርጅት የተወከሉ ሰዎች በተገኙበት ሰፊ ስልጠና አዘጋጅቷል፡፡ የዚህ ስልጠና ውጤትም ከኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ጋር በመቀናጀት በየዓመቱ ጥቅምት 5 የነጭ በትር ቀን ታስቦ እንዲውል ከማድረጉም በላይ ለትራፊክ ባለሙያዎችና ለአሽከርካሪዎች በመንገድ የነጭ በትር አገልግሎትን እንዲያውቁ ሰፊ ትምህርት ሰጥቷል፡፡

በየዘርፉ ግንዛቤ መፍጠር ቢያስፈልግም በመመሪያና በፖሊሲ ካልተደገፈ ዘላቂነት ስለማይኖረው በዘመቻ መልክ ተጀምሮ እንዳይቀር ኤልዳ ትኩረቱ የሕግ ማሕቀፉ ላይ ነው፡፡ ይህ ጥረቱ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከግለሰባዊ ቅንነት መንጠልጠል ተላቆ ተቋማዊ መሠረት እንዲይዝ ለማድረግ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሁሉም የአካል ጉዳተኞች ማህበራት በስምምነት ያዘጋጁት ሁሉን አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ረቂቅ አዋጅ ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀርቦ ለፍትህ ሚኒስቴር መመራቱን አቶ ሙሴ ይናገራሉ፡፡

ይህ አዋጅ እውን ከሆነ የሚወጡ ወቅታዊ ሕግና ፖሊሲዎችን ከአዋጁ አኳያ የሚፈትሽ፣ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በየዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት እየለየ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያቀርብና በአካል ጉዳተኞች የሚመራ የራሱ በጀት ያለው የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በበላይነት የሚመራ ተቋም እንደሚኖር ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ እንደ ጀርመን ባሉ ያደጉ ሀገራት ከ 2 ነጥብ 5 በመቶ በላይ የሠራተኛ ብዛቱ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ድርጅት ከግብር ነፃ እንደሚደረግና ይህ ተሞክሮም በኬንያ እንደሚተገበር አንስተው በብዙ በሚጠበቀው ሁሉን አቀፍ ረቂቅ አዋጅ የተሻሉ ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን እንደቀመሩበት ሥራ አስኪያጁ ይገልጻሉ፡፡ በሥራ ክህሎት ስልጠና ከሚገኙ እድሎች አካል ጉዳተኞች 10 በመቶ እንዲጠቀሙ፣ የስልጠና ማእከላትም አካታች እንዲሆኑ፣ የሥራ ፈጠራ እና የትምህርት ስልጠና የሚሰጡ የመንግሥት ተቋማት ከዓመታዊ በጀታቸው 10 በመቶ የሚሆነውን ለአካል ጉዳተኞች እንዲመድቡ፣ ለአካል ጉዳተኛ የመንግሥት ሠራተኞች ከሚያወጡት የተለያዩ ወጪዎች አንፃር የግብር ማበረታቻ እንዲደረግ ማስቻል በሁሉም አቀፍ ረቂቅ አዋጅ የሰፈሩ ነጥቦች ናቸው፡፡

ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እአአ በ2012 ያወጣው የ10ዓመት ጥናት እንደሚያሳየው 95 በመቶ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች ከድህነት ወለል በታች ናቸው፡፡ አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሴቶች አካል ጉዳተኛ ካልሆኑት ሴቶች በላይ 5 እና 6 እጥፍ ፆታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት እንደሚያሳየው 89 የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ርቀዋል፡፡ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍም በባለቤትነት የመንግሥት ተነሳሽነት አግዞት ለግንዛቤ ፈጠራ ለአዲስ አበባና ለፌዴራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ200 አባላት ስልጠና ሰጥቷል፤ ይሁን እንጂ የአካል ጉዳተኞች ወቅታዊ ጉዳይና መፃኢ ህይወት ዙሪያ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ይገደዋልና ለአካታች ሀገርአዊ ግንባታ አካል ጉዳተኞች የየድርሻቸውን ሃሳብ እንዲያዋጡ ሞራል ይሆናቸው ዘንድ ኤልዳ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You