ባለዘርፈ ብዙ ፋይዳው የፕላስቲክ ፎርምወርክ ፋብሪካ

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረችውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ ዘርፉ ለውጥ እያሳየ ይገኛል፡፡ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ዘርፉ እየተቀላቀሉ፣ ነባሮቹም የማምረት አቅማቸው እያደገ መሆኑም ይህን ያመለክታል።

ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ያላቸው ፋይዳ በብዙ መልኩ ይገለጻል፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየወጣባቸው ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት አንዱ ፋይዳቸው ነው፤ በዚህም የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ለዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ፡፡

በሀገሪቱም ይሄው እየታየ ነው፤ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ብቻ ባለፉት አስር ዓመታት ከ300 ሺ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል፤ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ አቅርበዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየወጣባቸው ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን የመተካት አቅማቸውም እየጨመረ፣ የሀገር ውስጥ ግብአትን በመጠቀም የሚያመርቱትም ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለእዚህም አመራረታቸው፣ የሚጠቀሙት ግብአትም ሆነ የኃይል አማራጫቸው አካባቢን የማይበክል መሆን ይኖርበታል፡፡ በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ያገለገሉ ቁሶችን በመጠቀም የሚያመርቱ ሲሆኑ ደግሞ ፋይዳቸው ዘርፈ ብዙ ይሆናል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የፕላስቲክ ፎርምወርክ ፋብሪካም ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል፡፡ ፋብሪካው ለኮንስትራክሽን ሥራዎች አስፈላጊ የሆነውን ፎርምወርክ የሚያመርተው ያገለገሉ የፕላስቲክ ቁሶችን በግብአትነት በመጠቀም ነው፡፡

ያገለገሉ የፕላስቲክ ቁሶች የመላ ዓለም ችግር ናቸው። መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በዓለም በየዓመቱ 300 /ሶስት መቶ/ ሚሊዮን ቶን የሚገመት ፕላስቲክ ይመረታል፣ ከዚህ ውስጥ ዘጠኝ በመቶ ብቻ የሚሆነው ነው ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረገው፣ የተቀረው ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች፣ ማቃጠያ ሥፍራዎች ወይም ውሃ አካላት በመጣል በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።

በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናትን ዋቢ ያደረገ መረጃ እንዳመለከተው፤ በዓመት ስምንት ሚሊዮን ቶን ያገለገለ ፕላስቲክ ወደ ውቅያኖስ እንደሚጣል ይገመታል፣ በዚህ ምክንያትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወፎች እና 100ሺ የባሕር ውስጥ አጥቢ እንስሳት ለሞት ይዳረጋሉ። ፕላስቲኮች ለመበስበስም እስከ አንድ ሺ ዓመታት ሊፈጁ ስለሚችሉ አካባቢን የመበከል አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡

በየብስ ላይ የሚጣለው ያገለገለ ፕላስቲክ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ቁስ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ቀውስ ለመቋቋም እና ለመቀነስ ሀገራት ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡

ኢትዮጵያም ከዚህ ተጽዕኖ ለመውጣት በቅርቡ የፕላስቲክ ቆሻሻ በተለይ የስስ ፌስታል አወጋገድን በተመለከተ አዲስ አዋጅ ማውጣቷ ይታወሳል፡፡ አዋጁ ስስ ፌስታሎች አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ጭምር ይከለክላል፡፡

ያገለገሉ የፕላስቲክ ቁሶችን መልሶ ጥቅም የማዋል ሥራም ሌላው ችግሩን የመከላከል ጥረት ነው፡፡ በዚህም ግለሰቦች በራሳቸውም ይሁን ተደራጅተው ያገለገሉ የፕላስቲክ ቁሶችን በመሰብሰብ ቁሶቹን ለድጋሚ አገልግሎት ለሚያውሉ ድርጅቶች ያቀርባሉ፤ ድርጅቶቹም ከእነዚህ ቁሶች ሌሎች የፕላስቲክ ውጤቶችን እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

ያገለገሉ የፕላስቲክ ቁሶችን ለመልሶ አገልግሎት በግብአትነት በመጠቀም ፎርምወርክ የሚያመርተው ፋብሪካም አካባቢንም ጭምር የሚታደግ ነው፡፡ ይህ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘውና በ10 ሚሊዮን ዶላር /በአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር/ የተገነባ ፋብሪካ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑም በተመረቀበት ወቅት የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

ፋብሪካው ከሌሎች ፋብሪካዎች የሚለይባቸው ሁኔታዎችም አሉት፡፡ ቆሻሻን ወደ ጠቃሚ ቁስ መለወጡ ብቻ አይደለም የተለየ የሚያደርገው፡፡ ያገለገለውን የፕላስቲክ ቁስ ከፍተኛ የግብአት እጥረት እና ውድነት ላለበት የግንባታው ዘርፍ አስተዋጽኦ ወደሚያደርግ ፎርምወርክ መቀየሩም ሌላው ፋይዳው ነው፡፡ በዚህም የቆሻሻ አወጋገድን አዘምኗል፤ የደን ሀብትንም ከውድመት መታደጉም ሌላው ፋይዳው ሆኗል፡፡ እነዚህ ፋይዳዎቹ ፋብሪካውን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ከሚባለውም በላይ ነው ያሰኙታል፡፡

ያለፎርምወርክ የኮንክሪት ሙሌትን ማሰብ በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ይቆጠራል፤ ፎርምወርክ የተሞላውን የኮንክሪት ውህድ ደግፎ እስኪደርቅ ማቆየት የሚያስችል የግንባታ መሳሪያ ነው፡፡

ይህ ፎርምወርክ ከእንጨት ወይም ከጣውላ ተዘጋጅቶ አገልግሎት ሲሰጥ ኖሯል፤ ከላሜራና ሌሎች ላሜራና ከብረታ ብረቶችም ይሰራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከእንጨት ኢንዱስትሪ ውጤትም እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከእንጨት የሚዘጋጅ ፎርምወርክ ለደን መጨፍጨፍ አንድ ምክንያት በመሆን ይታወቃል፤ ይህ ፎርምወርክ በየጊዜው የሚበላሽ ወይም ከአገልግሎት ውጪ የሚሆን በመሆኑም ለተደጋጋሚ ወጭ እና ለግንባታ ጥራት መጓደል ምክንያት እንደሚሆንም የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡

አሁን ደግሞ ይህን ሁሉ ችግር የሚቀርፍ ኢንዱስትሪ ነው እውን የተደረገው፡፡ ይህ የኤች.ኬ ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የፎርምወርክ ማምረቻ ፋብሪካ ለምርቱ የሚጠቀመው ግብአት ያገለገሉ ፕላስቲኮችን ነው፡፡

ፋብሪካው ባለፈው ሳምንት በተመረቀበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳስታወቁት፤ መንግሥት የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ኢንዱስትሪ በተለይ በሴት ባለሀብት እውን መደረጉ ደግሞ ፋብሪካውን ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል ለተወሰኑ ዘርፎች ብቻ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለምጣኔ ሀብት ያላቸው ፋይዳ ታይቶ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ ማዕድን ቱሪዝምና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዘርፎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የፖሊሲ ማሻሻያ እና ድጋፎችን በማድረግ እየተሥራ እንደሚገኝ ያብራራሉ፡፡

ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት አቅምን ለማሳደግ፣ ገቢ ምርትን ለመተካት፣ ኤክስፖርትን ለማሳደግ፣ የሥራ እድልን ለመፍጠርና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ ገብተዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረበት ከ2014 አንስቶ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨባጭ ውጤቶች እየመጡ ናቸው፤ በንቅናቄው የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሻሻል ተችሏል፡፡

‹‹የጠንካራ ሀገር መሰረት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በቅርቡ የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን ስትራቴጂ ተቀይሶ በሁሉም የገጠር ወረዳዎች ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ጀምሮ አቅም የፈቀደውን ኢንዱስትሪ እውን ለማድረግ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት 200 ዓመታት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጠንክረው የሠሩ ሀገራት ለዜጎቻቸው የሥራ እድል በመፍጠር የኑሮ ደረጃቸውን በማሻሻልና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚም መገንባት መቻላቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ስኬታቸው በዓለም ኃያልነታቸውን ለማረጋገጥ ያስቻላቸውን የዘርፉን መሰረት ጥሎላቸዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓለም በቴክኖሎጂ በፍጥነት እያደገ ባለበት ወቅት ላይ ብንገኝም፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪ እና ለዜጎቿ የተመቸች ሀገር ለመፍጠር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በየደረጃው ማስፋፋትና ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም ዘርፉን ማበረታታት እና ኢንቨስት ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተመቸ የአገልግሎት አሰጣጥ፤ ማበረታቻ እና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀው፣ በኮንስትራክሽን፣ ግብርና፣ ሆቴል እና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ባለሀብቶች ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ማበረታቻዎችን ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የፕላስቲክ ፎርምወርክ ፋብሪካው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ፎርምወርኩ ከፕላስቲክ የሚመረት በመሆኑ የደን ጭፍጨፋን በመቀነስ በኩል የሚጫወተው ሚናም ከፍተኛ ነው፡፡ በግምታዊ ስሌት የ12 እና 18 ሚሊሜትር ፎርምወርክ ከእንጨት ለማምረት ከ66 እስከ 198 ሄክታር መሬት የደን ሀብት ያስፈልጋል፡፡

የዚህ ፋብሪካ ወደሥራ መግባት ይህንን ሀብት ማዳን ያስችላል ሲሉ የፋብሪካውን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ ደን ጭፍጨፋን ማዳን የሚችል ሥትራቴጂክ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡

አንድ ሚሊዮን ስኩዌር ካሬ ሜትር ፍሬምዎርክ ለማምረት እስከ 80 ሺህ ኩንታል የፕላስቲክ ግብዓት ያስፈልጋል፡፡ ፋብሪካው ከ80 እስከ 90 በመቶ የደረሰ ያገለገለ በካይ የፕላስቲክ ቁሳቁስን በግብዓትነት መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል በመሆኑ ብክለትን ለማስወገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡

ፋብሪካው ለቴክኖሎጂ ሽግግር ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ ገቢ ምርትን በመተካት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት በኩልም ያለውን ፋይዳም አመልክተዋል፡፡ ምርቶቹን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚያስችልም ይናገራሉ፡፡

የኤች ኬ ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ካሳነሽ አያሌው እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር ስኩዌር በላይ ፎርምወርክ ማምረት ይችላል፤ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እና ምንም አይነት ወደ ከባቢ የሚለቀው ፈሳሽ ወይም ጠጣር በካይ ነገር የለውም፤ በዚህም ከአካባቢ ጋር ይስማማል፡፡

በአንድ ፕሮጀክት ግንባታ ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ወጭ የሚወስደው የፎርምወርክ ወጪ ነው የሚሉት ሥራ አስፈፃሚዋ፣ ለዚህ ዘላቂ ችግር መፍትሄ ፍለጋ በሚል ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮዎች በመውሰድ ይህ ዘመናዊ ፋብሪካ መገንባቱን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ካሳነሽ ገለፃ፤ ፎርምወርኩ ከፍተኛ ጥራት ያለውና በዓለማችን በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ የሚባል የፎርምወርክ ዓይነት ነው። በዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው ፎርምወርክ የማምረት አቅምም ያለው በመሆኑም፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉን የፎርምወርክ ፍላጎት በአስተማማኝ ደረጃ ማሟላት ይችላል።

ፋብሪካው ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል፡፡ ከፍተኛ የማምረት አቅም ያለው በመሆኑ ወደ ውጭ መላክ ሲጀምር ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለግንባታ የሚውሉት ከእንጨት የሚሰሩ ፎርምወርኮች ሦሥት ወይንም ቢበዛ አምስት ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ መሆናቸውን የሚናገሩት ሥራ አሥፈፃሚዋ፣ አልሚዎች በተደጋጋሚ ፎርምወርክ በመግዛት ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋሉ ብለዋል፤ ፎርምወርኮቹ አገልግሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደገና ጥቅም ላይ መዋል እንደማይችሉና ተሰባብረው የግንባታ ቦታውን እንደሚያቆሽሹ ያብራራሉ።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በእንጨት ፎርምወርኮች የሚካሄዱ ግንባታዎች ወጣ ገባ የሚበዛባቸው በመሆኑም ለልስን ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃሉ፡፡ ይህንንም በመመልከት ኤች ኬ ቢዝነስ ግሩፕ በእንጨት የሚሰሩ ፎርምወርኮችን የሚተካ የፕላስቲክ ፎርምወርክ ምርት ወደ ማምረት ገብቷል። በዚህም የደን መጨፍጨፍን ለመቀነስ ይጠቅማል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ከ50 ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል በመሆኑ ለፎርምወርክ የሚወጣው ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ያስቀራል፡፡

ድርጅቱ ፋብሪካውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ ለግንባታውም ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበታል። አዲስ የቴክኖሎጂ ስሪትና ዘመናዊ የሆነ ማሽን የሚጠቀም በመሆኑም በዘርፉ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና ሙያ ያላቸው ሰራተኞች አሉት፡፡ የምርት ጥራቱም በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ማረጋገጫ ያገኘ ነው፡፡

የኤች ኬ ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ ብሩ ዊርቱ የፋብሪካው የፎርምወርክ ምርት በተለይ ለሕንፃና ለድልድይ ግንባታዎች ሊያገለግል እንደሚችል ገልጸዋል።ምርቱ ከፍተኛ ጥራት ያለውና ወጪ ቆጣቢ እንዲሁም ለሥራ ቅልጥፍና ምቹ መሆኑና ከአካባቢ ጋር ምንም አይነት ተቃርኖ የሌለው መሆኑ ከሌሎች ፋብሪካዎች ይለያል ብለዋል።

የድርጅቱ የወርክሾፕ ማናጀር አቶ ሙሉጌታ የትዋለ በተቋሙ እህት ኩባንያ ለ20 ዓመታት ሰርተዋል፤ በዚህም በርካታ ልምድ አካብተዋል፡፡ በዚህ አዲስ ፋብሪካም ከቻይና በመጡ ባለሙያዎች ለወራት ሥልጠና እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፣ ማሽኖቹ አዳዲስ እና ዘመናዊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ምንም አይነት የጤና ጉዳት የማያስከትሉ፣ ድምጽም ሆነ ጭስ አልባ በመሆናቸው ለሰራተኞች ምቹ ናቸው ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

አቶ መልካሙ አያሌው የፋብሪካው ሰራተኛ ናቸው። በተቋሙ እህት ኩባንያ ለ17 ዓመታት ሰርተዋል። በሀገሪቷ እንደዚህ አይነት የፎርምወርክ ፋብሪካ ሲከፈት የመጀመሪያ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ የፋብሪካው የፎርምወርክ ምርቶች የማይከብዱ እና ጥንካሬያቸው አስተማማኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ለኮንክሪት ሥራዎች ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል፡፡

ፎርምወርኩ የአገልግሎት ጊዜውን ሲጨርስም ፋብሪካው ያንን አገልግሎቱን የጨረሰ ምርት ተቀብሎ ለዳግም አገልግሎት እንደሚያውለውም ገልጸዋል፡፡ ይሄውም አካባቢ ላይ ሊከሰት የሚችለውን ብክለት ከማስቀረት በተጨማሪ ለገንቢዎች የሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You