
አዲስ አበባ፡– አፍሪካ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊና መስኮች ውጤታማ ሥራን በማከናወን ወደፊት መራመድ ይጠበቅባታል ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ገለጹ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት 46ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፤ አፍሪካ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሌሎች ዘርፎች ላይ ውጤታማ ሥራን በማከናወን ወደፊት መራመድ ይጠበቅባታል።
ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ችግሮች ምርታማነታችንን ቢቀንሱትም፤ ችግሩን መቋቋም የሚያስችል መፍትሔን በጋራ ማፈላለግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በኅብረቱ እየተደረጉ ያሉት ተቋማዊ ማሻሻያዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ኅብረት በሊቀመንበርነት ዘመናቸው በኢኮኖሚ በተለይም በግብርናው ዘርፍና በማህበራዊ መስኮች የአፍሪካን አንድነት የሚያጠናክሩ ተግባራት ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
የአህጉራዊ ተቋማዊ ሪፎርምን ጨምሮ በኃላፊነት ዘመናቸው የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገባቸውን አመልክተው፤ አሁንም የአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ሪፎርም መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው፤ በተባበሩት መንግሥታት የዓለምአቀፍ የፋይናንስ መዋቅር እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ሊሻሻሉ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ ውስጥ ያለውን የንግድና የኢንዱስትሪ ልማት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ያነሱት ዋና ፀሐፊው፤ በአፍሪካ የማዕድን ሀብት ላይ እሴት በመጨመር አፍሪካውያንን በቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ዋና ጸሐፊው አፍሪካ የዓለምን 30 በመቶ የማዕድን ክምችት እና 65 በመቶ የሚታረስ ለም መሬት ባለቤት ብትሆንም በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋሉ ሁሉንም አፍሪካዊ የሚያስቆጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
እንደ ዋና ጸሐፊው ገለፃ፤ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ሁሉም አፍሪካውያን በእኩልነት የሚኖሩበትን መጪው ጊዜ ምቹ ለማድረግ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ ለመሥራት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለዚህም ከአፍሪካ ዲያስፖራዎች ጋር ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ትብብርን ለማበረታታት፣ ቀጣናዊ ትብብርን ለማሳደግ የአፍሪካ ኅብረት አፍሪካውያን በአህጉሩ ያለቪዛ የሚንቀሳቀሱበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የአፍሪካን ውህደት ማፋጠን እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአፍሪካ የወደፊት እጣ ፋንታ በጋራ ፈቃደኝነት እና ተግባር ላይ የተመሠረተ ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፤ አፍሪካ ያሉባትን ችግሮች ለመፍታትና መጪውን ጊዜ በስኬት ለመወጣት ትብብርና አንድነት ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለአፍሪካም ሆነ ለቀሪው ዓለም ፈታኝ የሆነ የለውጥ ሂደትን እየተጋፈጥን ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚቻለው በአንድነት እና በትብብር መሥራት ሲቻል መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገለጻ ፤አብዛኛዎቹ በአፍሪካ የሚያጋጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የአካባቢ ብክለት እና መራቆት ናቸው፡፡እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ለመቋቋም አፍሪካውያን በአንድነትና በትብብር መፍትሔ እንድናመጣባቸው የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
“አፍሪካውያን ዕድሎችን እንዴት መጠቀም፣ ፈተናዎችን ደግሞ እንዴት ማለፍ እንዳለብን አይነተኛ መፍትሔ ማበጀት ይኖርብናል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአፍሪካን ጥቅም ለማስጠበቅም በትብብር ከመሥራት ባሻገርም የአፍሪካ ሀገራት በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ትብብርን እና አጋርነትን ማስቀደም እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ፣ በረሃማነት፣ የብዝኃ ህይወት ጥበቃ፣ የጤና ሥርዓት ተደራሽነት፣ የጎርፍ እና የአፈር መሸርሸርን የመከላከል ሥራዎች በአህጉሪቱ ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡
መጪውን ጊዜ በስኬት ለመወጣት ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ ችግሮችን በመቋቋም ዕድገቷን ማፋጠን እንድትችልም ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ኅብረት 2063 አጀንዳን ለማሳካት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አመልክተው፤በዚህም የ2063 አጀንዳዎችን በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ እና አፍሪካን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ከጉባኤው ውጤታማ ውይይቶችና ውጤቶችን እንጠብቃለን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፤የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮችን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የአፍሪካ ኅብረት ተቋማትና አደረጃጀቶች፣ በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የአጀንዳ 2063 የአፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያዳምጥ ተመላክቷል።
በኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ምክር ቤቱ የሥራ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁ ኮሚሽነሮች በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ስር የሚገኙ የስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ ያካሂዳል። በተጨማሪም የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ለሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም