እንደ ሳይንሳዊ ባህሪው ያልተሠራበት ሬዲዮ

ነገ የካቲት 6 ቀን (ፌብርዋሪ 13) ዓለም አቀፍ የሬዲዮ ቀን ይከበራል:: በኢትዮጵያም ወጣ ገባ እያለም ቢሆን ሲታወስ ቆይቷል:: በተለይም በ2014 ዓ.ም የሬዲዮ ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለአንጋፋ ጋዜጠኞች እውቅናና የገንዘብ ሽልማት ማበርከቱን አስታውሳለሁ::

በየዓመቱ የሬዲዮ ቀንን ምክንያት በማድረግ የሬዲዮ ጣቢያዎች ያወሩበታል:: ጋዜጠኞች በማህበራዊ ገጾቻቸው ስለቀኑ ይጽፋሉ:: በሁሉም ውስጥ የታዘብኩት ነገር፤ የሚያወሩት አሁን ስላለበት ሁኔታ ሳይሆን ድሮ ስለነበረው ትዝታ ነው:: ትዝታ ምን ያህል ስሜትን እንደሚቀሰቅስ ጠፍቶኝ አይደለም፤ እኔም ብዙ የሬዲዮ ትዝታ አለኝ:: ግን ከትዝታው ጋር ተያይዞ አሁን ያለበትን ሁኔታ መታዘብም ይገባ ነበር:: ወይስ ሬዲዮ እንደ ሙዚዬም ዕቃ ትዝታ ብቻ ሆኖ ይቅር?

ሬዲዮ ከመገናኛ ብዙኃን አይነቶች ሁሉ ቀላል (በዋጋም በአያያዝም፣ ተደራሽ እና ምቹ) የሚባል የመገናኛ አይነት ነው:: አሁን ደግሞ በየኪሳችን ያለ ነው:: የአጠቃቀም ምቹነቱ፣ ድንበር አልባ ስርጭቱ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ተደራሽነቱ፣ ምስል ከሳችነቱ ሳይንሳዊ ባህሪው ነው:: ንፅፅሩ ከጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ከቴሌቪዥን እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሥር ከሚጠቃለሉት የማህበራዊ ትስስር መገናኛ ዘዴዎች ጋር ነው:: ሁሉም የሬዲዮን ያህል አይሆኑም:: ‹‹ለምን?›› የሚለውን ልብ እንበል!

በሀገራችን በተለይም በገጠሩ ማህበረሰብ ውስጥ አሁንም የተማረ የሚባል ዜጋ የለንም:: ጋዜጦችና መጽሔቶችን አያነብም፣ አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ማንበብና መጻፍ ቢችል እንኳን ቁጭ ብሎ ጋዜጣ የሚያነብበት ጊዜ የለውም:: ሬዲዮ ግን የትኛውንም ሥራ እየሠሩ ለማድመጥ ምቹ ነው:: አርሶ አደሩ እንደዚያ ነው እያደረገ ያለው:: የግብርና ሥራውን እየሠራ ያዳምጣል::

ነጋዴውም እንደዚያው ነው:: ለዚህም ነው ዛሬ ድረስ ሱቅ ውስጥ ቴሌቪዥን ተከፍቶ ሳይሆን የምናየው ሬዲዮ ተከፍቶ ነው የምንሰማው:: በፀጉር ቤቶችም ሆነ በተለያዩ የእንጨት ሥራዎች አካባቢ የሚሰማው ሬዲዮ ነው፤ ሬዲዮን ከጋዜጣና ቴሌቭዥን የሚለየው ይሄ ባህሪው ነው::

አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በቤቱ ውስጥ ቴሌቪዥን ቢኖረውም በሥራ ቦታ ግን አይመቸውም፤ በዚያ ላይ በሁሉም የሀገራችን ክፍል መብራት የተሟላ አይደለም:: ሬዲዮ ግን በባትሪ ድንጋይና በፀሐይ ኃይል (ሶላር) ይሠራል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንኑ ታሳቢ አድርጎ ይመስላል በሶላር የሚሠሩ የሬዲዮ አይነቶች መጥተዋል::

የቴክኖሎጂ መገናኛ ዘዴዎች (ማህበራዊ ገጾች) ነገር ምንም ማብራሪያ ሳያስፈልገው ለአርሶና አርብቶ አደሩ እንዲሁም ለነጋዴው ማህበረሰብ ምቹ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው:: ጋዜጣ፣ መጽሔት እና የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተማረ የሚባለው የከተሜው ማህበረሰብ ናቸው:: ያም ሆኖ ግን አዲስ አበባ ውስጥ ራሱ ሬዲዮ ብቻ የሚጠቀመው የማህበረሰብ ክፍል ቀላል አይደለም:: በታክሲዎችና በግል የቤት መኪናዎች ውስጥም ሬዲዮ በባህሪው ቀላልና ምቹ ነው፤ በተማረውም ባልተማረውም የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ይደመጣል::

እነዚህን ከላይ የዘረዘርኳቸውን የሬዲዮ ባህሪያት መጥቀስ የፈለኩበት ምክንያት ሬዲዮ ምን ያህል አስፈላጊ ነው የሚለውን ለማየት ነው:: አስፈላጊነቱን ይህን ያህል ካየን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከሬዲዮ ጣቢያዎች የምታዘበውን ላካፍል::

የሬዲዮ ጣቢያዎች በተለያየ አካባቢ የማሰራጫ አንቴና ቢኖራቸውም ዋና ስቱዲዮ የሚኖረው ከተማ ቦታ ነው:: አብዛኞቹም አዲስ አበባና የክልል ከተሞች ውስጥ ነው፤ ከጥቂት የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በስተቀር::

እነዚህ ከተማ ውስጥ ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች ገጠር ውስጥ ላለው ማህበረሰብ የሚያደርሱት መረጃ ፈጣንና ለዚያ ማህበረሰብ ምቹ የሆነ አይደለም:: ይህን ነገር በሰፊው የታዘብኩት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ገና አፍላ በነበረበት በ2012 ዓ.ም መጋቢት፣ ሚያዚያና ግንቦት ወራት ውስጥ ነበር:: በእነዚህ ወራት ቤት መዋል ሁሉ ተጀምሮ ነበር:: በእነዚያ ጊዜያት የታዘብኩት ነገር የሬዲዮ ጣቢያዎች የሬዲዮን ሳይንሳዊ ባህሪ እንዳልተጠቀሙበት ነው::

የወቅቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በማህበራዊ ገጻቸው ትኩስ ትኩስ መረጃዎችን ይለቃሉ:: እኔ አዲስ አበባ ውስጥ ስለሆንኩና የቴክኖሎጂውም ተጠቃሚ ስለሆንኩ ወዲያውኑ አየዋለሁ:: የሬዲዮ ጣቢያዎችን እያቀያየርኩ ሳዳምጥ አላዩም አልሰሙም:: በሙዚቃ ላይ ሙዚቃ እየደራረቡ መቆየት ነው:: ከዚያ በኋላም ወደ መደበኛ ፕሮግራሞች መሸጋገር ነው:: ከብዙ ሰዓታት ቆይታ በኋላ (በመሐል ብዙ ነገር ተፈጥሮ) የጠዋቱን መረጃ ሲናገሩ እሰማቸዋለሁ::

በሬዲዮ ሰበር ዜና መስማት ቀርቷል:: የሚገርመው ግን ከቴሌቪዥን በተሻለ ሁኔታ ፈጣን ሬዲዮ ነበር:: ቴሌቪዥን ብዙ ጣጣ አለበት፤ ሬዲዮ ግን ቀጥታ ስቱዲዮ ገብቶ ማውራት ነው:: ዋናው ነገር የክስተቱን እውነትነት ማረጋገጥ ነው:: ቴሌቪዥኑን መቅደም ቢቀር እንኳን ቢያንስ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ የተናገረውን ዜና ቶሎ መነገር ነበረበት:: አሁንማ የትዝብቴን እውነትነት ለማረጋገጥ ብዬ ቴሌቪዥን ላይ ሰበር ዜና ሳይ ወዲያውኑ የሬዲዮ ጣቢያዎችን ከፍቼ አቀያይራለሁ፤ አብዛኞቹ ምን እንደተፈጠረ ያልሰሙ ናቸው::

በዚህ ጉዳይ ላይ በኮሮና አፍላነት ወቅት በማህበራዊ ገጼ ላይ ትዝብቴን ጽፌ የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ የሰጠኝን አስተያየት አስታውሳለሁ:: በተለይም የግል የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሲያወጡ ትኩረታቸው መዝናኛ ላይ ነው፤ በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ ፈቃድ የሚያገኙት እንቶ ፈንቶ ነገሮች ላይ የሚያተኩር ፕሮፖዛል ካቀረቡ ነው:: በዚህም ምክንያት ምናልባትም ከጥቂቶች በስተቀር ፈጣን መረጃዎችንና ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን አይሠሩም የሚል አስተያየት ሰጥቶኝ ነበር::

በሌላ በኩል ደግሞ የንግድ ጣቢያዎች ስለሆኑ የአየር ሰዓቶቻቸው ለተባባሪ አካላት የተሸጡ ናቸው:: የአየር ሰዓቱን የገዛው አካል (ግለሰብም ይሁን ተቋም) የራሱን ፕሮግራም ብቻ ያስተላልፍበታል እንጂ ዜና አይሠራም:: በእነዚህ ምክንያቶች የሬዲዮ ተፈጥሯዊ(ሰው ሰራሽ ቢሆንም ሳይንሳዊ ባህሪውን ማለቴ ነው) ባህሪ በትክክል እንዳይሠራበት ሆኗል::

ሌላው የታዘብኩት ነገር ደግሞ ማታ ማታ ዜናዎቻቸውን ስሰማ ነው:: አብዛኞቹ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ተደራሻቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ ነው:: መስማት የሚፈልገው ለየት ያለ ዜና ነው:: የሚገርመው ግን በተመሳሳይ ሰዓት ጣቢያ ብንቀያይር የምንሰማው ያንኑ አንዱን ዜና ሊሆን ይችላል:: በቃለ መጠይቅ የሚሠራ የፕሮጀክት ዜና የላቸውም:: አንድ ተቋም በማህበራዊ ገጹ የለቀቀውን መረጃ መዘርዘር ነው:: ጠዋት የተለቀቀ ዜና ማታ እንደ አዲስ ያቀርቡታል:: አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ የሁሉም ነገር ተደራሽ ስለሆነና ዜናውን ስለሚሰማው አዲስ አይሆንበትም:: ወይም ደግሞ በሰዓቱ መነገር ነበረበት:: የግድ የዜና ሰዓታቸው ማታ ስለሆነ ብቻ የተሰለቸ ዜና ማቅረብ አይለም፤ መጨመር ያለበትን ነገር ጨምረውበት ቢሰራ አዲስ ነገር ስለሚጨምር መረጃ ይሆናል::

ሬዲዮ ታስቦበትና ታቅዶ ሊሠራበት ይገባል:: ልክ እንደ ቴሌቭዥን ጣቢያዎች የራሱ የፕሮጀት ዜናዎች ሊኖሩት ይገባል:: ይህን የሚያደርጉት በጣም ጥቂት (ምናልባትም ሁለት ወይም ሦስት) የሬዲዮ ጣቢያዎች ብቻ ናቸው:: ብዛታቸው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው:: በዚያው ልክ ግን የተደማጭነት ሥራ ሊሠሩ ይገባል:: ፕሮጀክት ቀርጸው የራሳቸውን ሥራ የሚሠሩት ተወዳጅ ሆነዋል::

ስለዚህ የሬዲያ ጣቢያዎቻችን የሬዲዮን ባህሪ የሚመጥን ሥራ ይሥሩልን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You