
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንደሀገር ሊከሰቱ የሚችሉ ሠው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሊያስከትሉት የሚችሉትን አደጋ ሥጋት በመለየት እና የአደጋ ምክንያቶችን በጥናት በመለየት መከላከልና ለመቀነስ ስትራቴጂዎችን ቀይሶ መሥራት፣ የአደጋ ሥጋት ዝግጅት ማድረግና ምላሽ መስጠት ከተልዕኮቹ መካከል ናቸው:: እንደሀገር ባለፉት አምስት ዓመታት ግጭቶች፣ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት ንዝረትና መሰል ሠው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተከስተዋል:: አደጋዎችን በመከላከልና ሰብአዊ ድጋፍ በማቅረብ ረገድ ኮሚሽኑ ምን ሠራ? የሰብአዊ ድጋፍ አቅምን በራስ ለመሸፈን እንደሀገር ምን ያህል ሥራ ተከናወነ? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) የተጠየቅ ዓምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል::
አዲስ ዘመን፡- በትግበራ ላይ ያለው የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ በተጨባጭ ምን ውጤት እያስገኘ ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡– በበጀት ዓመቱ በኮሚሽኑ በተለየ መንገድ የተሰራው በተለይ በሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም የመገንባት ጉዳይ ነው:: ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ላይ ዓመታዊ እቅድ ተብሎ የሚወሰደው ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መያዝ ነው:: ከዚህም ውስጥ 500 ሺ ሜትሪክ ቶን መጠባበቂያ ነው:: አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለዕለት ደራሽ ድጋፍ የሚውል ነው:: ይህ ድጋፍ ሁሉንም የሚያካትት ነው:: ይህም በመንግሥትና በተለያዩ አጋር አካላት የሚቀርበውን የሚያጠቃልል ነው:: ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም በሚለው ማሕቀፍ ውስጥ ትልቅ ጉዳይ ተደርጎ የተወሰደው የምንመገበውንም ያመረትነውንም ሀገር በቀል ማድረግ ነው:: ይህን በምናደርግበት ጊዜ የምግብ ሉአላዊነትን ማሳካትን መሰረታዊ ጉዳይ የሚያደርግ ነው::
የምግብ ሉአላዊነት ሳናረጋግጥ የተሟላ ነጻነት፣ ሕልውና፣ ሥብዕና እና ክብር መኖር የማይታሰብ ነው:: የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲያችን በሀገራችን ሠው ሰራሽም ይሁን በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን በየደረጃው መሰረት እንዲደገፉ ማድረግ ነው:: ይህም በተለያዩ ጥናቶች ተጋላጮችን መሰረት በማድረግ የሚያስችሉ ድጋፎች ሲሰሩ ቆይተዋል::
በሰብአዊ ድጋፍ ማሕቀፍ ውስጥ 10 የሚሆኑ ክልሎች የሰብአዊ ድጋፍ አይነቶችን በራሳቸው አቅም እየሸፈኑ ነው:: በግጭት ምክንያትና ቅጽበታዊ አደጋዎች ሳቢያ የተቸገሩ አካባቢዎችን ግን እናግዛቸዋለን:: ለምሳሌ ትግራይ፣ አፋር፣ አማራና ሱማሌ ክልል፤ በተወሰነ መልኩ ደግሞ ኦሮሚያ በጣም አነስተኛ አካባቢዎች ላይ ካልሆነ ለሌሎች ክልሎች የምናስተላልፈውና የምንልከው ድጋፍ የለም:: ይህ አንዱ ውጤት ነው:: ይህ ማለት ግን የሚደገፍ ሠው የለም ማለት ሳይሆን የሚደገፍ ሲኖር በራሳቸው አቅም ይሸፍናሉ ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ክልሎች በራሳቸው አቅም እየሸፈኑ ከሆነ ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራ ያለው በየትኞቹ ክልሎች ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡– ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው አራቱ ክልሎች በተለይም አፋር ላይ ከወቅታዊው የመሬት ንዝረት ጋር ተያይዞ፤ ትግራይ ላይ ደግሞ በማገገም ሂደት ላይ የሚፈጥረው ችግር መሰረት በማድረግ እንዲሁም አማራ ክልል ላይ ከአንዳንድ ተፈናቃዮች ጋር ተያይዞ የሚደረግ ድጋፍ አለ:: በእነዚህ ድጋፎች ውስጥ የቀድሞ ተገኝነት ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ 252 ሺ ኩንታል በተጠቀሱት ክልሎችና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ እንዲደርስ ተደርጓል::
በሌላ በኩል የሚሰራው ሥራ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ዕቅዶችን በማካተት ይሰራል:: ስለዚህ በሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም እንቅስቃሴ በቅጽበታዊ አደጋዎች ምላሽና በተቋማት እቅድ ውስጥ የአደጋ ሥጋት ቅነሳን አካቶ እየተሰራ ነው:: ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን ከሥራ አካባቢ በመጀመር፣ ሥራን በማቀላጠፍና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ ለውጦች ታይተዋል:: መዋቅሩን መልሶ ከመስራት ጀምሮ ማስተካከልና የመንግሥት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል በማድረጉም በኩል እንቅስቃሴዎች ታይተዋል::
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋጥ ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን አዲስ ፖሊሲ ነድፎ እየሰራ ስለመሆኑ ሲነገር ቆይቷል፤ በክልሎች ሰፋፊ መሬቶች ላይ ምርት የማምረት እንቅስቃሴው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡– ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም በሚመለከት በየጊዜው የሚኖሩንን የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቶች በእያንዳንዱ ክልል ላይ የተለያዩ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት እንደመነሻ ተይዟል:: ከዚህ ውስጥ 500 ሺ ሜትሪክ ቶኑ መጠባበቂያ፣ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ደግሞ የዕለት ደራሽ ነው:: ይህንን ለማሳካት ወደ 253 ሺ ሄክታር መሬት ማረስን ይጠይቃል:: ከዛ ውስጥ በክረምት ጊዜ እስከ መኸር ያለው ተጠቃልሎ ተይዟል:: ምርት ማረት የሚቸገሩባቸው ቦታዎች ላይ የመሬትን ስፋት በመጨምር እየተሰራ ሲሆን፣ እስካሁን 110 ሺ ሄክታር መሬት ታርሶ ምርቱ እየተሰበሰበ ነው:: ከ600 እስከ 700 ሺ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል:: እቅዱ ግን የሁለት ዓመት እቅድ ውስጥ ወይም በአንድ ዓመት እቅድ ውስጥ መኸርን፣ በጋንና በልግን በማካተት የሚሰራ ስለሆነ እስከ መኸር ያለው ተጠቃሏል::
በአሁን ወቅት የበልግ ወቅት እየገባ ስለሆነ እነዚህን በአንድ ላይ በመጨመር ወደ አሰብነው መጠባበቂያም ይሁን የዕለት ደራሽ ድጋፍ እንደምንደርስ ይታሰባል:: ለምሳሌ 10 ከልሎች ተብለው የተጠቀሱት ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረሪ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከኮሚሽኑ የሚላክ ሰብአዊ ድጋፍ የሚባል የለም:: ከዚህ በፊት ሲላክ የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ በራሳቸው አቅም እየሸፈኑ ነው:: የቀሩት ክልሎችም ቢሆኑ የምንልከው በ30/70 መስፈርት ነው:: ይህ ማለት 70 ከመቶ የሚሸፍኑት በራሳቸው አቅም ሲሆን፣ ኮሚሽኑ የሚደግፈው 30 ከመቶውን የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎትን ነው:: ስለዚህ ከፖሊሲያችን ተነስተን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የምግብ ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ተግባራዊ እያደረገ ነው::
በጋ ላይና ክረምትን ጨምሮ 2017 እና 2018 ዓ.ም ላይ በአመዛኙ ራሳችንን ችለን እንወጣለን የሚለውን እንደምናሳካው ጅምሮቹ ተገቢ ማሳያዎች ናቸው:: የምግብ ሉአላዊነትን ስናነሳ ዋናው ጉዳይ ማምረትንና ያመረትነውን ደግሞ ለራሳችን ፍጆታ ማዋልን የሚጠይቅ ነው:: በአንድ በኩል ማምረት አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያመረትነውን ለራሳችን ፍጆታ መጠቀም ስላለ የተለያዩ ሀገራዊ የምግብ ሉአላዊነት ማረጋገጫ ሥራዎች እየተሰሩ ነው:: ለአብነት የሌማት ትሩፋት፣ ክሕሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራና አትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት ስናጤን ቤተሰብ እንደ ቤተሰብ ወደ ማምረት ገብተዋል::
ማምረት አንድ ነገር ሲሆን፣ የተመረተው ወደ ገንዘብ ተቀይሮ አሊያም በክምችት መልክ ማኖር ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ያመረትነውን ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ይደረጋል:: ይህ ሲሆን፣ የውጭ እርዳታ ፈላጊነትና ጥገኝነት፤ ተረጂነት እየከፋ ሲሄድም ወደ ልመና የሚወስድ አባዜ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው:: ስለዚህ ይህን ለማስቀረት ውጤታማ ሥራ እየተሰራ ነው:: እንደ አማራጭ ቀርቦ በምግብ ዋስትና ላይ የሚሰራ ሥራ ነው::
ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው ስለሚያስገድድ ሁላችንም ተረባርበን ቤተሰብ እንደ ቤተሰብ፤ አካባቢዎች እንደየአካባቢያቸው፤ ወረዳዎች፣ ዞኖችና ክልሎች በጋራ ተረባርበን ካልወጣን ሌላ አማራጭ የሌለበት ነው:: በእርግጥም ይህ መንግሥታዊ ስለሆነ ራሳችንን መቻል የክብራችን፣ የነጻነታችንና የሉኣላዊነታችን መገለጫ ነው:: በዚህ መንገድ ያለው ርብርብም እንደ መንግሥትም እንደ ገዥ ፓርቲም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ ስለሆነ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው፤ በእርግጥም ከዚህ በፊት የምንታወቅበትን የሉአላዊነት ገድል በዚህም በኩል ልናሳካ የምንችል መሆናችን ማረጋገጫ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት በሀገር ውስጥ ከተፈጠሩ ግጭቶች ጋር በተያያዘ የነበረው ሠብአዊ ድጋፍ ምን ይመስላል? ችግሩን በመከላከል ሂደት ፖሊሲው ያስገኘው አዎንታዊ ውጤት ምንድን ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡- ኮሚሽኑ ሀገር አቀፍ ነው:: ፖሊሲዎች ጸድቀው በሚተገበሩበት ጊዜ እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ መፈጸም ቢችሉም ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው:: በዛ ላይ አከታትለን የምንሰራቸው ሥራዎች ሀገር አቀፍ ተደርገው የሚሰሩ ናቸው::
አንዱ ትልቁ ነገር የአስተሳሰብ ለውጥ ሲሆን፣ ሁላችንም የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ተዋናዮች ነን በሚል እሳቤ በራሳችን አቅም ተረጅነትንና ርዳታን የሚጸየፍ፤ ራሱን ከተረጂነት ወደ ረጂነት የሚያሸጋግር አስተሳሰብ መፍጠር ነው:: ሁለተኛው ተቋም መገንባት ሲሆን፣ ይህም የአደጋ ቅነሳ ሥራ በኮሚሽኑ ብቻ የሚፈጸም አይደለም::
ኮሚሽኑ የማስተባበርና የማቀናጀት ሥራ ቢሰራም ሁሉም ተቋማት ያላቸው ሠው ሰራሽ ይሁን ተፈጥሯዊ ተጋላጭነት እና ተጋላጭነቶቹ አደጋ ሆነው ቢከሰቱ ምላሽ የምንሰጥበትን በማቀድ እንሰራለን:: ይህም ከቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓታችን ጀምሮ ምን ተጋላጭነት አለ? ብለን ባሰብነው ጉዳይ እቅዶችን አቅዶ ከመተግበር ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ነው:: ሶስተኛው የፋይናንስ አቅም ሲሆን፣ በተለያየ መንገድ ያለውን ተጋላጭነት መቀነስን ይጠይቃል:: ሰብአዊ ድጋፍ የሚዘለል ጉዳይ ሳይሆን በየትኛውም ሰዓት ሊኖር የሚችል፤ ድጋፉን ደግሞ በራስ አቅም መሸፈን የሚጠይቅ ነው:: ስለዚህ ፋይናንስ ያስፈልጋል::
ፋይናንሱ ለማምረትም ሆነ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በሚፈልጉት መንገድ ሊጠቀሙት ስለሚችሉ አቅም መፍጠሩ ትልቅ ነገር ነው:: በራስ አቅም በሀገር በቀል ትብብሮች የሚፈጸሙ ይሆናል:: ይህን ለማሳካት ሁሉም ክልሎችና አካባቢዎች ጋር ተናበን፣ ተቀናጅተንና ተደጋግፈን እየሰራን ነው:: እንደሚታወቀው የውጭ ርዳታ ሲባል ውጭ ሀገር ያሉ ዜጎች ማለት ግብር ከፋዮች የሚባሉት ወይም ግብር የሰበሰቡ ሀገሮች መልሰው የሚያመጡት ነው:: ‘ክብራችንና ነጻነታች’ የምንል ዜጎች እርስ በርስ የምንደጋገፍበትን ሥርዓት ፖሊሲው አንድ ላይ ያመጣል:: ስለዚህ ክልልም ሆነ ፌደራል ሀሳቡን ለማምጣት አንድ ላይ ይሰራል::
የፌደራል መንግሥት በመደበኛነት ለክልሎች ከሚያሸጋግረው በተጨማሪ ክልሎች በራሳቸው ጊዜ እያስተባበሩ የሚሰሩት ሰፋፊ ተግባራት አሏቸው:: ከሁሉም በላይ ደግሞ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ የሆነ የመተጋገዝ ሥራ ይሰራል:: 70 ከመቶ የሚባለውን የሰብአዊ ድጋፍ ሸክም ማኅበረሰቡ ራሱ ይሸፍናል:: ስለዚህ ፖሊሲያችን ተጣጥሞ በፌደራል መንግሥትም በክልልም በተዋረድ ሁሉም አንድ አካባቢ ላይ ችግር ሲያጋጥም የመደጋገፍ አቅማችን ትልቅ አቅም እየሆነ ነው::
የሀገራችን ሕዝብ እርሰ በርስ የመደጋገፍ አቅም፤ ክብርን፣ ነጻነትንና ሉአላዊነትን በጠበቀ ሁኔታ የሚካሄድ ነው:: ከሌላ አካባቢ ከሌላ አድራሻ ሆኖ የሚመጣው ግን ውስጡ ያለውን ጭምር ለማሳካት የሚከናወን ነው:: ስለዚህ ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም በማለት ክልሎችና ፌደራል መንግሥት በጋራ የሚሠሩት ሥራ ተደምረንና ተሰባስበን እንዲሁም ተደጋግፈን ነጻነታችንና ሉአላዊነታችን የማስጠበቅ አካል ስለሆነ በበጎ መንገድ እየሄደ ያለ እና በየጊዜው ተጠናክሮ የሚሠራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም የሚለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ጥረትናን ትጋትን የሚጠይቅ ሥራ ስለሆነ ፈተና አይገጥመንም ብላችሁ ታስባላችሁ?
አምባሳደር ሽፈራው፡- አንዳንድ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ይኖራሉ:: ዓለም በፈተና የተሞላች ናት:: ነገር ግን ዋናው ጉዳይ እነዚህን ፈተናዎች እንዴት እንሻገራለን የሚለው ነው:: ፈተና ይጠፋል ብሎ መጠበቅ ሳይሆን ፈተናውን የሚቀንሱትም ሆነ የሚያባብሱት ለፈተናዎቹ የምናደርገው ዝግጅት ነው:: በዚህ ላይ እንደሚታወቀው የሰላም ግንባታ ሥራ በየደረጃው እየተሰራ ነው:: እንደሀገር የምንሠራቸው የሀገራዊ ምክክር ፕሮግራሞች፤ ሕዝብ በይቅርታ እንዲያልፍ የሚያስችል የሽግግር ፍትህ ማሕቀፎች በሙሉ፤ ግጭቶችና አለመግባባቶች ወደ ከፋ አቅጣጫ እንዳይወስዱ የሚያደርግ ነው::
ተፈናቃይ ማኅበረሰብ ተብሎ ከሚሰላው 70 ከመቶ የሚሆነውን ሰብአዊ ድጋፍ የሚሸከመው ማኅበረሱ ነው:: የተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ ያሉትን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተን የምንሰራው ሥራ አለ:: ነገር ግን ማኅበረሰቡ ደግሞ በራሱ አቅምና ልምድ እየተንከባከበ ያለው ለኮሚሽኑ ትልቅ አቅም ነው:: ችግሮችን ከማኅበረሰቡ ጋር ሆኖ ለመሻገር የሚያስችል አቅም ነው:: በሀገራችን ውስጥ እጅግ የምንኮራበትና የምንደግፍበት አቅም ነው:: አቅሙም ሰብአዊ ድጋፍ በራስ ለመቻል ትልቅ ጉልበት ነው:: በራስ አቅም የሚለው እንደ ሀገር ሲታይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ማኅበረሰቡን በመደገፍ በተቻለ መጠን ከውጭ ርዳታና ጥገኝነት ለመገላለገል ያስችላል::
ሰብሰብ ሲባል የፌደራል መንግሥት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሥራ ክልሎችም በኮሚሽኖቻቸው አማካኝነት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የአደጋ ሥራ አመራር ምክር ቤት ያለ ሲሆን፣ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል ፕሬዚዳንቶችና ኮሚሽኖች ሥራዎችን የጋራ እያደረጉ እየታቀደ የሚሠራ ሥራ ነው:: አደጋዎችን አካቶ ከመተግበርም አኳያ በዘለቄታዊነት የራስን አይበገሬነት መፍጠር ላይ የየራሳቸው ሚና እና ድርሻ አላቸው::
የዕለት ደራሽ የሰብአዊ ድጋፉን በአብዛኛው እየሸፈን ስንሄድ ወደ ልማቱና አይበገሬት ግንባታው፣ ወደ ውሃ ልማት፣ የተለያዩ የእርሻ ሥራዎችን እንዲደግፉ ማድረግ እንዲቻል የዕለት ደራሹን መደገፍ አለብን:: የዕለት ደራሽን ከልማቱ ጋር አስተሳስረን የመሸከም የእኛ ኃላፊነት ይሆናል:: ሌሎቹ ግን እንደሚሰጡት ድጋፍ ይቀጥላሉ::
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ አደጋን ቀድሞ ከመከላከል አኳያ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎቹ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው? የዝግጁነት አቅማችሁ እንዴት ይገለጻል?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡– ትልቁ ጉዳይ ተብሎ የሚወሰደው የተፈጥሮ አደጋዎችን ሁሉንም እንገምታለን፤ ሁሉም ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርሱ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ዓለም ላይ አልተፈጠረም:: በተለይም ከቅጽበታዊ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ያለውን ለአብነት ብንወስድ ቅርብ ጊዜ ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ንዝረት፤ ከዚህም ቀደም ብሎ አጋጥሞ የነበረው የመሬት መንሸራተት አልፎ አልፎም በደራሽ መልክ የሚከሰቱ የጎርፍ፣ የእሳት አደጋዎች፣ ባልተወሰነ ሁኔታ እና ባልታሰበ ሰዓት ላይ የሚፈጠር ክስተት በጣም ዘግናኝ የሆነ ውጤት የሚያስከትሉበት ሁኔታ አለ:: እነዚህን አደጋዎች ቀድሞ ገምቶ ቀድሞ በመገኘት የሚሰራባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ:: አቅሙን በየጊዜው እየገነቡ መሄድ ያስፈልጋል:: ፈጣን የሆነ ምላሽ መስጠትና ማዳን ላይ ያሉ አቅሞችን ማጠናከር እንዳለብን በመረዳት እንዲሁም የፖሊሲያችን አካል ስለሆነ የቅጽበታዊ አደጋዎች አገልግሎት ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ጭምር በማድረግ በአግባቡ እንዲመራ ዝግጅት እየተደረገ ነው:: ስለዚህ ተቋማዊ አቅም ጭምር ለመፍጠር እየተሰራ ነው::
ከድርቅና መሰል አደጋዎች ጋር በተያያዘ በዘገምተኛነት የሚፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ የአየር ንብረት ለውጡ አደጋ በሚያስከትልባቸው አካባቢዎች የአይበገሬነት ግንባታ ሥራ ትኩረት የሚጠይቅ ነው:: የትም አካባቢ ላይ ምን ሊከሰት ይችላል? የሚለው ከወዲሁ ገምቶ የመሥራት ባሕልን አዳብሮ በተጠያቂነት መሥራት የፖሊሲያችን አንዱ አካል ነው::
ከፊሉ የልማት ጥያቄ ነው:: የመስኖ ልማትን፣ የተቋማት ግንባታንና ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ክልሎች የሚሰሯቸው ሥራዎች ሲሆኑ፣ አንዱ አካቶ መተግበር ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው:: ለምሳሌ የቆላማ አካባቢዎች የሚሰራ ልማት አለ:: ልማቱ አንድ ጊዜ ሁሉንም ያዳርሳል ወይ? የሚለው ደረጃ በደረጃ የሚኬድበት ነው:: ሁሉም ነገር በታሰበው ልክ ተሟልቷል ተብሎ የሚያዝ አይደለም::
በልማት የሚመለሱ ጥያቄዎቸ እንዲመለሱ እያደረጉ በመሄድ አንዳንዱ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ እና ተከታታይ የሆነ ነገር ሲኖር እየተከናወነ ያለው የልማት ሥራ የዜጎችን ሕይወት እንዳይጎዳ የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎች ይሰራሉ:: ይህ እየተሰራ እያለ ቅጽበታዊ አደጋዎች ሲኖሩ ከአቅም በላይ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ:: ዘገምተኛ ሁኔታዎች ሲኖሩ አስቦና አቅዶ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ እንዳይከሰት አድርጎ በመሥራት ላይ ተሻሽሏል:: ነገር ግን አሁንም መሥራት ይጠይቃል::
በአሁኑ ወቅት አራት ተቋማት ለዚህ እንዲሆኑ እየተደራጁ ነው:: ለምሳሌ የቅጽበታዊ አደጋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም እየተደራጀ ነው:: ተቋሙ ሁሉንም አይነት አደጋዎች ሲከሰቱ የተሟላ ሊሆን ይችላል:: ለዚህ በተደራጀ አግባብ የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ፈጥኖ ማዳን የሚችል በከፊል ወታደራዊ (paramilitary) ያለው አቅም የያዘ ተቋም ግንባታ አልቆ መንግሥት በሚወስንበት ደረጃ ላይ ይገኛል:: ከመጠባበቂያ ክምችት የሥትራቴጂክ መጠባበቂያ አገልግሎት የሚሰጥ ዘርፍ በማቋቋም ወደ 50 ሺ ሜትሪክ ቶን የሰብአዊ ድጋፍ አከማችቶ የሚጠብቅ ተቋም ይደራጃል::
በየትኛውም ጊዜ አደጋ ሲከሰት አውጥቶ መልቀቅ ሳይሆን በሚታይ፣ በተጨባጭና በተጠና መንገድ እንዲሰራ የማንንም ድጋፍ ሳይጠብቅ የሚሄድበት የሥትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት ሥርዓት እየተገነባ ነው:: የዕለት ደራሽ ክምችት በእለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮችን ለመቋቋም እንደ ኮሚሽን ወደ 600 ሺ ሜትሪክ ቶን ለመያዝ እየተሰራ ነው:: ለዚህ የሚሆን የክምችት አቅም መፍጠር ሲሆን፣ የማከማቻ መጋዘኖች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግ ነው:: ይህም ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል ላይ በማስቀመጥ የምንቸገርበት ቀን ካልመጣ ያከማቸነውን በማቀያየር ወደ ገንዘብ በመቀየር ወይም እህል ነክ ወዳልሆኑ ሰብአዊ ድጋፎች እየቀየርን የምንሄድበት ሁኔታ አለ::
ለሁሉም ነገር እጅግ መሰረታዊ ነገር የሚባለው የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ ማደራጀት ነው:: የተነሱት ነገሮች በሙሉ የገንዘብ ፍላጎት የሚጠይቁ ስለሆኑ የምንፈልጋቸውን ገንዘቦች ከሌላ ቦታ ለማፈላለግ ከመሞከር ይልቅ በራሳችን አቅም ሁሉም ዜጋ በአንድም በሌላ መንገድ በአደጋ የሚጎዳ ከሆነ በአጋርነት የምንቆምበትን አሰራር ለመትከል የሚያስችል ነው:: የአደጋ ምላሽ ፈንድ ማቋቋም የፕሮግራሙ አካል ሲሆን፣ ክልሎች ቀድመው ጀም ረዋል::
ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ብንወስድ ‘ቡሳ ጎኖፋ’ የሚባለው አደረጃጀት የተጀመረው ማኅበረሰቡ፣ ሠራተኛው፣ አመራሩና በየደረጃው ያለው ሕብረተሰብ ራሱን አደራጅቶ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ታስቦ ሲሆን፣ ሚናውንም እየተወጣ ነው:: ለገንዘብ ድጋፍ፣ ለትምህርት ቤት ምገባ፣ ለተቸገሩ ዜጎች ለሰብአዊ ድጋፍ ምላሽ የሚሆን ሀብት ማሰባሰብ ያስፈልጋል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በትልቁ የሚታየው የማኅበረሰቡ እርስ በርስ መደጋገፍ ሲሆን፣ ሥርዓቱ ተለምዷዊ በሆነ መንገድ የቆየ ነው:: ይህን ተለምዷዊ አሰራር ፈጥሮ እውቀትና ክህሎት ተጨምሮበት የዕለት ደራሽ ድጋፍን በዘላቂነት ጭምር እንዲካተት መሥራት ያስፈልጋል:: እነዚህን መሥራት ከተቻለ የምናስባቸው የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ በተለይ የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ የሚሹ ቀደሞ ለመድረስ የሚያስችል አቅም መፍጠር እንችላለን::
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር ውስጥ ከተፈጠሩ ግጭቶች ጋር በተያያዘ የነበረው ሠብአዊ ድጋፍ ምን ይመስላል? ችግሩን በመከላከል ሂደት ፖሊሲው ያስገኘው አዎንታዊ ውጤት ምንድን ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡- ለሰብአዊ ድጋፍ በሀገራችን ያለው አቅም ሕዝባችን ነው:: ብዙ አጋሮችና የመንግሥት አቅሞች ተሰባስበው የሚፈጥሩት ነገር ቢኖርም፤ ሕዝባችን ውስጥ ያለው የአይበገሬነትና የመደጋገፍ ሥራው ከምናስበው በላይ ጠንካራ ነው:: በየአካባቢው ባለው እንደ እድርና እቁብ ያሉ አደረጃጀቶች የሚሠራው ሥራ ከፍ ያለ ነው:: ሕዝቡ በባሕላዊም ሆነ በኃይማኖታዊ መንገድ ያለው የመደጋገፍና የመተጋገዝ ልምምዱ ከፍተኛ ነው::
ከመንግሥታዊ መዋቅራችን በተለይም በለውጡ ስሪት ውስጥ የሚሰራው ሠው ተኮር ሥራ ነው:: ይህም ሲባል ዜጎች ሲጎዱ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ የሚሠራ ሥራ ነው:: አንድ መንግሥት ለዜጋ ካለው ኃላፊነት የሚመነጭ ግዴታ በመሆኑ ዝግጅቶች አሉ:: ለአብነት በኮሚሽን ደረጃ ሁልጊዜም ቢሆን የመጠባበቂያ ተቋም አለ ብለን ባንናገርም ግን መጠባበቂያ ይዘናል:: ባለፈው ክረምት ላይ ጎርፍና ሌሎች አደጋዎች ሊከሰት ይችላል የሚል የአየር ጠባይ ትንበያ ስለነበር በየክልሉ ወደ 252 ሺ ኩንታል የዕለት ደራሽ በየቦታው በማድረስ በየማከማቻ መጋዘኑ አስቀምጠን ነበር:: ነገር ግን እንደ አጋጣሚ ጎርፉ እንደ ትንበያው አልሆነም:: በየዓመቱ ለዚህ ሥራ መንግሥት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ይመድባል:: በተያዘው በጀት ዓመትና ባለፈው ዓመት 15 ቢሊዮን ብር ድረስ የሚገመት ሀብት መድቧል::
ሰብአዊ ድጋፍ በራሥ አቅም በሚለው እሳቤ እንያንዳንዱ ክልል በራሱ ጊዜ አምርቶና አከማችቶ የሚሰራበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ክልሎች የሚሸፍኑት በራሳቸው አቅም ነው:: በሂደት ዘላቂ የሆነ ምርታማነት፤ ወደ አይበገሬነት እያለፉ የሚሄዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ስለዚህ በተለያየ መንገድ የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን የሚሉ ሠዎች እንደሚያራግቡት አይደለም::
ከ10 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ከ30 እስከ 40 ሺ የሚሆን አመራርም ተወያይቶበት እንደሀገር ሰብአዊ ድጋፍ በራስ የመቻል አቅም እየተገነባ ነው:: ይህ አቅም የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አቅም ነው ማለት ሳይሆን፤ የሁሉም ተቋማትና ማኅበረሰብ እንዲሁም የሁሉም ክልሎችና ማኅበረሰቡም በየደረጃው የሚፈጥረው አቅም ነው::
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ባለፈው ዓመት የምግብ ማስቀየስ ሥራ ፈጥረዋል ተብሎ ከስድስ እስከ ሰባት ወር ድረስ የአጋር ተቋማት የሰብአዊ ድጋፍ ተቋርጦ ነበር:: በዚህ ወቅት ሕዝባችን ምንም የሆነው ነገር የለም:: በኮሚሽኑ በኩልም አቅም በመጨመር ቅድሚያ ሰርቷል:: ነገር ግን ተቋረጠ ተብሎ ከሚታወቀው የበለጠ ጉዳት ተፈጥሮ ማኅበረሰቡ ችግር ውስጥ ገብቷል ተብሎ ሪፖርት የሚደረግ ነገር የለም:: ይህ ማለት ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው የመደጋገፍ አቅም እየሰራ ነው::
ድሮውንም ቢሆን 15 ኪሎ ግራም የሰብአዊ ድጋፍ ሕይወቱን አቆይቷል ማለት ሳይሆን፤ የመደጋገፉና የመተባበሩ ሥራ ሁልጊዜም ስላለም ጭምር ነው:: መዋቅሮቻችንም በቅርበት በመሆን ችግሮችን በመለየት በማስተባበር የሚሰራ ሥለሆነ ነው:: በዚህ ሁሉ ድምር አቅም ሕዝባችንን ከተረጂነት ለማውጣት እየተሰራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚቀጥለው በልግ ወቅት የሚኖረውን የአየር ጠባይ አስመልክቶ በሰጠው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ትንበያ ሰጥቷል፤ እናም የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የኮሚሽኑ ዝግጁነት እስከምን ድረስ ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡- እስካሁን ጥሩ ነገሩ ከባለፈው ዓመት በልግ ጀምሮ የዝናብ ሁኔታው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ነው:: በሚቀጥለው በልግ የሚታየው ዝናብ ደቡብና ሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢ ላይ መደበኛና ከመደበኛ በታች ሊሆን የሚችል የዝናብ ሥርጭት ትንበያ ተሰጥቷል:: በትንበያው መሰረት እያንዳንዱ አካባቢ ላይ ምንድን ነው? ማድረግ ምንችለው የሚል ምክረ ሀሳብ ይሰጣል:: ትልቁ ምክረ ሀሳብ በእንስሳቱ፣ በግብርናው፣ በውሃ ተቋማትና በጤና ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጉዳቶች እንዳይከሰቱ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል::
የእኛ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት በቅርብ ጊዜ ተቋማትና ክልሎች ባሉበት ምክክር ያደርጋል:: በምክክሩ ምን አይነት ቀድሞ ተገኝነት ይኑር፤ የሚል ሲሆን፣ አንዱና ትልቁ ሥራ ይህንን በማወቅ እጅ ላይ የገባው ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይባክን ማድረግ ነው:: የዝናቡ ሁኔታ አገባቡና አወጣጡ ምን መልክ ሊኖረው ይችላል? እንጂ ምንም ነገር እንደማይኖር አልተተነበየም:: የእኛ ችግራችን ቀድሞ ውሃ አከማችቶ ይዞ የመጠቀም ከፍተት ነው::
መረጃዎች በየጊዜው እየተሰጡ ነው:: ዝግጅቱ ላይ ከክልሎች ጋር ምክክር በማድረግ ጎን ለጎን የምናደርገው መልዕክቶችን ማስተላለፍ ነው:: የድርቅ ማንቂያ መልዕክቶች ይተላለፋሉ:: ከዚህ ጎን ለጎን አደጋ ቢከሰት መደገፍ የሚያስችለን የሰብአዊ ድጋፍ የክምችት አቅም፣ የፈንድ አቅምና ማኅበረሰቡ እርስ በርስ የሚደጋፍበት አቅም እያጎለበተ ሲሄድ ከየአር ንብረት ለውጥ ጋር የሚመጡ ችግሮች እየተቀረፉ ይሄዳሉ::
አዲስ ዘመን፡- የሰብአዊ ድጋፍ ከማከማቻ መጋዝን ተጭነው ድጋፍ ለሚሻው ማኅበረሰብ በትክክል እንዲደርስ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ ይነገራል፤ የኮሚሽኑ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ እስከምን ድረስ ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡- የዕለት ደራሽም ይሁን በተለያዩ መንገዶች የሚጓጓዙ ድጋፎች ከሁሉም በላይ በቅንጅት ይሰራል:: ከኮሚሽኑ የሚላኩ ድጋፎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለተረጂው እንዲደርስ ከክልሎች ጋር ይሰራል:: ክልሎች ወደ ሚሄድበት ቦታ በሚደረገው የማጓጓዝ ሥራ የሰላምና የጸጥታ ዘርፉ ተቀናጅቶ ካልተሠራ ላልተገባ ዓላማ ይውላል:: ወደ አካባቢዎች ከደረሰ በኋላ ማኅበረቡም የአካባቢው መዋቅርም የጸጥታ አካላት፤ የሰላምና ደህንነት መዋቅር በጋራ እያንዳንዱ ሰብአዊ ድጋፍ ወደ አልተፈለገ ቦታ የሚሄድበት ሁኔታ ስለሚኖር የጋራ ክትትል ማድረግ ይፈልጋል:: በዚህ ረገድ ከዚህ በፊት ከነበረው ይልቅ ተጠያቂነትን በሚመለከት የረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ለጠቅይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ገብቷል:: ይህ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ አላስፈላጊ የሆኑ ጥቅሞችና እጃቸው የሚያስገቡ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል ሕግ ነው:: ከዚህ በፊትም ተጠያቂ የሆኑ አካላት አሉ::
ነገር ግን በተደራጀ መንገድ የሕግ ረቂቅ አካል አድርገን በማስቀመጥ ወንጀል የሠሩ ሠዎች ከተያዙ በኋላ የሚጠየቁበት አንቀጽ በተድበሰበሰበ መንገድ የመሄድ ሁኔታዎች ነበሩ:: ስለዚህ ግልጽነት ያለው ሕግ እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ ነው:: ችግሩ በአንድ በኩል በሚታወቅ አሰራር እንዲመራ ሕግ ተዘጋጅቶ የጋራ እያደረግን ነው:: ቤተሰብ ውስጥ ማን ነው ተጠቃሚ መሆን የሚገባው? የሚለው የቤተሰብ ደረጃ ልየታ ሥራ ተግባራዊ እያደረግን ነው:: ከሁለቱ ወጥቶ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲህ አይነት ድርጊት ላይ የሚሳተፉ ሠዎችን ልንሸከም እንደማንችል የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል::
ሕጋዊ ሂደቱ ላይ ተጠያቂነት ሲፈጠር የመሸፋፈን ሁኔታ እዳይኖር ግልጽ የሆነ የሕግ ረቂቅ ቀርቧል:: የራሱን ችግር በራሱ እየፈታ የሚሄድበት ሥርዓት ሲተከል ወደ ሆነ ቦታ የሚሄደው ድጋፍ እየቀነሰ ስለሚሄድ እንዲህ አይነት ችግሮች እየቀነሱ ይሄዳሉ:: የዚህ አይነት ፍላጎት ከስንፍና እና ከሌብነት የሚያያዝ ነው:: የአካባቢውን ማኅበረሰብ አስተባብሮ፣ አቀናጅቶና ደግፎ ግብዓት አቅርቦ ወደ ምርት ከመውሰድ ይልቅ ቀለል ባለ መንገድ ለመሄድ የመፈለግ ሁኔታ ይታያል:: ስለዚህ ስንፍና እና ሌብነትን መታገል ከማኅበረሰቡ ጋራ በጋራ የሚሰራ ሥራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከውጭ የሚመጡ የሰብአዊ ድጋፎችን የምታስተናግዱት በምን መልኩ ነው? የግንኙነት መርሃችሁ መሰረቱ ምንድን ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡- ከአጋር ተቋማት ጋር ሰብአዊ ድጋፍን የምናስተናግድበት ማሕቀፎች አሉ:: ሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት እየተባለ በዓመት ሁለት ጊዜ በክረምትና በልግ አካባቢ ላይ የሚሰሩ ጥናቶች አሉ:: ጥቶችን መሰረት በማድረግ ምን አይነት የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት ይኖራል የሚለው የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣… ወዘተ እየተባለ የምግብ ጉዳዮች የሚያካትት ጥናት እየተሰራ በየዓመቱ ይህን ያህል ሀብት ያስፈልጋል የሚል ለዓለም ዓቀፍ ማሕበረሰቡ ይቀርባል:: በዚህ መንገድ የሚመጣው ሀብት ወደ እኛ የሚመጣ አይደለም::
ራሳቸው የዩናይትድ ኔሽን ተቋማት ለተቋማት ድጋፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ:: በዚህ አይነት ሥራ ላይ የሚውለው ሀብት በዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ነው:: ከ20 ዓመት በፊት ከጠቅላላ ፍላጎት 96 ከመቶው ይሸፍናል ተብሎ ከሚታሰበው በዚህ ዓመት 20 በመቶም አይሸፍንም:: ለምሳሌ ባለፈው እኤአ 2024 ላይ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት ወደ አራት ቢሊዮን አካባቢ ተገምቶ የነበረ ሲሆን፣ የተገኘው 30 ከመቶ ነው:: አሁን ያለው ደግሞ 22 ከመቶ ነው:: በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ ሁኔታው ተገማችነቱና ፖለቲካው፣ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ በፈቃደኝነት የሚደረግ እንጂ የሚያስገድዳቸው ነገር የለም:: ይህ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ቅድሚያ ወደ ምንሰጠው መሄዳቸው አይቀርም:: ስለዚህ ዓለም አቀፍ ሁኔታው ሲታይ ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ተብሎ የጀመርነውን የበለጠ አጠናክረን እንድንቀጥል ነው::
አዲስ ዘመን፡- ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም በሚል እሳቤ ሀገራዊ አቅም እየተገነባ ነው፤ ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ሙሉ በሙሉ መሸፈን የሚቻለው መቼ ነው?
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡- የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማሕቀፉ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው:: የተፈጥሯዊ አደጋዎች በዚህ ጊዜ ይቆማሉ በዚህ ጊዜ ይጠፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም:: ሁልጊዜም ቢሆን የሰብአዊ ድጋፍ ሥራ መሥራት ዝግጁነትን የሚጠይቅ ነው:: ሰብአዊ ድጋፍ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ይሆናል፤ የዜጎችና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ይሆናል:: በተለይ ወደ ሀገር ልማት ግንባታ ሲመጣ የዘላቂ ልማት ግንባታ ጥያቄ ነው:: ስለዚህ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ስንል የአንድ ወቅት ሥራ አድርገን አንሰራም:: ሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ድጋፉን በራሳችን አቅም እንሸፍናለን:: በራሳችን አቅም የመሸፈን ሂደት ላይ ቋሚ ተጧሪ እንዳይሆን ሁልጊዜም ራሱን እያሻሻለ አቅምና እየፈጠረ የራሱን ሚና እያበረከተና እየደገፈው ከችግሩ የማስወጣት ሥራ ይሰራል::
እጃችን ላይ ያለው ግልጽ እቅድ በ2017 እና 2018 በጀት ዓመት በወሳኝ መልኩ በሰብአዊ ድጋፍ እንሸፍናለን የሚል ነው:: ይህ ማለት ዓለም አቀፍ መደጋገፍና መተጋገዝ የለም ማለት አይደለም:: ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በአጋርት አብረን የምንሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ:: ዋና ገዥ ሀሳቡ ከተረጂነት መላቀቅ ነው:: ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ኃላፊነት መውሰድ አለበት::
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን::
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)፡- እኔም ለሰጣችሁኝ ዕድል ከልብ አመሰግናለሁ::
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም