
አፍሪካውያን የብዙ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት ናቸው። ጸጋዎቻቸውን በአግባቡ አውቀው ዛሬና ነገዎቻቸውን ከትናንቶች የተሻሉ ለማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መረጋጋት አጥተው ረጅሙን ዘመናቸውን በድህነት እና በኋላ ቀርነት ለማሳለፍ የተገደዱ እንዲሁም ግጭቶች እና ጦርነቶች በሚፈጥሯቸው የሰላም እጦቶችም ለስደት የተሰጡ ሕዝቦች ናቸው።
አፍሪካውያን ቀደም ባሉት ዘመናት የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ሲጀምሩና ለትግሉ ስኬት ከፍ ያለ የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ፣ የተሟላ ፖለቲካዊ ነጻነታቸውን ማስከበር፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን ተጨባጭ ማድረግ እና አንገት ከሚያስደፋ ሁለንተናዊ ባርነት ቀና ብሎ የሚያራምድን ሁለንተናዊ ነጻነት ተስፋ አድርገው ነበር።
ይህ እውነታ ለቀደሙት የአፍሪካ አባቶች ሆኑ አሁን ላይ ላለው አፍሪካዊ ትውልድ ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም፤ አፍሪካውያን ዛሬም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነጻነታቸውን ባሰቡት ልክ እና በከፈሉት የመስዋዕትነት መጠን ተጨባጭ ማድረግ አልቻሉም። አሁንም በእጅ አዙር አገዛዝ እና ሴራ ብዙ ዋጋ የከፈሉለትን ነጻነታቸውን ተነጥቀው በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለመኖር ተገደዋል።
ዛሬም በብዙ ጣልቃ ገብነት እና መልከ ብዙ ሴራዎች በቅኝ አገዛዝ ዘመን እንደሆነው የሀብቶቻቸው እውነተኛ ባለቤት መሆን አልቻሉም፤ አሁንም የራሳቸውን እጣ ፈንታ እንዳይወስኑ የብዙ ወከባ እና ግራ መጋባቶች ሰለባ ናቸው። ሕዝቦቻቸው ዛሬም የቅኝ አገዛዝ ዘመን ጥላ በሆኑ ትርክቶች ብዙ ያልተገባ ዋጋ በሚያስከፍሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ውስጥ ናቸው።
አፍሪካውያን የአባቶቻችን የነጻነት ትግል እና ትግሉ ካስከፈለው ዋጋ አንጻር የትግሉን ተስፋ /ራዕይ የራሳችን ማድረግ አልቻልንም፤ በአባቶቻችን የነጻነት ተጋድሎ የተገኘውኝ የፖለቲካ ነጻነት ወደ ሁለንተናዊ ነጻነት (ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ) ለማሸጋገር የሚጠይቀውን ተጨማሪ ትግል በቁርጠኝነት ማስቀጠል አልቻልንም። የሀገር እና የማንነት የተሟላ ክብርን እውን ለማድረግ ለሚያስፈልገው ትግል ራሳችንን አላዘጋጀንም።
እጁን አጣምሮ እርዳታ መጠበቅን፣ ሕይወቱን አደጋ ውስጥ በመክተት ስደት እና በስደት ውስጥ ያለውን አንገት የሚያስደፋና ልብ የሚሰብር ሕይወት አማራጭ አድርጎ መሄድን መርጠናል፤ በዚህም ሰብዓዊ ክብርን በሚፈታተኑ ቀናቶች ዘመናትን ለማሳለፍ ተገድደናል። ዕጣ ፈንታችን ከእጃችን ወጥቶ በሌሎች እጅ ገብቷል።
አባቶቻችን ትውልድ ተሻጋሪ ለሆነ ነጻነት ትግል ከጀመሩ ከሰባት እና ከስምንት አስርት ዓመታት በኋላ ዛሬም ልጆቻቸው፣ የፖለቲካ ነጻነታችንን ሙሉ በሙሉ በእጃችን ማስገባት አልቻልንም፤የብዙ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤቶች ሆነው ሳለ ዛሬም ቀናትን አሸንፎ ለማለፍ የሌሎችን እጅ እየጠበቅን ነው፤ ዛሬም ለማህበራዊ ማንነታችን ተገቢውን ስፍራ ሳንይዝ በማንነታችን አንገታችንን የምንደፋበት ሁኔታ አልተለወጠም።
ከዚህ ይልቅ የቅኝ ግዛት ዘመን ትርክቶች በፈጠሯቸው የልዩነት ግራ መጋባቶች በመካከላችን የነበረው አንድነት እየተሸራረፈ ፤ እንደቀደመው ዘመን ለጋራ አጀንዳዎቻችን በአንድነት የምንቆምባቸው እድሎች እየጠበቡ ነው፤ ባለመተማመን እና ከዚህ በሚመነጭ የጠላትነት እሳቤ በተፈጠሩ ግጭቶች እና ጦርነቶች ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን ነው።
የቅኝ ግዛት ዘመን ትግሉን ሲፈታተን የነበረው ባንዳነት፤ እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ ከትናንት ወጥተን ነገዎቻችንን የተሻሉ ለማድረግ በምናደርጋቸው ትግሎች ውስጥ ትልቁ ተግዳሮት እየሆነ ነው። የሕዝብን የሰላም እና መልማት መሻት አሳልፎ ለግል ፍላጎት መስጠት፤ ከዚህም የተሻለ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ ማሰብ እና ለተግባራዊነቱ የሀገርን ሀብት እና የሕዝብ አቅም መባከን ዛሬም ትልቁ ፈተናችን ነው።
የልዩነት ትርክቶችን ምንጭና አጠቃላይ ዓላማ በአግባቡ ሳንረዳ፤ ትርክቶቹ በፈጠሯቸው ግራ መጋባቶች እና ውዥንብሮች አፍሪካውያን የጋራ አጀንዳዎቻችንን እውን ለማድረግ የሚያስችለንን አንድነታችንን አደጋ ውስጥ ከተናል። በዚህም ለጋራ አጀንዳዎቻችን የምናደርጋቸው ትግሎች ትርጉም ያለው ውጤት ሳያመጡልን ቀርተዋል።
ለዚህ ትልቁ ማሳያ አፍሪካውያን በፓን አፍሪካዊነት እሳቤ አንድነታቸውን አጽንተው የተሟላ ነፃነታቸውን እውን ለማድረግ፤ በአህጉሪቱ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያደረጉት ትግል ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ብዙም እርምጃ መራመድ የቻለ አይደለም፤ ዛሬም አፍሪካውያን ኅብረታቸውን በተቋም ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ቢችሉም በጋራ አጀንዳዎቻቸው ዙሪያ ግን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው የሚጠበቀውን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር አልቻሉም።
አፍሪካውያን ተጨባጭ የሆነ አንድነት ማጣታቸው የጋራ አጀንዳዎቻቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ድምጽ እና በላቀ ቁርጠኝነት ማስፈፀም እንዳይችሉ ፈተና ሆኖባቸዋል። አህጉሪቱ እና ሕዝቦቿ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ውክልና ማግኘት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
ከነጻነት ትግሉ ዋዜማ ጀምሮ አፍሪካውያንን እንደ ጥላ ሲከተል የኖረውን ይህን ያለመተባበር ተግዳሮት በተገቢው መንገድ ተረድቶ መፍትሔ ማፈላለግ የዚህ ትውልድ ዋና ኃላፊነት ነው። አፍሪካውያን ዓለም በጥቂት ኃይሎች በብዙ እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት ከሁሉም በላይ ከቅኝ ግዛት የጥፋት ትርክቶች ወጥተው አንድነታቸውን ማጠንከር ይጠበቅባቸዋል።
በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ አፍሪካውያን የራሳቸውን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ አዲስ የፖለቲካ መነቃቃት እና ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ ካልቻሉ መጪዎቹ ዘመናት ለአፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ዘመን ከነበረው የሕይወት ትርክት የተለየ ይጠብቃቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።
ለዚህ ደግሞ የአፍሪካውያን መሪዎች ኃላፊነት ከፍ ያለና የማይተካ ነው። በተገኘው አጋጣሚ ሆነ በተፈጠሩ አጋጣሚዎች አፍሪካውያን የራሳቸውን እጣ ፈንታ ተጨባጭ ማድረግ የሚችሉበትን የትግል ስትራቴጂ መንደፍ እና ለተግባራዊነቱ ቁርጠኞች መሆን ይኖርባቸዋል። የቀደሙት አባቶቻችንን ብዙ የሕይወት መስዋዕትነት የጠየቀው የነጻነት ትግል ሙሉ ማድረግ የምንችለው ይህን በብቃት መፈፀም ስንችል ብቻ ነው።
ከግጭት እና ከጦርነት፣ ከጠባቂነት እና ከልመና፣ ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ለዘለቄታው ልንወጣ የምንችለው የራሳችንን እጣ ፈንታ በራሳችን መወሰን ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ተፈጥሮ ያደለችንን ሀብት ወደ ልማት መለወጥ የሚያስችል ቁርጠኝነት ያስፈልገናል። ለጋራ አጀንዳዎቻችን በአንድነት በጽናት መቆም ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም