
በአንድ ወቅት ፆታውን ደብቆ ለ48 ዓመታት በቀሚስ የኖረው ሸዋዬ ጉዳይ እጅግ አነጋጋሪ ነበር። ራሱ በራ ስለሆነም ማንነቱ እንዳይገለጥ ሻሽ ያስራል። ያንን ሁሉ ዘመን ማንም ሳያውቅበት በሴትነት ስለኖረውና ተከሶ ፍርድ ቤት ስለቀረበው ሸዋዬ ደገፉ፤ ከአዲስ ዘመን ማኅደር እናስታውሰዋለን። ሻይ ቤቶች ደግሞ በኅብረተሰቡ ላይ ጠንቅ እያስከተሉ ናቸው ተብለው የተወቀሱበት ዘመን እናስታውሳለን። ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ተሰውረው፣ በሻይ ቤቶች ውስጥ በጠረጴዛ ዙሪያ ተኮልኩለው ጫት እያኘኩና ሲጃራቸውን እያቦነኑ የአሉባልታ ወሬ ያወራሉ። ከወስላቶችም ጋር በመሆን ለውስልትና ሊዳረጉ ነው በሚል ሻይ ቤቶቹ ላይ የርምጃ ክስ ቀርቧል። በሌላ በኩል ደግሞ “ፊደል የማይማር ሠራተኛ ይቀጣል” ይላል። በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ፣ እነኚህን መሰል ጉዳዮችን እያነበብን እናስታውስበታለን።
ሻይ ቤቶች በኅብረተሰቡ ላይ ጠንቅ በማስከተላቸው ርምጃ ይወሰዳል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያና አካባቢ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ተስፋፍተው የሚገኙት ሻይ ቤቶች ለወጣቱ ዜጋ መጥፎ የወንጀል ዘዴ መወያያና የወስላቶች መደበቂያ ሆኖ በመገኘቱ ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጠንቅ የሚያስከትል በመሆኑ ወላጆች አሳዳጊዎችና ቤተሰቦች እንዲሁም የፖሊስ አባሎች በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰፊው ተወያይተው በኅብረት ርምጃ በመውሰድ ላይ መሆናቸውን የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ትላንት ገለጠ።
በአዲሱ ከተማ ዋና መንገዶችና ሠፈሮች እንዲሁም ስውር ሠፈሮች በተከፈቱ የሻይ ቤቶች ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት እስከ 17 ዓመት መካከል የሚገኙ ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ተሰውረው ወርቃማ ጊዜያቸውን በአሉባልታና በንዝህላልነት በጠረጴዛ ዙሪያ ተኮልኩለው ጫት በማኘክና ሲጃራ በማቡነን ተሰብስበው ማሳለፍ የመጥፎ ጠባይና የወንጀል ባለቤት ስለሚያደርጋቸው መንግሥትም ሆነ ዕድሮች እንዲሁም የወላጆች ቤተሰቦች በኅብረት አድራጎቱ የሚወገድበትን ዘዴ በቅድሚያ መውሰድ አስፈላጊ ስለሆነ በዚህ ረገድ የሚወሰደው ቁጥጥር የቀጠለ መሆኑን የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ አስረድቷል።
ተስፋፍተው በሚገኙት ሻይ ቤቶች ውስጥ ልጆች ከትምህርት ዓለም ተሰውረው ጫት በማኘክና ሲጃራ በማቡነን የሚያካሄዱት ውይይት በልዩ ልዩ ወንጀል፤ በሌብነት፤ በዘረፋ ቅጣታቸውን ከፈጸሙ ወስላቶች ጋር መሆኑን አንዳንድ ቤተሰቦችና የዕድር አባሎች ከፖሊስ ጋር በመሆን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ጉዳዩ አሳሳቢና ለኅብረተሰቡ ጠንቅ ስለሆነ ሁኔታውን በማውገዝ ወላጆች የዕድር ዳኞች ከፖሊሶች ጋር በመተባበር ብርቱ ቁጥጥር በማድረግ አጥፊዎች ወደ ሕግ ቀርበው የሚቀጡ መሆናቸውን የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ቃል አቀባይ አስጠንቅቋል።
በከተማው መገበያያ ዙሪያና አካባቢ በሚገኙት ሻይ ቤቶች ውስጥ ወስላታውን ከደኅናው መለየት በማይቻል አኳኋን ወጣቶቹ ተኮልኩለው ጫት በመዘርጋትና በማኘክ ወሬ ሲደረድሩ ቀኑን ሙሉ ካሳለፉ በኋላ በምሽት ለወንጀል ተባባሪ ወይም ተካፋይ ሆነው በመገኘታቸው ወላጆች የልጆቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ ባለባቸው ኃላፊነት ልጆቻቸው ከወንጀል ንጹሕ የሚሆኑበትን ቁጥጥር እንዲያደርጉና በዚህም አንጻር ቤተሰቦችና የዕድር አባሎች ከፖሊስ ጋር እንዲተባበሩ የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ቃል አቀባይ በተጨማሪ አሳስቧል።
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 1966 ዓ.ም)
ፊደል የማይማር ሠራተኛ ይቀጣል
ከትሪፖሊ፤(ሮይተር)- የሊቢያ መንግሥት ማንኛውንም ያልተማሩ የመንግሥት የግል መሥሪያ ቤቶች አባል በቅርቡ በሚከፈተው የፊደል ሠራዊት ኮርስ በግዴታ እንዲከታተል የሚያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ይህንንም ለማድረግ ማንኛውም መ/ቤት በውስጡ ተቀጥሮ የሚያገለግለውን መሐይም ስም እንዲያሳውቅ ተጠይቋል። ይህም ከተደረገ በኋላ፤ መንግሥቱ ስሙን በመዝገብ ይዞ በኮርስ እንዲካፈል የሚያስገድደው መሆኑን ከዚያ የደረሰን ዜና ያመለክታል፡፡
(አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 1960ዓ.ም)
ለ 48 ዓመታት ቀሚስ የለበሰው
ወንድ ተከሰሰ
48 ዓመት ሙሉ እንደ ሴት ቀሚስ በመልበስ ሸዋዬ ደገፉ በመባል በሴት ስም ይጠራ የነበረ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ሸዋዬ ደገፉ የወንድ ፆታውን በመደበቅ ቀሚስ ለብሶ በሴት ስም በመጠራት ካሳለፈው 48 ዓመታት ውስጥ በናዝሬት 10 ዓመት፣ በአሰላ ከተማ አራት ዓመት፣ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ 11 ዓመት በታላላቅ ሰዎች ቤት በሴት ሥራ ሙያ እየተቀጠረ መኖሩን ገልጿል።
ሸዋዬ የወንድነት ፆታው እንዳይታወቅበት በአገጩ ግራና ቀኝ በመጠኑ የሚበቅለውን ጢም በየዕለቱ ይላጫል። ጠጉረ በራ በመሆኑም ዘወትር እንደ ሴት ሻሽ ይጠመጥማል። የጆሮ ጉትቻም እንደማይለየው ታውቋል።
ሸዋዬ በትውልድ ሀገሩ በየረርና ከረዩ አውራጃ በኢጀሬ ከሕጻንነቱ ጊዜ ጀምሮ የሴት ቀሚስ ይለብስ እንደነበር ጠቅሶ ወደ ፊትም እስከ ዕለቱ ሞቱ ድረስ ቀሚስ መልበሱን እንደማይተው አስረድቷል።
ተከሳሹ የሴቶቹን ሙያ አጠናቆ የሚያውቅ መሆኑን ገልጾ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ዘፈን የሚወድ፤ በዚህም ሙያ ብዙ ጊዜ እንደተጠቀመበት አረጋግጧል።
ሸዋዬ ደገፉ በናዝሬት፣ በአሰላና በአዲስ አበባ እየተዘዋወረ ለ25 ዓመታት ተቀጥሮ በሚያገለግልበት ጊዜ የወንድነት ፆታው ያልታወቀበት መሆኑን አስረድቷል።
ሸዋዬ ዘመዶቹን ለመጠየቅ ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ኤጀሬ ሲጓዝ ለጥቂት ጊዜ በናዝሬት ከተማ በሴት ሥራ ሙያ ተቀጥሮ ገንዘብ ለማግኘት ባለው ዕቅድ መሠረት በከተማው ውስጥ ሲዘዋወር ፖሊሶች በጥርጣሬ ያዙት። ከዚያም ሲጠየቅ ወንድ መሆኑንና በዚሁ በሴት ሁኔታ 48 ዓመታት ሙሉ መኖሩን አስረድቷል።
በዚህም ፆታ የመለወጥና ቀሚስ የመልበስ አድራጎቱ ተከሶ አዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቧል። ሆኖም በዚሁ ሁኔታ ለመኖር የፈለገበት ምክንያት በሚገባ እስኪጣራ ድረስ በዋስ መለቀቁ ታውቋል።
(አዲስ ዘመን የካቲት 6 ቀን 1963 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም