
“በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ የ8 ዓመቷ ሕፃን ሲምቦ ብርሃኑ ከቤት ተወስዳ ከተደፈረች በኋላ ተሰቅላ እና ተገድላ ተገኘች” የሚለው ሰሞኑን እጅግ አሳዛኝ ወሬ ሆኖ ከርሟል፡፡ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ወላድ አትስማው የሚያስብል ክፉ ዜና።
ከዚህ ቀደም በ5 ዓመቷ ሕፃን ሄቨን ዓወት እና በሌሎችም ሴቶችና ሕፃናት ላይ የደረሰው አሰቃቂ ፆታዊ ጥቃት እና የወንጀል ድርጊት ስንሰማው የከረምነው ነው። ደግነቱ ጆሮ ጠገብኩ፣ በወሬ ደከምኩ፣ ወንጀል መስማት ሰለቸኝ፤ አሰቃቂ ወሬ ማድመጥ ዘገነነኝ ብሎ አይገፈትርም። የሀገር ውስጡንም የውጪውንም አሰቃቄ ወሬ ወደድንም ጠላንም ጆራችንን በሁለት እጆቻችን ደፍነንም ቢሆን እንሰማዋለን።
ይህን የሰማ ጆሮ ይህን ወደ ውስጡ የከተተ አእምሮ ዝም ብሎ ተኝቶ ያድራል?። ደስተኛ ሆኖ እየኖረ ነው ? ብሎ ማሰብ ግን አይቻልም። እያንዳንዱ ሰው ይጨነቃል። ይሰጋል። ነገ ልጆቼ ብሎ ያስባል። ሰዎችን ለማመን፣ እንደ ቀድሞ አኗኗራችን አደራ ለመባባል ጭምር ይቸግራል። በአጠቃላይ መተማመንን ያጠፋል። አብሮነታችን ላይ ጥያቄ ይፈጥራል።
ምንም ይሁን ምን እያንዳንዱ ጤነኛ የሆነ ሰው አንድ ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም። ለምንድነው ይሄን አይነት አሰቃቂ ወንጀል የበረከተው? ማንነታችን (ሃይማኖተኛ) መገለጫችን የነበረው ኢትዮጵያዊነት የት ሄዶ ነው ወይንስ… እያልን በርካታ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን። እያንዳንዱ አሰቃቂ የወንጀል ድርጊት ደግሞ በሴቶችና በሕጻናት ላይ ሲሆን ደግሞ ችግሩን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል።
ሴት ልጅ ናት፣ እህት ናት፣ ሚስት ናት ከሁሉም በላይ እናት ናት። ይህች የዛሬ ሕጻን ሲምቦ ታዲያ በምን ወንጀሏ በምን ጥፋቷ አሰቃቂ ድርጊት ይፈጸምባታል። እንዲህ አይነት እና ሌሎችም አሰቃቂ ወንጀሎች የሚፈጸሙት በቅርብ ቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በዘመድ፣ በጓደኛ፣ በቅርብ ሰው መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ ሕመሙን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል።
በትንሽ ግጭት፣ በቅናት ተነሳስቶ፣ በምቀኝነት፣ በቂም በቀል … እየተባሉ የሚፈጸሙ ስሜታዊነትን ወደፊት ያመጣ የወንጀል ድርጊት ሁልግዜም አስከፊና መራር ነው። ብዙዎችን ጎድቷል። ሕይወት አሳጥቷል። አካለ ጎዶሎ አድርጓል። በቤተሰብና ወገን ላይ የማይድን ጠባሳን ፈጥሯል። አሁንም ይሄው ቀጥሏል። ከአዕምሮ የማይጠፋ ከልብ የማይፋቅ አሳዛኝ ሀዘን ነው።
አሁን አሁን የወንጀል ድርጊቶች ተበራከቱ ሲባል ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር ስለሚሰራጭ ሊሆን ይችላል እንጂ ቀደም ሲልም የማይገለጡ በቤተሰብ ተዳፍነው የሚቀሩ (ሚስጢር) የሚደረጉ ጾታዊ ጥቃቶች ብዙ ናቸው የሚሉ ተከራካሪዎች ያጋጥማሉ። በእርግጥ ቀደም ብሎ በነበሩት ዘመናት ምንም አይነት ጾታዊ ጥቃቶች አልነበሩም ብሎ መከራከር አይቻልም። ይኖራሉ፤ ነበሩም።
አሁን ግን ስብዕናችን የት ሄደ፣ የክርስቲያን የሙስሊሙ ተከባብሮ ተዋዶ የሚኖርባት ሀገር ኢትዮጵያ የሚለው ስማችንንና ዝናችንን ማን ነጠቀን? በእህቶቻችን ላይ አሰቃቂ ጾታዊ ጥቃት የምንፈጽመው ለምን ይሆን ? ብለን ማንሳት አለብን። የወንጀል ድርጊቱ እየጨመረም ይሆን እየቀነሰ ማንነታችንን የሚገልጸን አይደለምና ቆም ብለን እናስተውል።
“ በ2015 የበጀት ዓመት አንድ ሺህ 334 ሴቶችና ሕፃናት ‹‹የግብረ ሥጋ ጥቃት በደል›› ተብሎ በሕግ የተቀመጠው ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በ2016 የበጀት ዓመት የወንጀሉ ተጠቂዎች ቁጥር ወደ አንድ ሺህ 355 ከፍ ብሏል፡፡ በዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ደግሞ አንድ ሺህ 195 ሴቶችና ሕፃናት የወንጀሉ ሰለባ ሆነዋል፡፡
ይሄ በዚህ አላበቃም። በ2017 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የተፈፀመባቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሴቶችና ሕፃናት ቁጥር ባለፈው ሙሉ የበጀት ዓመት ከተመዘገበው የበለጠ ነው፡፡ “ ይሄ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ላይ የታየ መረጃ ነው።
ከዚህ በመነሳት የጾታዊ ጥቃት ወንጀል እየጨመረ ነው፤ ወንጀሉም አሰቃቂ እየሆነ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ይሄ የማኅበራዊ ሚዲያ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የተደረጉ ጥናቶችም ይሄንኑ የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህ ቁጥሮች ሪፖርት የተደረጉት ብቻ ናቸው፡፡ ሪፖርት ያልተደረጉት ሲታከልባቸው ምን ያህል ችግሩ እየገነነ እንደመጣ መረዳት ይቻላል።
የአሁኑ ጥያቄ መሆን ያለበት ችግሩ ቀደም ሲልም ነበር አልነበረም፤ የወንጀል ድርጊቱ ጨመረ ወይስ ቀነሰ የሚለው ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ እና ይበልጥ ጭካኔ የተሞላበት እየሆነ መምጣቱ ለምንድነው የሚለው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ ላይ ነው።
ለምን ጥቃቱ እየጨመረ ሄደ ? ለምን ሕጉ (የሚሰጠው የቅጣት ውሳኔ) አስተማሪ አልሆነም የሚለው ነው መታየት ያለበት። እናም ሁሉም ሠው ለምንድ ነው ይሄ የወንጀል ድርጊት የበዛው ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል። መጠየቅ ብቻም ሳይሆን ችግሩን የመከላከል አካል መሆንም አለበት።
እያንዳንዱ ርምጃ ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ መሆን አለበት። የምንሰማው አሰቃቂ ጾታዊ ጥቃት የአንድ ሰሞን ወሬ፤ የአንድ ሰሞን ቁጭት ብቻ ከመሆን የዘለለ መሆን አለበት። አጥፊው አስተማሪ የሆነ ለሌላውም መቀጣጫ በሆነ መልኩ ርምጃ የሚወሰድበት መሆን አለበት። ግን እየሆነ ነወይ ? የሚለው አሁንም ጥያቄ ያስነሳል። ምላሽ ያሻዋል።
መገናኛ ብዙሀንም ሆኑ ሌሎች ማኅበራዊ ድረ ገጾች የወንጀል ድርጊቱን ባራገቡት ልክ የቅጣት ውሳኔዎችን ለሕዝብ በማቅረብ ረገድ ተከታትለው ሰርተዋል ወይ ድርጊቱን የሚያወግዙ ተከታታይነት ያለው ትምህርት ሰጥተዋል ወይ የሚለውን ብናይ ሁሉም የድርሻውን መውሰድና ራሱን ማየት ያስፈልገዋል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ በእጮኛዋ በአሰቃቂ ሁኔታ ራሷን ማዳን በማትችልበት አኳኋን ተገደለች። ሙሽራዋ በጫጉላ ቤት በባለቤታ ሕይወቷን አጣች። ሌላም ሌላም የሚሰሙ የጾታዊ ጥቃትና የግድያ ዜናዎች ምናልባትም የሕጉ ልል መሆን ይሆን ወንጀሎቹ እንዲባባሱ ያደረገው ብለን ጣታችንን ወደ ሕጉ እንድንቀስርም የሚያደርገን አጋጣሚ አለ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ጉርባ በሚባል ቀበሌ የገዛ እጮኛውን ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት አንገቷን በመቁረጥ ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደረገው ወጣት በ20 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ጋፋሮ ቶማስ አስታውቀዋል።
በፍቅረኛዋ የደስታው የምርቃቱ እለት ልታስመርቀው ወዳጄ ፍቅረኛዬን ላስደስተው የደስታው ተካፋይ ልሁን ብላ መንገድ ቆርጣ የሄደችው እሷም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችውን ወጣት የገደለን ወንጀለኛ በዚህ መልኩ ቅጣት ማግኘቱ ተገቢነት ቢኖረውም የቅጣቱ መጠን አስተማሪ ነወይ በቂ ነወይ ብሎ ጥያቄ ለሚያነሳ ግን አሁን ሕጉ ይፈተሽ የሚያሰኝ ይሆናል።
ፆታዊ ጥቃት የሚፈጸመው በተለያየ መልኩ ነው። ጾታዊ ትንኮሳ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሌሎችም ጥቃቶች በሴቶች ላይ የሰፋ ይሁን እንጂ በወንዶች ላይ ጥቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰማ ይገኛል። የግብረ ሰዶም ጥቃት ሰለባዎች በአብዛኛው ሕጻናት ሲሆኑ፤ ድርጊቱ በብዛት የሚፈፀመው በትምህርት ቤቶች አካባቢ ነው፡፡
በመሆኑም ይህን ጉዳይ ከአቃቤ ሕግ፤ ፖሊስና ፍርድ ቤት ባሻገር ማየት ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ማኅበረሰቡም ሊመለከተው ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሕብረተሰቡ በራሱ ሰፊ ጥንቃቄና ክትትል ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ልጆችን መምከር፣ ከአልባሌ ቦታዎች እዲርቁ ማድረግ የመጀመሪያው ርምጃ መሆን አለበት።
ቤተሰብ የልጆቹን አዋዋል፤ አካላዊ ሁኔታና የሚመለከታቸውን ፊልሞች በአግባቡ ማየት፤ መምህራንና የሀይማኖት ተቋማት ግብረገብነትን በማስተማር ረገድ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
አንዳንድ የቅጣት ውሳኔ ደግሞ በሕጻናት እና ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት የፈጸመ ግለሰብ “በአምስት ዓመት፣ በስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደበት” የሚለውን ዜናም እንዲሁ አንብበነዋል።
ምንም ይሁን ምን የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ወይም ነገ ደርሳ ቤተሰቡን ትቀይራለች፤ ትልቅ ደረጃ ትደርሳለች፤ የቤተሰቡ አለኝታ ትሆናለች ተብላ ብዙ የተደከመባት፤ ወላጆች ትልቅ ተስፋ የጣሉባት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ የሚሰጠው ፍርድ በቂ ነው ? ሌላው በተመሳሳይ ወይም በባሰ ሁኔታ ወንጀል እንዳይፈጽም ያስተምራል ? ከተባለ ግን ምን አላት ሀያ ዓመት ነገ ታስሮ ይወጣል፤ ይለቀቃል ያሰኛል።
ምክንያቱም እስር የተፈረደበት ወንጀለኛ ጊዜው በዛም አነሰም ቅጣቱን ጨርሶ ይወጣል። ሌላው ተመልካችም ይሄንኑ ያያል። ማን ምን ሆነ ታስሮ መውጣት ነው ወደሚለው አስተሳሰብ እንዳይገባ ያሳስባል። ወንጀለኛ ከፊት ለፊቱ ምንም ጨለማ ነገር አይታየውም ነገ ብርሀን አለ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይሄ ማለት ምንም አይነት አሰቃቂ ወንጀል የሠራ ሠው ታስሮ ይወጣል፤ ሌላውም ከዚህ ብዙም የሚማረው ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም።
በእርግጥ የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ምንም አይነት ጥፋት ያጠፋን የወንጀለኛ ቅጣት ውሳኔ የመጨረሻው ደረጃ የሞት ፍርድ ቢሆንም ይሄ ወደ ሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቀርቦ ወደ እድሜ ልክ የሚቀየርበት ሁኔታ አለ። ቢያንስ አንድ ወንጀለኛ እድሜ ልኩን ቢታሰር ማን ምን ሆነ ለሚሉ አጥፊዎች መልስ የሚሰጥ ሊሆን ይችላል።
በተደጋጋሚ ከተለያዩ አካላት የሚሰነዘረው ሀሳብ የወንጀል ሕጉ መሻሻል አለበት። የሚሰጡ ቅጣቶች በቂ አይደሉም። አስተማሪም አይደለም የሚሉ ናቸው። የወንጀል ሕጉ መሻሻል እንደተጠበቀ ሆኖ ሕብረተሰቡ ከፍትህ አካላት ጋር ተባብሮ መሥራት ይገባዋል።
በተለይም፣ የጾታዊ ጥቃት እና የሕፃናት ግድያ የሚፈፀሙት በቅርብ የሚታወቁ ሠዎች በኩል ሲሆን ይህ የማኅበረሰቡን መተማመን እያሳጣው ነው። ይህ የሚያሳየው የማኅበረሰቡ የሥነ-ምግባር እሴቶች እየተዳከሙ መምጣታቸው በመሆኑ ባሕልና ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥበቃዎች እንዲሁም እሴቶችን የመመለስ ጠንካራ ሥራ መሠራት አለበት። በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የሕግ እና የቅጣት ሥርዓት በቂና አስተማሪ አይደለም የሚለውን ሀሳብ
መነሻ በማድረግ የሚከተሉትን መፍትሔዎች መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል።
- መንግሥት ሕጉን የማጠናከር፡ የወንጀል ሕግ መሻሻል እና በቂ የሆነ ቅጣት ማስተዋወቅ፤
- የማኅበረሰብ ግንዛቤ ላይ ሕብረተሰቡ በራሱ ሰፊ ግንዛቤ እና ክትትል ማድረግ አለበት።
- የትምህርት ማኅበረሰብ ሚና ደግሞ የሥነ-ምግባር እሴቶችን በማስተማር ረገድ የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት።
- የሃይማኖት ተቋማትም የሥነ-ምግባር እሴቶችን በማስተማር ረገድ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው። በሚያስተምሩበት አውድ ምሕረቶች ላይ ከሀይማኖታዊ ምግባር ውጪ የሆኑትን ጾታዊ ጥቃት ማውገዝ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ የማኅበረሰቡ ጥሩ እሴቶችን ወደፊት በማምጣትና ጸያፎቹን በማውገዝ ማስተማር ይገባል። በጋራ የተጠናከረ ሥራ መሥራት ሲቻል ብቻ ነው የጾታዊ ጥቃትን ማቆም ባይቻል መቀነስ የሚቻለው። ለዚህም ሁሉም ከሕጉ ጎን መቆም አለበት።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም