አንዳንዶች በግል ጥረትና ትግላቸው እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ለትውልድና ለሀገር ያሻግራሉ። በታሪክ የማይዘነጋ አሻራቸውን ያስቀምጣሉ። ይህንን የሚያደርጉት አርቀው ያለሙትን ራዕያቸውን እያሳኩ፣ አሰቡበት በመድረስ ጭምር ነው። ይህም ተግባራቸው የታሪክ ባለድርሻነታቸው ካለፈም በኋላ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ቋሚ ሐውልት ሆኖ ያስታውሳቸዋል። የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን አቶ ጀማል አህመድም የታሪክ ሐውልታቸውን ተክለው ያለፉ ሰው ናቸው።
አቶ ጀማል ከልጅነታቸው ጀምሮ ታታሪ ሠራተኛ በመሆን አንቱታን ያተረፉ፤ የበርካታ ሥራዎች ባለቤትም ናቸው። በተለይም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ሆኖ ዘመናትን በተሻገረው የቡና ምርት ላይ በማምረትና ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ዛሬም ይህንን ሥራቸውን ሳይለቁ የሆራይዘን ፕላንቴሽን ማኔጅንግ ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ቡናን የማምረት እንዲሁም ወደ ውጭ የመላክ ሥራ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ በማምጣት ከትናንሽ አርሶአደሮች እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በመጣመር የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል አቶ ጀማል። በአገኙት መድረክም ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ባደላት የቡና ምርት ማደግ የምትችልበትን መንገድ በጥናት አስደግፈው በማስረዳትም ይታወቃሉ። «በዘርፉ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት ከቻልን ገና ብዙ ማድረግ እንችላለን» የሚል ትልቅ እምነትም አላቸው። ይሄንንም ሀሳብ ሳይሰለቹ በማራመድም ይታትራሉ።
የልጅነት ጊዜ
ጠንካራ ሠራተኛ የሆኑት አቶ አህመድ አብዲ ሽኩር ከጉራጌ ዞን ገደባኖ ከሚባል አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ተክለሃይማኖት ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ይመጣሉ፤ በዛም አነስተኛ ንግድ በመነገድ ህይወታቸውን እየመሩ ባሉበት ወቅት ከወይዘሮ ፈለቀች መሀመድ ጋር በመተዋወቅ ወደ ትዳር ገብተው ኑሯቸውን «ሀ» ብለው ይጀምራሉ። በዚህ ትዳር ውስጥም 12 ልጆችን በመውለድ ቤታቸውን የፍቅርና የበረከት ያደርጉታል። ከእኚህ ጠንካራ አባት አብራክም የቤተሰቡ ዘጠነኛ ልጅ የሆኑት አቶ ጀማል አህመድ በ1963ዓ.ም መስከረም 13 ቀን ይህችን ምድር ይቀላቀላሉ።
የአቶ ጀማል አባት ልጆቻቸውን ጥሩ በሚባል ሁኔታ ለማሳደግና ለቁምነገር ለማብቃት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በዚህም መጽሀፍትን እያዞሩ በመነገድ ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ ነበር። የመጽሀፍ ንግዱንም ጠንክረው በመሥራታቸውና ትንሽም ብትሆን ጥሪት በመያዛቸው አነስተኛ ሱቅ (ኩዮስክ) ለመክፈት ቻሉ፤ ከዚያም የተለያዩ ሸቀጦችን በመነገድ ረዘም ያለ ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አለ የሚባል የሲጋራ አከፋፋይ ለመሆን በቁ።
«አባቴ ከሥራውና ከጥረቱ ጎን ለጎን ለቤተሰቡ በተለይም ለልጆቹ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ስለነበር ሀብት ሳይኖረው እንኳን እንደ ሀብታም ልጅ አሞላቀው ነው ያሳደገን» ይላሉ አቶ ጀማል ስለአባታቸው ሲያስታውሱ።
ትምህርት
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ቤተልሄም ትምህርት ቤት ያመሩት አቶ ጀማል፤ ከእኩዮቻቸው ጋር ጥሩ የሚባል የትምህርት ጊዜን እንዳሳለፉ ያስታውሳሉ። ይሁንና በጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ለመከታተል ሲገቡ ግን ያልታሰበ አደጋ ገጠማቸው። ታታሪና የልጆቻቸው መጻኢ ማረፊያ የሚያሳስባቸው አባታቸው በሞት ተለዩዋቸው። ስለዚህም ሁሉ ነገር በእርሳቸው ጫንቃ ላይ እንደወደቀ በማሰባቸው ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጠዋት እየተማሩ ከሰዓት አባታቸው ባቆዩላቸው ሱቅ ውስጥ በመሥራት ቤተሰቡን ይደግፉ ጀመር።
« በወቅቱ አባታችን ሲጋራን ያከፋፍልበት የነበረው ትልቅ የንግድ ማዕከል በእናት የማንገናኘው ወንድማችን እንዲያስተዳድረውና 12ቱን የአባቱን ልጆች እንደ ሞግዚት ሆኖ እንዲያሳድግ ተደረገ። እኔም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በማጠናቀቄ ሱቅ ከመነገድ ወጥቼ ሥራን መልመድ አለብኝ በሚል ሀሳብ አውቶቡስ ላይ በረዳትነት መሥራት ጀመርኩ። ጥቂት ጊዜም በዚህ ሁኔታ አሳለፍሁ። እንደፈለኩትም ሥራን መልመድ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት መሸከምንም ችዬ ነበር» ይላሉ ያለፈውን ትዝታቸውን እያስታወሱ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ራሳቸውን ትልቅ የማድረግ ህልማቸውን አልተውም ነበርና የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ አሜሪካ አገር አቀኑ። የቢዝነስ አስተዳደር ትምህርት ምርጫቸው አደረጉ። ሆኖም ግን በትምህርቱ ላይ የመቆየት ዕድላቸው ከአንድ ዓመት በላይ አልዘለለም። ቤተሰባዊው ጉዳይ ወደ አገር ቤት መለሳቸው።
«እናቴ እኛን በሞግዚትነት ያሳድግ ከነበረው የአባቴ ልጅ ጋር ተጣላች። ስለዚህም በቶሎ መምጣት አለብህ በማለቷ ትምህርቴን ባለበት በማቆም ወደ አገር ቤት ተመለስኩ» በማለት የመመለሳቸውን ምክንያት ይገልጻሉ።
በወቅቱ ሁሉም እህትና ወንድሞቻቸው በዛው አሜሪካን አገር የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የነበረ ቢሆንም ጥሪው ግን ለቤተሰቡ ቅርብና ከልጅነት ጀምሮ ኃላፊነት ለመሸከም ቆርጠው ለተነሱት አቶ ጀማል ሆነ። እናም በ1984 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ወደ አገር ቤት ተመልሰው የአባታቸውን ሱቅ ተረክበው እናታቸውን ጨምሮ ሌሎች ቤተሰቡን በማስተዳደር ሥራ ላይ ተጠመዱ። ከልጅነታቸው ጀምሮ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰው ነበሩና «ትምህርትህን አቋርጠህ ና» ሲባሉ አላቅማሙም።
« ከልጅነቴ ጀምሮ እናቴም ሆነች ሌሎች የቤተሰብ አባላት ‛ አንተ ኃላፊነት የሚሰማህ ልጅ ነህ ‛ በማለት የተለያዩ ሥራዎችን እንዳከናውንና ቤተሰቡንም እንድመራ እምነት ይጣልብኝ ነበር። ለዚህም ነው ስምንት ታላቆች እያሉኝ እኔ የምመረጠው» ይላሉ ትምህርታቸውን አቋርጠው እንዴት እንደመጡ ሲያወሱ። እናም እምነት የተጣለባቸው አቶ ጀማል ቤተሰቡን አላሳፈሩም ነበር። የአባታቸውን ቦታ በመተካትና ቤተሰቡን በተገቢው ሁኔታ በማስተዳደር የንግድ ሥራውንም ወደፊት በማራመድ ብቃታቸውን አሳይተዋል። ታናናሾቻቸውንም ሆነ ታላላቆቻቸውንም አስተምረው ለወግ ማዕረግ በማድረስ የተጣለባቸውን እምነትና ብቃት አስመስክረዋል።
ይሠሩት የነበረው የንግድ ሥራ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ችግር ውስጥ ሲገባ ደግሞ ፊታቸውን ወደ ሌሎች አማራጮች አዞሩ። የዘይት ንግድን የቤተሰባቸው መተዳደሪያ አደረጉ። ይህ ሥራቸው ደግሞ ሌላ ሰፊ የሥራ ዕድልን አብሮ አመጣላቸው። ሥራቸው ከሼህ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ጋር አስተዋወቃቸው። ለዛሬ ማንነታቸውም ትልቅ መሰረት የነበረው ይህ እንደሆነ አልሸሸጉም። ምክንያቱም ሁለቱም ሰዎች የሚሠሩትን ሥራ ለማስፋፋት ትውውቃቸው የበረታ ክንድ ሆኗቸዋልና ነው። «ሆራይዘን ፕላንቴሽን» የተባለውን ድርጅት ለመመስረትም የበቁት በዚህ ምክንያት ነበር።
ሥራቸው አንዱ አንዱን እየመራ ዘይት፣ የጎማ ዛፍ፣ ከዚያም የጎማ ፋብሪካ እያሉ ሰፋፊ የመንግሥት የቡና እርሻዎችን በመግዛት መሥራት ቀጠሉ። 10 እና 11 ቤተሰብን በማስተዳደር የተጀመረው መሪነትም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ወደ ማስተዳደር ተጓዘ። አሁን በ 15 ድርጅቶች ውስጥ 57ሺ ሠራተኞችን ከእነሱ ጀርባ ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቤተሰቦችን ለማገዝ ችለዋል።
ለቡና ሥራ ልዩ ተሰጥኦ
ለቡና ግብርና ትልቅ ቦታ የሚሰጡት አቶ ጀማል፤ አገሪቱ የቡና መገኛ፣ በርካታ አርሶአደሮች ከነቤተሰባቸው የሚኖርባት ብትሆንም አሁን ላይ ያለበት ደረጃ በጣም እንደሚያሳዝናቸው ይናገራሉ። በዚህም የቡናውን ችግኝ አፍልቶ፣ ዘር አቅርቦ፣ ተክሉን ተንከባክቦና አሳድጎ ከዚያም አቀነባብሮ መሸጥ ድረስ ስለሚሠሩም ስለ ቡና ያገባኛል ይላሉ። ለቡናው የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ደግሞ በተለይም የሚያስተዳድሯቸው 10ሺህ ሠራተኞች ከነቤተሰባቸው ያሳስቧቸዋል። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የቡና ሥራቸውን ከሌሎች ሥራዎቻቸው ሁሉ አብልጠው ወደፊት ማራመድ ይፈልጋሉ።
«ኢትዮጵያ ከቡና የተረፋት ዘፈኑ ብቻ ነው» ሲሉ በቁጭትም ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የሚያነሱት ኢትዮጵያ የዓለም ምርጫ የሆነው አረቢካ ቡና መገኛ መሆኗ ነው። ብራዚል ከኢትዮጵያ በወሰደቻቸው የቡና ዝርያዎች አሁን ላይ 23 ዓይነት ቡና ማምረት ችላለች፤ ይህን ሲሉ በቁጭት ነው።
ኢትዮጵያ በየጫካው ብቻ ከ10ሺ ያላነሰ የቡና ዝርያዎች አሏት፤ ይህንን ስጦታ ግን ወደ መሬት አውርዶ መጠቀም እንዳልተቻለ የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ ይህ የሆነው በዘልማድ ከሠራነውና ከምንሠራው ውጪ ለዘርፍ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ የምርምር ሥራ አለመኖርና አርሶአደሩ የተሻሻሉ የቡና ዘሮችን ያለማግኘቱ በዋናነት ይጠቀሳል። ቡና ትኩረት የሚፈልግ ዘርፍ ነው። ከዚህ አንጻር የባለድርሻ አካላትን ትኩረት ማግኘት መቻል አለበት። አገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድጋትም ይኸው ነው። ለምሳሌ እኛ በቡና ዝርያ በጣም ሀብታም ነን፤ ምንም የሌላቸው እነ ብራዚል ከእኛ እየወሰዱና የራሳቸውን ምርምር እያከሉበት ዛሬ ላይ ጥሩ ቡና እያመረቱ በዓለም ገበያ ላይ ተመራጭ ብሎም ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ሆነዋል። ስለዚህ ቢያንስ ከእነርሱ ለመወዳደር የምርምር አማራጮችን ማስፋትና ጠንክረን መሥራት የግድ ይለናል ባይ ናቸው።
ትኩረት ለምርምር
እንግዳችን እንደሚሉት፤ በቡና ላይ ምርምር ለማድረግ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች አሉ፤ አንዱ የዘር ሀብት ሲሆን፣ ሌላው ተመራማሪ ባለሙያዎችን ማግኘት ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ተዝቆ የማያልቅ የቡና ዘር ሀብት ባለቤት ናት፤ የሚሠራ ከተገኘ ይህ ችግር አይሆንም፤ በተመራማሪ በኩልም ቢሆን ከየትኛውም ዘርፍ በበለጠ ሁኔታ በቡናው ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረጉና እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ያላቸው ባለሙያዎች ይገኙባታል። ግን መንግሥት ብቻውን ይሠራበት በነበረበት የደርግ ጊዜ እንኳን ቡና ብቸኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ስለነበረ ከፍተኛ ትኩረት ነበረው። በዚህም የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን በማቋቋምና በቡና ምርታማነት ላይ በርካታ ሀብትን በመመደብ የተለያዩ የምርመር ሥራዎች ተሠርተዋል።
በተለይም በ1972 ዓ.ም ገደማ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የቡና እሸት የሚያበላ በሽታ ተከስቶ እንኳን ኢትዮጵያ በበሽታው ላይ ምርምር በማድረግ እርሱን ሊቋቋም የሚችል ዘር በ1974 ዓ.ም ያገኘች የመጀመሪያዋ አገር ነበረች። ሌሎች አገሮች የቡና እሸታቸውን ከበሽታ ለመከላከል የተለያዩ ጸረ -ተባይ መድኃኒቶችን ሲረጩ አገሪቱ ግን ምንም ዓይነት መድኃኒት አትጠቀምም። እስከ አሁንም የሚተከለው ያን ጊዜ የወጡት ዝርያዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
«ታዲያ ዛሬ ይህ ሁኔታ ለምን ቆመ?» ሲሉ ይጠይቃሉ። ቀጥለውም ዛሬ ላይ ዓለም በቡና ምርታማነት፣ በሽታን በመቋቋም እንዲሁም የጣዕም ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ሰፊ ምርምሮችን በማድረግ ጥሩ ቡናና ምርታማ ዘር ያስፈልጋል፤ በዚህም ቬትናም፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢንዱራንስ ብዙ እየሠሩ ነው። እኛ ግን በ1974ዓ.ም ያወጣነውን የምርምር ውጤት ታቅፈን ቁጭ በማለታችን በምርታማነታችን በምናገኘው ጥቅም ወደኋላ እየተጎተትን ነው። ስለዚህም ተመራማሪው አደራ እየበላ የሚቀመጥ ሳይሆን አደራ አስረካቢ መሆን አለበት። ምርምሮችን በማድረግ ለትውልድ መሥራት ላይ ሊያተኩር ይገባል ይላሉ።
ተወዳዳሪ ለመሆን ምን እንስራ
«አሁን በተለይም ከሁለት ዓመት ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ደርግ ከሥልጣን ከወረደ በኋላ እንዲፈርስ የሆነው ቡናና ሻይ ባለሥልጣን እንደገና እንዲቋቋም ሆኗል፤ ለውይይትም እየጋበዘን በመሆኑ ጥሩ ጅምር ይታያል። ይህም ቢሆን ግን የተቋቋመው ገበያውን ታሳቢ በማድረግ ነው። እኛ ደግሞ ምርምሩ ላይ ትኩረት ይደረግ እያልን ድምጻችንን በማሰማት ላይ ነን።» የሚሉት አቶ ጀማል፤ አሁን ላይ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ መመሪያ ወጥቷል እየተባለ በመሆኑ መመሪያው ተግባራዊ ሲደረግ ተስፋ እንደሚኖር ይናገራሉ።
እንግዳችን ተወዳዳሪነትን ሲያነሱ፤ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም በፖሊሲ አውጪዎች፣ በአምራቹ እንዲሁም ገበያ ላይ ያሉት ሁሉ ተሳትፎን በማድረግ ቡናን ከወደቀበት ማንሳት አለበት ይላሉ። በአገሪቱ ብዙ የተለመደው በተለይም ቡናን ለመተቸት ሲያስቡ ዝም ብለው የቆዩ መረጃዎችን ያዩና «ቬትናምና ኢትዮጵያ» እያሉ ያወዳድራሉ። ዕቅድም ሲታቀድ ቬትናምን እንበልጣለን ነው። ይህ ግን የማይሆን ነገር ላይ እንደመዳከር ይቆጠራል ባይ ናቸው።
ምክንያታቸውም ቬትናሞች ርካሹን (ሮቡስታን) ነው ሲያመርቱ የኖሩት፤ አሁን ነው አረቢካን ማምረት የጀመሩት፤ በዓለም ገበያ ላይ እንኳን አረቢካ አሜሪካ ነው ሮቡስታ ደግሞ ለንደን፤ እኛ ደግሞ ከአረቢካም በጣም ጥራት ያለውንና ተፈጥሯዊ ይዘትን የተላበሰ ቡና ነው የምናቀርበው። በመሆኑም እኛ መወዳደር ያለብን ከቬትናም ሳይሆን በእኛ እኩል ደረጃ ቡናን ማምረት ከሚችሉ አገራት ጋር ነው። «ምናልባትም የእኛ አቻ ኮሎምቢያ ብቻ ናትና ከአቻችን ጋር ለመወዳደር መሥራት አለብን» የሚል እምነት አላቸው።
ከኮሎምቢያ ብንማርስ
ከኮሎምቢያ የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ቡና በርካታ አርሶ አደሮችን የያዘላቸው ቢሆንም በምርት መጠናቸው ግን የኛን አያክሉም፤ ብዙ የቡና ማሳቸውም አሮጌ ነበር፤ ይህንን ለመቀየር የተጠቀሙት መንገድ በጣም አስገራሚ ብሎም አስተማሪ ነው፤ መንግሥት በጀት መድቦ ለአርሶ አደሩ ብድር ሰጥቶ ያረጁ የቡና ማሳዎችን በማንሳትና በአዲስ ምርት መተካት በመቻሉ ምርታቸው በአሁኑ ወቅት በአምስት እጥፍ ማደግ ችሏል።
ኢትዮጵያ በደቡብና በኦሮሚያ ሰፊ የቡና ምርት አላት፤ በኦሮሚያ ብቻ 70 በመቶ የሚሆነው ቡና የምርታማነት ጊዜውን የጨረሰ ነው። አርሶ አደሩ « በገጃ » ይለዋል፤ ይህ እንግዲህ ተጎንድሎ በሌላ ዝርያ መተካት ያለበት ነው፤ በመሆኑም የኮሎምቢያን ተሞክሮ መከተል የግድ ይለናል።
እዚህ ላይ የራሳቸውን ተሞክሮም ሲናገሩ በ 1974 ዓ.ም የተቋቋመው «በበቃ» የተባለው የመንግሥት የቡና እርሻ በ2003 ዓ. ም መጨረሻ ላይ በመግዛት በቦታው ላይ የነበረውን 70 ከመቶ ያህል ቡና በመንቀል በተሻለ ዝርያ የመተካት ሥራ ተከናወነ። ቀሪውንም በመጎንደል ወደ ሥራ ገባ። በበቃ በ 30 ዓመት ታሪኩ አምርቶ የሚያውቀውን 40 ሺ ኩንታል ቡና ተለቀመ። ዘንድሮም 128 ሺ ኩንታል ቡና ተለቅሟል። ይህ ምርት በአራት እጥፍ ሊያድግ የቻለው በዋናነት ዛፎቹ ስለታደሱ እንደሆነ ይናገራሉ።
በአገር ደረጃ ያለውን ገጽታ የሚያመላክት ነው። በዚህ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ መሥራት ከተቻለ ምርቱ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ 5 እጥፍ ያድጋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ 5ነጥብ 2 ሚሊየን ቡና አምራች ገበሬን ከነቤተሰቡ ህይወቱን መለወጥ ተቻለ ማለት ነው። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድና ሁለት ላይ መሰረታዊ የቡና ችግር ታቅዶ አልተሠራም። በመሆኑም በዚሁ የምንቀጥል ከሆነ ዓለም ጥሎን ስለሚሄድ በገበያው ላይ ያለን ድርሻም ዋጋ ያጣል።
የቡና አምራች አርሶ አደሩ ተጠቃሚነት
ዓለም ላይ ባለው አሰራር አምራች ገበሬዎች በውጭ ንግዱ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ናቸው። በእኛ አገር ገበሬው አምርቶ ያገኘውና ወደ ውጪ ተልኮ የሚገኘው ገንዘብ ልዩነት «ትራንዝ አክሽን ኮስት» ይባላል። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ 40 በመቶ በመሆኑ በጣም ከባድ ነው። አምራቹ የሚያገኘው 60 በመቶውን ብቻ ነው። የብራዚል ገበሬ 90 በመቶ፣ ኮሎምቢያ 80 በመቶ ያገኛሉ። ታዲያ እንደ ምርት ገበያ ያሉ ተቋማት ይህንን መቀነስ ካልቻሉ ምን ያደርጋሉ፤ እኛስ ቢያንስ ኮሎምቢያ ላይ ለምን አንደርስም? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ገበሬውን ተጠቃሚ ባላደረግነው ልክ ቡና አደጋ ውስጥ እየወደቀ ይሄዳል የሚሉት እንግዳችን፤ ገበሬው ጫት መትከል ይችላል፤ ጫት ቢተከል ኢሴክስ የለበትም፣ ባንክ አይጠይቀውም፣ የውጪ ንግዱም አያስጨንቀውም ፤ ቢፈልግ መንደሩ ላይ አልያም አዲስ አበባ አመጥቶ ይሸጣል፤ ምርቱ ግን ጎጂና ለስራ የደረሰን ወጣት የሚያሽመደምድ ነው። በአሁኑ ወቅት ሐረር፣ ሲዳማም ወደዚህ እየሄዱ ነው። በጠቅላላው ግን ገበሬውን ተጠቃሚ በማድረጉ በኩል አንድ ነገር ማድረግ ካልተቻለ ቡና ኢትዮጵያ ላይ ላይቆይ ይችላል የሚል እምነታቸውን ያስቀምጣሉ።
ሆራይዘን በተመክሮ
«እኛ የሞከርነው ነገር አለ ሆኖም መንግሥትና ህዝብ አብሮ ካልሄደ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ይቆጠራል» የሚሉት አቶ ጀማል፤ ከመንግሥት ተቀብሎ በራስ በለሙት ሸካ፣ ከፋ፣ አማራ ክልል ላይ ያሉት በአማካይ አምና 15 ኩንታል በሄክታር ሰጥተዋል፤ በአገር ደረጃ ያለው 6ነጥብ 2 በሄክታር ነው። ኮሎምቢያ 12 ኩንታል በሄክታር ታገኛለች። እንግዲህ ሆራይዘን ከኮሎምቢያም በላይ ቢኖረውም ይህንን ዳታ ወስዶ እናንተ ምን ሰርታችሁ ነው እዚህ የደረሳችሁት ብሎ የጠየቀ የመንግሥት አካል አለመኖሩን ይናገራሉ።
ይህ ውጤታማ ሥራ ወደ አርሶ አደሩ መድረስ መቻል አለበት የሚል እምነትም አላቸው። በሆራይዘን አማራ ክልል ብቻ ሞዴል አርሶ አደሮቻቸውን አሰልጥኑልን ብሎ በጠየቀው መሰረት ለ400 አርሶ አደሮች ሥልጠና ተሰጥቷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደ ምርት ከተቀየረ አማራ ክልል በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡና አምራች ይሆናል። ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ይህንን ተሞክሮ ማስፋት ከተቻለ ከአገር ልጅ ብቻ ሊያገኙት የሚችለው በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሉ። እናም ተሞክሮው የአገሪቱን ቡና ለማሳደግ ይዋል ይላሉ።
የአደራ መልዕክት
ዘርፉ ሁሉንም አሳታፊ መሆን አለበት። በችግሮቹም ሆነ በመልካም ጎኖቹ እንዲሁም በመፍትሔዎች ላይ ግልጽ የሆነ ውይይትን ማድረግ ያስፈልጋል። ብዙ ጊዜ በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሉ ባለስልጣናት ብቻ ናቸው የሚወያዩት ሆኖም ቡና ላይ የተሻለ መደራጀት ስላለ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ኦሮሚያም ፣ ሲዳማ፣ ይርጋጨፌም ካሉ የቡና ዘርፍ ላይ ከሚሰሩ ሰዎች እንዲሁም በቡናው ላይ ከተመራመሩ ምሁራን፣ ገበያውን ከሚያውቁ ነጋዴዎች ጋር በመቀናጀት አሳታፊ የሆነ ማንም ማንንም የማይተችበት መመሪያ ማዘጋጀት ይችላል።
ሌላው ደግሞ የቡና ፈንድ (ኮፊ ፈንድ) መቋቋም አለበት። አገር ውስጥም ወደ ውጭም ከሚላከው ቡና ለፈንዱ ቢለገስና በጀቱ ደግሞ ለምርምር ቢውል ሌላ ሀብት ሳያስፈልግ ስራዎችን መስራት አዳዲስ ዝርያዎችን እያወጡ ለአርሶ አደሩ ማዳረስ ይቻላል።
እንደ አበባና ሌሎችንም አዳዲስ ነገሮች መሞከር መልካም ነው። ነገር ግን ቡና ኢትዮጵያን በውጪ ንግድ ለረጅም ዓመታት ይዟት የመጣ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት ብዙ ነገር ተሰርቶ ከ 25 በመቶ በላይ ማግኘት አልተቻለም። ከ 5 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደር የሚያመርተው ምርት በመሆኑ በሁሉም ዘንድ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የቤተሰብ ሁኔታ
ሥራ ሥራዬን ስል ለቤተሰቤ ብዙ ጊዜ የለኝም የሚሉት አቶ ጀማል ሆኖም እጅግ ሥራቸውን ከምትረዳው ወይዘሮ ሂክማ አሊ ጋር ጋብቻን ፈጽመው የአንዲት ሴት ልጅ አባት ለመሆን በቅተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
እፀገነት አክሊሉ