ምርትና ምርታማነቱ እየጨመረ የመጣው የሆርቲካልቸር ዘርፍ

ሀገሪቱ የሆርቲካልቸር ልማትን በስፋት ማካሄድ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብትና ምቹ የአየር ንብረት እንዳላት ቢታወቅም፣ ይህን እምቅ ሀብት በሚገባ በማልማት ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነች ይታወቃል።

ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ መሥራት እንደሚገባም የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲያስገነዝቡ ይደመጣሉ። የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥ ባለፈ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ያለው አበርክቶ የላቀ መሆኑን በመገንዘብ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ።

በዚህ ረገድም መንግሥት በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት ዘርፉ ለአጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ያለውን ድርሻ በመገንዘብ ፖሊሲ በማሻሻልና በሕግ ማሕቀፍ በመደገፍ በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ ይገኛል።

በዋናነትም የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ ገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ፣ ለሥራ እድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የላቀ አስተዋፅኦ ማበርከት ያስችላሉ ተብለው የተለዩ ኢንሺቲቮች ተቀርፀው መተግበር ከጀመሩ ወዲህ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል።

ለዚህም እንደ አብነት መጥቀስ የሚቻለው የሆርቲካልቸር ሰብሎችን ልክ እንደ ስንዴና ሩዝ ሁሉ በክላስተር ማልማት መጀመሩ፣ ከዚህ ቀደም የዘርፉ እድገት ማነቆ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ ከመቻሉም ባሻገር በቴክሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለው ምርት በስፋት ለማቅረብ እያስቻለ ስለመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ እንደ ሀገር የሆርቲካልቸሩን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

በአረንጓዴ ዐሻራ ከታቀደው አንፃር አብዛኛውን የፍራፍሬ ልማት ከማሳ ሥራዎች ጋር በማያያዝ በርካታ ችግኞች ተዘጋጅተው በክላስተርና ከክላስተር ውጭ እንዲለሙ ተደርገዋል። ይህም የፍራፍሬ ልማት በማሳ መጠኑም ሆነ በምርታማነት ረገድ እየሰፋ የመጣበት ሁኔታ እንዲፈጠር አስችሏል። የአትክልት፣ የእፀ-ጣዕምና እንደ እንሰት ያሉ የሥራ ሥር ሰብሎች ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል።

በዘርፉ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከልም በተለይም በመኸር ወቅት አንድ ሚሊዮን 295 ሺ 130 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እንደነበር አቶ አብደላ አስታውሰው፤ ‹‹ይህንን እቅድ ለማሳካት በርካታ የንቅናቄ ሥራዎች በመሠራታቸውና ድጋፍ በመደረጉ ከእቅዱ በላይ አንድ ሚሊዮን 651 ሺ 58 ሄክታር ማልማት ተችሏል›› ይላሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከዚህም 191 ሚሊዮን 511 ሺ 240 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር፤ ይሁንና የማሳ መጠን በመጨመሩ፣ ምርትና ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶች በመቅረባቸውና በተለይ ደግሞ የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም በመቻሉ ከፍተኛ ምርት ማግኘት የታቸለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ሪፖርቱ እስካሁን ሙሉ ለሙሉ በክልሎች ያልተጠናቀቀበት ሁኔታ መኖሩን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ገልጸው፤ እስከ አሁን 212 ሚሊዮን 224 ሺ 288 ነጥብ 69 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የሆርቲካልቸር ልማትን በክላስተር አምርቶ የተሻለ ምርት ለማግኘት ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን አቶ አብደላ ይናገራሉ። ‹‹በዚህም እስከአሁን ድረስ በመኸር ወቅት 21 ሺ 64 ሄክታር ማሳ በማልማት 3 ሚሊዮን 890 ሺ 948 ኩንታል ተሰብስቧል›› ብለዋል።

ይህ አበረታች ውጤት የተገኘው ለክላስተር ልማት የተለየ ትኩረት በመስጠቱ መሆኑንም ተናግረዋል። በተለይ በግብዓት አቅርቦት ድጋፍ መደረጉና ለአርሶ አደሮቹ ለምርት የገበያ ትስስር መፈጠሩ የላቀ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ያስረዳሉ።

በአካባቢው የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፣ ትልቁና ዋነኛው ለሆርቲካልቸር ልማት ወሳኝ ሚና ያለው የቀዝቃዛ ሰንሰለት ሥርዓት እንዲዘረጋ የተደረገበትን ሁኔታ በአብነት ይጠቅሳሉ። የቀዝቃዛ መጋዘን መሠረተ ልማቶችን በመሥራትና የክላስተር ሥራውን በማጠናከር ምርቱን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ በስፋት ማቅረብና ለኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ አቶ አብደላ ማብራሪያ፤ በሆርቲካልቸር ዘርፍ በሁለት ዙር መስኖ የሚለማ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዙር መስኖ በአሁኑ ወቅት ተጠናቆ የሁለተኛው ዙር መስኖ ልማት ተጀምሯል። እንደ አጠቃላይ በአንደኛው ዙር መስኖ ልማት 752 ሺ 10 ነጥብ 4 ሄክታር መደበኛና 36 ሺ 838 ሄክታር መሬት በክላስተር ይለማል ተብሎ ታቅዶ ነበር። ነገር ግን በመስኖም ላይ ልክ እንደመኸሩ የንቅናቄ ሥራዎች በየክልሉ እስከታች ድረስ በመሠራታቸው፣ በዚህም መነቃቃት በመፈጠሩ በመደበኛውም፤ በክላስተሩም የለማው የመሬት መጠን ጨምሯል።

ይህም በመሆኑ እንደ አጠቃላይ 909 ሺ 171 ነጥብ 98 ሄክታር መሬት ታርሶ 904 ሺ 893 ነጥብ 57 ሄክታሩን በልማቱ መሸፈን ተችሏል። ከዚህ ውስጥ በመደበኛ የተሸፈነው 864 ሺ 846 ነጥብ 4 ሄክታር ሲሆን፤ በክላስተር የተሸፈነው ደግሞ 40 ሺ 47 ነጥብ አንድ ሄክታር ነው።

የክልሎች የሆርቲካልቸር ምርትን በክላስተር የማልማት ተሞክሮ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ መምጣቱን መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተናግረው፤ ‹‹ሰሞኑን ባደረግነው የመስክ ምልከታ በሲዳማ ክልል በክላስተር የሚለማው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን አይተናል ብለዋል። በተለይም የክልሉ መንግሥት ከአመራሩ ጀምሮ አጠቃላይ የመንግሥት መዋቅር ድረስ ለእነዚህ ሥራዎች ትኩረት በመስጠቱ፤ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችንም በማሟላቱ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ለመታዘብ ችለናል›› ሲሉ አስታውቀዋል።

ይህም በመሆኑም እንደ ሀገር ካለው የሆርቲካልቸር ልማት ሰፊውን የመሬት ሽፋን በመያዝ ክልሉ መሪ መሆን መቻሉንም አመልከተዋል። እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በሌሎችም ክልሎች በክላስተር የማምረቱ ባሕል እያደገ መምጣቱን መረጃዎችን ጠቅሰው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል እንደ ሀገር የሆርቲካልቸር ምርትን በክላስተር ማልማት መቻሉ በአርሶ አደሩ ዘንድ ይነሱ የነበሩ የግብዓት፤ የቴክሎጂና የገበያ ትስስር ጥያቄዎችን መመለስ የተቻለበትን ሁኔታ መፈጠሩን ያብራራሉ። ‹‹በክላስተር መመረት ከጀመረ ወዲህ አርሶ አደሮቹ ተመሳሳይ ዝርያዎችን፤ በተመሳሳይ ቴክሎጂና ግብዓት ስለሚያመርቱ፤ በተጨማሪም የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ተደራጅተው የሚያቀርቡበት ሥርዓት በመፍጠሩ ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን መፍታት እየተቻለ ነው›› ሲሉም አብራርተዋል።

በክላስተር እርሻ በተለይ ከፍተኛ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ዝርያዎች በሚቀርቡበት ጊዜ ተገቢው ቁጥጥር ከተካሄደ ምርታማነቱን ከእጥፍ በላይም ማሳደግ እንደሚቻል አቶ አብደላ አስታውቀዋል፤ አርሶ አደሩ በተደረጃ አግባብ አሠራሩን እንዲያሻሽልም የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ይጠቅሳሉ።

‹‹ለዚህም ይረዳ ዘንድ በባለድርሻ አካላት ድጋፍ የመስክ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም አርሶ አደሩ እየተማረ ፤ ክህሎቱንም እያዳበረ የመጣበት ሁኔታም ተፈጥሯል›› ይላሉ።

አቶ አብደላ፤ ምርታማነቱን ከማሳደጉ ጎን ለጎንም እንዲሁ የአግሮ ኢንዱስትሪውን አቅም ማጎልበቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠረት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ‹‹ሰሞኑን የመስክ ምልከታ ባደረግንባቸው የሲዳማ ክልል ክላስተር እርሻዎች ክልሉ ከዚህ በኋላ አነስተኛ የሆኑ ማቀነባበሪያዎችን ታሳቢ ማድረግና ኢንዱስትሪውን ማነቃቃት እንደሚያስፈልገው ተገንዝበናል›› ሲሉ ይጠቅሳሉ።

በተለይም በስፋት ከተመረተ በኋላ ከገበያው የሚተርፈው ምርት ወደማቀነባበሩ መሄድ እንዳለበት አመልክተው፣ ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚው ማብራሪያ፤ በአጠቃላይ በአንደኛ ዙር ከለማውና ቀድሞ ወደ መስኖ ከገቡ አካባቢዎች ከ41 ሺ 224 ሄክታር ማሳ ላይ 7 ሚሊዮን 486 ሺ 214 ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል።

ይህም የሆርቲካልቸር ልማት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል። በመሆኑም በቀጣይ ትልቁ ትኩረት መደረግ ያለበት በእውቀትና በክህሎት በማምረት ጥራትን ማስጠበቅ ላይ ነው። ከዚህ አንፃር የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን በተለይ የቀዝቃዛ ሰንሰለቱን ጠብቀው እንዲሄዱ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

በዚህ ዓመት በክላስተር እየሠሩ ለሚገኙ ክልሎች የቀዘቃዛ ተሽከርካሪና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴሩ ገዝቶ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። በአንዳንድ ክልሎችም አቅም በፈቀደ መጠን እንደዚሁ የቀዝቃዛ መጋዘን ለመሥራት ዝግጅት እያደረግን መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ አንፃር ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ የምርት ብክነቱ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመው፣ በተለይ የሆርቲካልቸር ሰብሎች በቀላሉ ለብልሽት እንደሚጋለጡ ተናግረዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማፍለቅ፤ ከውጭም በማምጣት የዘርፉን የምርት ብክነት ለመቀነስ እንደሚሠራም ያመለክታሉ።

‹‹እንደ ግብርና ሚኒስቴር ሰብሎች ላይ ትኩረት የሚደረገው ካላቸው ሀገራዊ ፋይዳ በመነሳት ነው፤ ክልሎች ደግሞ በራሳቸው ለይተው ይሠራሉ›› የሚሉት አቶ አብደላ። ከዚህ አንፃር ሚኒስቴሩ ከምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትና፤ ከሥራ እድል ፈጠራ፤ ከውጭ ምንዛሬ ግኝትና እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚሠራባቸው የፍራፍሬ ሰብሎች መለየታቸውን ይጠቁማሉ።

‹‹ሁሉንም በአንድ ጊዜ ይዘን መሄድ አንችልም፤ የአቅም ጉዳይም ስለሚገድበን በአራት የሆርቲካልቸር ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው›› ይላሉ። እነዚህም ከአትክልት ሽንኩርትና ቲማቲም ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው፣ ከዚህ አንፃር ትልቅ ችግር አለ ተብሎ የተለየው የተሻሻለ ዘር አቅርቦት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ዘር አቅርቦቱን ለማሻሻል በማምረት ሂደቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ከፍራፍሬ አንፃር ደግሞ አቮካዶና ሙዝ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል። ለኢንዱስትሪ አቅርቦት ግብዓትና ለምግብም ከሚያገለግሉት አንፃር በስትራቴጂ ረገድ የስኳር ድንችና ድንች ልማት ፕሮግራም ተቀርጾ እየተሠራ መሆኑን ነው ያመለክታሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚኒስቴሩ ኢንሼቲቭ የእንሰት ልማት ፕሮግራም ተቀርጾ እየሠራ መሆኑንም አቶ አብደላ አስታውቀዋል፤ የቀደሙ ጥናቶች ዋቢ አድርገው እንዳመለክቱትም እንሰት እስከ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች የምግብ ዋስትና የሚረጋግጥበት ነው።

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ የሚጠቀመው የሆርቲካልቸር ምርት እንደሆነ ይገመታል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የእንሰትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ትኩረት እንደተሰጠውም ጠቅመዋል፤ ሚኒስቴሩም በዚህ ልማት ላይ በተለየ መልኩ ድጋፍ እያደረገና ከፍተኛ ንቅናቄ ፈጥሮ እየሠራ ስለመሆኑ ያብራራሉ።

ምርታማነቱን ለማሳደግ ሲባል የሶዶ ቃል ኪዳን ( ሶዶ ዲክለሬሽን) እንዲጀመር መደረጉን አቶ አብደላ አስታውሰው፤ ዘንድሮም አርባ ምንጭ ላይ እንደዚሁ የንቅናቄ ሥራዎች መሠራታቸውን ይጠቁማሉ።

የእንሰት ተክል በበሽታ እየተጠቃ መሆኑን አመልክተው፣ ይህንን መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ሊያግዝ በሚችል መልኩ ከፍተኛ የንቅናቄ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ይህንንም ኢንሼቲቭ ክልሎች ወስደው እንዲሠሩ ስምምነት ላይ መደረሱንም አመልክተው፣ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በማውረድ ከዘርፉ የላቀ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑ አስታውቀዋል።

‹‹ይህንን ስንል ግን ሌሎቹን አንደግፍም ወይም አንከታተልም ማለት አይደለም›› የሚሉት አቶ አብደላ፤ ሌሎች ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለባቸውና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ተብለው የሚመረቱ የአትክልት፤ የእፀ-ጣዕምና ሌሎች የፍራፍሬ ዓይነቶች እንዳሉም ይጠቁማሉ። ለዚህም ሮዝመሪ፣ ላቫንደር፣ በሶብላና የመሳሰሉት ተጠቃሽ መሆናቸውን ይናገራሉ። የተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎች ተመርተው ወደ ውጭ የተላኩበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰዋል።

ከፍራፍሬ እንደ እንጆሪና ብላክቤሪ ያሉትን በኢንቨስትመንት ደረጃ በማልማት ወደ ውጭ የሚላኩበት ሁኔታ እንዳለም ያመለክታሉ። በመሆኑም በአጠቃላይ እስከ አሁን የተከናወኑት ተግባሮች እንደ ሀገር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደሚያስችሉ ቢታመንም፣ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት አግሮ ኢንዱስትሪውን ከመደገፍ አኳያ የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You