
ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢኮኖሚውን ማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሪፎርሞች ተካሂደዋል፡፡ በተለይ በመጀመሪያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ሦስተኛ በአፍሪካ ደግሞ አምስተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኗም በሪፎርም የተከናወኑ ተግባሮች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ከሚያመለክቱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ይህን ስኬታማ አፈጻጸም የሚያልቁ ሪፎርሞችም በቅርቡ ተካሂደዋል፡፡ ሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተተገበረ ያለበት ሁኔታ፣ ሀገሪቱ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግብይት አስተዳደር ማሻሻያ ማድረጓ የምጣኔ ሀብቱን ዕድገት ቀጣይነት እንዲሚያረጋግጡት ይጠበቃል።
2017 ያለፉት ስድስት ወራት የአንዳንድ ዘርፎች አፈጻጸምም ይህንኑ እያመላከተ ይገኛል፡፡ በወጪ ንግድ፣ በማዕድን፣ በግብርናው ዘርፍ የታዩ አፈጻጸሞች ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ፡፡ በተለይ የወጪ ንግዱ አፈጻጸም ያሳየው ለውጥ የሪፎርም ሥራዎቹን ተገቢነት ያመላክታል፡፡
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከወጪ ንግዱ ሶስት ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ አፈጻጸሙ የበጀት ዓመቱ ዕቅድ እንደሚሳካ ብቻ ሳይሆን ከእቅድም በላይ አፈጻጸም እንደሚመዘገብ ይጠቁማል፡፡ አፈጻጸሙ ከ2009 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ከነበሩ ዓመታዊ የወጪ ንግድ አፈጻጸሞች የላቀ ሆኖም ተገኝቷል፡፡ ይህም በስኬትነት ሊያዝ ይገባዋል፡፡ በስድስት ወር በቀደሙት ዓመታት በየዓመቱ ይመዘገብ ከነበረው የውጪ ምንዛሬ ገቢ የሚልቅ ገቢ መሰብሰብ መቻል የአፈጻጸሙን እየላቀ መምጣትም ይጠቁማል፡፡
ለአፈጻጸሙ እዚህ ደረጃ መድረስ የሪፎርም ሥራዎቹ ሚና ከፍተኛ መሆኑ እንደመሆኑ በቀጣይም በላቀ መልኩ እንደሚጨምር ይታመናል፡፡ በዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር የሰበሰበች ሀገር በስድስት ወራት ሶስት ነጥብ 28 ቢሊዮን መሰብሰብ ስትችል ዓመታዊ አፈጻጸሟ የላቀ ሊሆን እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር አይቸግርም፡፡ በቡና፣ በማዕድን የወጪ ንግድ እየተመዘገበ ያለው ለውጥም ይህ አፈጻጸም እንደሚቀጥል ይጠቁማል፡፡
እንደሚታወቀው ሀገሪቱ በቅርቡ የችርቻሮና ጅምላ ንግዱን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ያደረገችበት ሁኔታ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ በነጻ ገበያ እንዲወሰን ማድረጓና የመሳሰሉት ርምጃዎችም የወጪ ንግዱ አፈጸጻም እየጨመረ ይሄዳል ተብሎ እንዲጠበቅ የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው፡፡
ሀገሪቱ ለዚህ ውጤት ምቹ ከባቢ መፍጠሯን መቀጠሏ እንዳለ ሆኖ አስቀድማ የፈጠረቻቸው ምቹ ሁኔታዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ላይ ያለች እንደመሆኗም ዘርፉ በርግጥም በውጤታማነቱ ይቀጥላል፡፡
በወጪና ገቢ ንግድ ላይ የሚሰሩ ባለሀብቶች መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ የኖረው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እና አጠቃቀም ጉዳይም ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ የውጭ ምንዛሬ ግብይት አስተዳደር እንዲሁም ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ የተወሰነውን በቀጥታ እንዲጠቀሙ የተቀረውን ደግሞ በመንግሥት ባንኮች እንዲያስቀምጡ መፍትሄ ተቀምጦለታል፡፡ እነዚህ ሁሉ የወጪ ንግዱ የበለጠ እንዲሳለጥና ውጤታማ እንዲሆን የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡
ንግድን ተወዳዳሪ፣ የተቀላጠፈ፣ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህ ወሳኝ ሚና እንደሚጨጫወት የታመነበት የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣናም ሰሞኑን ቦታ በመስጠት ባለሀብቶችን መቀበል ጀምሯል፤ በቀጣይም ጥያቄያቸው በሂደት ላይ የሚገኝ 13 ባለሀብቶች ወደ ቀጣናው እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ቀጣናው ለመግባት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ መንግሥትም ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ቀጣናው በመግባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ እያስተላለፈ ይገኛል፡፡
የባለሀብቶቹ ወደዚህ የንግድ ቀጣና መግባት በወጪና ገቢ ንግዱ ላይ ሌላ ተጨማሪ አቅም እንዲፈጠር ያስችላል፤ ሸቀጦችን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ አስመጪዎች ሸቀጣቸውን በጅቡቲና በዱባይ በሚገኙ ነጻ የንግድ ቀጣናዎች በኩል ሲያስመጡ ኖረዋል፤ የድሬዳዋው ነጻ የንግድ ቀጣና ወደ ሥራ መግባት ሸቀጦቹን ከአምራች ሀገሮች ወደ ወደብ ከዚያም በቀጥታ ወደ ድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና እንዲገባ በማድረግ በውጪ ነጻ የንግድ ቀጣናዎች የሚያወጡትን ወጪ ያስቀርላቸዋል፤ ሸቀጦችም በተቀላጠፈ መንገድ እንዲገቡ ያስችላል፡፤ በተመሳሳይም ለውጭ ገበያ የሚላኩ ምርቶችም እንዲሁ ወደዚህ ነጻ የንግድ ቀጣና እንዲገቡ በማድረግ በቀጥታ በጅቡቲ በኩል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ያስችላል፡፡
መንግሥት ቀጣናው የታለመለትን ግብ እንዲመታ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል እያረጋገጠ ነው፡፡ እስከ አሁን እንዳደረገው ሁሉ ባለሀብቶችን ወደ ቀጣናው ለመሳብ የሚያደርገውን ጥሪ ማጠናከር፣ ፈጥነው ወደ ቀጣናው መግባት ይችሉ ዘንድ ግንዛቤ ከመፍጠር አንስቶ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ባለሀብቶች ቦታ ተረክበው ወደ ቀጣናው እየገቡ ሲሆን፣ ሌሎችም ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ቀጣናው ያለው እምቅ አቅም ግን አያሌ ባለሀብቶችን ይፈልጋል፡፡ ባለሀብቶች / የንግዱ ማኅበረሰብ/ ይህን ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ግዙፍ ማዕከል ፈጥነው በመቀላቀል ራሳቸውንም ሀገሪቱንም ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም