ባይተዋሩ- በ19 የሞት ጥላ

“ባይተዋር ሆኛለሁ” ብሎ ዘፍኖ ባይተዋር ሆነ:: “ብቻዬን” እንዳለም ብቻውን ሆነ:: የዘፈነው ሁሉ በህይወቱ ላይ እንደሠራበት ስንመለከት ሳያስገርመን አልቀረም:: በርከት ያሉ የሙዚቃ ሥራዎቹ፣ በኋላ ህይወቱ እንደጥላ መከተላቸውን ሲያስተውል ጊዜ ራሱንም አስደምመውታል::

የባይተዋሮቹን ሆድ እያባባ፣ በስሜት ባህር ንጦ፣ በትካዜ ደፈቀቻው እንጂ የእውነትም ባይተዋር እሆናለሁ ወይም ይሆናል ብሎ ያሰበ አልነበረም:: በድፍን 19 ዓመታት ለስደት ሲያድር አንዳቸውም አልራሩለትም:: በሞት ጥላ ከታጀቡ አሥራ ዘጠኙ ዓመታት መካከል አንዳቸውም እንባውን አላበሱለትም:: አንዱም አብረውት ሆነው፣ ከባይተዋርነት መቃብር ውስጥ አላወጡትም:: እየተፈራረቁ በተቀባበሉት ቁጥር፤ ይባስ ከድጡ ወደማጡ፣ ከሰቀቀን ወደ ሰቆቃ መሩት::

ሁሉን አስጥላ ከሀገሩ የሸኘችው ስደት ፊቷን አዙራ የመከራ ጀርባዋን ሰጠችው:: ታበራልኛለች ያላት ፀሐይ ይባስ ጨልማ አሳልፋ ለመከራ ገበረችው:: ነጻ ታወጣኛለች ብሎ ቢያምናት ጊዜ የ19 ዓመታት የቁም እስር ፈረደችበት:: የናፈቁትን ጠብቆ፣ የወደዱትን እንደማጣት ልብን የሚሰብር ነገር የለም:: ዝነኛው ድምጻዊ ዓለማየሁ ሂርጶ፤ ከዚህ ሁሉ የሞት ጥላ አምልጦ በስተመጨረሻም ከ19 ዓመታት በፊት ጥላት ወደ ነጎደው እናት ሀገሩ ተመልሶ መጣ::

ዳግም ሀገሩን ለማየት የበቃባት ቅጽበት፣ ከሞት አፋፍ ያመለጠባት ልዩ ዕድል ነበረች:: የሀገሩን አፈር እንደረገጠም “ኢትዮጵያ ልጄ ብላ እጆቿን ዘርግታ ተቀበለችኝ” ሲል በደስታ ሲቃ ገለጸው:: ቀድሞም ሲሄድ ከእቅፏ ውስጥ ነበር፤ አሁንም ተመልሶ ሲመጣ ወደ እቅፏ ነው::

ዓለማየሁ ሂርጶ ከገባበት መአት ከመግባቱ አስቀድሞ፣ በሀገሩ ላይ ታላቅ ስም የነበረው ድምጻዊ ነበር:: የሙዚቃ ሥራዎቹን ያላጣጣመ የለም:: ከልጅ እስከ አዋቂው አብሮት እኩል አንጎራጉሯል:: በግጥምና ዜማዎቹ ብስለት ከስሜት ጋር ተብሰልስሏል:: ጆሮን ብቻ ሳይሆን ልብንም የሚቆጣጠረው ማራኪ ድምጹ ጋር ከምናብ ሱባኤ ገብቷል:: በሙዚቃዎቹ ውስጥ አንድ ጊዜ ፈገግ፣ ሌላ ጊዜም ትክዝ እያስደረገ ስንቱን ዘመን ያስዋበ የ90ዎቹ ግርማ ሞገስ ነው::

በ1990ዎቹ የምንጊዜም ምርጥ ስብስብ ውስጥ ከፊት ከምናገኛቸው አንዱ ነበር:: የሙዚቃን ጠረን የማገው ገና በልጅነቱ ነበር:: መርካቶ ሰፈር ውስጥ የተወለደው ዓለማየሁ ሂርጶ፣ ዕድገቱ ግን በአመዛኙ ዓለም ገና፣ ኬንቴሪ መንደር ውስጥ ነው:: ዓለም ገና በሚገኘው ሙሉጌታ ገሌ እና ሰበታ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተምሯል:: በሰበታ አጠቃላይ ሳለ ግን፤ ሁሌም ሲያስበው የነበረ ምኞቱን እውን ለማድረግ ከዕለታት በአንዱ ቀን ቆርጦ ወደ አንድ የምዝገባ ጣቢያ አመራ:: ምዝገባውም የውትድርና ምልመላ ነበር:: ወደ መዝጋቢዎቹ ጠጋ ብሎም ለመመዝገብ እንደሚፈልግ ይገልጽላቸዋል:: ግን ዓለማየሁ ትንሽ ልጅ የነበረ በመሆኑ ለአቅመ ውትድርና አልበቃህም ብለው ሸኙት::

ይህ ወታደር የመሆን ህልሙ ዛሬም ድረስ ከውስጡ ባይጠፋም፣ ዛሬም ግን ሊሆነው ያልቻለውና አብዝቶ የሚሻው የእናት ሀገር ፍቅራዊ ምኞቱ ነው:: ሆኖም ከዚህ ምኞት ላይ የሰረቀችው የሙዚቃ ጥሪ ዛሬም እንደያዘችው ቀጥላለች:: “ለበጎ ነው፤ ሁሉም ነገር ለበጎ ነው” ብሎታል በሙዚቃው::

ዓለማየሁ ዓለም ገና ውስጥ ከነበረው የልጅነት ህይወቱ፣ ዳግም ወደ ትውልድ መንደሩ መርካቶ ተመለሰ:: የሙዚቃ ህይወቱን ጅምር አጥብቆ የያዘውም የዚህን ጊዜ ነበር:: መርካቶ ሰፈር ውስጥ የነበረው፣ ከፍተኛ አምስት የተሰኘው ኪነት ቡድን ስር መሠረቱን ጣለ:: የሁልጊዜም የህይወቱ ጓዳ ለመሆን የቻለውን ድምጻዊ ታደለ ሮባን የተገናኘውም በዚህ ኪነት ውስጥ ነበር:: ትውውቅና ወዳጅነታቸውም ገና በዕድሜ ሳይጎለብቱ በፊት ነው:: የሁለቱም ህልምና ትልም ሙዚቃ ስለነበር፤ ውስጣዊ የጥበብ ነብስያቸውን ተጋርተውታል:: አደግ ሲሉም አብረው በአንድ ቤት ውስጥ ኖረዋል:: ምኞታቸው እውን እየሆነ ሲሄድ፣ ሁለቱም የምሽት ክለቦች ውስጥ መዝፈንም ጀመሩ::

ከጊዜ በኋላ ዓለማየሁ ሂርጶ “ቲክ ፋይፍ” የተሰኘ፣ የመጀመሪያ ካሴቱን ለመሥራት ወደ ዝግጅት ገባ:: ይህን ካሴት ለመሥራት ደፋ ቀና በሚልበት ሰዓትም ሌላ አንድ ልዩ ወዳጅ ወደ ህይወቱ መጣ:: ይህም ሰው ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ነበር:: ዓለማየሁ ልቡ ለእውነተኛ ወዳጅነት የተፈጠረ ነውና ከጎሳዬም ጋር አብሮ ለመተንፈስ ምንም ያልቀራቸው ወዳጅነት መሠረቱ:: ካሴቱንም ተባብረው ለአድማጭ ጆሮ አደረሱት::

በመጀመሪያ ሥራው ብቅ ሲል ገና በትክክልም ለሙዚቃ የተፈጠረ ሰው መሆኑን አሳየ:: “ሻላላ!” ቅሉ የሌላ ሙዚቀኛ ሥራ ቢሆንም ይህም ተወዶለታል:: “ሆድዬ፣ ተመቸሽ ወይ፣ ኢቫንጋዲ” አንድ ሌላ በጥምረት የሠራበትን ጨምሮ፣ በድምሩ ወደ አምስት ያህል አልበሞችን አከታትሏል:: በሁሉም ተወዳጅነት እየተጎናጸፈና ተደማጭነትን እያትረፈረፈ “ዓለማየሁ ሂርጶ” የሚለው ስም መግነን ጀመረ::

የበኩር ካሴቱ የነበረው “ኢቫንጋዲ” ወጥቶ ሳይቆይ፣ ዓለማየሁና ጎሳዬ የተጣመሩበት የሙዚቃ ድግስ ተሰናዳ:: በጊዜው ይህ ጥምረት እንዲያመልጠው የሚፈልግ የሙዚቃ አፍቃሪ አልነበረም:: ከውስጥ አዳራሹ ሞልቶ፣ ሳልሰማ አልሄድም ያለው ታዳሚም፣ ጆሮውን አቁሞ ድግሱን በሽታው ብቻ ጨርሶ ተመልሷል::

ዓለማየሁ በሙዚቃ ህይወቱ ምናልባትም ጥሩና የተሳካለት ሊባል የሚችል ነበር:: በሙዚቃ አንድን ዘመን ዋጅተው፣ “የ90ዎቹ” ለመባል ያበቃቸውን ሥራ በጋራም ሆነ በግል ከሠሯቸው ሥራዎች ውስጥ ስሙን ለማስቀመጥ የቻለ ድምጻዊ ነው:: በሀገር ውስጥና በውጭ ዓለማት እየዞረ፣ ከአቻዎቹም ከእነርሱ አንጋፋ ከነበሩትም ጋር አብሮ ሠርቷል:: ከዚህ ሁሉ ውስጥ ለኑሮው የሚሆነውንም ቢሆን አላጣም ነበር:: ብዙ ይሠራ ስለነበር፣ ብዙ ያገኙ ከነበሩትም ውስጥ ነው:: ግን አንዲት አመሉ ለራሴ እንዳይል አደረገችው:: ባገኘ ቁጥር ሁሉ መስጠትን የሚወድና አብዝቶ በመስጠት የሚረካ ነበር:: እንካችሁ! የሚያበዛ ሆነናም ቀጣይ ህይወቱን ሳያደላድል ቀረ:: ቢሆንም በነበረውና በሚያደርገው ሁሉ ደስተኛ ነበር::

ከጊዜያት በኋላ፤ ድንገት ነገሮችን ሁሉ የሚለዋውጥ፣ የነበረውን እንዳልነበር የሚያደርግ አጋጣሚ ተፈጠረ:: በ1998 ዓ.ም ከሞት ያልተናነሰው የስደት ማዕበል፣ ወጀቡን እየነቀነቀ አጠገቡ ደረሰ:: የተሻለች ነገን አገኛታለሁ ብሎ በስደት ነጎደ:: የተወለደባትን መርካቶ፣ ያደገባትን ዓለም ገና፣ የህይወት ሀሁ የተማረባትን አዲስ አበባን፣ ስሙን በሙዚቃ የሰቀለባትን ውድ ሀገሩንና ቤተሰቡን…ሁሉንም ጥሎ ድንገት ብን አለ:: እመጣለሁ ብሎ ሳይመጣ ቀረ:: ሰሞናትን ሲያስብ ዓመታትን ከረመ:: ድንገት ኮብልሎ የውሃ ሽታ ሆነ::

በአንዳች መና ተስፋ ተጀቡኖ፣ በባይተዋርነት አንሶላ ውስጥ ተጠቀለለ:: በመጀመሪያ እግሩን ከሀገሩ አውጥቶ ሲሄድ እየሆነበት ያለው ነገር ይሆናል ብሎ ፍጹም አልጠረጠረም ነበር:: ወደዚህ መዓት የገባበት፣ የመጀመሪያ በረራው ወደ ስዊድን ነበር:: ከጎሳዬ ተስፋዬ ጋር በዚያ ቀጠሮ ነበራቸው:: ቀጠሮው ደግሞ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ለሚያቀርቡበት መድረክ ነበር:: እዚያ ይጠብቀኛል ባለው የሙዚቃ መድረክ ፈንታ ግን፣ ህይወት ሌላ የራሷን መድረክ አዘጋጀችለት:: ሥራውን ለማቅረብ እስከማይችል ድረስ መታመም ጀመረ:: ህክምና አገኛለሁ ሲል ኖርዌይን የቀጣይ መዳረሻው ያደረጋትም ከዚህች አጋጣሚ መልስ ነበር::

ከስዊድን ወደ ኖርዌይ ተሰደደ:: ኖርዌይ ደርሶ እንደማንኛውም ስደተኛ ሁሉ በካምፕ ውስጥ ተጠለለ:: ውሎ ባደረ ቁጥር ሁሉ የሚገጥመው ፈጽሞ ያልጠበቀውን ነበር:: ያሰበውና እየሆነበት ያለው ነገር ለየቅል ሆኑበት:: ዛሬ ባይሆን ነገ ይሆናል፤ እያለ ብዙ ተስፋ ቢያደርግም፣ አንዱም ዛሬ አንዱም ነገ ሳይሆንለት ቀረ:: እዚያች የስደተኛ ካምፕ ውስጥ የቁም እስረኛ ሆኖ ዓመታት ተቆጠሩ:: እንደ አብዛኛዎቹ ዝነኛ ስደተኞች ለመታየት እንኳን አልሆነለትም::

ሀገሩ ውስጥ ያለው ስምና ዝናው ለስደት ህይወቱ አንዳችም ሳይፈይድለት ቀረ:: የመኖሪያ ፈቃድ ሊያስገኝለት አልቻለም:: የሚያውቁትም አብረውት ያሉ ጥቂት ሀበሾች ብቻ ናቸው:: ዝነኛው ድምጻዊ ዓለማየሁ ሂርጶ፤ ስደተኛው ብቻ ተባለ::

እየታገለ ካለው የስደት ህይወት ጎን ብቅ ያለበት ህመም ግን የኖርዌይን የስደት ካምፕ፣ ካታካንቡ አደረገበት:: አንድ እጁን ለስደት፣ ሁለተኛውንም ለህመሙ ሰጠ:: ሌላ እጅ ያጣለት እስርም ጊዜ እየተበቀ ይመጣበታል:: በ19 ዓመታት ውስጥ መኖሪያ ፈቃድ የለህም በሚል ሦስት ጊዜ እስር ቤት ገብቶ ወጥቷል:: እርሱም ነብሱን ለማትረፍ ሲል የሙጥኝ ብሎ ቆየ:: በየጊዜው ህክምናውን የሚከታተል ቢሆንም፣ ህመሙ ግን እየጠናበትና ጭለማውም እየገፋ ሄደ::

ከብዙ የሐኪሞች ጥረት በኋላም በህይወት የመቆየቱ ነገር የመነመነ ሆኖ ታየ:: ከእግዜር በታች ፈውስን የሚሰጡት የሐኪሞቹ እጆች የጻፉለት፤ ከሌላው ተለይተው ለመሞት የቀራቸውን ቀናት የሚቆጥሩ ህመምተኞች ወደሚገኙበት (የሞት ምድብ) ወደተባለው ክፍል ይዘዋወር የሚል ነበር:: ዓለማየሁም 14ኛው ባለተራ ሆኖ ወደክፍሉ ገባ::

ያ ክፍል እጅግ አስፈሪና ባይተዋርነት ከሞት ጋር የነገሰበት ነበር:: ክፍሉ በጭራሽ አይከፈትም:: ዓለማየሁና ቀሪ 13ቱ ህሙማን ከክፍሉ ወደየትም አይሄዱም:: ለ24 ሰዓታት ከዚያው ውለው ያድራሉ:: ከውጭ ወደዚህ ክፍል የሚገባው ሰው እንኳን፣ በተቻለው ተሸፋፍኖ ስጋት ካዘለ ጥንቃቄ ጋር ነው:: በመኖርና ባለመኖር፣ በቀጭን ህይወትና በወፍራም ሞት ተንጠልጥለው ያሉትን አሥራ አራት ሰዎችን መመልከት በራሱ የሚያሳቅቅ ነው:: በሩን አንኳኩቶ ተረኛውን የሚጠራውን የሞት እጅ እየተጠባበቁ፣ ቀጣይ ማን ይሆን ሲሉ እርስ በርስ ተፋጠዋል:: “አሥራ አራት ብርጭቆ በግርግዳ ላይ፣ አንዱ ሲሰበር ስንት ይቀራል” ዓይነት ሆነ::

ብዙም ሳይቆይ አንድ በአንድ መርገፍ ጀመሩ:: የዓለማየሁ ሃሳብም ስንተኛው ሟች ሊሆን እንደሚችል እንጂ፤ ለተአምር ስለመትረፍ አልነበረም:: የሐኪሞቹ ውሳኔና ግምት እስከ 13ኛው ሟች ድረስ ልክ ነበር:: 14ኛው ዓለማየሁ ሂርጶ ጋር ሲደርስ ግን ሐኪሞቹንም ያስገረመ፣ ማንም ያልጠበቀው ተአምር ተፈጠረ:: አሥራ ሦስቱ ሞተው አንድ እርሱ ብቻውን መቅረቱ፤ ተአምር እንጂ ሌላ ምንም ልንለው አንችልም::

ከህመሙ ጋር ሲታገልም ሆነ ወደ ማገገሙ መንገድ ሲገባ ትልቁ ፈተናው ነጋ ጠባ ሀገሬን ልቀቅ የሚለው የኖርዌይ መንግሥት ጉዳይ ነበር:: ምንም እንኳን ሀገርህ ግባ እያለ መውጫ መግቢያ ቢያሳጣውም፣ ለህመሙ ሊያደርግ ከሚገባው ሰብአዊ ደግነቱ ግን አላጎደለበትም:: እንዲያውም እንድናመሠግነው የሚያደርገውን ምስክርነት ዓለማየሁ በአንደበቱ ተናግሮታል:: በየጊዜው ለነበረው ለዚህ ህክምናው፣ ወደ 1 መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ አድርጎለታል ቢባል ማን ያምናል…ወረቀቷን ቢከለክለውም ያደረገለት ታላቅ ነገር ግን ይህን ያህል ነው:: ይህንን ሁሉ የገንዘብ መጠን የወጣበት ህክምናም ምን ያህል ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ ይናገራል::

ዓለማየሁ በኖርዌይ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ሲኖር እንደ ቁም እስረኛ ነበር:: ከዚያ የሚወጣው አልፎ አልፎ ወደ ከተማ ደረስ ለማለት ሲፈቀድለት ብቻ ነው:: በታመመ ጊዜ ሁሉ ወደ ሆስፒታል ከሄደባቸውና ከታሰረባቸው ሦስቴ ጊዜያቶች በስተቀር፣ ለድፍን 19 ዓመታት ባይተዋር ሆኖ የኖረው በካምፑ ውስጥ ነው:: በዚህ ስቃይ መካከል ሆኖ ሀገሩ እንዳይገባ ያደረገው አንድም የህክምናው ጉዳይ ነበር:: “ከህመሜ ጋር ሀገሬ ገብቼ ለሌላው ሸክም ለመሆ ን አልፈለግሁም” ሲል በወቅቱ አድሮበት ስለነበረው ፍራቻ ያወሳል::

የተሻለ ነገን ፈልጎ ከተሻለ ዛሬ ጋር ተገናኝቶ ነበር:: ያ ዛሬም ትናንት ነበር፣ ያ ነገም ዛሬን ሆነ:: ያለፈው ሁሉ አልፎ፣ በስተመጨረሻም የጣለውን ለማንሳት ቻለ:: በባዕድ ሀገር ያነባውን እንባ አሁን በሀገሩ ሊታበስ፣ በአዲስ ታሪክ ዳግም ተነስቷል:: ዓለማየሁ ሂርጶ ዳግም ተመልሶ ወደ ሀገሩ ገባ:: ሲገባም ጠረኗ የናፈቀው የሀገሩ አፈር ላይ ገና ከመቆሙ የባይተዋርነት ሸክሙ ተራገፈለት:: ያንን ጥሎት የሄደውን ሙዚቃ ዳግም ለማንሳት በጉጉት ተወጥሮም ነበርና እንዲህ አለ “ውድ የሀገሬ ልጆች እንደምን ከረማችሁልኝ? እኔ ወንድማችሁ ዓለማየሁ ሂርጶ ከ19 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ለሀገሬ በቃሁ:: …አሁን ደግሞ በሙያዬ ራሴንና ሀገሬን ለመጥቀም በሙሉ አቅሜ ወደ ሥራዬ ተመልሻለሁ:: ለምሠራቸው ሥራዎችም የእናንተ የሁላችሁም ጸሎትና መልካም ምኞታችሁ ስለሚያስፈልገኝ፣ ባላችሁበት ሆናችሁ እንድታስቡኝና መልካሙን ሁሉ እንድትመኙልኝ ስል በፍቅር እጠይቃለሁ” ሲል በአዲስ የመንፈስ ብስራት ውስጥ ሆኖ ነበር:: ከሞት ጎጆ ውስጥ ጠፍንገው ያሰሩትን፣ 19ኙንም ዓመታት ድል ባደረገ መንፈስ ውስጥ ሆኖም ነበር::

ያኔ መነሻው ላይ ዓለማየሁ ሀገሩን ለቆ ሲወጣ የነበሩት ሁለት ትንንሽ ልጆቹ፤ ዳግም ከ19 ዓመታት የስደት ትንቅንቅ ኋላ ሲመልስ ልጆቹ የልጅ ልጆች ታቅፈው ጠበቁት:: አባት ሆኖ ከወጣበት አያት ሆኖ ገባ:: ሀገሩ ሲገባ በጣም ደስ ካሰኙት ነገሮች አንዱ ይህ ነበር:: ህይወት ሁሌም የለውጥ ናትና እርሱም ከነውጡ ተርፎ ወደ ለውጡ ዓለም ተቀላቅሏል:: አሁን ሁሉም ነገር ለበጎ፣ በጎም እየሆነለት ነው::

ያለፉት እነዚያ 19 የሞት ዓመታት፣ ዛሬ ላይ እንደ አዲስ እየገነባው ላለው ህይወቱ ትልቅ መማሪያ ሊሆኑት እንደቻሉ ይናገራል:: ምንም መጥፎና ለማሰብ የሚያስቀይም ትዝታ ቢሆንም፤ የኋልዮሽ ጊዜና ሁኔታን ወደፊት ስቦ ሊለውጣቸው አይችልም:: በመጥፎው ትውስታ ከመብሰልሰል ግን፤ ወደ አንዳች ኃይል ሰጪ ግብአትነት ሊቀይረው እንደሚሻ ያነሳል:: “በመከራ ውስጥ ልታልፍ ትችላለህ፣ በበሽታ ውስጥም ልታልፍ ትችላለህ፤ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብታልፍ ግን መኖር ደስ ይላል” ይላል::

ዓለማየሁ ሂርጶ ከሚወደው የሙዚቃ ሥራው ጋር ዳግም ተገናኝቷል:: ሰሞኑንም ‹‹መኖር ደስ ይላል›› እና ‹‹የኢትዮጵያ እናቶች›› የተሰኙ ሁለት ነጠላ ዜማዎችን ለአዳማጮቹ ጆሮ አድርሷል:: ከመሃል ያባከናቸውን 19 ዓመታት ለመካስ አዲስ አልበም፣ በአዲስ መንፈስ፣ በቅርቡ ሊያስደምጠን ነው:: ሥራው መጠናቀቁን የገለጸ ሲሆን፤ በዚህ አልበም ላይ “ባይተዋር” የተሰኘውን ሙዚቃ የጻፈለት ዓለማየሁ ደመቀ፣ አብዱ ኪያር፣ ብስራት ሱራፌል እና ሌሎችም ዕውቅ ሙዚቀኞች በግጥምና ዜማ ተሳትፈውበታል:: ከሞት መልስ ያለች ህይወት ገነት፣ ከመከራ መልስ የተገኘች ደስታ ዕንቁ፣ ከረጅም ዓመታት በኋላ የምትገኝ ሙዚቃም ጣፋጭ ናትና ለመስማት እንቸኩላለን::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You