“ቅድሚያ ለሴቶች” ውድድር በ16 ሺህ ተሳታፊዎች ይካሄዳል

“የሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች” 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በመጪው መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በ16 ሺህ ተሳታፊዎች እንደሚካሄድ ታውቋል። የውድድሩ ተሳታፊዎች ምዝገባም የፊታችን ሰኞ ይጀመራል።

በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ካለፉት አስራ ሦስት ዓመታት ጀምሮ ሴቶችን ብቻ በማሳተፍ የሚካሄደው ይህ ዓመታዊ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዘንድሮ ከ200 በላይ ታዋቂ ሴት አትሌቶች እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል።

ውድድሩን የተሳታፊዎች ምዝገባ አስመልክቶ ሰሞኑን በተሰጠው መግለጫ የአዘጋጁ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ በሰጡት ማብራሪያ፤ ባለፉት በርካታ ዓመታትን በስኬት በተጓዘው በዚህ የሴቶች ውድድር ላይ ዘንድሮ 16 ሺህ ተሳታፊዎችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል። የፊታችን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም በM-Pesa መተግበሪያ እና በተመረጡ የሳፋሪኮም እና ዳሸን ባንክ ቅርንጫፎች ምዝገባ እንደሚጀመርም ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለጻ፤ የምዝገባ ዋጋው 540 ብር ነው። M-Pesa’ን የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ተጠቅመው ለሚመዘገቡ ተሳታፊዎች ልዩ የ30 በመቶ ቅናሽ የሚኖረው ሲሆን፤ ለተማሪዎችም ልዩ ቅናሽ እና አቅም ለማይፈቅድላቸው ሴቶች አማራጮች ተመቻችተዋል። ተሳታፊዎች ሲመዘገቡ በቀጥታ የመወዳደሪያ ካኒቴራ(ቲሸርት) እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።

የተወዳዳሪዎች ምዝገባ አምስት የምዝገባ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በእናት ባንክ አራት ቅርንጫፎች በመገናኛ አበበች ጎበና ቅርንጫፍ፣ በካሳንቺስ እቴጌ ጣይቱ ቅርንጫፍ፣ በሜክሲኮ ደራርቱ ቱሉ ቅርንጫፍና በአዲሱ ገበያ ሜሪ አርምዴ ቅርንጫፍ እንዲሁም በአምስተኛው በካፒታል ሆቴልና ስፓ ተሳታፊዎች መመዝገብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

ውድድሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት በቀረበው “ሁሉም መብቶች ፣ ለሁሉም ሴቶች ” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ፣ የኢትዮጵያ ሴቶችን ስኬት ለመዘከርና ዕውቅና ለመስጠት ታስቦ መሆኑም ታውቋል። በተጨማሪም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ከተባበሩት መንግሥታት 17ቱ የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የፆታ እኩልነት ጉዳይን ትኩረት በማድረግና ከፆታ ጋር የተገናኙ ጥቃቶችን ለማስቆም እንዲሁም ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣትና ከግብ ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ተወዳዳሪዎች ርቀቱን ከ35 ደቂቃ በታች በመግባት ሩጫውን እንዲያጠናቅቁ ለማድረግ እንደታሰበም ተጠቁሟል። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮኗና የውድድሩ በጎ ፈቃድ አምባሳደር አትሌት መሠረት ደፋርም ይህን ለማሳካት መነሳቷ ተጠቅሷል፡፡ መሰረት ደፋር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና መመረጧን ተከትሎም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በውድድሩ መስራች ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ አማካኝነት ልዩ ስጦታ አበርክቶላታል።

ተምሳሌት ሴቶችን ጨምሮ ከ11 ሺህ በላይ ሴቶችን ብቻ ሲያሳትፍ የቆየው ውድድር በአሁኑ ወቅት ለዓለም አቀፍ ዕውቅና ከበቁ አትሌቶች መካከል አሰለፈች መርጊያና ሰንበቴ ተፈሪን የመሳሰሉ ኮከቦች የተገኙበት ነው፡፡ በዚህ ውድድር ላይ አሰለፈች 15፡57 ደቂቃ ማስመዝገቧ የሚታወስ ሲሆን፣ ሰንበሬ ተፈሪ ደግሞ 15፡55 መሮጥ እንደቻለች መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል ላለፉት በርካታ ዓመታት በስኬት የተጓዘው የቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ በብዙ አጋር ተቋማት ድጋፍ ስኬታማ እየሆነ መጥቷል። በዘንድሮ ውድድር ላይም ከዚህ ቀደም ከነበሩት አጋር ድርጅቶች በተጨማሪ ሌሎች ተቋማትም አጋር ሆነው መምጣታቸው በመግለጫው ተጠቁሟል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You