ኃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ ምድጃዎች የፈጠረው ወጣት

ከልጅነቱ ጀምሮ እንስቶ የፈጠራ ሥራዎችን እየሞካከረ፣ እየተለማመድና እየሠራ አድጓል:: ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከገባም በኋላ የተፈጠረ አንድ አጋጣሚ ደግሞ የያኔ የፈጠራ ሃሳቡን የዛሬ ሥራውን አስፍቶ የሚመለከትበትን እድል ከፈተለት::

ይህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ60ሺህ በላይ ሰዎች በመተንፈሻ አካል ላይ በሚደርስ ችግር ምክንያት እንደሚሞቱ የሚያመላክት ሪፖርት ማንበቡ ነው:: ከዚህም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ከማገዶ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር ብክለት የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን ይረዳል::

የዚህ ችግር መፍትሔው በእጁ እንዳለ በወቅቱ የተሰማው የዛሬው የስኬት ገጽ እንግዳችን፣ ለችግሩ መፍትሔ ያለውን የኤሌክትሪክ ምድጃ እውን ወደ ማድረግ ገባ፤ ያሰበውን አሳካ። ይህ ባለስኬት ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮመካኒካል ኢንተርፕራይዝ መሥራችና ባለቤት ወጣት አብዲ መሉጌታ ነው::

አብዲ ወደዚህ ሥራ ለመግባት ያነሳሳውን ሃሳብ ያገኘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ተማሪ እያለ ነው። ችግሩ አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ መሆኑን ቀድሞውን ስለተረዳ ትምህርቱን እስኪጨርስ መጠበቅ አልፈለገም፤ ወዲያወኑ ሥራውን ለመጀመር በመወሰን ጥናት ወደ ማድረግ ገባ:: ጥናት ሲያደርግም የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም በማከለ መልኩ ተሠርተው ሁሉንም ሰው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ንጹህ የኤሌክትሪክ ምድጃዎች እንደሌሉ ይረዳል::

ይህንን በውስጡ ሲያሰላስል ቆይቶ ሙያውን ተጠቅሞ ችግሩን ለመቅረፍ በማሰብ ሥራውን በመጀመር የኤሌክትሪክ ማብሰያ ምድጃዎች ሰርቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በእጅጉ ጉጉት አደረበት::

‹‹በሀገሪቱ አነስተኛ ገቢ ያላቸውና ከሰል የሚጠቀሙ ሰዎች በቤት ውስጥ አየር ብክለት ስለሚጎዱ መተንፈሻ አካላቸው ላይ የጤና እክል ይገጥማቸዋል። በተለይ ቀደም ሲል የጠቀስኩን ጥናታዊ ጸሁፍ ካነበበኩ በኋላ ችግሩ ባጣም አሳሳቢ መሆኑ ስለገባገኝ ለመቅረፍ በማሰብ ንጹህ ምድጃዎች በማምረት ለተጠቃሚ ተደራሽ ለማድረግ ወሰንኩ ››ይላል::

ለሚሠራው የኤሌክትሪክ ምድጃ አስፈላጊውን ጥናት አድርጎ ካጠናቀቀ በኋላ ለሥራው የሚሆኑ ግብዓቶችንና መሥሪያ ቦታዎችን ካመቻቸ በኋላ በ2012ዓ.ም አብዲ ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮመካኒካል ኢንተርፕራይዝ የተሰኘ ድርጅት በመመሥረት ሥራውን ጀመረ::

አብዲ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ሥራውን አጠናክሮ በማስቀጠል ሳሪስ አካባቢ በትንሽ ቦታ ላይ ይሠራ የነበረውን ሥራ የበለጠ ለማስፋት በሚያስችለው አየር ጤና አካባቢ ምድጃውን ማምረቱን አጠናከረ::

በሦስት ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ሥራውን የጀመረው ይህ ባለስኬት፣ ንጹህ የማብሰያ ምድጃዎችን እያመረተ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማድረስ ሲጀምር ወርሃዊ ገቢው 150ሺህ ብር እንደነበርም ያስታውሳል:: ከዚያ ለተወሰኑ ዓመታት በዚሁ መንገድ ምድጃዎቹን እያመረተ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ሳለ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር /ኮይኮ/ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የአምስት ወራት ሥልጠና እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋል::

በሥልጠናው በሚደረግለት ድጋፍ በመታገዝ ለውጦችና መሻሻሎችን ማሳየት ቀጠለ:: ሥልጠናው በምርትም ሆነ በገቢ በአምስት እጥፍ እድገት በማስመዝገብ ከ12 ስታርትአፖች ተመርጦ አንደኛ በመውጣት እውቅናና የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቶለታል::

ከሥልጠናው በፊት ድርጅቱ በወር ያገኝ የነበረው ገቢ መጠን 150ሺህ ብር እንደነበር አስታውሶ፤ ከሥልጠናው በኋላ ደግሞ ይህ ገቢው 830ሺህ ብር መድረሱን ይገልጻል:: ‹‹ለአምስት ወራት የወሰደው ሥልጠናና የምክር አገልግሎት የሚያመርተውን ምድጃና ከዚህም የሚያገኘውን ገቢ ብቻ አይደለም ያሳደገለት:: ‹‹ቢዝነሳችንን በትክክለኛ መስመር እንድንመራ አስችሎናል›› በማለትም የሥልጠናውን ፋይዳ አስታውቋል:: ‹‹ብዙ ድጋፍና የማማከር አገልግሎቶች አግኝቼበታለሁ፤ ድርጅቱ ለውጦችን እንዲያመጣና እንዲሻሻል ያደረገውም ሥልጠናው ነው›› ይላል::

አብዲ እንደሚለው፤ ድርጅቱ ምድጃ ለማምረት‹‹ሀ››ብሎ ሥራ ሲጀምር ያለው አቅም ውስን በመሆኑ የምርቱም ብዛት በዚያው ልክ አነስተኛ ነበር:: በወር 10 ያህል የማብሰያ ምድጃዎችን ነበር የሚያመርተው:: ከሥልጠናው በኋላ ግን በመጀመሪያ በወር 92 የኤሌክትሪክ ማብሰያ ምድጃዎች ማምረት ችሏል:: የማምረት አቅሙ በየወሩ እየጨመረ መጥቶ ባለፈው ወር 613 ምድጃዎች ማምረት ገባ:: በአሁኑ ወቅትም ለ13 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል::

እነዚህን ሃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ ምድጃዎች በተለይ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እያቀረበ ነው፤ በአብዛኛውን በሴፍትኔት ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግሯል:: ከአዲስ አበባ ከተማ ወረዳዎች ጋር በመተባበር ምርቶቹን በማስተዋወቅ ምድጃዎቹን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድም ፈጥሯል:: ምርቶቹን ገዝተው የመጠቀም አቅም ለሌላቸው ሰዎች በሦስት ጊዜ ክፍያ ገዝተው እንዲጠቀሙበት እያደረገ መሆኑን ይጠቁማል::

ድርጅቱ ይህን ሥራ ቀደም ሲል ብቻውን ነበር የሚሠራው:: አሁን ላይ ደግሞ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር ይሠራል:: በዚህም ህብረተሰቡ ያለምንም ወለድ ምርቶቹን ገዝተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራል::

የኤሌክትሪክ ማብሰያ ምድጃዎቹ በዋጋም ቢሆን ተመጣጣኝና የህብረተሰቡን ኪስ የማይጎዱ ናቸው የሚለው አብዲ፤ ድርጅቱ አራት አይነት የኤሌክትሪክ ምድጃዎች እንዳሉትም ይገልጻል:: ባለአንድና ባለሁለት የኤሌክትሪክ ምድጃዎች ያሉት ሲሆን፤ ምድጃዎቹም ከውጭ የሚመጣውን የሚመስሉና በሸክላ ተሠርተውም በአማራጭነት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ናቸው::

በዋጋቸውም በኩል ባለአንድ ምድጃ በስምንት መቶ ሃምሳ ብር እንዲሁም ባለሁለቱ ምድጃ ደግሞ በአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ለገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ::

የኤሌክትሪክ ማብሰያ ምድጃው ጥራትና ደረጃ ከውጭ ከሚመጣው የሚያንስ እንዳልሆነ ይናገራል:: የምርቱ የጥራት ደረጃውም በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ተፈትሾ ደረጃ ሦስት አግኝቶ ሰርተፊኬት ተሰጥቶታል:: 54 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቆጥብ መሆኑንም ይገልጻል:: ይህም የሚጠቀመውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ሙቀት የመቀየር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻል::

ወጣት አብዲ እንደሚያብራራው፤ ድርጅቱ የካርበን ኬሬዲት ተጠቃሚ መሆንም ችሏል፤ በተሸጠው ምድጃ ቁጥር የሚቀንሰው ጋዝ መጠን ይታወቃል:: ይህም ድርጅቱ በሸጠው ምድጃ ልክ የሚቀንሰው በካይ ጋዝ ልቀት መጠን ስላለ የካርበን ልቀት የሚቀንሱ ምርቶችን በማምረት የተመዘገበ ነው::

የካርበን ልቀት ከመቀነስ አኳያ የካርበን ፋይናንሲንግ ተጠቃሚ ለመሆንም እየሠራ ነው:: በካይ ጋዝ ልቀት በመቀነስ ረገድ ተጠቃሚ ለመሆን የካርበን ፋይናንሲንግ ከጀመረ ሁለት ወራት ያህል ማስቆጠሩን ተናግሯል:: ይህንን በትክክል ተግባራዊ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል::

ድርጅቱ ወደፊት ሌሎች የማብሰያ ምድጃዎችን በማምረት ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የንጹህ ማብሰያ ምድጃ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረጉን ጥረት ለማጠናከር፣ ማቀዝቀዣ(ፍሬጅ)፣ ኦቨን፣ እና የመሳሰሉትን ከምርቶቹ መካከል ለማካተት እየሠራ መሆኑን ጠቁሟል:: በድርጅቱ የቢዝነስ ሞዴል ላይ ከታቀዱት ሥራዎች መካከል ምርቶቹን ለሴፍትኔት ተጠቃሚዎች ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ ነው:: ምርቶቹንም በተለምዶ እቃዎችን ባገለገሉ ልብሶች በመለወጥ ሥራ ‹‹ በሚታወቁት /ልዋጭ/ በኩል ለማቅረብ ማቀዱን ጠቁሟል::

ወጣት አብዲ አሁን ላይ በከተማው የተለያዩ እቃዎች በመለወጥ ሥራ ላይ የተሠማሩ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ጠቅሶ፤ የእሱ ምርቶችም ለእነዚህ ሰዎች ተጨማሪ የሥራ እድል ይፈጥራል የሚል እምነትም አድሮበታል፤ አቅም ለሌላቸው ሰዎችም በተለያዩ እቃዎች ለውጠው መጠቀም እንደሚችሉ አስታውቋል::

ይህም ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ህብረተሰቡ ሃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን የሚጠቀምበትን እድል ያሰፋል የሚል እምነት አድርቦታል:: ‹‹ይህንን መንገድ በመጠቀም ሥራችንን በደንብ ለማሳደግ አቅደን እየሠራን ነው:: ሥራው አዋጭ ከመሆኑም በላይ ምርቶቻችንን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ይረዳናል ብለን አስበን የገባንበት ነው ›› ይላል::

እነዚህ ምርቶች ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉት የሀገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ጠቅሶ፤ በተለይ አሁን ላይ በጅማና ባህርዳር ከተማ ላይ ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አመልክቷል:: በሌሎች ክልሎች ተደራሽ ለመሆንና በየዓመቱ ቢያንስ ሁለት ክልሎችን ለመድረስ አቅዶ እየሠራ ይገኛል::

በቀጣይም ድርጅቱ ምርቶቹን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለመሆን ከሚሠራው ሥራ ጎን ለጎን በተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ምርቶቹን እያመረተ ህብረተሰቡ ዘንድ እንዲደርሱ ለማድረግ እንደሚሠራ ይገልጻል::

በስታርትአፕ የድህረ ምህዳር የእውቅና ፕሮግራሙ አብዲ ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮመካኒካል ኢንተርፕራይዝ ላይ ስታርትአፖች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ እውቅናና ሽልማት የተበረከተለት ከመሆኑም በላይ ለቀጣዩ ፕሮግራም እንዲያልፉና የሁለት ወራት ተከታታይ ሥልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ ከተመረጡ ሁለቱ ስታርትአፖች በአንደኝነት ተመርጦ የ 10 ሺህ ዶላር የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል::

ይህንንም ሽልማት ድርጅቱ የተሟላ ማሽን ስለሌለው ከፍሎ በሌሎች አካላት በሚያሠራቸው ሥራዎች የተነሳ ለተጨማሪ የትራንስፖርትና የጊዜ ውጭ እየተዳረገ መሆኑን አመልክቶ፣ ማሽኖችን ገዝቶ ለማሟላት ማሰቡን ይገልፃል:: በተለይ እንደሲኤምሲ ፕላዝማ ከተር አይነት አስፈላጊ ማሽኖች ለመግዛት ሃሳብ እንዳለው ይገልጻል::

ሥራው ከጀመረ በኋላ ለሥራው እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለማግኘት ተግዳሮት ገጥሞት እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣት አብዲ፤ እነዚህ ግብዓቶች በተፈለገው ልክ ገበያ የማይገኙና ቢገኙም ደግሞ ዋጋቸው በየጊዜው ልዩነት ያለው መሆኑን ይገልጻል:: ጥራቱን የጠበቀ ግብዓት እንደሚፈለገው ገበያ ላይ ማግኘት የማይቻል መሆኑን ጠቅሶ፤ ከውጭ ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳጋጠማቸው ይናገራል::

ችግሩን ለመፍታት አስፈላጊ ሆኑ ግብዓቶችን ከውጭ ለማምጣት የሚያስችል ፍቃድ በማውጣት ለማምጣትም አቅዷል:: ከዚህም በተጨማሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ያመላክታል:: በተለይ የኤሌክትሪክ ማብሰያ ምድጃዎቹ ኃይል መጨመሪያና መቀነሻ መቆጣጠሪያ፣ ማብሪያና ማጥፊያ እና ኃይል የሚሰጠው አካል ከውጭ እንደሚመጡ ይገልጻል::

አብዲ ከትንሽ ተነስቶ አሁን ለደረሰበት ስኬት ለመብቃት ብዙ ጥረቶች ሲያደርግ እንደነበር አስታወሶ፤ የሚፈልጉበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ጥረት ማድረግን እንደሚጠይቅ ተናግሯል፤ ትግስት ሊኖር እንደሚገባም አስገንዝቧል።

ስታርትአፖች ወደፈጠራ ሥራ ሲገቡ በጣም ብዙ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉም ይናገራል:: የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዳሉ አውቀው ለችግሮች እጅ ሳይሰጡና ሳይበገሩ እየተጋፈጡ ሌሎች አቅጣጫዎች እየቀየሱ መጓዝ እንዳለባቸው መክሯል፤ ሁል ጊዜ መፍትሔ አለ ብሎ እንደሚያምን ይናገራል:: ስታርትአፖች ተስፋ ሳይቆርጡ ችግሮችን እየተጋፈጡ ወደፊት መገስገስ ከቻሉ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉም አመላክቷል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 1 2017 ዓ.ም

Recommended For You