
ነዋሪነታቸው በካናዳ ቶሮንቶ ነው። በፖለቲካ ባሕል ዙሪያ ሰፊ ጥናቶችን አድርገዋል፤ አሁንም እያደረጉ ነው። የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ ጣሊያን ቬኑስ አካዳሚ፣ ዩኒቨርሲቲ ፊንላድ ኦቦ አካዳሚ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ተምረዋል። የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ላይ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል ሰለሞን ኃይለማርያም (ዶ/ር)።
ሰለሞን (ዶ/ር) ጋዜጠኛ ሆነው አገልግለዋል። የፓኖስ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር፣ የፔን ኢትዮጵያ መሥራችና ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል።
«የበርት ሽልማት ለአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ» በተባለው ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የሥነ ጽሑፍ ውድድር ላይ ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከል ለውድድር ያቀረቡት «ዘያንግ ክሩሴደር» የተሰኘው መጽሐፍ አንደኛ በመውጣቱ በወቅቱ የ13ሺ ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል። በአሁን ወቅት ደግሞ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል አዙረዋል። ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ስላለው የልሂቃን የፖለቲካ ባሕል ምን ይመስላል የሚለውን ጉዳይ አንስተን ተወያይተናል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የልሂቃን የፖለቲካ ትርክት ሰላምና አንድነትን ከማምጣት አንጻር እንዴት ያዩታል?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- ትርክት በጊዜ ሂደት የሚገነባ ነው። ዘመን ሄዶ ሌላ ዘመን በተተካ ቁጥር አዲስ ትርክት ሲፈጠር ይታያል። በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ትርክት ቀስ በቀስ እየተገነባ በሂደት የሚመጣ ነው። ትርክት እንዳያያዙ ጠቃሚም ጎጂም ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ትርክት ክፍፍልን፤ አለመግባባትን፣ ቁርሾንና መነጣጠልን የሚፈጥር፤ ሀገረ መንግሥቱን፣ የሕዝቡን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነበር።
ከለውጡ በፊት የነበሩ ትርክቶች እንደ ሀገርም፤ እንደ ሕዝብም ተግባብቶ በአንድነት ሀገርን ለመገንባት ተግዳሮት የፈጠሩ ነበሩ። ከለውጡ በፊት የማያግባቡንን ትርክት እያቆሙ፣ በሚያለያየን፤ በሚያጋጨን ትርክት ላይ ትኩረት ተደርጎ ስለነበር ይሄ አሁን ለምናየው በየቦታው ላለው ግጭት መንስኤ ሆኗል።
ትርክት ሲባል የታሪክ ትርክት አለ። የፖለቲካ ሥርዓት ትርክት አለ እንዲሁም የአብሮ መኖር ትርክት አለ፤ ከእያንዳንዱ ዘውግ ለሚነሱ ለራሳቸው የሚሰጡት ትርክት አለ። እነዚህ ትርክቶች ናቸው ከውዝግብ አልፈው ግጭት የሚያመጡት።
ይሁን እንጂ የተለያየ ትርክት መኖሩ ክፋት የለውም። ነገር ግን ትርክቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ጎጂ የሆኑ ትርክቶች ለመማማሪያነት፣ ጠቃሚ የሆኑትን ደግሞ እንዲሰፉና እንዲጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄንን በምሳሌ ማንሳት ይቻላል። አንድን ወንዝ ትልቅ የሚያደርጉት የተለያዩ መጋቢ ወንዞች ስብስብ ነው። ወንዞቹ በራሳቸው መንገድ ይመጣሉ፤ ወንዙ አንድና ትልቅ ከሆነ በኋላ ደግሞ ጉዳት እንዳያደርስ ማሰላሰልና በተገቢው መንገድ ማስተዳደር ይገባል፤ ያስፈልጋል። ትርክቶችም እንደ ወንዝ ከተለያየ ቦታ ቢመጡም አንድ ላይ ሲሆኑ ግን መግባባት አለባቸው።
ከተለያየ አካባቢና አቅጣጫ የሚመጣውን ትርክት ሰብስቦ ያለፈውን ጊዜና ሥርዓቶች የሚመለከተውን ተምሮበት በማለፍ፤ አሁን ያሉትን የወል ትርክቶች ደግሞ አስፍቶ እና አጠንክሮ መጠቀም ያስፈልጋል። እንደ ሀገር ልንሠራ የሚገባውም የሀገራችን አንድነት በሚያጸና መግባባት፣ ሰላምና ብልፅግና በሚያረጋግጥ የወል ትርክት ላይ መሆን አለበት። አሁንም የወንዙን ምሳሌ ማንሳት ይገባል። አንድ ወንዝ በመጋቢ ወንዞች ጎልብቶና አቅሙን አጠናክሮ መጥቶ የደረሰበት ቦታ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደመጣህበት ተመለስ ማለት ይቻላል? ይሄ የማይሆን ነው። ስለዚህ የሚጠበቀው ነገር ጉዳት እንዳያደርስ አድርጎ ማስተዳደር ነው። ትርክትም ይሄው ነው። በአንድ ወቅት የሆነን ነገር ዛሬ እዚህ አምጥተን ለምን ሆነ ብንል ምንም ልናደርገው አንችልም። ለወደፊቱ ግን ግጭት በማይፈጥር መልኩ እንዴት ተስተካክሎ ሊሄድና ሁሉንም የሚያስማማ ሆኖ መቀጠል አለበት በሚለው ላይ ግን አተኩሮ መሥራት ይገባል፤ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የወል ትርክቶችን ወደፊት በማምጣት ረገድ ከፖለቲካ ልሂቃኑ ምን ይጠበቃል?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- በመሠረቱ ትርክት የሚፈጠረውም ሆነ የሚደረጀው በልሂቃን ነው። ልሂቃን ዋናዎቹ ተዋናይ ናቸው። ልሂቃኑ ብዙ ጊዜ ለራሳቸው መጠቀሚያ፤ ለግል ፍላጎታቸው ማስፈፀሚያ ስለሚያደርጉት ነው መሠረታዊ ችግር የሚሆነው። ከራሳቸው ፍላጎትና ስሜት አልፈው ስለማህበረሰቡ፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ሕዝብ ማሰብ ከጀመሩ ለውጥ ይመጣል፤ ትርክቱ ይስተካከላል። ስለዚህ ልሂቃን ከግል ፍላጎታቸው፣ ስሜታቸውና ጥቅማቸው ተሻግረው ስለሀገር እና ሕዝብ ማሰብ አለባቸው። ያን ጊዜ ነው ትርክት የሚስተካከለው፣ ሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት የሚሰማት።
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ትርክትን በሕዝቡ ውስጥ እንዴት ማካተት ይችላሉ ?
ሰለሞን(ዶ/ር)፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩት ሥልጣን ለመያዝ ነው። ሥልጣን ሲይዙ ሀገሪቱ ሰላም ከሌላት የእነሱ ወደ ሥልጣን መምጣት ምንም አይፈይድም። ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወል ትርክት ቢኖር የሚጠቅማቸው ለራሳቸው ነው። የፖለቲካ ፓርቲ የመጨረሻ ግቡ ሥልጣን መያዝ ነው። ሥልጣን ይዞ የተረጋጋና ሰላም ያለው ሀገር መምራት ሲችል ነው። ለዚህ ደግሞ የተሰናሰለ፣ የተስማማና የሚያግባባ ትርክት ሲኖር ነው። ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የወል ትርክቶችን ወደፊት ማምጣት ካልቻለ ነገ ሊመሩት የሚፈልጉትን ሀገር በሰላም መምራት አይችሉም፤ ሀገር ከሥልጣንም በላይ ነው። ስለዚህ ሀገር ሀገር ሆና እንድትቀጥል የሚያግባቡን ትርክቶች ወደፊት መምጣት መቻል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የጋራ ትርክቶችን ለመፍጠር ምን ዓይነት ስልቶችን መጠቀም ይቻላል ?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- የጋራ የሚያደርጉንን ትርክት ለመፍጠር ሁለት ዓይነት መንገድን መከተል ያስፈልጋል። አንደኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በጣም ወሳኝ ናቸው። ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ልጆችን እየኮተኮቱ ማምጣት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከላይ ያለው የማያግባባውን ትርክት ለማስተካከል የሚደረግ ጥረት ነው። እስካሁን ድረስ እላይ ያለው ትርክት ግጭት፤ አለመግባባትን ፈጥሯል። ጦርነትን ፈጥሯል። ኢትዮጵያን ወደ ኋላ አስቀርቷል። ስለዚህ ይሄንን ቆም ብሎ ማሰቢያው ጊዜ አሁን ነው፤ አሁን ጥሩ እድል፤ ጥሩ ሁኔታ ተፈጥሯል። ቆም ብሎ ሰው እንዲያስብ ሀገራዊ ምክክሩም፤ የሽግርር ፍትህ የሚባለውም ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሯል። የሽግግር ውይይት ችግሮቻችንን ማየት ያስፈልጋል። እነዚህ ሁለቱ የችግሮቻችን መፍቻ መሳሪያዎች ናቸው። ልሂቃኑም ቆም ብሎ ሊያስብበት የሚችልበት መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መገናኛ ብዙሃን የወል ትርክቶችን ለማስረጽ ምን ያህል ተጽዕኖ መፍጠር አለባቸው ?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- መገናኛ ብዙሃን በተቻለ መጠን ለማንም ሳይወግን የሁሉንም ድምጽ ማሰማት መቻል ይኖርባቸዋል ። ማንም ሰው ሀሳቤ ቀርቶብኛል ሳይል ሁሉም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚንጸባረቁ ሃሳቦች እንዲወጡና ሃሳቡ እንዲንሸራሸር ማድረግ ነው። ሕዝቡ በበቂ ሁኔታ ሃሳቡን እንዲያንሸራሽርና እንዲወስን ማድረግ ነው ትልቁ ዓላማ። ሚዲያው ተአማኒነት አግኝቶ ሲሠራ ኅብረተሰቡ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠሩ ደረጃው ከፍ ይላል። በተቻለ መጠን ሚዲያ የሁሉንም ማኅበረሰብ ድምጽ ማሰማት አለበት። አድሏዊ መሆን የለበትም። ለዚህም ሚዲያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት።
በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙሃን በጣም በስፋት ስለብሔራዊ መግባባት፣ ስለ ውይይት፣ ስለድርድር ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ናቸው። ስለጋራ ትርክት፣ ስለ ብሔራዊ ምክክር፣ ስለ ሽግግር ፍትህ ሀገራዊ አጀንዳው ወደፊት መጥቷል። ይሄ በጣም ጥሩ ነው። አሁን የሚቀረው ጉዳይ ዋና ዋና ሃሳቦች ነጥሮ እንዲወጡ ማድረግ ላይ ነው። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሏቸው ሃሳብና አጀንዳ ምንድን ናቸው ? የሚለውን ነጥቦች ጉልቶ ማውጣት ይቀረዋል። ይህም ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ታሪካዊ ትርክቶች ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ ?
ሰለሞን(ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ዋናውና ትልቁ የግጭት መንስኤ ታሪክ ነው። ለምሳሌ ያህል የጋራ ጀግኖቻችንን ሁሉም ሰው የጋራ ጀግኖች አያደርጋቸውም። ሁሉም የእኔ ጀግና ብሎ የሚያስበው አለው። የጋራ የሀገር የሆኑ ጀግኖችን በዘውግ ከፋፍሎ የእኔ የእኔ የሚል ስያሜ ውስጥ ገብተናል። ለምሳሌ አበበ በቂላን ሁሉም ሰው የእኛ ይለዋል። ይቀበለዋል። ጥላሁን ገሰሰን ብዙ ሰው የእኛ ነው ብሎ ያስባል። ልክ እንደነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ጀግኖችንም የእኛ ናቸው ብሎ መቀበል አለበት። የእኔ የሚለውን አስተሳሰብ ወደ እኛ መቀየር ማለት ነው።
እስካሁን ብዙ የማያግባቡን የኋላ ታሪኮች ናቸው። የኋላ ታሪኮችን ምን ማድረግ ይቻላል ? የፈሰሰ ውሃ እንደማለት ነው። የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም። በትርክታችንም የፈሰሰውን ውሃ መተውና ወደፊት ውሃው እንዳይፈስ አድርጎ መሄድ ላይ ማተኮር አለብን። ያለፉ ትርክቶችንም ሆነ ስህተት የነበረባቸውን ታሪኮች ወደፊት እያመጡ አሁን ላይ የመከራከሪያ ግብዓት ከማድረግ ይልቅ ከአሁን በኋላ ሁሉም ሰው የሚስማማበትን ታሪክ ፈጥሮ ወደፊት መሄድ ይበጃል።
ይሄ ታሪክ ሀገራችንን ከድህነት እናውጣ የሚል ነው። ሀገራችን ሁልጊዜ የድንቁርና የመሃይምነት፣ የድህነት፣ የረሀብ፣ የበሽታ ምልክት መሆን የለባትም። የእድገት፣ የብልፅግና የሰላም ዘመን እንዲመጣ ሁሉም ሰው አብሮ ተባብሮ ወደፊት እንዲሄድ መሥራት ይገባል። በሀገራችን ሰላም ይስፈን፣ ወጣቶቹ የሥራ ዕድል ይመቻችላቸው፤ እድገት ይምጣ፣ የተሻለ ኑሮ እንኑር የሚለው ሃሳብ ገዢ መሆን ይኖርበታል። ሁሉም ሰው ተስማምቶ ወደፊት መሄድ አለበት እንጂ ስላለፈው እያነሱ ‹‹እከሌ እንደዚህ አድርጓል፤ እከሌ እንደዚያ ፈጥሯል›› እየተባባሉ መጓተቱ ከግጭት በስተቀር ጠብ የሚያደርገው ጥቅም አይኖርም። ሀገርንም ወደ ኋላ ያስቀራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፖላራይዝድ ትርክቶች ምን አደጋ አላቸው ?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- ፖላራይዝድ ትርክት ጽንፍና ጽንፍ የያዘ ማለት ነው። ጽንፍ መያዝ አንዱ የሚመጣው ከትርክት ነው። ለምሳሌ የዛሬ 200 ዓመት አካባቢ የሆነውን ጉዳይ አንስቶ የአንድ አካባቢ መኳንንቶች የእገሌን ብሔር በድለዋል ብሎ በዛ ቂም መናቆር ምንም ፋይዳ የለውም። በእዛ ላይ ተመሥርቶ ጽንፍ መያዝ ማንንም የሚጠቅም አይደለም። የጽንፈኝነት መጨረሻው መለያየት ነው። ጽንፈኝነት ወደ መሀል የሚያስገባ ድልድይ ስለማይፈጥር መጨረሻው መለያየት ይሆናል። ጽንፍ የያዘ አካል ለውይይት አይጠቅምም፤ አንዴ ጥግ ይዟል ፤ ወደ መሀል ለመምጣት ይቸገራል። ቁጭ ብሎ ለመነጋገር ለመወያየትም አይመችም። ስለዚህ ጽንፈኝነት የጋራ ትርክት ለመፍጠር አንዱ ተግዳሮት ነው። ጽንፈኝነት ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካ ትርክቶችን ወደ መሀል አምጥቶ የጋራ ትርክት እንዲኖረን በማድረግ ረገድ የትምህርት ተቋማት ሚና ምን መሆን አለበት ብለው ያስባሉ ?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ትርክት የሚፈጠረው አንደኛ ከልጅነት ጀምሮ ነው። እኔ በምኖርበት ካናዳ ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ከሚማሩት አንዱ ስለንጽህና አጠባበቅ ነው። ቆሻሻ በየትኛውም ቦታ አይጣልም፤ የሚጣለው በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ነው ተብሎ ነው የሚነገራቸው እናም ምንም ዓይነት ቆሻሻ የሚጥሉት በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ነው።
እርስ በርስ መረዳዳት ፣ መከባበር የሚማሩት ከታችኛው ዕድሜያቸው ጀምሮ ነው። ሀገር መውደድ፣ መከባበር፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ በሀገራቸው ስላሉ ቋንቋዎች፣ የሀገሪቱ ዓላማ እና ዋና ዋና ጉዳዮች ምንድናቸው የሚለውን፤ በዕድገት በሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርቱ መጠን በየክፍላቸው ደረጃ እየሰፋና እየጠነከረ ይመጣል። ትርክትንም መፍጠር የሚቻለው ከዚህ ጀምሮ ነው። ይሄ እያደገ ሲመጣ ማህበረሰቡ እየተስተካከለ ይመጣል።
አዲስ ዘመን፤ የቋንቋ አካታችነት በፖለቲካ ትርክቶች ዙሪያ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያመጣል?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- የጋራ ትርክቶችን ለመፍጠር በመጀመሪያ ደረጃ መከባበር ያስፈልጋል። ለመከባበር ደግሞ የሰዎችን ባሕል፣ ልማድና ትውፊት ማክበር ያስፈልጋል። የሰዎች ባሕልና ትውፊት ሲከበር ቋንቋም አንዱና ዋነኛው ነው። እኔ የማምነው በዚህ ነው። የእኔ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባሕል ይሄ ነው ካለ ያንን ማክበር ያስፈልጋል። የአንድ ሰው ቋንቋ፣ ባሕል፣ ትውፊት፣ ሃይማኖት ካከበርን በዛ መካባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት ለመፍጠር አይከብድም።
ቋንቋ በመስማማትና በመግባባት የሚወሰን ነው። የሌላውንም ባሕልና ቋንቋ ሳያንቋሽሹ፤ የራስንም ከሌላው ሳያስበልጡ በተቻለ መጠን በስምምነት የሚፈጠር መሳሪያ ነው። የራሱ ባሕል ቋንቋ… እንዲከበርለት የሚፈልግ የሌላውንም በዛው ደረጃ ማክበር አለበት። ቋንቋ በሕገ – መንግሥቱ የሚወሰን ሲሆን ሕገ – መንግሥቱ በሁሉም ስምምነት የሚፈጠር ነው የሚሆነው። በቅድሚያ ውይይት እና እርስ በርስ መነገጋር ያስፈልጋል። ትርክት ላይ ሰዎች ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ መጀመሪያ መከባበር አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት፣ ያልጠሩ ትርክቶች፣ በደሎች… ለማስታረቅ ያለመ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፤ የዚህን ውጤታማነት እንዴት ያዩታል ?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- የሽግግር ፍትህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቋቋም አሁን አዲስ ነገር አይደለም። ከዚህ በፊትም ኃይለሥላሴ ሲወድቁ ደርግ የምርመራ ኮሚሽን ብሎ አቋቁሞ ነበር። የጃንሆይ ሚንስትሮችን ለመመርመር ሙከራም ተደርጓል። ሆኖም ግን በአንድ ምሸት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሚኒስትሮች ገድሏቸዋል። ስለዚህ ራሱ ፍትሁን ሰጥቷል ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ የሽግግር ፍትህ የሕዝብ ግንኙነት እንጂ ትርጉም ያለው የሽግግር ፍትህ አልነበረም። ሚንስትሮቹ ሲገደሉ የሽግግር ፍትሁም አብሮ ተገደለ፤ ቆመ።
እንዲሁም በ1983 ዓ.ም ደግሞ ሕወሓት ሥልጣን ሲይዝ በደርግ ባለሥልጣኖች ላይ ምርመራ ማድረግ ተጀምሮ ነበር። እነሱም በፍርድ እንዲዳኙ ተሞክሯል። ያ ደግሞ በጣም የዘገየ ለረጅም ዓመታት የምርመራና የፍትህ ሂደቱ የተጓተተ ስለነበር ብዙዎቹ በማረሚያ ቤት ምንም በፍርድ ሳይፈረድባቸው ሞተዋል። የዘገየ ፍርድ እንዳልተፈረደ ይቆጠራል እንደሚባለው የደርግ ባለሥልጣናት ፍርድ ሳያገኙ ነው የሞቱት። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ እንደ ብቀላ ነው የሚቆጠረው።
አሁን ለሶስተኛ ጊዜ እድሉ ተገኝቷል። የሽግግር ፍትህ የሚባለው ያለፈውን በደል፤ ያለፈውን ቁስል አሽሮ እና ክሶ ወደፊት ለመራመድ ነው። ተበድያለሁ ያለ ሰው ቂም እንዳይዝ ለማድረግ ነው። የፍትሁ ዋና ዓላማም ልሂቃኑ ቂም ሳይዙ ወደፊት እንዲሄዱ ያለፈውን በመካስ፤ አጥፊውን ደግሞ ተመጣጣኝ ፍርድ በመስጠት ሊሆን ይችላል፤ ያለፈውን ክሶ፣ አክሞና አድኖ ወደፊት መሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሽግግር ፍትህ በዓለም ላይ ውጤት ያመጣባቸው ሀገሮች አሉ ?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- የሽግግር ፍትህ በእውነተኝነትና በፖለቲካ ቁርጠኝነት ከተተገበረ ውጤታማ ነው። የዓለም ተሞክሮም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው። ነገር ግን የመንግሥት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። የመንግሥት ባለሥልጣን የሆነ ሰው በማስረጃና በመረጃ ተደግፎ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ አሳልፎ መስጠትን ይጠይቃል፤ ለዚህ መንግሥት ፈቃደኛና ቁርጠኛ መሆን አለበት። ኅብረተሰቡ በደሉን ምንም ሳያስቀር ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ ከሆነ እና እውነት ነው ተገቢ ነው ብሎ ካመነ ፍትሁ ውጤታማ ይሆናል።
ይሄ በብዙ ሀገሮች ተሞክሯል። ውጤቱንም ሆነ ጉዳዩን ዓለም ላይ ከታየው ጋር አንድ ዓይነት ይሆናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ምክንያቱም በሴራሊዩን፣ በዑጋንዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በጋምቢያ፤ በላይቤሪያ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፤ በቺሊ ወይም በሌሎች ላይ የተፈጸመውን ነገር አምጥቶ ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ቀይ ሽብር ተካሂዷል። በሌላው ሀገር ግን ይሄ አልተካሄደም። ስለዚህ ለሁለቱ ሀገሮች የሚሰጠው የሽግግር ፍትህ አንድ ዓይነት ሊሆን አይችልም። የራሳችንን ሀገር ታሪክ የራሳችንን የፖለቲካ አካሄድ መገምገም ተገቢ ነው። የሌሎችን ሀገሮች ተሞክሮ አምጥቶ እንዳለ እንተግብረው ብሎ ማሰብ ይከብዳል፤ ውጤታማም አያደርግም። በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ ሀገሮች ምንም የምንቀስመው ልምድ የለም ብሎ ማሰብ ደግሞ አይቻልም። ከእነሱ የምንማረው በእውነተኛነትና በቁርጠኝነት ከተሠራ ውጤታማ መሆን እንደሚችል ነው።
የሽግግር ፍትህ ውጤታማነት የሚለካው ማኅበረሰቡ በሚወስነው ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ፍርድ ሲፈረድ ፍርዱ ትክክል ነው፤ ፍትሃዊ ነው ከተባለ የተፈረደለት ወገን ደስ ይለዋል፤ ሌላው ቀርቶ የተፈረደበትም ራሱ ልክ ነው፤ ይገባኛል የሚልበት አካሄድ መፈጠር አለበት። ምንም ዓይነት ነገር ወደ ውስጥ መቅረት የለበትም።
ሆኖም ግን በሽግግር ፍትህ ውስጥ ሁሉንም ነገሮች ማየት አይቻልም። ተበድያለሁ፤ እንደዚህ ዓይነት ጉዳት ደርሶብኛል ብሎ ማኅበረሰቡ የሚከነክነውን ጉዳይ ሁሉ ለመወሰን አቅም ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል የተበደሉ ወገኖች ይካሱ ቢባል ብዙ ሰው መካስ ይፈልጋል። ሁሉንም ሰው ደግሞ መካስ አይቻልም። ስለዚህ ዋና ዋና ጉዳዮችን አንስቶ መፍትሔ መስጠት ይቻላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፤ ከሁለት ክልል ውጭ በሁሉም ክልሎች ላይ አጀንዳ የመለየት ሥራ ተሠርቷል። ይሄ ምን ያህል ውጤታማ ያደርገዋል?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- ብሔራዊ ምክክር በብዙ ሀገሮች ተሞክሮ ውጤታማ የሆነበት ቦታ አለ፤ ውጤታማ ያልሆነበትም አለ። ውጤታማ በሆነበት ቦታ ላይ የሚያመለክተው አንደኛ ብሔራዊ መግባባት አሳታፊ ሲሆን ነው። ሁለተኛ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን ሲችል ነው፤ ሶስተኛ የኮሚሽኑ አባላት ነፃ ሲሆኑና በሕዝብ ያላቸው ተቀባይነት ሙሉ ሲሆን ነው። እንዲሁም ግልጸኝነት መኖሩና በጣም ትልልቅ አጀንዳዎች ማንሳት መቻሉ ነው። ትልልቅ አጀንዳዎች ማንሳቱ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ጉዳይ ያላቸው ሁሉ ጉዳያቸው መካተቱ፣ ሁሉም ሃሳቡን ያንጸባረቀበት ከሆነ፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ካለ እንዲሁም የውጭ ጣልቃ ገብነት ከሌለ ውጤታማ ይሆናል። በኢትዮጵያም ይህንኑ አካሄድ ከተከተልን ውጤታማ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- የሀገራችን የፖለቲካ ባሕል እርስዎ ካደረጉት ጥናት በመነሳት ምን ይመስላል ?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- የፖለቲካ ባሕል በሶስት ይከፈላል። አንደኛው የልሂቃን የፖለቲካ ባሕል ነው። ሁለተኛው የተቋማት የፖለቲካ ባሕል ነው። ሶስተኛው የሕዝቡ የፖለቲካ ባሕል ነው። ከእነዚህ ውስጥ እኔ ያጠናሁት የልሂቃን የፖለቲካ ባሕል ላይ ነው። የልሂቃን የፖለቲካ ባሕል ስንል መጀመሪያ ባሕልን ማየት ይገባል። ባሕል አብሮን የሚወለድ አይደለም። ባሕል የወረስነው ወይም የፈጠርነው፤ የተማርነውና በሂደት ያገኘነው ነው።
ይሄ ማለት ቀስ በቀስ በአእምሯችን የፈጠርነው ስለሆነ ሊቀየር ይችላል ማለት ነው። የኢትዮጵያ የልሂቃን የፖለቲካ ባሕል ጽንፈኝነት ላይ የተንጠለጠለ ነው። ብዙዎቹ ለመደራደር ፈቃደኛ አይሆኑም፣ ትልልቅ ነገሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ጦርነትን እንደ መፍትሔ የሚቆጥሩ ናቸው።
ልሂቃኑ ጦርነት አምላኪዎች ናቸው። እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን፣ ‹‹እኔ ትክክል ነኝ ሌሎች ትክክል አይደሉም›› ብለው የሚያስቡ ናቸው። ሌላው ደግሞ የዜሮ ድምር አለ። ሁሉም ነገር ለእኔ ነው የሚገባኝ የሚል አስተሳሰብ። ለምሳሌ «ይሄ የእኔ ነው ፤ ያኛው ደግሞ የእኛ ነው፡፡» ይላል። ይሄ ማለት እዚህም እዛም ላይ ድርሻ አለኝ ብሎ ማሰብ ነው። የጋራችን ነው የሚል አስተሳሰብ የለም። ይሄ ትልቁ ችግር ነው። እንዲሁም የጋራ ጀግና የላቸውም። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ሁሉም የራሱን ታሪክ በመምዘዝ በአንድ ዓይነት ታሪክ ላይ አለመግባባት፤ እና የተለያየ ታሪክ መተረክ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። በአንድ ሀገር በአንድ ጉዳይ ላይ አራት አምስት ታሪክ ሊኖር አይችልም። ልሂቃኑ በአብዛኛው ከሀገር ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው ለግል ጥቅማቸው ነው ትኩረት የሚሰጡት። በጥላቻና በንቀት ላይ ተመስርተው ነው ሃሳባቸውን ማስረጽ የሚፈልጉት፤ መከባበር የለም። ብዙዎቹ ልሂቃን በመስማማት በመከባበር በሙሉ መረጃ ተመስርተው ሳይሆን ቁርሾ ይዘው ነው ወደ ውይይት የሚሄዱት።
አሁን የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በልሂቃኑ እጅ ላይ ወድቋል። እናም ልሂቃኑ የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ሊያስተካክሉ መልካም ሊያደርጉና ሊያሻሽሉ ይችላሉ። የኢትዮጵያን እጣ ፈንታም ሊያጨልሙ እና የግጭት አዙሪት እንዲቀጥል ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለዚህ ልሂቃኑ በሀገር ጉዳይ ላይ ቆም ብሎ ማሰቢያው ወቅት አሁን ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- መፍትሄው ምን ይሁን?
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- መፍትሄው ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ነው። ያለፉ ታሪኮችን ትቶ አዲስ ታሪክ አብሮ መፍጠር ሲሆን ሌላው ደግሞ የሽግግር ፍትህን መሠረት በማድረግ ተበድያለሁ ተጎድቻለሁ የሚለውን በመካስና በደሉን በማከም ወደፊት መሄድ መቻል ብቻ ነው መፍትሔው። ይህ ሲሆን ችግሮቻችን በሙሉ መፍትሔ ያገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ሰለሞን (ዶ/ር)፡- እኔም ስለሰጣችሁኝ እድል አመሰግናለሁ።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም