ኢትዮጵያ እንኳን ተወልዶ እትብቱ ከአፈሯ ተቀብሮ ደሙ ከስሯ ተመዝዞ ይቅርና ውሃዋን የቀመሰ፣ አፈሯ ጫማውን የነካው ሁሉ በፍቅር የሚከንፍላት አገር ናት። በፍቅር እንደሚሞካሹት እንደነ ፈረንሳይ፣ በኪነ ህንጻ እንደደመቁት የዓረብ ከተሞች፤ እንደፈላስፎቹ አገራት እና እንደሌሎቹ በዓለም መድረክ ስሟ ይጠራበት እልፍ ምክንያት አላት። ይህ ሆኗል ወይ? ደፍረን «አዎን ሆኗል» ወይም «ጭራሽ አልሆነም» አንልም።
በራሷ ስልጣኔ፣ በራሷ ሕዝብ ልበ ሙሉነት፣ የማንነት ክብርና እምነት ዓለም አድንቆ የተመለከታት ዘመን ግን ብዙ ነው። የዓድዋ ድል፣ የራሷ ፊደል፣ ከቋንቋ የዘለለ የባህል ብዝሃነት እና ሌሎችም አጉልተው አሳይተዋታል። ተፈጥሮም አድልታለች፤ የዓባይ ምንጭ የኤርታሌ ምድር፤ የሉሲ አገር አድርጋታለችና።
ኢትዮጵያ በሊቃውንቷ፣ በነገስታቷ ምክንያት እጅ የተነሳችበትና በዓለም መድረክ ከፍ ብላ የታየችበት ዘመን አለ። በአንጻሩ ድርቅ አጎሳቁሏት የረሀብ ምሳሌ ሆና ቀርባ ታውቃለች። ፈገግ የሚያሰኛት ትዝታ እንዲሁም አንገቷን አስደፍቶ የሚያስነባ ሀዘንን ቀምሳለች፤ በዘመናት መካከልም መውጣትና መውረድን አይታለች። ይህን ሁሉ በልቡና በጫንቃው የተሸከመ ሕዝቧ፤ ቀለሟን ወስዶ ቀለሙንም አልብሷት፤ ባህሏን ተረክቦ ባህሉን አቀብሏት ዘመናትን ተሻግራለች።
የምንወደው ባህል
ባህል ሰዎች ተስማምተውና በጋራ ለመኖር ይሆነናል ብለው በዘመናት ውስጥ የተሻገሩበትና ያሻገሩት ልምድ ነው። በአለባበስ፣ በአመጋገብ፣ በአኗኗር፣ ስሜትን በመግለጫ፣ ከሌሎች ጋር በሚኖር ትስስርና ዝምድና እንዲሁም በሌላ በብዙ መልኩ ይህ ባህል ይገለጻል። በእርግጥ የተለያዩ ምሁራን ለባህል የተለያየ ትርጓሜ ሰጥተውት እናያለን። ሁሉንም የሚያስማማው አንድ ነገር ግን አለ፤ ሁሉም ባህል በራሱ ውብ መሆኑ። ይህ ውበት ደግሞ አንድ ዓይነት ሳይሆን አንድ በመሆን ይደምቃል።
ብዙ የሚባልና በብዝሃነት የደመቀ ባህል የሌላቸው አንዳንድ የዓለም አገራት፤ በየጊዜው አዳዲስ ባህሎችን ፈጥረው በዛ ውስጥ የሚገኘውን አንድነት ሲያጣጥሙ እናያለን። ለምሳሌ ምስጋና መስጫ ቀን /Thanks giving/፣ በተለያዩ አልባሳት የመድመቅ ቀን /Halloween/ ወዘተ እያሉም የራሳቸውን መልክና ቀለም ሠርተው አሳይተዋል። ወደ አፍሪካ ምድር በመጡ ጊዜም በሚያዩት ባህል የሚደነቁት ስለዛ ነው።
በአንጻሩ ያላቸውን ታሪክና ባህል አጉልተውና አድምቀው ለማስተዋወቅ የሚደክሙ፤ በዛም የሚሳካላቸው እንደ ቻይና እና ህንድ ያሉ አገራት አሉ። ከእነዚህ ተሻግረን ወደ አገራችን ስንመለከት፤ ኢትዮጵያ አንድ ባህል የላትም፤ የአንድነት ባህል ግን አላት። ብዙ የታወቁ እንዲሁም ገና ሊመረመሩ የሚገባቸው ባህሎች ባለቤት ናት። እንዲህ እንደ ትላንትናውና እንዳለፉት ቀናት የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ስናነሳም፤ የባህል ብዝሃነትን እንመለከታለን። ይህንን ደግሞ የማይወደው የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ/ፒ.ኤች.ዲ/ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተገኝተው ኢትዮጵያውያንን በአነጋገሩባቸው መድረኮች የኢትዮጵያን ክብርና የሕዝቧን ታላቅነት ሳያነሱ አያልፉም። አንድ ጊዜም እንዲህ ያለ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፤ ይህም ልክ ባህሉንና ጭፈራውን ሁሉም ወድዶ በጋራ እንደሚጨፍረው ሁሉ እርስ በእርስ መዋደዱም በዛው ልክ እንዲሆን የጠየቁበት ነው።
አዎን! ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ባህላቸውን ይወዳሉ፤ እንወዳለን። በሰርግ፣ በተለያየ ድግስና ተሰብስበን በተገኘንበት «ተነሱ እንጂ ጨፍሩ» ሲባል፤ ሁሉም ሰው ሁሉንም ዓይነት ጭፈራ ችሎ አብሮ ይወዛወዛል። ምግቡ ቢቀርብለትም ደስ ብሎት ይበላል፤ አልባሳቱን ያደንቃል። ታድያ ይህ ባህልን መውደድ እንዴት ወደ እርስ በእርስም አጥብቆ መዋደድ አላመራም? ይህን እንድንጠይቅ የሚያደርገን በአንጻሩ አሁን በአገራችን እየሆነ ያለው ክስተት ነው።
የብሔር ግጭቶችንና ግለኝነትን ዜና በብዛት እየሰማን እንገኛለን። በኢትዮጵያውያን ባህል ደግሞ ክፋት አስቦ የመጣ ወራሪ እንኳ ቢማረክ፤ አቅም የለውም ተብሎ በይቅርታ ይሸኛል እንጂ በምን ተዓምር ዘር ቆጥሮ ወገን በወገኑ፤ ወንድም በወንድሙ ላይ እጁን በክፋት ያነሳል?
ባህላችን እና እኛ
የኢትዮጵያውያን ባህል መከባበርን፣ መዋደድንና አንድነትን ያስቀደመ መሆኑ ይታወቃል። አሁን ያለው ሁኔታ ግን እንግዳ ሲመጣ ወይም ጭቅጭቅ ሲነሳ «ወደ ጓዳ ግባ» እንደሚባል ህጻን ልጅ፤ ባህል ከውስጥ ተቆልፎበት እንዳይሰማና እንዳይናገር የተደረገ፤ አልያም «ወደ ውጪ ውጣ» ተብሎ እንደማያገባው ሁሉ አስተያየት እንዳይሰጥ የተገደበ ይመስላል።
አቶ እሽቱ ማሞ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆኑ፤ 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ ነው ያገኘናቸው። ከደረቡት ካባ እንዲሁም ካደረጉት ቆብ በላይ ዕድሜ የደፋባቸው ጥጥ የመሰለ ነጭ የሽበት ዘውድ፤ አባትነታቸውን ያሳብቃል። «በዓሉ እጅግ በጣም ማራኪና ጥሩ ነው፤ መከበሩም እጅግ በጣም ያስደስተናል» ሲሉ ጀመሩ።
«ኢትዮጵያ ዓለም ሳይሰለጥን የሰለጠነችና የተመሰረተች፤ ቀድማ የተገኘች አገር ናት። እንዲሁም የሰላም አገርና ሐዋርያም ናት። ኢትዮጵያውያን ለዳር ድንበራቸው ሲሉ እኔ ልቅደም ብለው ይዋጋሉ እንጂ እርስ በእርስ አሁን እንደምንሰማው አይሆኑም።» አሉ። ኢትዮጵያ የሚያኮራና የሚያስከብር ባህልና ውበት ያላት ቢሆንም፤ አሁን ላይ እየሆነ ያለው የእርስ በእርስ ግጭት ግን አባቶችን እያስከፋ መሆኑንም አያይዘው ጠቅሰዋል።
የምንወደውን ባህል እርስ በእርስ ግን አልተዋደድንበትም፤ ይህ አሁን ላይ በግልጽ የሚታይ ነው። ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው ምን ሊሆን ይችላል ለሚለውም ምሁራን ምንም ዓይነት አስተያየት ሲሰጡ አይታይም። የምታውቀው ምንጭ እያለ ከማታውቀው ወንዝ ውሃ እንድትቀዳ እንደተላከች ኮረዳ፤ መፍትሄውን ከምናውቀው ባህል ሳይሆን ከማናውቀው የሌላ ዓለም ጥናትና ወረቀት እየፈለግን ነው።
ለምን አልተዋደድንም?
ሰዎች እርስ በእርስ የሚጋጩበት ብዙ ምክንያት አላቸው፤ እንደሚገናኙበት አውድም ይወሰናል። እረኞች የሚጠብቋቸው በጎችና ከብቶች ከሰው ማሳ ሲገቡባቸው ከማሳው ባለቤት ጋር ይጋጫሉ። ልጆች «መጫወቻዬን ቀማሽኝ» በሚል ሰበብ ይኮራረፋሉ፣ ባለትዳሮች፣ እህትና ወንድም፣ ቤተሰብ፣ ጓደኛማቾች፣ የሥራ ባልደረቦች፤
ተሳፋሪና ረዳት ወይም ረዳትና አሽከርካሪ ጸብ በየቦታው አለ። ይህ ችግር አይደለም፤ ከብሂላችንስ «እግርና እግርም ይጋጫል!» እንል የለ? የሚከፋው ቂም መያያዙ ነው። ከዛም አልፎ ግጭቱን ከመነሻው ነጥሎ ከሌሎች ጉዳዮችም ጋር ማያያዝ ሲከተል ክፋቱ ይበረታል።
በአገራችን እየታየ ያለው ግጭት እንደዛ ነው፤ እንደውም ግለኝነት ከመስፋፋቱ የተነሳ «የእኔ ወገን ነው» በሚል ሰበብ ብቻ ጥፋት ያጠፋውንም ሳይቀር የሚደግፉና በርታ የሚሉትን እናያለን/እኛም እንደዛው እንላለን። ያልተዋደድነው እንድንጠላላ ሆነን ተፈጥረን ሳይሆን፤ ባህላችን ላይ በር ስለቆለፍንበት ነው። በአንድ ዘመን ሞትኩልሽ፣ አበድኩልሽ ያላትን ሴት ዓይንሽን ለአፈር ብሎ ለፍቺ ፍርድ ቤት እንደሚያቆም ባል፤ ባልተስማማ ንባቸው ሃሳቦች ምክንያት ውበታችንን እንዳናይ ተከልለናል። መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የመከባበር፣ የመዋደድና የግጭት አፈታት ባህላችን ላይ ስንሠራ ብቻ ነው።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን – እንድንዋደድ
እንደሚታወቀው 13ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ትላንት በድምቀት ተከብሯል። ትላንት በድመቀት ይከበር እንጂ፤ ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናትም የተለያዩ መርሃ ግብራት ለበዓሉ መግቢያ ሲከናወኑ ነበር። ከእነዛ ዝግጅቶች መካከል የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ ያዘጋጀው አንዱ ነው። በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፤ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሠራተኞች እንዲሁም የቴአትር ቤቱ ሰዎች በተገኙበት ዝግጅቱ በድምቀት ተከውኗል።
በቦታው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልዩ ቤተመጻሕፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከሆኑት ፍጹም አባተ /ፒ.ኤች.ዲ/ ጋር ተገናኘን። እርሳቸውም የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የኢትዮጵያ ቀን ማለት እንደሆነ ደመቅ አድርገው ገለጹ። እንዲህም አሉ «የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የኢትዮጵያ ቀን ማለት ነው። ከዚሁ ጋር ብዝሃነትና አንድነት የሚለውን ቃል አያይዘን እናነሳለን። ብዝሃነትም ልዩነት አይደለም»
ሁሉም ልብ ሊለውና መታወስ አለበት ያሉትንም ሃሳብ ሲያነሱ፤ ብዝሃነት በባህል ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብ፣ በእምነትና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎችም በርካታ ነጥቦች ሊገለጽ ይችላል። ይህንንም ልዩነት ማለት አግባብ እንዳይደለ ይጠቅሳሉ። «ብዝሃነት /Diversity/ የሚለው ቃል ልዩነት ማለት አይደለም። ልዩነት የሚለው ቃል ብዙ አንድምታ ስለሚኖረው ይህን ቃል ባንጠቀም መልካም ነው» ሲሉም አብራሩ።
የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዚህ እሳቤና መንፈስ ማክበር፤ ብዝሃነትንና አንድነትን ወደ መቀበል ያሸጋግራል። ይህም ወደምንፈለገው አንዲት ኢትዮጵያ ይመራናል ባይ ናቸው። እዚህ ላይ ታድያ የምሁራንን ሚና እንዲሁም የፖለቲከኞችን አድማጭነት አስፈላጊነት ያነሳሉ።
«አሁን ላይ የምሁራን ሚና በሰነዶች ውስጥ ሳሳ ብሏል። ለምንፈልገው አንድነት ምሁራን ትልቅ ሚና አላቸው። ፖለቲከኞችም ምሁራንን ማዳመጥ አለባቸው። ካዳመጡ ነውጥና ሁከት አይኖርም ነበር።» ያሉት ዶክተር ፍጹም፤ የሃይማኖት አባቶችም የሚኖራቸውንና ያላቸውን ትልቅ ሚና ሳይጠቅሱ አላለፉም። ምሁራን በቀለም ትምህርት ተደግፈው ዲግሪ የያዙቱ ብቻ አይደሉም፤ «ምሁራን በየአካባቢው ዕድር ውስጥም አሉ።» ነው ያሉት። እናም እነርሱ መሰማት አለባቸው። እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር ግን ለአንድነት ቀዳሚውና ብቸኛው አማራጭ ብዝሃነት መሆኑን ሁሉም ሊረዳ ይገባል ብለዋል።
መለስ ላድርጋችሁ፤ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን እንደ ኢትዮጵያ ቀን መጠቀም፤ ለአንድ ቀን ብቻም ሳይሆን በየእለቱም ወደዛ በሚያመራ መልኩ መንቀሳቀስ ወደ መዋደድ ይመልሰናል። «ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን ይወዳሉ» ብቻ ሳይሆን፤ «ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸውም ይዋደዳሉ» እንዲባል፤ እንደዛም እንዲሆን የሁሉም ጥረት አስፈላጊ መሆኑ አያጠራጥርም።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበርም፤ ፖለቲካዊ መልክ ሳይሆን የባህል ቀን እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ባህልም ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲተርፍ፤ አልፎም «እዚህ አልተጠራህም!» ተብሎ በር ካልተዘጋበት፤ እረፍት የሚሰጥ መፍትሄ መድኃኒት እንደሚሰጥ ይታወቃል። ይህን ለማረጋገጥ ከወራት በፊት የጋሞ አባቶች የሠሩትን ማየት ብቻ በቂ ነው። ይህም ነው አሁንም በአገራችን ተስፋ እንዳንቆርጥ አድርጎ ማንነታችን በሚገኝበት ባህላችን ወደ ቀደመ ክብራችን እንደምንመለስ ሹክ የሚለን።
ለዚህም በባህል ዘርፍ የሚሠሩ ባለሙያዎች ከደመወዝ የበለጠ ክፍያ ያለው ሥራን እንደሚሠሩ ልብ ሊሉ ይገባል። ተንበርክከው ስለአገር ሰላም ልጆቻቸውን እንደለመኑት እናቶች፤ ሰሚ ወጣቶች አሉና ያለመታከት ሁሌም መንገርና ማሳወቅ ይገባል። ሰዎች ተጣልተው ሲሰዳደቡ አንዱን አብርዶ ነገሩን ለማረጋጋት ስንፈልግ ተው የምንለው አንድ ነገር አለ፤ «አንተኮ ትልቅ ሰው ነህ! አንቺኮ እናት ነሽ! ክፉ ነገር አትናገሩ እንጂ!» እንላለን። የሰውን ክብሩንና ማንነቱን ማስታወስ ከራሱ ጋር አስታርቆ ያነቃዋልና፤ ባህል ላይ በዚህ መልክ መንቀሳቀስና መንቃት ከሁሉም ይጠበቃል።
የአገር ፍቅር መድረክ
ስለባህል አንስተናል፤ ስለብሔር ብሔረሰቦች ቀንም አውስተናል። ከመቋጨታችን በፊት በጥቂት አንቀጾች የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከተከበረባቸው መድረኮች መካከል የአገር ፍቅር ቴአትር ቤትን መድረክ እንድንዳስሰው ወደድን። ባሳለፍነው ሐሙስ ህዳር 27 ቀን 2011ዓ.ም ነው። የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ ውስጥ አንድ ግሩም የሆነ ሙዚቃዊ ቴአትር ቀርቦ ነበር።
የቴአትሩ ደራሲ ዘላለም ጌትነት ሲሆን፤ በአዘጋጅነት ሜካኤል ህጻነወልድ እና አንዷለም ደጀኔ ተሳትፈውበታል። በመድረክ ላይ ሰላሳ አምስት ደቂቃ ቆይታ ያለው ይኸው ቴአትር ከስልሳ እስከ ሰባ የሚደርሱ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ነው። ሙዚቀኞች፣ ተወዛዋዦችና ተዋንያን ይገኙበታል።
ሙዚቃዊ ቴአትሩን በዚህ በባህል ዓምድ ልንዳስስ የወደድነው አንደኛ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን በመሆኑ ነው። ከዛም በተጓዳኝ ባህልንና ኢትዮጵያዊነትን መሰረት አድርጓልና፤ አቀራረቡም ማራኪ ሆኖ መገኘቱን ልብ ይሏል።
ቴአትሩ ሲጀምር መድረኩ ላይ ብርሃን ብቻ እንጂ ተዋንያን አይታዩም፤ ተዋንያኑ የሚወጡትም ከታዳሚው መካከል ነው። ቃል በቃል ባልይዘውም፤ ወደመድረክ ሲወጡ እንዲህ የሚል ሃሳብን መነሻ አድርገው ነው። «ቴአትሩ ይጀመራል ከተባለ ስንት ሰዓት አለፈ? ለምን እኛ ራሳችን አንሠራውም? ስለኢትዮጵያ አይደለ የሚሠሩት? ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያን ማሳየት አይከብደንም። በሃሳቡ የምትስማሙ ተከተሉን» ይላሉ።
በመጀመሪያ ትዕይንት እንዲህ ብለው የሚወጡት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት የለበሱ ወጣቶች ናቸው። በአንድ ዜማ በተቃኘ አገርኛ ሙዚቃም የየብሔሩን ውዝዋዜ፤ የሕዝቡን መተሳሰብ፣ ፍቅር፣ አንድነትና መተባበርን በምሳሌነት ያሳያሉ። ከዚህ በኋላ ዳግም ከታዳምያን መካከል ሌላ ድምጽ ይሰማል፤ «ይህ ኢትዮጵያን አይገልጽም» የሚል።
የቀደሙትም ከታዳሚው መካከል ወጥተው ነበርና የሠሩት፤ ተከታዮቹም፤ «እናንተ በትክክል ኢትዮጵያን አላሳያችሁም። ቴአትረኞቹ ቢኖሩ ኖሮ ይስቁባችሁ ነበር። ኢትዮጵያ ሰዎች እርስ በእርስ የሚጋደሉባት፣ መከባበርና መዋደድ ድሮ የቀረባት፣ በብሔር ግጭት ሰዎች የሚተላለቁባት አገር ናት» ሲሉም ያንን በሙዚቃዊ እንቅስቃሴዎች አሳምረው ያሳያሉ።
በዚህ ሁለት ሃሳብ መካከል «እኔ ነኝ ትክክል!» በሚል ሁለቱ ሃሳቦች በእነዚህ ተዋንያን ምክንያት ይነታረካሉ። በመካከልም ሃሳብና ቡድን የቀየሩትን «የእኔ ነው» እያሉ ሲጣሉባቸው፤ «እኔ የለሁበትም» ያሉቱ ተነጥለው ይታያሉ። ነገሩ ሲለይለትም ድብድብ ይሆንና አስታራቂ ሽማግሌ በመካከል ይመጣል።
በእኚህ ሽማግሌ ወይም አባት በኩል የሚተላለፈው መልዕክት ልክ እንደ ሙሉ የቴአትሩ ጭብጥ ትልቁንም መልዕክት የያዘ ነው። እኚህ አባት ተከፋፍለው ያሉትን ሁለቱንም በያሉበት ሃሳባቸው ባይሳሳትም ትክክል እንዳይደሉ ግን ይነግሯቸዋል። ቃል በቃል ባይሆንም ለሁለቱ ጸበኞች ያሉት እንዲህ ነው፤
«እናንተ ኢትዮጵያ ፍጹም ሰላምና መዋደድ እንዳለባትና ምንም ችግር እንደሌለባት አድርጋችሁ ነውና ያሳያችሁት ተሳስታችኋል። ሌሎቻችሁ ደግሞ ኢትዮጵያ ችግር ብቻ ያለባት መሆኗን እንጂ ያሏትን መልካም ጎኖች አላሳያችሁም። የለሁበትም ያላችሁም ትክክል አይደላችሁም፤ በአገር ጉዳይ ላይ አያገባኝም የሚባል ነገር አይሠራም» ሲሉ ተናገሩ። ከዚህ በኋላ በሁለቱ መካከል መግባባት ይሆንና ስለአገር ያላቸው እሳቤ መስመር ይይዛል። ቴአትሩም እንዲህ እንዲህ እያለ ይጠናቀቃል።
የዚህን ሙዚቃዊ ቴአትር ደራሲና አዘጋጆች እንዲሁም ተሳታፊና ተዋንያኑን አለማድነቅ አይቻልም። በእለቱም መታየትና መቅረብ የነበረበት ትክክለኛ ሥራ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። እኛም! ከዚህ ሙዚቃዊ ቴአትር ከተነሳንበት ጉዳይ ጋር የሚዛመድ አንድ ሃሳብ እናገኛለን። ባህላችንን ስንወድ ጽንፍ ይዘን ሳይሆን ባህልም የተፈጠረው የሰው ልጆችን ለማገልገል እንደሆነ በማሰብ መሆን አለበት። ስለዚህም ለሰው ልጅና ለባህሉ ባለቤትም ፍቅርና ክብር መስጠት ያስፈልጋል።
ሌላው ቴአትሩ ላይ ተቧድነው በአገራቸው ጉዳይ ላይ በመቆርቆራቸው ምክንያት ሲጋጩ የነበሩ ሰዎች በአንድ አባት ቁጣና ተግሳጽ ብቻ ርጭ ሲሉና ለማዳመጥ ጆሯችውን ሲሰጡ እንመለከታለን። አሁንም አባቱን የሚሰማና ለአባቱ የሚታዘዝ ትውልድ መኖሩን ይኸው ቴአትር ያሳየናል። የመከባበር ባህላችን ጨርሶ እንዳልጠፋና ባሰብነውና በሚመስለን ልክ እየጠፋን እንዳልሆነም ይነግረናል።
በጥቅሉ በቴአትሩ ውስጥ እንደተመልካቹ አቅም ብዙ የሚገኝ እውነት እንዳለ ማየት ይቻላል። እንዲህ ያሉ ቴአትሮችም በአንድ በኩል ባህልን ለማውጣትና ሰዎችን ለመቀስቀስ ያገለግላሉና ይበል ልንል እንወዳለን። የባህል ዘርፍ ላይ የሚሠሩ አካላትም፤ «ታላላቅ ሰዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና መገናኛ ብዙኅን ድርሻቸውን ይወጡ» የሚል መዝጊያ ካለው የተለመደ ጥናታዊ ወረቀት በዘለለ፤ ይህን በዓል እንዲሁም ባህልን ለተሻለች አገር የምንጠቀምበትን መንገድ በማበጀቱ ላይ እንዲንቀሳቀሱ እንላለን።
እንግዲህ የሚሰማ ልጅ ካለ የሚናገር አባት፣ የሚመክር ታላቅ ሰው ነው የሚፈለገው ማለት ነው። እናም ከውጪ በር ተዘግቶበታል፤ ከውስጥም ብቻውን ሆኗል አልያም «አያገባህም!» ተብሎ ወጥቷል ያልነው ባህል፤ በፖለቲካው ውጥንቅጥ ገብቶ አብሮ እየነፈሰ ካልሆነ በቀር፤ አሁንም ወርቅ የሆነውንና ሁላችን የምንወደውን ኢትዮጵያዊ ባህል ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ክብሯ ሕዝቧም ወደ ለመደው መዋደድ እንዲያመራ ማድረግ ይቻላል።
በየትምህርት ቤታቸው የባህል ቀንን የሚያከብሩ ተማሪዎችና ህጻናት፤ የሚረከቧት አገር ውበትና ብዝሃነት እንዲያዩ እንጂ ልዩነት እንዳይመስላ ቸውም አሁን ሊሠራ ይገባል። ቀጣዩ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን- የኢትዮጵያ ቀን- የባህል ቀን ሆኖ ባህሉን ብቻ ሳይሆን እኛም ተዋደን የምንገኝበት እንዲያደርግልን ጸሎትና ምኞታችን ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ሊድያ ተስፋዬ