‹‹ቅድመ ስድብ!››

ከወራት በፊት ነው:: የመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ አውቶቡስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ከመነሻው ፒያሳ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አጠገብ ተሰልፌ ቆሜያለሁ (በኮሪደር ልማት ምክንያት በወቅቱ በአራት ኪሎ አያልፍም ነበር):: ሰልፌን ጠብቄ ገባሁና ተቀመጥኩ:: በዚህ ሰርቪስ በተደጋጋሚ ስለምሄድ በቋሚነት የሚሄዱ ሰዎችን ባልግባባቸውም ቢያንስ በዓይን አውቃቸዋለሁ:: አንዳንዶቹ (በተለይም ከኋላና ከፊት አካባቢ የሚቀመጡ ሰዎች) ተላምደው ቤተሰባዊ ጓደኝነት ፈጥረዋል፤ ይቀላለዳሉ ይጫወታሉ::

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከኋላ በር አጠገብ ያለው ወንበር ላይ የሚቀመጥ ነው:: ዋናው ተቆጣጣሪ በማይኖርበት አጋጣሚ እንደ ተቆጣጣሪ ነገርም ነው፤ የሚገቡ ሰዎችን መታወቂያ ያያል፤ ያም ሆኖ ግን ዋናው ተቆጣጣሪ ከፊተኛው በር በመስኮት በኩል ያለው ነው:: ከኋላ በኩል ያለው አልፎ አልፎ ነው ‹‹መታወቂያ›› ሲል የምሰማው:: አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ!

ይህ ከኋላ በር በኩል የሚቀመጥ ሰውዬ አንድ ቀን ሰልፉ አልቆ፣ የሚገባው ሰው ሁሉ ገብቶ፣ ሰዓቱ ደርሶ ሰርቪሱ መንቀሳቀስ እስከሚጀምር ድረስ ከሚግባባቸው ሰዎች ጋር ውጭ ላይ ወሬ ይዞ ቆየ:: በእሱ እምነት የእሱን ወንበር ማንም አይቀመጥበትም፤ በየትኛውም ሰዓት ቢገባ ያገኘዋል:: የሚገባው ሰው ሁሉ የእሱን ወንበር ያውቀዋል:: ልብ በሉ! ፐብሊክ ሰርቪሱ በሚሄድበት መስመር የሚሄድ መታወቂያ ያለው የመንግሥት ሠራተኛ ሁሉ መግባት ይችላል:: ይሄ ማለት በዚያ ሰርቪስ ሄዶ የማያውቅ የመንግሥት ሠራተኛም (መታወቂያው ካለው) ሊገባ ይችላል ማለት ነው::

ይህ ሰውዬ ውጭ ላይ ሲንጎራደድ ቆይቶ አሽከርካሪው ሞተር ሲያስነሳ ገባ:: ሲገባ እሱ ከሚቀመጥበት ወንበር ላይ ከዚህ በፊት የማያውቀው ሰው ተቀምጦበታል:: ወደ መሃል አካባቢ ባዶ ወንበሮች አሉ:: ከወንበሩ ላይ የተመቀጠውን ሰውዬ ትዕዛዝ በሚመስል ድምጸት ‹‹ተነሳ እዚያ ሁን!›› ብሎ ወደ መሃል አካባቢ ካሉ ባዶ ወንበሮች ጠቆመው:: አዲሱ ሰውዬውም ግራ ገብቶት ‹‹አንተ እዚያ አትሆንም እንዴ?›› አለው:: አሁንም በትህትና ከማስረዳት ይልቅ ‹‹ይሄ የኔ ቦታ ነው! እዚያ ሂድ!›› አለው:: ይህኔ እንግዳው ሰውዬ ጭራሽ እልህ እየያዘው መጣ::

በዚህ ጊዜ የዚህ በቋሚነት የሚሄደው ሰውዬ ጓደኞች ፀጥ አሉ፤ በነገራችን ላይ ይህ የአስመሳይነት ባህሪያችን ውጤት ነው:: በቋሚነት የሚሄደው ሰውዬ መደበኛ ተቆጣጣሪ አይደለም፤ በቋሚነት የሚቆጣጠረው ከእሱ በቀኝ በኩል (በመስኮት በኩል) የሚቀመጠው ነው:: ስለዚህ ጓደኞቹ ‹‹ስላላወቀ ነው ተወው፣ አንተ ራስህ ወደ መሃል ሂድ!›› ማለት ነበረባቸው:: እንደዚህ እንዳይሉ ጓደኛቸው ሆነባቸው፣ እንግዳውን ‹‹ተነስ!›› እንዳይሉት ደግሞ ትንሽ ይሉኝታ ነገር አለ፤ በሌላ በኩል እንግዳው ጥፋት የለበትም:: ባዶ ወንበር ያገኘበት ላይ ተቀመጠ:: እሱ የሚያውቀው በአንድ በር በኩል አንድ ተቆጣጣሪ ነው፤ እሱ መታወቂያ እያየ እያስገባ ነው:: ታዲያ የዚህን ሰው ወንበር ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ነው የማይቀመጥበት? ይህ ቀድሞ የገባ ሰው የሚቀመጥበት የተጓዦች ወንበር እንጂ የፓርላማ ወንበር አይደለም::

በዚህ ሁኔታ እየተጨቃጨቁ ሳለ እንግዳው ልቦና ሰጥቶት ተነሳ:: ‹‹ሞኝ ሲያከብሩት የፈሩት ይመስለዋል›› እንዲሉ በቋሚነት የሚሄደው ሰውዬ የአሸናፊነት ስሜት እየተሰማው ተቀመጠ:: እዚህ ሰውዬ ላይ ያለውን መሃይምነት እና በወጣቶች ቋንቋ ‹‹ፋራነት›› ልብ በሉ!

አንድ እዚህ ድረስ የተማረ ሰው (ቢያንስ ዲግሪ ይኖረዋል) በትንሹ እንዲህ አይነት ቀላል ነገሮችን እንኳን ሊረዳ የሚችል መሆን ነበረበት:: ከጓደኞቹ ጋር ለመጫወትም ሆነ የለመደው ወንበር ላይ ለመቀመጥ ከፈለገ ቀስ ብሎ በትህትና እና በፈገግታ ‹‹ይቅርታ ይቺ ቦታ የኔ ነበረች፤ እዚያኛው ላይ ብትሆን ይደብርሃል?›› ቢለው ምን ችግር አለው? ችግሩ ይህን እንዳይል የገነባው ኋላቀር የግል ክብር ልማድ ይከለክለዋል:: ለእሱ እንደዚህ ማለት የሥልጡንነት ምልክት ሳይሆን ምናልባትም የፈሪ ሰው ምልክት መስሎ ታይቶታል::

ትንሽ እንኳን ማገናዘብ የሚችል ቢሆን ኖሮ አዲስ የገባው ሰውዬ ከዚህ በፊት የለመደው ሰው እንዳልሆነ ተመለከተ፤ ስለዚህ ይህ እንግዳ ሰውዬ ሳያውቅ ሊቀመጥ እንደሚችል መገመት ያን ያህል ሩቅ ነበር?

ይህ ነጠላ ምሳሌ ‹‹ብዙዎችን አይወክልም! እንዴት የአንድ ግለሰብ ወፈፌ ባህሪ ምሳሌ ይደረጋል?›› ሊባል ይችላል:: ይህን ነጠላ ምሳሌ ግን ለምሳሌ ያህል ብቻ ጠቀስኩት እንጂ ይህ ችግር ብዙ ቦታ የማየው ነው:: በዚሁ በሰርቪስ ውስጥ ብቻ እንኳን ከዚህ በፊት በነበሩ የትዝብት ጽሑፎቻችን ለድብድብ እስከመገባበዝ የደረሱ ገጠመኞችን ጠቅሻለሁ:: እንኳን እንዲህ አይነት ተራ ቦታ ላይ ይቅርና እንደ አገር ያለን ችግር ራሱው ይሄው ነው፤ ከትህትና ይልቅ የግል ክብርን ማስቀደም!

ብዙ ቦታ በተደጋጋሚ የምታዘበው ነገር፤ ነገሮችን በትህትና እና በሰለጠነ መንገድ ከመግለጽ ይልቅ ከቁጣ መጀመር ልማዳችን ነው:: ታክሲ ውስጥ ልብ በሉ:: በትህትና ‹‹እዚች ጋ ብታወርደኝ ይመችሃል?›› የሚሉት ጥቆቶች ናቸው:: አብዛኞቹ መውረጃቸው ጋ ሲደርቁ ቆጣ ብለው ‹‹ወራጅ አለ!›› ይላሉ:: ይህን የሚሉት ገና ቦታውን ሳያሳልፋቸው ነው፤ የሚናገሩትም ገና የመጀመሪያቸው ነው:: መቆጣት እንኳን ቢያስፈልግ አንድ ጊዜ ተናግሮ አልሰማ ካለ ወይም ሊያሳልፍ ሲል መሆን ነበረበት::

ይመስለኛል ይህ ችግር የሚመጣው ረዳትና ሾፌሮች ብዙ ጊዜ ጭቅጭቅ ይወዳሉ፣ ቶሎ አይሰሙም፣ ሥርዓት የላቸውም ከሚል ግምት ነው፤ ግምት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ከሚያስተውሉት ገጠመኝም ሊሆን ይችላል:: ዳሩ ግን ሾፌሮችና ረዳቶች እንዲህ አይነት ባህሪ አላቸው በሚል እሳቤ ራስንም የእነርሱ ባህሪ ወራሽ ማድረግ ልክ አይደለም፤ ሲቀጥል እነርሱንም ትህትና እና ሥልጡንነት ለማስተማር ራስ ትሁት በመሆን ነው:: እንዲህ አይነት ኋላቀር ልማድ ስላለን እኮ ነው እነርሱም የዚሁ መጥፎ ልማድ ውጤት የሆኑት::

ብዙዎቹ ላይ የምታዘበው የቅድመ ስድብ አገልግሎት ነው:: የቅድመ ስድብ አገልግሎት ማለቴ ገና ለገና ሊሰድበኝ ይችላል፣ እሺ ላይለኝ ይችላል በማለት አስቀድሞ መቆጣት ማለት ነው:: ይህ ችግር ምናልባትም ከበታችነት ስሜት የሚመጣ ነው:: ይንቁኝ ይሆናል፣ ለእኔ እሺ ላይሉኝ ይችላሉ ከሚል ስሜት የሚመጣ ሊሆን ይችላል::

የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የበታችነት ስሜት ያለባቸው ሰዎች ነገሮችን በነገሮች ዓውድ መረዳት አይችሉም፤ ከዚያ ይልቅ ንቀውኝ ነው የሚል ስሜት ውስጥ ይገባሉ:: ራሳቸውን ለመቆጣጠር ይቸገራሉ:: ‹‹ልኬን አሳይሃለሁ›› የብዙ ሐበሻ ባህሪ ነው::

በብዙ አገልግሎት ማግኛ ቦታዎች ላይ የምታዘበው ነገር፤ ተገልጋዩ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ያሟላ አያሟላ ሳያውቁ ኮስተር ብለው ‹‹እንደዚህ ያስፈልጋል! ምንንትስ መያዝ አለብህ!…›› እያሉ የዱቤ ቁጣ ይቆጣሉ:: ግልምጫ እንኳን ካስፈለገ ቢያንስ ‹‹አልያዝኩም›› ካለ በኋላ አይሻልም ነበር?

በአጠቃላይ የቅድመ ስድብና ቁጣ ባህሪዎቻችን መጥፎ ናቸውና ትህትና ይልመድብን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You