
ሰዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በፈቃደኝነት ከሚያቋቁሟቸው አደረጃጀቶች መካከል የኅብረት ሥራ ማህበራት ይጠቀሳሉ:: ማህበራቱ የአባሎቻቸውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ ገበያ ለማግኘት፣ ዋጋን በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን ለመከላከል፣ የፋይናንስ ችግርን ለመፍታትና ለመሳሰሉት አላማዎች ይቋቋማሉ::
በኢትዮጵያም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችል የኅብረት ሥራ ማህበራትን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማቋቋም ከተጀመረ 50 ዓመታት መቆጠራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ::
የማህበራቱን ፋይዳ በሚገባ የተረዱት የሀገሪቱ መንግሥታት ማህበራቱን አዋጆችን፣ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን በማውጣት፣ ማህበራቱን የሚደግፍ መንግሥታዊ አደረጃጀት በመፍጠር ጭምር ሠርተዋል:: የሥልጠና፣ የገበያ ትስስር፣ የፋይናንስ ድጋፍና የመሳሰሉትን በማድረግ ጭምር እንዲጠናከሩ ያደርጋሉ::
በሀገሪቱ በርካታ አባላትን በማቀፍ እየሠሩ ከሚገኙ ማህበራት መካከልም፣ የአርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማህበራት ይጠቀሳሉ:: እነዚህ የኅብረት ሥራ ማህበራት በመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ በዩኒየኖች እንዲሁም በፌዴሬሽን ጭምር ሰብሰብ ብለው በመደራጀትና አቅማቸውን ይበልጥ በማጎልበት የአባሎቻቸውም የሀገርንም ምጣኔ ሀብት በመደገፍ ላይ ይገኛሉ::
የአርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማህበራትን ብቻ ብንመለከት በተለያዩ አደረጃጀቶቻቸው አማካይነት የአርሶ አደሩን ምርት ለገበያ በማቅረብ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ፣ ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን በማቅረብ ይሠራሉ:: በዩኒየኖቻቸው በኩልም እንደ ዱቄት፣ ዘይት፣ ብስኩትና የመሳሰሉትን ፋብሪካዎች በመትከል በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ምርቱ ጥሩ ዋጋ እንዲያገኝ እያደረጉ ናቸው::
በከተማ ከሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ከተሜው የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዲችል በማድረግ የዋጋ መረጋጋት ላይ አጥብቀው ይሠራሉ:: በዚህም መንግሥት ገበያ እንዲረጋጋ ለሚያከናውነው ተግባር ወሳኝ አቅም በመሆን እያገለገሉም ይገኛሉ::
በዚህም ሸማቹንም አምራቹንም ከደላላ ወይም ከሶስተኛ ወገን ነፃ በሆነ መልኩ ግብይት እንዲፈጸም በማድረግ ለሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚነት አጥብቀው ይሠራሉ:: የሀገሪቱን የግብይት ሥርዓት በማዘመን የሸማቹንና የአምራቹን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አላቸው። ሸማቹ በዋጋ ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኝ ያስችላሉ::
የኅብረት ሥራ ማህበራት ገበያ እንዲረጋጋ ከማድረጋቸው ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም ይታወቃሉ:: በዚህ በኩል የአግሮ ኢንዱስትሪዎቻቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው:: ኢንዱስትሪዎቹ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ለመጨመር በሚያከናወኑት ተግባር ማሽነሪዎችን ቢጠቀሙም ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል መጠቀምንም የግድ ይላልና ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ::
የሀገራችን የሥራ ባሕል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቀየረ ይገኛል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሥራ ማግኛ አርገው ይመለከቱ ነበር። አሁን ላይ ይህ እየተለወጠ መጥቷል:: ወጣቶች በማህበራት በመደራጀት በተለያዩ መስኮች ሥራ በመፍጠር ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ::
መንግሥት ለእነዚህ የኅብረት ሥራ ማህበራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል:: ማህበራቱ ለአርሶ አደሩ ግብዓት እንዲያቀርቡ፣ የግብርና ምርቶችን ሰብስበው ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩም ሸማቹም እንዲጠቀሙ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠርም የማህበራቱ አቅም እንዲጎለብት ማድረግ ላይ ይሠራል::
ከዚህም ባሻገር የኅብረት ሥራ ማህበራት የቁጠባ ባሕልን ስለሚያሳድጉ ለሀገር ኢኮኖሚ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው:: አባሎቻቸው እንደ መኖሪያ ቤት ያሉትን እንዲገዙ፣ እንዲገነቡ፣ ወዘተ እያስቻሉ ናቸው:: ማህበራት ምርቶችንና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች በማድረስ መልካም የገበያ ትስስርን በመፍጠር ገበያውን በከፍተኛ ሁኔታ ያረጋጋሉ።
የኅብረት ሥራ ማህበራት የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን እያስቀሩም ይገኛል። አርሶ አደሮች ግብዓቶችም ከማቅረብ በተጨማሪ ትራክተሮችን ኮምባይነሮችንም ወደ ማቅረብ ገብተዋል:: በዚህም ሀገሪቱ ግብርናውን ለማዘመን እንዲሁም ኢኮኖሚው ፈጣን ዕድገት ማስመዘገቡን እንዲቀጥል ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ናቸው::
የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽንም እነዚህ የኅብረት ሥራ ማህበራት አቅም በሥልጠናና በመሳሰሉት እንዲገነባ ይሠራል:: ምርቶቻቸውን ለሸማች የማህበረሰብ ክፍሎች ማቅረብ የሚችሉበትን ዕድሎችን ያመቻቻል:: ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት የሚያካሂዷቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሮች፣ ከዚሁ ጎን ለጎን በሚያካሂዷቸው ሲምፖዚየሞች በማህበራቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩባቸው ሁኔታዎች ይጠቀሳሉ::
ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሮች አምራቾች በቀጥታ ከሸማቹ ጋር ይገናኛሉ:: ለግብርና ምርት እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ይዘው በማቅረብ ያስተዋውቃሉ፤ የገበያ ትስስርም ይፈጥራሉ::
ዘንድሮም ይህ ኤግዚቢሽንና ባዘር ከዛሬ ጀምሮ ለቀናት ይካሄዳል:: ይህ የኢፌዴሪ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ጋር ያዘጋጀው 11ኛው ሀገር አቀፍና 4ኛው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ከጥር 28 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎንም ሲምፖዚየም ይካሄዳል::
ኤግዚቢሽኑን በሚመለከት ያነጋገርናቸው የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ጫልቱ ታምሩ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ እንደዚህ ዓይነት ሁነቶችን በተለያዩ ጊዜያት በማዘጋጀት ይታወቃል፤ በኤግዚቢሽን፣ ባዛር እና ሲምፖዚየሙ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የኅብረት ሥራ ማህበራት አባላት፣ ሸማቾች፣ የልማት ድርጅቶች እና ሌሎች የግብይት ተዋናዮች እንደሚገኙ ይጠበቃል:: ኤግዚቢሽንና ባዛሩ “የኅብረት ሥራ ሚና ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነው::
እንደዚህ ዓይነት ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች አምራቹን ከሸማች በከፍተኛ ደረጃ የማገናኘት ዕድላቸው ሰፊ ነው:: ኮሚሽኑም እንደዚህ ዓይነት ሁነቶችን ሲያዘጋጅ ዋነኛ አላማው ያደረገውም የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጠቃሚዎች በማስተዋወቅ፣ ዘላቂ የግብይት ትስስር በመፍጠር አባላትን ተጠቃሚ ለማድረግ እና የኅብረት ሥራ ዘርፉን ገጽታ ለመገንባት ነው::
ሁነቶቹ በዋነኛነት ትልቅ የገበያ ትስስርን መፍጠር ያስችላሉ፤ የደላላ ጣልቃ ገብነትን በማስቀረት አምራቹ የኅብረተሰብ ክፍል ከሸማቹ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ የማድረግ ከፍተኛ ሚናም አላቸው::
አምራች የኅብረት ሥራ ማህበራት በቀጥታ በአጭር የግብይት ቅብብሎሽ ከተጠቃሚው ጋር ዘላቂ የግብይት ትስስሮችን በመፍጠር የአባላትን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ይሆናልም ሲሉ ወይዘሮ ጫልቱ ይገልፃሉ።
የኅብረት ሥራ ማህበራት በቀጥታ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ከግብዓት አቅራቢ ድርጅቶች፣ አቀነባባሪ የፋብሪካ ባለቤቶች፣ የሜካናይዜሽን ማሽኖችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከሚያመርቱ እና ከሚያከፋፍሉ ድርጅቶች ጋር የግብይት ትስስር ያደርጋሉ። በዚህም ሁነት ላይ እነዚህ ድርጅቶች በቀጥታ ተሳታፊም ይሆናሉ::
እንደዚህ ዓይነት ሁነቶች አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ምሁራን፣ አቅም ገንቢዎች ስለ ኅብረት ሥራ ማህበራት ጠቀሜታና ፋይዳ በውል ለመረዳት ለኅብረት ሥራ ዘርፉም የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እና ተቀናጅተው እንዲሠሩ እንደሚያግዝም ወ/ሮ ጫልቱ ጠቁመዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ፤ የዘንድሮው የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም_ መሪ ቃል “የኅብረት ሥራ ማህበራት ሚና ለኢትዮጵያ ብልፅግና!” የሚል መሆኑን ጠቅሰው፣ መሪ ሃሳቡ ይህ እንዲሆን የተመረጠበት ምክንያት ኅብረት ሥራ ማህበራት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡና ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሕዝባዊ ተቋማት መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው ሲሉ አስታውቀዋል:: ይህን በተጨባጭ በማሳየት የኅብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴን መደገፍ ማለት የዘላቂ ልማት ግቡንና የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ዕውን ማድረግ መሆኑን ለማስገንዘብ ሲሉም አመልክተዋል::
በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ በቀጥታ ከአርሶ አደር የሚመጡ የግብርና ምርቶች ይቀርባሉ፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እንዲሁ ምርቶቻቸውን ይዘው ይቀርባሉ::
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ 292 መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች እንዲሁም 59 ልማታዊ ድርጅቶች በድምሩ 351 አምራቾች እንደሚሳተፉ ኃላፊዋ ጠቁመው፣ 264 ዓይነት የግብርና እና የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች በቀጥታ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርቡም ተናግረዋል። ምርቶቹ በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውንም ጠቁመው፣ ሸማቹ የኅብረተሰብ በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ተገኝቶ መገበያየት እንደሚችልም አመልክተዋል::
በእንደነዚህ ዓይነት ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ላይ ግብይት መፈፀም ገበያውን በሚረብሹና ሕጋዊ ባልሆኑ ደላሎች ከሚደርስ የግብይት አሻጥርና ከማይገባ የዋጋ ጭማሪ መጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል::
ወይዘሮ ጫልቱ እንዳብራሩት፤ ይህን ኤግዚቢሽንና ባዛር ከ120 ሺ በሚበልጡ ሰዎች እንደሚጎበኝ ይጠበቃል:: ከግብርናና የፍጆታ ምርቶች ግብይት ባሻገር ኅብረት ሥራ ማህበራት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ልማት በተጨባጭ ምን እየሠሩ እንደሚገኝ ለማመለከትም ያስችላል፤ ለሀገር ዕድገት ያላቸው ጠቀሜታ ምን ያህል እንደሆነ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሥራዎች የሚሠሩበትም ነው::
እነዚህ ሁነቶች መካሄዳቸው በዋናነት አምራቹ የኅብረተሰብ ክፍል ምርቱን ለሸማች በስፋት እንዲያስተዋውቅና እንዲሸጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው፤ ሸማቹ የኅብረተሰብ ክፍልም የሚፈልገውን ምርት በአንድ ሥፍራ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችለዋል:: ኅብረተሰቡም ይህንን ሁነት በጉጉት ይጠበቃል::
እንደዚህ ዓይነት ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች በአምራችና በሸማቹ መካከል ያለውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ መመለስ ችለዋል ማለት ባይቻልም በተወሰነ መልኩ ግን መመለስ ችለዋል ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ በተለያዩ ዝግጅቶች ይካሄዳል:: ከመጀመሩ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን አስመልክቶ በአራቱም የከተማዋ በሮችና ሸገር ከተማ አስተዳደር የመኪና ላይ ትርኢትና ቅስቀሳ ተደርጓል::
ዛሬ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ በስካይላይት ሆቴል ሲምፖዚየም ይካሄዳል:: በሲምፖዚየሙ ላይ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይሳተፋሉ፤ የውጭ ሀገራት ተሞክሮዎች፣ የልምድ ልውውጦችና የኅብረት ሥራ ማህበራቱ የሪፎርም ሥራዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይገለጻል:: 5 ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ 500 ተሳታፊዎችም ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል::
ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የኅብረት ሥራ ማህበራትና አባሎቻቸው፣ ሸማቾች፣ የልማት ድርጅቶች እና ሌሎች የግብይት ተዋናዮች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል::
ሁሉም በመዲናዋ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በእነዚህ ቀናት በኤግዚቢሽን ማዕከል በመገኘት ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቹ እንዲሸ ምቱ ጥሪ አስተላልፈዋል::
ሃይማኖት ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም