ሮማነወርቅ እና ጋንዲ

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ሁለት ጀግኖችን እናስታውሳለን። ኢትዮጵያዊቷን እንስት ጀግና ሮማነወርቅ ካሣሁንን እና ዓለም አቀፉን የሰላምና ነፃነት ታጋይ ማሕተመ ጋንዲን እናስታውሳለን።

የጠቅላላ ዕውቀት ጥያቄና መልስ ውድድሮች ላይ ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ማን ናት?›› ተብሎ ሲጠየቅ እንሰማለን። የሴቶችን ተሳትፎ ታሪክ በሚዘክሩ መድረኮችና የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ስሟ ይነሳል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ ካሣሁን።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 53 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም ሕይወቷ ያለፈውን ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ ካሣሁንን እና የነፃነት ታጋዩን ማሕተመ ጋንዲን ዘርዘር አድርገን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው ሌሎች የታሪክ ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ104 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 20 ቀን 1913 ዓ.ም ጀግናው ፀረ ፋሺስት አርበኛ ሌተናል ጄኔራል ጃገማ ኬሎ (የበጋው መብረቅ) ተወለዱ።

ጃጋማ ኬሎ ሙት ዓመታቸው በሚታሰብበት የመጋቢት ወር ውስጥ በዝርዝር እናስታውሳቸዋለን።

ከ117 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 22 ቀን 1900 ዓ.ም ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የፖስታ ኅብረት (Universal Postal Union) አባል እንድትሆን ለኅብረቱ ደብዳቤ ፃፉ።

ከ132 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 25 ቀን 1885 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አልጋ ወራሽ የነበሩትና ኢትዮጵያን ከ1903 ዓ.ም እስከ 1909 ዓ.ም ያስተዳደሩት ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ተወለዱ።

ከ48 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም የደርግ ሊቀ መንበር የነበሩትን ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲን ጨምሮ በኢ.ሕ.አ.ፓ ሰርጎ ገብነት የተጠረጠሩ የደርግ አባላትና የወዝአደር ሊግ (ወዝ ሊግ) ሊቀ መንበር የነበሩት ሠናይ ልኬ (ዶ/ር) ተገደሉ። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ከድርጊቱ መፈፀም በኋላ ‹‹ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው›› አሉ።

አሁን በዝርዝር ወደምናያቸው የዛሬ ሳምንቱ በታሪክ ጀግኖችና ክስተቶች እንሂድ። የጋዜጠኛ ፍፁም ወልደማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› መጽሐፍ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣና የተለያዩ ድረ ገጾችን በዋቢነት ተጠቅመናል።

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ተውኔት ሮማነወርቅ ካሣሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሣሁን እንግዳሸት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አለሙሽ ዓለም በ1914 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ።

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በመማር ዳዊት ደገሙ። ከዚያም ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ተማሩ። በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የወቅቱን ‹‹ሴት ለትምህርት አልተፃፈችም›› የሚለውን ልማድ በጥረታቸውና በትጋታቸው በመቋቋም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የአንደኛነት ደረጃን በመያዝ በአውሮፓውያን አስተማሪዎቻቸው ይሸለሙ ነበር።

በወቅቱ በነበረው ልማድም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ትዳር ይዘው የአንዲት ሴት ልጅ እናት ሆነዋል።

ሮማነወርቅ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ይማሩ በነበረበት ወቅት ከአውሮፓውያን መምህራን ያገኙት ዘመናዊ ትምህርት ከተፈጥሮ ችሎታቸው ጋር ተደምሮ በጥናትና ንባብ ያዳበሩትን እውቀታቸውን ወደ አደባባይ ማውጣት ስለፈለጉ በጥር ወር 1939 ዓ.ም በወቅቱ ‹‹የማስታወቂያና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር›› ተብሎ ይጠራ በነበረው መሥሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመሆን ተቀጠሩ።

በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በተሰጣቸው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሥራቸው የተለያዩ ጽሑፎችንና ዜናዎችን በማዘጋጀት በማራኪ አንደበታቸው ሲያንቆረቁሩት በዜና አቀራረባቸውና በፕሮግራም ዝግጅታቸው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትንና አድናቆትን ለማግኘት ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር።

በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሬዲዮ ዜና አጠናቃሪነት፣ በዜና አንባቢነት፣ በሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅነት ሠርተዋል። በወቅቱም ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመው በዝግጅቶቻቸው ላይ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሥራዎችን በማቅረብ ሕዝቡን ሲያገለግሉ በትምህርት ገበታ ላይ ለነበሩት ሴቶች ልጆች እንደብርቅዬና የበጎ ተግባር ምሳሌ በመሆን ይታዩ ነበር። በዝግጅቶቻቸው የተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በወቅቱ በሴቶች ዘንድ ጫና የሚፈጥሩ አመለካከቶችን ለመፋቅ በመገናኛ ብዙኃን የራሳቸውንና የብዙ ሴቶችን ድምፅ አሰምተዋል።

የሴቶች ማኅበራዊ ሕይወት መሻሻል ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችንም ይጽፉ ነበር ከሥራዎቻቸው መካከል የበኩር ሥራቸው የተጠናቀቀው በ1940 ዓ.ም ቢሆንም መጽሐፋቸውን ይዘው ወደ ኅትመት የሄዱት ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ በ1942 ዓ.ም ነበር። ይህንን ጉዳይ አስመልክተውም በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ በማለት ስለሕትመቱ ጉዳይ በትሕትና ገልፀዋል።፡

‹‹ … መጽሐፌን ጽፌ የጨረስኩት በ1940 ዓ.ም ነበር። ከዚያ ወዲህ ሁለት ዓመታት ቆይቼ ሳነበው ከእርሱ የተሻለ ለመፃፍ የምችል ሆኖ ተሰማኝ።

በዚህ ምክንያት ተሳንፌ ማሳተሙን ለማቆየት ከቆረጥሁ በኋላ የሰው እውቀት የእድሜ ደረጃን ተከትሎ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ አዋቂ አለመሆንን በማሰብ ዛሬ የተሻለ መስሎኝ ብሠራም ነገ መናቄ እንደማይቀር ተረዳሁት። ይህም የሰው አዕምሮ ያለማቋረጥ የሚሻሻል ለመሆኑ ዋና ማስረጃ ነው በማለት ይህን ሁሉ ካወጣሁና ካወረድሁ በኋላ ማመንታትን ትቼ አሳተምሁት። … ››

የመጀመሪያ ሥራቸውን ለአንባቢ ያቀረቡት ወይዘሮ ሮማነወርቅ ለመጽሐፋቸው የመረጡት ርዕስ ‹‹ትዳር በዘዴ›› የሚል ነበር። መጽሐፉ የገጠሩንና የከተማውን ትዳርና ኑሮ የሚያነፃፅር ሲሆን በውስጡም በገጠር ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ዘርዝሮ ያቀርባል።

ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹ለትዳር ፈላጊዎች ምክር አለኝ›› በማለት ስለትዳር የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ሞክረዋል። ሴቶች በማኅበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ያለባቸው ጫናም በመጽሐፉ ተዳስሷል። ከዚያ በኋላም በርካታ ጋዜጣ መጣጥፎችንና መጻሕፍትን ጽፈዋል። በሥራዎቻቸውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ተውኔት ሮማነወርቅ የጤና እክል አጋጥሟቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንትና ሠራተኞች እንዲሁም እጅግ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

ጋዜጠኛዋ ሞት ቀደማቸው እንጂ ‹‹ሔዋን››፣ ‹‹መልካም እመቤት››፣ ‹‹የቤተሰብ አቋም››፣ ‹‹የባልትና ትምህርት››፣ ‹‹የሕፃናት ይዞታ››፣ ‹‹ዘመናዊ ኑሮ››፣ ‹‹የኑሮ መስታዎት››፣ ‹‹ጋብቻና ወጣቶች››፣ እና ‹‹የባልና የሚስት ጠብ›› በሚሉ ርዕሶች መጽሐፍትን አዘጋጅተው ለሕትመት ለማብቃት እየጠበቁ እንደነበር ታሪካቸው ያሳያል።

የነፃነት ታጋዩ ማሕተመ ጋንዲ

የሕንዱ ማሕተመ ጋንዲ የመብት ተሟጋች ስለነበሩ በየትኛውም የዓለም ሀገር ይታወቃሉ። በሀገራችን ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ስማቸው ይነሳል። ሆስፒታል ተሰይሞላቸዋል።

ከ77 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 22 ቀን 1940 ዓ.ም የተገደሉትን ማሕተመ ጋንዲን እናስታውሳቸው።

ማሕተመ ጋንዲ የተወለዱት መስከረም 23 ቀን 1862 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ ኦክቶበር 2፣ 1869) ነው። ማሕተመ ጋንዲ ‹‹የሕንድ አባት›› በመባል የሚታወቁ የሰላማዊ ትግል መሪ እና የፀረ ቅኝ አገዛዝ አብዮተኛ ናቸው።

‹‹ፍልስምና›› በተሰኘው የቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው፤ ጋንዲ እንግሊዞችን ፍጹም ሰላማዊ በሆነና ለእነርሱ ጨርሶ ሊገባቸው በማይችል እምነትና መንገድ የታገላቸው ነው።

ከምዕተ ዓመታት ቅኝ ግዛታቸው ለማስወጣት የሕንድን ሕዝብ እያንቀሳቀሰ ስለሚፈታተናቸው ብዙ ጊዜ እስር ቤት ይከቱት ነበር።

ወደ መጨረሻው አስከፊ እስር ቤት በወረወሩበት ጊዜ ‹‹እናንተ አውሮፓውያን ወዳጆቼ ሆይ! የሰው ልጅ እኮ በአራት ግድግዳ የሚታሰር ግዑዝ ነገር አለዚያም እንሰሳ አይደለም። የሰው ልጅ መንፈስ ነው።

እዚህ በእስር ሳለሁ ጽናቱን እምነቴ ሕንዳውያን ወገኖቼን ያንቀሳቅሳል፤ እስር ቤት ክፉ የሚሆነው በመንፈስ ለታሰሩና በግድግዳ ለሚወሰኑ እውነተኞቹ እስረኞች እንጂ መንፈሳቸውን ከፍርሃትና ከጥላቻ ነፃ ላወጡ መንፈሳውያን እስራት አያስጨንቃቸውም፤ አያሸብራቸውም›› ብሏቸዋል።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ጋንዲን የመጨረሻዎቹ ዱርዬዎችና ነፍሰ ገዳዮች መካከል ይከቱታል። ጋንዲ ወደዚያ ሲገባ ‹‹እነሆ ወንድሞቼ መሐል ገባሁ። ከዛሬ ጀምሮ የዚህ ቤተሰብ አካል ነኝ›› ይላቸው ነበር። ኃዘን ቢሰማው እንኳ ኃዘኑን በተስፋና በፍቅር ሊታገለው ይጀምራል እንጂ ቅሬታና ማጉረምረምን አያሰማም ይሉታል። በእነዚህ የማይጠቅሙ ተብለው በተጣሉ ዱርዬዎች ውስጥ ፍቅርና መልካምነት እንዳሉ ያውቃል ብቻ ሳይሆን ያምናል። እናም ኃላፊነት ይወስዳል። የእስር ቤቱን ቆሻሻ ማፅዳት ይጀምራል። እነዚያን አይጠቅሙም እንደውም ማኅበራዊ አደጋ ናቸው ተብለው የተጣሉ ነፍሰ ገዳዮችን በማክበር አክብሮት ከሚሰጠው መልካም ስሜት ያስተዋውቃቸዋል።፡ ከእግዚአብሔር ያስተዋውቃቸዋል። ጤና አጠባ በቅን፣ አብሮ መኖርን ያስተምራቸዋል።

ታሪክ የማያውቁትን ታሪክ፣ መሐይማኑን ማንበብ መፃፍ ያስተምራቸዋል።፡ እንዲህ በመልካም ተግባር ተጠምዶ ሲውል ስለ እስር የሚያስብበት ጊዜ አልነበረውም። እንግዲህ ስለ ነፃነታቸው ሲል የራሱን ነፃነት ያጣላቸው ሕንዳውያን ማለት እነዚህን ወህኒ የተጣሉትንም እንደሚጨምር ያውቃል። እናም የብርሃን ተስፋውን በወህኒ ጨለማ ውስጥ ሳለ ይበልጡኑ ጸንቶና አምኖ እየታገለለት ነው ማለት ነው።

የትግሉ መንገድ ግን ጥላቻን በጥላቻ ማሸነፍ እንደማይቻል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ጥላቻን በፍቅር መፈተን ነው። ስለዚህ መታሰሩ አስጨንቆ ዓላማውን ጥሎ እጁን እንዲሰጥ አያስገድደውም።

ይልቁንም በዚያ ጨለማ ውስጥ ሕይወትን ይጀምራል። እናም መታሰሩን ይረሳዋል። በዚህ ጊዜ እነሱው አሳሪዎቹ ራሳቸው አስታውሰው ነው የሚፈቱት። ‹‹የረገጥኳትን መሬት ለመባረክ ሥልጣን ተሰጥቶኛል›› ነው የሚለው።

ማሕተመ ጋንዲ በዚህ የሕይወት መንገዱ ያስተማረኝ ትልቅ እውነት ‹‹በዙሪያህ የሚታይህን ክፋት መቋቋም ካቃተህ ‹እኔን ምን ነካኝ?› እንጂ ‹ዓለም ምን ነካት?› ብለህ አትጠይቅ›› የሚል ትምህርት ነው። እንዲህ ብለህ ብትጠይቅም መልስ አታገኝም።

ዓለም ክፉ ናት ብትል ራስህ ክፉ ናት ካልካት ከዓለም በእጥፉ የከፋህ ትሆናለህ። በምትጠላው ነገር ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የምታስተውልበት ዓይኖች ቢኖሩህ ክፉውን መልካም ታደርገዋለህ። እርሱን ፈውሰህ አንተም ትፈወሳለህ›› ይላል።

ማሕተመ ጋንዲ በዚህ ባሕሪው ራሳቸው እንግሊዛውያኑ ቅኝ ገዢዎች፣ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ፣ የሌላ እምነት ተከታዮቹ ሳይቀሩ ይወዱት፤ ይከተሉትና ያምኑት ነበር። እንግሊዞቹ ተብትበው በወጡት መከፋፈልና ጥላቻ ምክንያት በተፈጠረው ርስ በርስ የመጠፋፋት ጦርነት ውስጥ ሙስሊሞቹ ሂንዱዎቹን እያባረሩ በቆንጨራ በሚጨፈጭፉ ሰዓት እንኳ ማሕተመ ጋንዲን ግን ይሰሙት ነበር። ይከተሉት ነበር፤ እርሱ ዘንድ ሲደርሱ በፍቅሩ ጭካኔያቸውንና ቂም በቀላቸውን አሸንፎ ያንበረክካቸው ነበር።

የሁሉንም እምነት መጽሐፍት እየገለጠ በየዕለቱ ከሁሉም ሕንዳውያን ጋር አብሯቸው ይጸልይ ነበር። እናም ጋንዲ የቱንም መጥፎ የተባለን ቦታና ሃሳብ ወደ መልካም የመለወጥ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በመሸ ጊዜ ንጋትን በማሰብ ተስፋህን አምነህ ጉዞህን ጀምር የሚል እምነት አለው። የክፉ ነገር መጨረሻ ጥፋት ነው። መልካሙን የሚያመጣው የግለሰቦች ጽናት ነው። በመጨረሻው ጨለማ ውስጥ ወደ ብርሃንህ መመልከት የመሐተመ ጋንዲ እምነት ነው።

ይህ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ታጋይ ናታሁራም ቪናያክ ጎድሴ በሚባል ግለሰብ በጥይት ተገድሏል። ገዳዩም የሞት ቅጣት ተፈርዶበት በስቅላት ተገድሏል። እነሆ የማሕተመ ጋንዲ ስምና ሥራ ግን በዓለም ዙሪያ ሲወደስ ይኖራል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You