ጉባዔው አዳዲስ ስትራቴጂክ እይታዎች እና የውሳኔ ሀሳቦች የሚቀርቡበት እንደሚሆን ይታመናል!

በሕዝባችን ውስጥ የነበረውን የለውጥ መንፈስ የለውጥ ዘር አድርጎ የተነሳው እና በብዙ የሕዝቦች የመስዋዕትነት ትግል በድል ወደ ፖለቲካ አደባባዩ ደምቆ የወጣው የብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሀገሪቱን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚወስዱ ተስፋ ፈንጣቂ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ፓርቲው ገና ከጅምሩ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት እና ለመስዋዕትነት በተነቃቃ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ራሱን ያዘጋጀ መሆኑ፤ በለውጥ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተገማች እና ተገማች ያልሆኑ ፈተናዎችን በጽናት መሻገር ችሏል። ከቀደሙት ዘመናት ሀገራዊ የለውጥ ትርክቶች በተሻለ ስኬት ውስጥም ይገኛል።

በአንድ በኩል ለዘመናት የሕዝቦቿን የለውጥ መንፈስ ሲያመክን፤ እንደ ጥላ ወጊ ሲከተለን የኖረው አሮጌው የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ በሌላ በኩል ያለንበት ዓለም የፈጠረው የተዛባ የፖለቲካ አተያይ እና አተያዩ የሚፈጥረው ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ሀገራዊ ለውጡን እና የለውጥ ኃይሉን በብዙ ተፈታትኗል።

የለውጡ ሕዝባዊነት ስጋት የፈጠረባቸው፤ በተዛባ ትርክት፣ በተሳሳተ መንገድ ላይ ቆመው ትናንቶችን መመለስ የሚሹ፤ ከዚያም አልፎ በተሳሳተ ስሌት ከአጋጣሚ ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ኃይሎች በተናበበ እና በተቀናጀ መንገድ በለውጡ እና በለውጡ ኃይል ላይ በተቻላቸው ሁሉ ዘምተዋል።

ይህንን ውስጣዊ ክፍተት በመጠቀምም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሀገርን የማፍረስ ተልዕኮ ይዘው በስፋት ተንቀሳቅሰዋል። በብዙ ትውልዶች መስዋዕትነት ታፍራ እና ተከብራ የኖረችውን ሀገር ሕልውና ስጋት ውስጥ የጨመረ ታሪካዊ ክስተት ተፈጥሮ፤ እንደ ሀገር መላው ሕዝባችን ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ መሻገር ችለናል።

በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የብልፅግና ፓርቲ፤ ፈተናዎችን ወደ ዕድል መለወጥ በሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባሕል እና መነቃቃት፤ መላውን ሕዝብ ከጎኑ በማስከተል፤ የመለወጥን ተስፋ በተለወጠ ማንነት ተጨባጭ ማድረግ ችሏል። በዚህም እንደሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

የቀደመውን የሀገሪቱን አሮጌ የፖለቲካ ባሕል በመለወጥ ዘመኑን በሚዋጅ በድርድር እና በንግግር ላይ የተመሠረተ፤ ከጠላትነት ይልቅ ወደ አጋርነት፤ ከተቃዋሚነት ይልቅ ወደ ተፎካካሪነት የተለወጠ አዲስ የፖለቲካ ትርክት ጅማሬ ፈጥሯል። በዚህም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ መሥራት እንደሚቻል በተጨባጭ አሳይቷል።

ችግሮችን በሆደ ሰፊነት ከማስተናገድ ባለፈ፤ ራስን ዝቅ አድርጎ ለጋራ ተጠቃሚነት መሥራት ምን እንደሚመስል በተግባር በማሳየት፤ ሀገራዊ ፖለቲካው ከአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት እና ትርክቱ ከሚፈጥረው ስሜት ወጥቶ ሀገር እንደሀገር አሸናፊ የምትሆንበትን አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ መፍጠር ችሏል።

የሕዝባችንን ትናንቶች እና ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገዎችንም የሚገዳደረውን የነጠላ ትርክት እና ትርክቱ የፈጠረውን ግራ መጋባት እና ማኅበረሰባዊ ስብራት መጠገን የሚያስችል የጋራ ትርክቶችን እና ሀገራዊ እሴቶችን በማጎልበት ሀገረ መንግሥቱን በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም ረጅም መንገድ ተጉዟል።

በኢኮኖሚው ዘርፍም ዘላቂ ብልፅግናን፤ የሽግግር ወቅት ተገማች ፈተናዎችን ታሳቢ ያደረገ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ያጋጠሙንን ክፉ ቀናት ጭምር መሻገር ያስቻለ፤ የመጪዎችን ትውልዶች ዕጣ ፈንታ ብሩህ ማድረግ የሚያስችል የኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመንደፍ በብዙ መልኩ ስኬታማ መሆን ችሏል።

ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው ሀገራዊ ጉዞ በሁሉም መንገድ ስኬታማ እንዲሆን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀርጾ ወደ ተግባር በመግባት ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን ከማስመዝገብ ባለፈ፤ በምግብ እህል ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ውጤት አስመዝግቧል።

ብሔራዊ ተቋማት ሀገረ መንግሥቱን አጽንተው ከማቆም ባለፈ ለውጡን መሸከም የሚችሉበትን አቅም ለመፍጠር ብዙ ተሠርቷል። በተለይም በተወሳሰበ ችግር ውስጥ የነበሩትን የመከላከያ፤ የፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማት ዘመናዊነትን ተላብሰው በአዲስ መልክ እንዲገነቡ አድርጓል። በዚህም በሀገር ላይ ተደቅኖ የነበረውን ስጋት መሻገር አስችለዋል።

በነዚህ የለውጥ ዓመታት ውስጥ በብዙ ያልተሻገርናቸው የመልካም አስተዳደር፤ የኑሮ ውድነት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ወዘተ ችግሮች የለውጡን የጉዞ ፍጥነት ከመፈታተን ባለፈ የሕዝባችን የቅሬታ ምንጮች መሆናቸው ይታወቃል ።

ዛሬ የሚጀመረው የፓርቲው ጉባዔም የፓርቲውን ስኬታማ ጅማሬዎች በላቀ መንገድ ማስቀጠል፤ አሁንም ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ሀገራዊ ችግሮችን በተሻለ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ስትራቴጂክ ዕይታዎች እና የውሳኔ ሀሳቦች የሚቀርቡበት እና ለተፈጻሚነቱ የፓርቲው አባላት ቁርጠኝነት የሚንፀባረቅበት እንደሚሆን ይታመናል!

አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You