የኢትዮጵያ ስፖርት ትልቁ ፈተና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ብዙዎችን ያስማማል። የዘርፉ አስተዳደራዊ ችግር የሚመነጨው ደግሞ እውቀት፣ ልምድና ቀናዒ አመራር በየተዋረዱ ማግኘት አለመቻሉ መሆኑ አያከራክርም። በዚህም ምክንያት ከሠላሳ በላይ የሚሆኑት የተለያዩ የስፖርት ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች በብዙ መልኩ ከማደግ ይልቅ ወደ ኋላ እየተጓዙ እንደሚገኙ ማደባበስ አይቻልም።
እነዚህ የስፖርት ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች ላለማደጋቸው ትክክለኛ አመራር ማጣታቸው የአንበሳውን ድርሻ ቢይዝም ከዚያ በፊት አንድ ትልቅ ችግር እንዳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግልፅ እየሆነ ይገኛል። ይህም ግለሰቦች ስፖርቱን በመሪነት ለማገልገል ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ የሚያደርጋቸው የስፖርት ማኅበራት የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈፃሚ አባላት የምርጫ ሥርዓትና ሂደት እንዲሁም የተጠያቂነት ጉዳይ ነው።
የተለያዩ የስፖርት ማኅበራት ሁነኛ አመራር እንዳያገኙ እንቅፋት ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ስፖርቱን ለመምራት ለምርጫ ዕጩ አድርገው የሚያቀርቧቸው ግለሰቦች የእውቀትና አቅም ማነስ እንዲሁም ከዘርፉ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ሁሌም እንዳስወቀሳቸው ነው። ጥያቄው ግን ይህ ብቻ አይደለም፣ ስፖርቱን ለመምራት ለምርጫ ለሚቀርቡ ሰዎች ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወክለው ድምፅ የሚሰጡ ግለሰቦች አካሄድ ያልተፈተሸ አነጋጋሪ ጉዳይ ነው።
ስፖርቱን ለመምራት በምርጫ ዕጩ ሆነው የሚቀርቡ ግለሰቦች ተገቢ ላይሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ተገቢ ያልሆኑ ሰዎች ወደ ኃላፊነት እንዳይመጡ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚወከሉ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ባላቸው ድምፅ የመቅጣት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ይሁን እንጂ ይህን ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ስፖርቱን ለመምራት ተገቢ የሆኑ ሰዎች ከመንገድ ሲቀሩ ይታያል። ይህ ማለት የስፖርቱ አስተዳደራዊ ችግሮች የሚመነጩት ወደ ኃላፊነት ከሚመጡ ግለሰቦች አስቀድሞ ተገቢ ላልሆነ ሰው ድምፅ ከሚሰጡ አካላት ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አትሌቲክሱን ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚመራ ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማድረጉ ይታወሳል። በዚያ ምርጫ ላይ አንድ አነጋጋሪና የስፖርት ማኅበራቶቻችንን ምርጫዎች ቆም ብለን እንድንጠይቅ ያደረገ ክስተት ነበር። ይህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ዕጩ ያደረጋቸው ግለሰብ የወከላቸው ከተማ አስተዳደር ካለው ሁለት ድምፅ አንድ እንኳን አለማግኘታቸው ነው። አንድ ከተማ አስተዳደር ወይም ክልል በመሰል ምርጫዎች ላይ ዕጩ ሲያቀርብ ራሱ ለምርጫ ዕጩ አድርጎ ላቀረበው ግለሰብ ድምፅ እንደሚሰጥ አያከራክርም። ለራሱ ዕጩ ድምፅ ከነፈገ ግን መጀመሪያም ዕጩ ባደረገው ግለሰብ ላይ እምነት የለውም ወይም በእንዝላልነት ነው ዕጩ አድርጎ ያቀረበውና ሊያስጠይቀው ይገባል።
በዚህ ረገድ ክልሎችም ይሁኑ ከተማ አስተዳደሮች እንዲህ አይነት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ይፈፅማሉ ተብሎ አይታሰብም። ይህ ለራሱ ዕጩ ድምፅ ወደነፈገው ግለሰብ ጣት እንዲጠቆም የሚመራ ጠንካራ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር፣ የአንድን ክልልና ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ኃላፊነት ተሸክመው ድምፅ የሚሰጡ ግለሰቦች የወከሉትን አካል ፍላጎት ገሸሽ አድርገው የራሳቸውን ፍላጎት ያራምዳሉ ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል። በግለሰብ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ኃላፊነት ደግሞ ለሙስናና ለሌሎች የተሳሳቱ ውሳኔዎች የተጋለጠ መሆኑ ግልፅ ነው። “የስፖርት ማኅበራት ምርጫዎች ላይ ድምፅ በርከት ባለገንዘብ ይገዛል ይሸጣል” የሚሉ ቅሬታዎችንም የስፖርት ቤተሰቡ ከጥርጣሬ በዘለለ እንዲመለከት ገፊ ምክንያት ሆኗል።
ይህ ችግር በአትሌቲክሱ ምርጫ ላይ የአዲስ አበባው ዕጩ ከወከላቸው ከተማ አስተዳደር ሁለት ድምፆች አንድም ባለማግኘታቸው ገሐድ ወጣ እንጂ የሁሉም የስፖርት ማኅበራት የምርጫ ሂደትና ዕጣ ፋንታ ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ ብዙ ማሳያ መደርደር ይቻላል።
የስፖርት ማኅበራት ምርጫዎች እንደማንኛውም ምርጫ ድምፅ አሰጣጡ በሚስጥር ነው። ማን ለማን ድምፅ እንደሰጠ ሊታወቅ አይቻልም። ሰሞኑን በአትሌቲክሱ ምርጫ ላይ የአዲስ አበባው ዕጩ ቢያንስ ከከተማው ከሚጠብቁት ሁለት ድምፅ አንዱንም አለማግኘታቸው ነው ጉዳዩን ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው። ምናልባትም እኚህ ዕጩ ከወከላቸው አካል ውጪ ሁለት ድምፅ አግኝተው ቢሆን ኖሮ ይህን ጉዳይ ቆም ብለን ለማጤን ዕድሉን ባላገኘን ነበር።
በስፖርት ማኅበራት ምርጫዎች ላይ ግለሰቦች የወከሉትን አካል አቋምና ፍላጎት ትተው የራሳቸውን ሃሳብ ቢያራምዱ የሚጠየቁበት ሕጋዊ አግባብ አለመኖሩም አሠራሩን ለዚህ የተጋለጠ አድርጎታል። በአትሌቲክሱ ምርጫ የአዲስ አበባው ዕጩና የከተማውን ድምፅ አለማግኘት በተመለከተም ድምፅ እንዲሰጥ የተወከለው ግለሰብ እየታወቀ የከተማው ስፖርት ቢሮ ርምጃ ሲወስድ አለመታየቱ ለዚህ ማሳያ ነው። በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ተሻሽሎ በወጣው የስፖርት ማኅበራት ማቋቋሚያ መመሪያ ላይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ የሰፈረ አንቀፅ ወይም ደንብ የለም። ያም ነው ጉዳዩን በቀጣይም ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው።
ይህ በብሔራዊ የስፖርት ማኅበራት ምርጫ ላይ ተወስኖ የሚቀር ችግር አይደለም። ከታች እስከ ላይ ባለው የስፖርት መዋቅር በየደረጃው ችግር እንዳለ አመላካች ነው። ይህም የሀገሪቱ ስፖርት በተመሳሳይ መንገድ የሚጓዝበትን አቅጣጫ መቀየር ካልተቻለ ወደ ፊት ያለውንም ተስፋ እንዳያጨልም ስጋት ነው።
ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወክለው ስፖርቱን ለመምራት በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ ድምፅ የሚሰጡ ግለሰቦች ድምፅ የሚሰጡት በወከላቸውን አካል ፍላጎት መሠረት ነው ወይስ በራሳቸው የግል ስሜትና ፍላጎት? የሚለው ጉዳይ የስፖርት ማኅበራት ምርጫዎች እንዲሁም ድምፅ ሰጪዎች ያልተገለጠ ገመናና የስፖርት ቤተሰቡም ጥያቄ ነው።
ልዑል ከካምቦሎጆ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም