በክልሉ በ320 ወረዳዎች የዲጂታል ፓርክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሯል

አዲስ አበባ፡- በክልሉ የዲጂታል ትምህርትን ለማስፋፋት ከአምስት ሚሊዮን ኮደር ኢኒሼቲቭ ጋር ተያይዞ ከ320 በላይ ባሉ ወረዳዎች ላይ የዲጂታል ፓርክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ተጠሪ ካሣሁን ገላና (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ የዲጂታል ትምህርት የመማር ማስተማር ሥራው በተለያየ መልኩ የሚያግዝ ነው። ተማሪዎች ምንም አይነት ማስታወሻ (ኖት) ሳይዙ በቀጥታ እንዲማሩ የሚያስችላቸው ነው። በዲጂታል የተሰጣቸውን ትምህርትም ስካን በማድረግ ወስደው ቤታቸው የሚያነቡበትን ዕድል ያመቻቻል።

በተጨማሪም የሚሰጡት ትምህርቶች በተመረጡ መምህራን ስለሆነ ሁሉም በእኩል ደረጃ ትምህርቱን እንዲከታተሉ ያደርጋል ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ትምህርቱ በድምፅና በምስል ተቀርፆ የሚቀመጥ በመሆኑም ሌሎች ቦታዎች ጭምር በመውሰድ ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲያገኙት ያስችላል ብለዋል።

እስከ አሁን ባለ መረጃ በዲጂታል ትምህርት በክልሉ 317 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሚ መሆናቸው የሚያስረዱት ኃላፊው፤ ክልሉ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የስማርት ክላሶችን ጭምር እንደጀመረና ይህም ተግባራዊ እየተደረገ ያለው በልዩ ትምህርት ቤቶችና በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ እንደሆነ አመላክተዋል።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች ቁጥር በየጊዜው የሚጨምር ቢሆኑም አሁን ላይ ባለው መረጃ እንደ ኦሮሚያ ክልል በመጀመሪያው ዙር 41ዱ ላይ የስማርት ክላሶችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሞከረ እንደሆነም አብራርተዋል።

እንደ ኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በስማርት ክላስ በኩል አሁን ላይ በአንድ ትምህርት ቤት ወደ 82 ክፍሎች እንዲታቀፉ ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ካሣሁን (ዶ/ር)፤ ሁሉም ላይ በዲጂታል ትምህርት (ስማርት ክላስ)ን ለማስጀመር ያልተቻለበት ምክንያት ትምህርት ቤቶቹ ከሌሎች ጋር ተደርበው የሚሠራባቸው በመሆናቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በክልሉ የስማርት ክላስ ምሥረታን በተመለከተ ደረጃ በደረጃ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀው፤ በዘንድሮው ዓመት በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የመሣሪያና መሰል የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተከላ እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሥራውን እውን ለማድረግም መብራትና ኢንተርኔት ያላቸው የሌላቸው በሚል ትምህርት ቤቶቹ መለየታቸውን አውስተው፤ ስማርት ክፍሎች ቢቀሩም መደበኛ ክፍሎችን በማዘጋጀት የተወሰኑ ኮምፒውተሮችን በማስገባት ዲጂታል ትምህርት የሚጀምሩበት ሁኔታም እየተመቻቸ እንደሆነ አመላክተዋል።

ስማርት ክፍሎች የተማሪዎችን ክህሎት ከፍ ከማድረጉ ባሻገር የፈጠራ እንቅስቃሴያቸውን በእውቀት እንዲመሩት፤ አዳዲስ ነገሮችን እንዲያዩ ያስችላቸዋል ያሉት ካሣሁን (ዶ/ር)፤ በተጨማሪም የሳይበር ክበቦችን በማቋቋም የእርስ በእርስ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ፤ በጋራ የዲጂታል አቅማቸውን እንዲያሳድጉም፤ ተማሪዎች ለቀጣዩ ዓለም ውድድር ብቁ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

እንደ ክልል ይህ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል። ሥራው ጅምር ላይ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ብለዋል።

እንደ ካሣሁን (ዶ/ር) ገለጻ፤ እንደ ኦሮሚያ ክልል ካሉት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የዲጂታል ትምህርትን ተግባራዊ ማድረግ የተቻለው በአንድ ሦስተኛው ብቻ ነው። በቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው። አንዱ በቅርቡ ይፋ ከተደረገው 5ሚሊዮን ኮደር ኢኒሸቲቭ ጋር ተያይዞ እየተሠራ ያለው ተግባር ነው።

በክልሉ ከ320 በላይ ወረዳዎች እንዳሉ ገልጸው፤ በእያንዳንዱ ወረዳ ዲጂታል ፓርክ ማቋቋም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ይህም ከ20 በላይ ኮምፒውተር ያለው ክፍል በማቋቋም እያንዳንዱ ወረዳ አንድ ማዕከል ኖሮት ተማሪዎች የዲጂታል ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You