በሲዳማ ክልል በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጸመ

አዲስ አበባ፡– በሲዳማ ክልል በምሥራቃዊ ሲዳማ ዞን በቦና ዙሪያ ወረዳ በገላና ወንዝ ድልድይ በደረሰው አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ትናንት በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን ገልፀዋል።

በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰብና ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል። የክልሉ መንግሥት ለሟቾቹ ቤተሰቦች አራት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ሁላችንም ለሟቾቹ ቤተሰቦች ድጋፋችንን አጠናክረን ልንቀጥልና ልናጽናናቸው ይገባልም ብለዋል።

በሲዳማ ክልል ምሥራቅ ሲዳማ ዞን ቦና ዙሪያ ወረዳ ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከ 70 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል። አደጋው ገላና ወንዝ ድልድይ ላይ ሰዎች አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ የጭነት መኪና መንገድ ስቶ ወደ ወንዝ በመግባቱ እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል።

ተጎጂዎችን የመርዳት እና ሟቾቹን የማፈላለግ ሥራ በአካባቢው ማኅበረሰብ እና በመንግሥት አካላት እየተከናወነ መሆኑ ይታወሳል። ተጎጂዎች በቅርበት ወደሚገኘው ቦና አጠቃላይ ሆስፒታል በመወሰድ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

የትራፊክ አደጋ የደረሰበት አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ሠርገኞችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የአደጋው ምክንያት እየተጣራ መሆኑ ተመላክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You