አዲሱ የካዛንቺስና አካባቢው የልማት ተነሺዎች አዲስ መንደር

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ ቀጥሏል:: ከተማዋና ነዋሪዎቿ በአንደኛው ዙር የኮሪደር ልማት ብዙ ለውጦችን ተመልክተዋል:: የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት እንዲሁ ገና ከአሁኑ ብዙ ለውጦችን ማመላከት እያስቻለ ነው::

በልማቱ ለከተማዋ መንገዶች በዓይነት በዓይነቱ ተገንብተውላታል፤ ሰፋፊ የተሽከርካሪ መንገዶች /ለዚያውም ደረጃቸውን የጠበቁ/ ተገንብተዋል፤ የቦሌ መገናኛ መንገድን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል:: የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጭምር የተገነቡባቸው አካባቢዎች ብዙ ናቸው፤ ለዚህም አራት ኪሎን ማየት ይበቃል:: ከዋናው መንገድ ወጣ ማለቱ ቢገጥም ሌሎች ውብ መንገዶችን ማግኘት ይቻላል::

ከተማዋ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጥቂት አካባቢዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው ባይተዋር የነበረችባቸው የሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች ጉዳይ አሁን ምላሽ ማግኘት ጀምሯል:: ለሳይክል ሳትታጭ የኖረችው ከተማዋ አሁን የሳይክል መንገድ ባለቤት ሆናለች:: አልታይ ያለው ሳይክሉ ነው፤ አረንጓዴ ስፍራዎች በመንገድ ዳርቻና በሰፋፊ ክፍት ቦታዎች ላይ በብዛት ተገንብተውላታል::

ምሽት ላይ እንድትደምቅ ያስቻሉ የመብራት ሥራዎችም ተሰርተዋል፤ መንገዶች፣ ህንጻዎች፣ ዛፎች ተንቆጥቁጠዋል:: ፋውንቴኖች እንደ አሸን ፈልተውባታል:: የቴሌ እና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች እንዲሁም የወንዝ ዳር ልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ እዚህ ደርሰዋል። ከየትኛውም በላይ ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ሲሠሩ ታይተዋል።

እስካሁን በተከናወነው የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን እንደ ስሟ የማድረግ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማሳየት ጀምረዋል። ልማቱ ተጠናክሮ የቀጠለ እንደመሆኑ ገና ብዙ ለውጦች ይጠበቃሉ::

የኮሪደር ልማቱ በመንገድና በመሳሰሉት ልማት ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም:: ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስና ውብ እናደርጋታለን በሚል አስተዳደሩ ሲነሳ ሰብዓዊ ወይም ሰው ተኮር ልማትንም ታሳቢ አድርጎ ነው:: የተጎሳቆለው የከተማዋ ነዋሪም አኗኗር መሆኑ ተለይቶ ነው ወደ ሥራ የተገባው::

ለዚህም በልማት ተነሺዎች ላይ በስፋት ተሠርቷል፤ እየተሠራም ነው:: ቀደም ሲል ከነበሩበት የተጎሳቆለ መኖሪያ ቤት ወደ ተሻለ መኖሪያ ቤት የገቡት አያሌ ናቸው፤ ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ተነሺዎቹ ጭምር መስክረዋል:: ተነሺዎች በህልማቸውም አይተውት የማያውቁት ቤት ውስጥ መኖር መጀመራቸውን እየመሰከሩ ናቸው::

ከእነዚህ ተነሺዎች መካከል የካዛንቺስ ተነሺዎች ይጠቀሳሉ:: ከካዛንቺስ እና አካባቢዋ በልማት ለተነሱ አባወራዎች እና እማወራዎች በተለያዩ አካባቢዎች ምትክ ቦታ፣ የጋራ መኖሪያ ኮንደሚኒየም ቤት እንዲሁም የመጠለያ ቤት ተሰጥቷቸዋል። መንግሥትም የልማት ተነሺዎቹን እድር እና እቁብ የመሳሰሉ ማህበራዊ ትስስር በማያፈርስ ሁኔታ በአንድ አካባቢ የማስፈር ሥራዎችን በጥናት ላይ በመመስረት እያከናወነ ይገኛል። ለዚህም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ገላን ጉራ መንደር የገቡት እነዚህ የካዛንቺስ የልማት ተነሺዎችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል::

በዚህ መንደር በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ባለፈው ሳምንት በስፍራው ተገኝተን ተመልክተናል:: እኔ እስከዚህ ቀን ድረስ በሚገባ የማውቀው የኮሪደር ልማት የተከናወነባቸውን አካባቢዎች ብቻ ነበር:: ከሥራ ጋር ተያይዞ በዚህ መንደር መገኘቴ የልማት ተነሺዎች ያሉበትን ሁኔታ እንድረዳ አስችሎኛል::

እኛ ወደ መንደሩ የተጓዝነው በቦሌ ቡልቡላ ወደ ኮዬ ቂሊንጦ በሚወስደው ሰፊና ደረጃውን የጠበቀ መንገድ አድርገን ነው:: አካባቢው በመልማት ላይ የሚገኝ ነው:: ኦቪድ የሚሠራቸው 60 ሺ ቤቶች የሚሠሩት በዚህ አካባቢ ነው::

ኦቪድን በስተግራ አርገን ለተነሺዎቹ ወደ ተከተመው ገላን ጉራ ደረስን:: በመንደሩ በርካታ የኮንደሚኒየም ህንጻዎች ይታያሉ:: የከተማ አስተዳደሩ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአካባቢው አንድ ሺ ሁለት መቶ ያህል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፤ ምንም ቤት ያልነበራቸውና በቀበሌ ቤቶች ላይ ተለጣፊ ቤቶችን ሰርተው ለመኖር ተገደው ለነበሩ መጠለያ በሚል የተገነቡ ቤቶችን በመጨመር አጠቃላይ አንድ ሺህ 500 የሚሆኑ ቤተሰቦችን በመንደሩ ለማስተናገድ ተችሏል።

ተነሺዎቹ ወደ መንደሩ እንደገቡ ልጆቻቸው በጊዜያዊ ቤቶች ሲማሩ ቆይተው ነበር:: አሁን ሶስት ትምህርት ቤቶች ተገንብተውላቸዋል:: የአጸደ ህጻናት፣ የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የአጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው ተገንብተው በቅርቡ ሥራ የጀመሩት::

ህንጻዎቹን ተዘዋውረን ጎብኝተን፣ ተማሪዎችንና የትምህርት ቤቶቹን ኃላፊዎች እንዲሁም ነዋሪዎችን አነጋግረናል:: ተነሺዎቹ ወደ መንደሩ እንደገቡ በርካታ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንደነበራቸው እነዚሁ የህብረተሰብ ክፍሎች ነግረውናል:: ከማህበረሰቡ ጥያቄዎች መካከል የትምህርት ቤቶች ጉዳይ አንዱ እንደነበር ነግረውናል፤ ይህም ጥያቄ በፍጥነት ምላሽ በማግኘቱ ተደስተዋል::

በመሀል ከተማ አብዛኞቹ መንደሮች የሌሉ የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራዎች ሌሎች ለልማት ተነሺዎቹ በዚህ መንደር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ናቸው:: እኛም በአንዱ ሜዳ ገብተን ኳስ ለማንጠባጠብ ቃጥቶን ነበር:: እጅግ ውብ ሜዳዎች ናቸው:: የእንጀራ መጋገሪያ እንዲሁም የዳቦ መጋገሪያ ህንጻዎች ሌሎች በመንደሩ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ናቸው::

ለነዋሪዎች የሥራ እድል የሚፈጥሩ እንዲሁም መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ መደብሮችም በብዛት ይታያሉ:: በእዚህም ነዋሪዎች በአዲሱ መንደራቸው የሚሠሩበት ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። ይህም የልማት ተነሺዎች አንዱ ጥያቄ የነበረው የሥራ እድል ፈጠራ ጉዳይ በተለያዩ የተቀናጀ መሠረተ ልማት ሥራዎች ምላሽ እያገኘ መሆኑን ይጠቁማል። የውሃና የመብራት ጥያቄዎች አልሰማንም፤ ከዚህ ይልቅ መድኃኒት ቤት፣ የባንክ፣ የጤና ተቋማት ጥያቄዎች አሏቸው:: እነዚህም በቅርቡ ሊሟሉላቸው የሚችሉ ስለመሆናቸው የቀደሙት መሠረተ ልማቶች የተዘረጉበት ፍጥነት ያመለክታል::

የከተማ አስተዳደሩ ይህን የመሠረተ ልማት ጥያቄ እየመለሰ ያለው የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት በማካሄድ ነው:: አንዳንዶቹ መሠረተ ልማቶች ከተያዘላቸው የግንባታ የጊዜ ሰሌዳ በፊት የተጠናቀቁ ናቸው:: በቀጣይም ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማካሄድ ጊዜ የማይወሰድ ስለመሆኑ ይህ አፈጻጸም ያመለክታል::

ሥፍራው የአርሶ አደሮች ነበር፤ እነዚህን አርሶ አደሮች በማንሳት ነው ይህን የመሰለ መንደር መመሥረት የተቻለው:: ለአርሶ አደሮቹም መኖሪያ ቤቶች እየተገነባላቸው ስለመሆኑ በቅርቡ ከመገናኛ ብዙሃን ሰምቻለሁ:: ይህም ሌላው ትልቅ ልማት ነው::

የኮሪደር ልማቱ መሀል ከተማዋን ብቻ አይደለም እየቀየረ ያለው:: በመሀል ከተማዋ በአስከፊ ሕይወት ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎችንም ሕይወት ነው የሚለውን በተግባር ማየት ችለናል:: የተነሺዎቹ ሌሎች ጥያቄዎች ሲመለሱ፣ ተነሺዎቹ በራሳቸውም አካባቢያቸውን ማልማት ሲጀምሩ ደግሞ የነዋሪዎቹ ሕይወት፣ የአካባቢውም ገጽታ ምን ያህል ሊለወጥ እንደሚችል መገመት አይከብድም::

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You