“የአክሲዮን ገበያ የኢንቨስትመንት ማሳለጫ ነው” – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ቦርጂ (ዶ/ር) በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ተወልደው ያደጉት በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ ሲሆን፣ ልዩ ቦታው ሰፈረ ኬላ በመባል የሚታወቅ ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው በተወለዱት አካባቢ ሰፈረ ኬላ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፣ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን የተማሩት ደግሞ በአለታ ወንዶ ከተማ ነው። ዘጠነኛና 10ኛን ዲላ ከተማ የተከታተሉ ሲሆን፣ 11ኛ ክፍልን ለመቀጠል ግን ካሉበት ክልል ርቀው ወደ ምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ማቅናት የግድ በመሆኑ ወደ ጅግጅጋ ከተማ አቅንተው 11ኛ ክፍልን ተማሩ።

እዚያው ምሥራቁን አካባቢ ሳይለቁ ድሬዳዋ ደግሞ 12ኛ ክፍልን መማር ችለዋል። እኚህ የዛሬው የዘመን እንግዳችን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ቦርጂ (ዶ/ር) ናቸው።

እንግዳችን በደርግ ዘመን 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ከመቀጠላቸው በፊት የዚያኔው ተማሪ ብርሃኑን በ1969 ዓ.ም ለአየር ኃይል ትምህርት ወደራሽያ አቀኑ። እስከ 1971 ዓ.ም ድረስም በዚያው በራሽያ ቆዩ። ልክ ራሽያ ቆይተው ወደሀገራቸው እንደተመለሱም የተመደቡት አሰብ ነበር። አሰብ ለመማር እምብዛም ምቹ ስላልነበር 11ኛ ክፍል ላይ ያቋረጡትን ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም።

ነገር ግን በአየር ኃይል በኩል የተሰጣቸውን የአሰብ የቆይታ ግዳጃቸውን ጨርሰው ወደ ጅግጅጋ በማቅናታቸው 11ኛ ክፍል እዛው መማር ቻሉ። የጅግጅጋ ግዳጃቸውን እንዳጠናቀቁ የተዘዋወሩት ወደ ድሬዳዋ ነበርና 12ኛ ክፍልን ደግሞ በዚያው ለመማር በቁ። በወቅቱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱት በ1982 ሲሆን፣ ያመጡትም ነጥብ ሶስት ነጥብ ስድስት ነበር። ይህን ከፍተኛ ነጥብ ይዘው በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥት ከመውደቁ በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመቀላቀል በቁ።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት ነው። በኋላ ላይ ግን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲሰሩ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ማርኬቲንግ ማኔጅመንትን ነው። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት በሰሜን ህንድ ሲሆን፣ ሶስተኛ ዲግሪያቸውንም በዚያው በህንድ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ነው።

እንግዳችን፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቡት እኤአ 2001 ላይ ነው። በዩኒቨርሲቲ መምህርነት 25 ዓመት ያህል ማገልገል ችለዋል። የፕሮፌሰርነትን ማዕረግ ካገኙ አስር ያህል ዓመት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ስፔሻል ያደረጉት የትምህርት ዓይነት ደግሞ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት የሚስተምሩትም የማርኬቲንግ ተማሪዎችን ነው። ምርምርም የሚያካሔዱት በዚሁ በማርኬቲንግ ዘርፍ ላይ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ አርቲክሎችን ለሕትመት ያበቁ ናቸው። ለሕትመት ያበቁት አርቲክል ወደ 17 ያህል የሚጠጋ ሲሆን, Impact of Liberalization on Ethiopianበሚል ርዕስ አንድ መጻሐፍም ለንባብ ማብቃት ችለዋል። እንግዳችን እንዳሉት ከሆነ፤ በመላ ኢትዮጵያ በማርኬቲንግ ፕሮፌሰር ያሉት እርሳቸው ብቻ ናቸው። የሚያስተምሩትም የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ነው። አዲስ ዘመን እኚህን አንጋፋና በዘርፉ ከፍተኛ ምሁር እና ተመራማሪ የሆኑትን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ቦርጂ (ዶ/ር)ን የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በዋናነት ምርምር ሲያካሄዱ የነበረውና አሁንም እያካሄዱ ያሉት ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ላይ ነው፤ በዚሁ ዘርፍ ውስጥ የአክሲዮን ገበያ ሲባል ምን ማለት ነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የአክሲዮን ገበያ (ስቶክ ማርኬት) ሲባል ትርጓሜው ሰፊ ነው። በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል ግን አክሲዮን ለመሸጥና ለመግዛት የተመዘገቡ ኩባንያዎች ማለትም በይፋ የሚሸጡ ኩባንያዎች (Publicly Traded Companies) እንደ ማለት ነው። ይህ ማለት በሕጋዊነት የተመዘገቡ እና ሕጋዊነት የተሰጣቸው አካላት ናቸው። በጥቅሉ ኩባንያዎች የሚሸጡበትና የሚገዙበት ገበያ ማለት ነው።

በይፋ የሚሸጡ ኩባንያዎች (Publicly traded companies) በጣም ሰፊ ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች ማሟላት የሚገባቸው ነገሮች አሉ። እነዚያን ሁሉ አሟልተው ደግሞ አክሲዮኑን እንዲሸጡና እንዲገዙ ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት የሚባል አለ፤ ይህ ማለት ለምሳሌ ልክ እንደኒዮዎርክ ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት እንዲሁም ለንደን ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት የሚባለው ዓይነት ነው። እነዚያ ተቆጣጣሪ አካላት (Regulatory bodies) ናቸው። ተቆጣጣሪ አካላት ሲባል ደግሞ ለስቶክ ማርኬት ሕግ የሚያወጡ ናቸው። እንደዚያ ሲባል ደግሞ ኩባንያዎች አክስዮናቸውን የሚሸጡበትና የሚገዙበት ገበያ ማለት ነው።

አክሲዮን የሚገዙት እና የሚሸጡት ኢንቨስተሮች ብቻ አይደሉም፤ ሕዝብም ይገዛል። ስለዚህ ገበያው ክፍት ነው ማለት ነው። ክፍት ገበያ ነው ሲባል በሩ የተዘጋ አይደለም ማለት ነው፤ አንድ አካል አክስዮን ገዝቶ ገበያ ውስጥ በሚቆይበት ጊዜ ሁኔታውን አይቶ የሚያሰጋው ከሆነ ወዲያኑ ለሌላ ሰው መሸጥ ይችላል።

የአክሲዮን ገበያ በጣም ትርፋማ ስለሆነ ሌላው ማለትም ገዥው አካል ሳያቅማማ ይገዛል። በርግጥም ገዥዎችም ሆኑ ሻጮች ስቶክ ማርኬቱን ለመሸጥና ለመግዛት ገበያውን ማጥናት ይጠበቅባቸዋል። ገበያውን ከወዲሁ መገመት ያስፈልጋል። ገበያው እያደገ ነው ያለው ወይስ እየወደቀ ነው ያለው ወይ? የሚለው መጠየቅ አለበት፤ እየወደቀ ካለ ደግሞ የስቶክ ማርኬቱ ዋጋ ሊረክስና ሊቀንስ ይገባል። ስለዚህ ይህን

“የአክሲዮን ገበያ የኢንቨስትመንት ማሳለጫ ነው”

ከወዲሁ መገመት የሚችል ሁሉ ስቶክ ማርኬቱን ኢንቨስተሮችም ሌላው ሕዝብም ሊገዛ ስለሚችልና ከገዛም በኋላ ደግሞ መልሶ ሊሸጥ ስለሚችል በጣም ጥሩ የሚባል ገበያ ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የአክሲዮን ገበያ ዋና ዓላማው ምንድን ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የስቶክ ማርኬት ዓላማ ገንዘብ ማመንጨት ነው። ይህ ስቶክ ማርኬት በኩባንያዎች ሊሰበሰብ ይችላል። አንድ ኩባንያ ሌላ ኢንቨስትመንት ለማካሔድ ወይም ደግሞ ለመሥራት በሚፈልግበት ጊዜ ገንዘብ በእጁ ላይኖር ይችላል፤ በዚያን ጊዜ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ስቶክ ሊሸጥ ይችላል። ልክ ቀደም ሲል እንደተደረገውና መንግሥት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድን እንደሸጠው ዓይነት ሊሆን ይችላል። ይህ የዓባይ ግድብ ቦንድ የተሸጠበት ዓላማ መንግሥት ከሕዝብና ከኢንቨስተሮች ለመበደር በማሰቡ ነው።

ለምሳሌ አንድ ሰው ፋብሪካ የሚያቋቁም ከሆነ ስቶክ ይሸጣል፤ ስቶክ የገዛው አካል የዚያ የሚቋቋመውን ፋብሪካ የሆነች ያህል ባለቤትነትን ገዝቷል ማለት ነው። ለአብነት ያህል እኔ አንድ የስሚንቶ ፋብሪካ ማቋቋም እፈልጋለሁ ልበል፤ ነገር ግን ገንዘብ ደግሞ የለኝም። ገንዘብ ስለሌለኝ ለሕዝብ ስቶክ ሸጬ ገንዘብ ማሰባሰብ አለብኝ ማለት ነው። ስቶኩን የገዛው ሕዝብ ለዚያ ለሲሚንቶ ፋብሪካ የተወሰነውን ያህል ማለትም በገዛው ስቶክ ልክ ባለቤት ነው ማለት ነው። ስለዚህም ገንዘቡ ለሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤቱ፤ በዚህ መልክ የሚሰበሰብ ይሆናል። ስለዚህ የስቶክ ማርኬቱ ዓላማ ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማሰባሰብ የሚያስችል ነው።

አዲስ ዘመን፡- የአክሲዮን ገበያ ባህሪያት ምን ምን ናቸው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የስቶክ ማርኬት ባህሪያት ናቸው ከሚባሉት አንዱ ለምሳሌ የሚሸጠው ስቶክ በዚያ በሚሸጠው ኩባንያ ውስጥ ባለቤትነት እንዲኖረው ማድረጉ ነው። ገዥው ግለሰብ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ኢንቨስተር ሊሆን ይችላል። አንድ ስቶክ በሚገዛበት ጊዜ ስቶኩን በሚሸጠው ኩባንያ ውስጥ የራሱ የባለቤትነት መብት ይኖረዋል ማለት ነው።

ሌላው ደግሞ ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት የሚባለው ነው። በዚህ በስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት ውስጥ ተቆጣጣሪ አካል (Regulatory body) አለ። እንዲህ ሲባል ይህ አካል ገበያውን የሚቆጣጠር ነው ማለት ነው። ገበያውን መቆጣጠር ማለት ደግሞ አንደኛ ገበያው ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተሳለጠ እንዲሆን ማድረግ ነው፤ በገበያው ውስጥም ማጭበርበር እንዳይኖርም ቁጥጥር ያደርጋል። በሻጭ እና በገዥ መካከልም መተማመን እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዝ ነው። ለምሳሌ ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት የሚባለው ለምሳሌ ቀደም ብዬ ልጠቅስልሽ እንደሞከርኩት ኒዮዎርክ ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት ወይም ለንደን ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት የሚባል አለ፤ እነዚህ ስቶክ የሚሸጡት በእነዚያ ማርኬት ዝርዝር ውስጥ የተመዘገቡ መሆን አለባቸው። በዚያ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ከሆኑ ተዓማኒያን ናቸው ማለት ነው።

ለምሳሌ አንዳንድ አካላት አዲስ አበባ ውስጥ ሪል ስቴት በሚል ቤት እንሠራለን ብለው ገንዘብ ከሕዝብ ከሰበሰቡ በኋላ አድራሻቸውን የሚያጠፉ እንዳሉ ብዙ ጊዜ ይሰማል። ይህ ግን እንደዚያ ዓይነት አይደለም። ሻጮቹ በስቶክ ማርኬቱ ዝርዝር ውስጥ የገቡ ስለሆነ በማጭበርበር የትም መድረስ ስለማይችሉ ተዓማኒነት ያለው ነው። ከዚህ የተነሳ አክስዮን ገበያ (ስቶክ ማርኬቱ) ተዓማኒነት ያለው ነው። ለምን ከተባለ በስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት ውስጥ ዝርዝራቸው የተካተተ በመሆኑ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የስቶክ ማርኬት የአካሄድ ስልቱ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የስቶክ ማርኬት አካሄድ ግልጽ ነው። ማርኬት መካኒዝሙን በተመለከተ፤ ማንኛውም ባለሥልጣን ሆነ መንግሥት ማርኬቱን አያስተጓጉለውም። የስቶክ ማርኬቱ ዋጋ የሚወሰነው በአቅርቦቱና ፍላጎቱ ላይ ነው። ማርኬቱ ዋጋ የሚመራው በእነዚህ በሁለቱ ነው። ለምሳሌ ገበያ ውስጥ ዋጋው የሚወርደውና የሚጨምረው በአቅርቦቱና ፍላጎቱ አማካይነት ነው።

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ስቶክ ማርኬት ይቋቋማል ሲባል ማንም ምንም ጫና መፍጠር አይችልም። መንግሥት በዚያ ውስጥ ድርሻ አይኖረውም። የሚገዙ አካላት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላው አካል ጫና ነፃ የሆኑ ናቸው። ከማንም ነፃ ስለመሆናቸው ሊተማመኑ ይችላሉ ማለት ነው። ምክንያቱም ይህን መሸጥና መግዛት የሚችሉት ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬቱ ውስጥ ተመዝግበው ዝርዝራቸው ያሉ አካላት ናቸው።

ሌላኛው ስቶክ ማርኬት የኢንቨስትመንት ማሳለጫ (Investment vehicle) ነው ሊባል ይችላል። ይሁንና እንዲያ ማሳለጫ መሆን ሲገባው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢንቨስተሮች ወይም ኩባንያዎች ግን ለዚህ ለዚህ ዓይነት አካሔድ ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው አይደሉም።

እንዲያውም ስቶክ ማርኬት ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የነበረው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ ነው። ይሁንና በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመንም ቢሆን ገና በማቆጥቆጥ ላይ እያለ መንግሥት ስለወደቀ ሊቀጥል አልቻለምና ፈርሷል። ከእርሳቸው መንግሥት መውደቅ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ስቶክ ማርኬት የሚባል በጭራሽ አልነበረም። ስለዚህ አሁን እነዚህ ኢንቨስተሮች ስቶክ ማርኬት ለመግዛት የግድ ጉዳዩ ራሱ ሊኖር ይገባዋል ማለት ነው። የአክስዮን ገበያው ሲኖር ደግሞ ለኢንቨስተሮቹ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ዘዴ ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው። ለዚህም ነው ስቶክ ማርኬት የኢንቨስትመንት ማሳለጫ (Investment vehicle) ነው የሚባለው። ምክንያቱም ኢንቨስትመንትን ይፈጥራል።

የተመቻቸ ሁኔታ ያገኙት አካላት ስቶክ ማርኬት ይገዛሉ። ስቶክ ማርኬት ላይ ገንዘብ ይሰበሰባል። ገንዘብ የሚሰበሰበው ደግሞ ከኢንቨስተርና ከሕዝብ ነው። ከዚያ የካፒታል ቀመር ይሠራል። ወይም ደግሞ ካፒታል እንዲከማች ይደረጋል። የተከማቸ ካፒታል ለሌላ ኢንቨስተር በብድር መልክ ይሰጣል ማለት ነው። አንድ አካል ያን ብድር በሚወስድበት ጊዜ በመጀመሪያ ምን እንደሚሠራበት ያስጠናል፤ በዚህ ጊዜ መርቻንት ባንከር (Merchant banker) የሚባል አለ፤ መርቻንት ባንከር ማለት ለኢንቨስተሮች የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ አፈላልጎ እና የቢዝነስ ፕላን ሰርቶ ኢንቨስተሩን ከአበዳሪው ጋር የሚያገናኝ እንደ ማለት ነው። ስለዚህ እንደ እነዚህ ዓይነት ምቹ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ጊዜ ከዚያ ከተከማቸው ገንዘብ ይበደርና ይሠራል።

ለምሳሌ ኢንቨስተሩ ብድር ወሰደ እንበል፤ ብድር ከወሰደ በኋላ ማሸነሪዎችን ገዛ፤ ከዚያም ማሽን ብቻ መግዛት ሥራውን የሚያሳልጥለት ባለመሆኑ

 

ባለሙያዎችን ይቀጥራል። በድርጅቱ የተቀጠሩት ባለሙያዎችም የራሳቸውን ገቢ ማግኘት ይጀምራሉ። ካገኙት ገቢ ደግሞ የሚጠቀሙትን ተጠቅመው የሚተርፈውን (Discretionary income) ገንዘብ በባንክ ያስቀምጣሉ። ባንክ ደግሞ ልክ የዚህ ዓይነቱን የብዙዎቹን ሰብስቦ ለሌላ ኢንቨስተር ያበድራል። ሌላውም ኢንቨስተር በተመሳሳይ የራሱን ቢዝነስ ይከፍትና እንደዚያው በተመሳሳይ መልክ ይሄዳል። ሌሎችም እንዲሁ ደግሞ ይከተላሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያድጋል። ስለዚህ የአክስዮን ገበያ (ስቶክ ማርኬት) የኢንቨስትመንት ማሳለጫ ነው ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የስቶክ ማርኬት ዋናው ፋይዳ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የስቶክ ማርኬት አንደኛው ጠቀሜታ ካፒታል ምስረታው (capital for­mation) ነው። ማለትም የካፒታል ክምችትን መፍጠሩ ነው። ምክንያቱም የካፒታል ክምችት ባይፈጠር ኖሮ ኢንቨስተሩ የሚበደረው ነገር አይኖርም። ያዘጋጀው ጥሩ የሚባል የቢዝነስ ፕላን ቢኖረውም፤ ከፕላን ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ የሚሆነው ገንዘብ ሲኖር ነው። ገንዘብ የሚያበድረው ከሌለ ደግሞ ያንን ቢዝነስ ፕላን ማካሔድ አይችልም።

ስለዚህ የካፒታል ክምችት መፈጠር አለበት፤ የካፒታል ክምችት ደግሞ ከየት ነው የሚፈጠረው ከተባለ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ግለሰቦችና ኢንቨስተሮች አክሲዮን ሲገዙ ሲሆን፣ በዚያን ጊዜ የካፒታል ክምችት ይፈጠራል ማለት ነው። ክምችቱ ሲፈጠር ሌሎች መበደር ቻሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያሳድጋል። ስለዚህ ስቶክ ማርኬት አንደኛው ፋይዳ የካፒታል ክምችት መፍጠሩ ነው።

ሁለተኛው ጠቀሜታ የኢኮኖሚ እድገት ነው። ምክንያቱም የካፒታል ክምችት ሲኖር፤ ብድር ይፈጠራል፤ ብድር ተፈጠረ ማለት ደግሞ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ያደርጋል። ምክንያቱም ተበድሮ የሆነ ኢንቨስትመንት ይከፍታል። ኢንቨስትመንት ተከፈተ ማለት ደግሞ ባለሙያዎች ተቀጠሩ ማለት ነው። ባለሙያዎቹ ሠሩ ማለት ደግሞ ትርፋማ መሆን ቻሉ እንደማለት ነው። ከሠሩት ላይ እነርሱም መቆጠብ ይጀምራሉ። በዚህ ውስጥ የሥራ እድል ተፈጠረ ማለትም ጭምር ነው። የሥራ እድል ተፈጠረ ማለት ደግሞ ሠራተኛው ለመንግሥት የሥራ ግብር መክፈል ቻለ ማለት ነው። በዚህ ዓይነት ውስጥ መተላለፍ ሲቻል ኢኮኖሚው ያድጋል ማለት ነው።

ሌላው ደግሞ ለኢንቨስትመንት መልካም አጋጣሚዎች (Increase Investment Opportuni­ties) እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ኢንቨስተሩ የቢዝነስ ፕላን ካለው ይበደርና መሥራት ይችላል። ስለዚህም የስቶክ ማርኬት ውጤቱ ብዙ ኢንቨስትመንቶች መልካም አጋጣሚዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉም ጭምር ነው።

አዲስ ዘመን፡- የአክሲዮን ገበያው ቀጥተኛ የሆነ የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ የሚገለጸው እንዴት ነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ስቶክ ማርኬት የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስብ ነው። የውጭውንም ካፒታል ይስባል፤ እንዲሁም አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የስቶክ ማርኬቱ ለሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በሚሸጥበት ጊዜ ይስብና የካፒታል ክምችት እንዲፈጠር ያደርጋል። የስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት መፈጠሩ ደግሞ መልካም አስተዳደር እንዲጠናከር ያደርጋል፤ ስለዚህ ይህ ሌላኛው ጥቅሙ ነው። በተለይም ግልጽነትና መተማመን እንዲኖር ያደርጋል። ግልጽነትና መተማመን ሲኖር አሠራሩ የተሳለጠ ይሆናል። ሌላኛው ጥቅሙ ደግሞ ለሁሉም የሚጠቅመው የስቶክ ማርኬቱን እያንዳንዱ ግለሰብ ስለሚገዛው ነው፤ በገዛው አክሲዮን ላይ የሚያገኘው ትርፍ ይኖራል፤ ስለዚህም እያንዳንዱ ግለሰብ የግል ሀብት (personal wealth creation) መፍጠር ይችላል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስቶክ ማርኬት ጉዳት ይኖረው ይሆን?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ወደ ጉዳቱ ስንመጣ የስቶክ ማርኬት ዋጋ የሚዋዥቅ መሆኑ ነው። ዋጋውን የሚወስነው አቅርቦቱና ፍላጎቱ ነው ብለናል። ወሳኙ አቅርቦቱና ፍላጎቱ በመሆኑ የስቶክ ማርኬት ዋጋ ወጥ አይደለም። መንግሥትም የሚቆጣጠረው አይደለም፤ የሚቆጣጠረው አቅርቦቱና ፍላጎቱ ነው። በመሆኑም ዋጋው እንደ አየሩ ጸባይ፣ እንደ ገዥው ሕዝብና እንደ ገበያው ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው። ገበያው አንድ ጊዜ ከፍ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ሊል ይችላል። ስለሆነም የገበያው ተለዋዋጭ መሆን በራሱ ጉዳት ነው።

ምክንያቱም አንድ ሰው የስቶክ ማርኬቱ ዋጋ ነገ እንደዚህ ይሆናል ብሎ መወሰን አይችልም። የሚወስነው የወቅቱ የገበያ ሁኔታ ነው። ስለዚህ አንድ ግለሰብ አክሲዮኑን ገዝቶም ሊያተርፍ እንደሚችለው ሁሉ ሊከስር መቻሉ ደግሞ ጉዳት መኖሩን ያሳያል። ስለዚህ በመጀመሪያ ለመግዛት ሲታሰብ ሁኔታዎችን በማጥናት መሆን አለበት። ምክንያቱም ገበያው ነገ እንዲህ ይሆናል፤ ከነገ ወዲያ ደግሞ እንዲዚህ ይሆናል ብሎ የተወሰነ ነገር አይኖረውም። የሚቆጣጠረው ራሱ ገበያው ነው። በመሆኑም የገበያ መረጋጋትን ሊያስተጓጉል ይችላል። ይህ ሲሆን ደግሞ በመካከል ሻጩም ሆነ ገዥው ይጎዳል።

ሌላው የኢንቨስትመንት ግንዛቤ እጥረት (lack of Inevstment awareness) መኖሩ ነው። በኢትዮጵያ ነገሮች ሲታዩ እኛ ኋላቀር ነን ማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም ስቶክ ማርኬት በሌሎች ሀገራት የቆየ ሲሆን፣ እኛ ዘንድ በኃይለሥላሴ ጊዜ ነበር ስንል በብዙ ዘግይቶ የመጣ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የእኛ ኢንቨስተሮች የዚያን ያህል ግንዛቤው የላቸውም። የስቶክ ማርኬት እውቀት የላቸውም። ትንሽም እንኳ ጭላንጭሉ ያለው ቦንድ በመግዛት ረገድ ነው ማለት ይቻላል። የገዛነው ቦንድ አደግ ሲል ደግሞ ገንዘብ እያገኘን የመሄዳችን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በስቶክ ማርካት ያለን መረዳት ገና ብዙ የሚቀረን እንደሆነ አስባለሁ።

ስለዚህ የስቶክ ማርኬት ግንዛቤው በሌለበት ኢንቨስተሮች ደግሞ ደካማ የኢንቨስትመንት ውሳኔ (poor investment dicission) ሊወስዱ ይችላሉ። ደካማ ውሳኔ በሚወስዱበት ጊዜ ደግሞ ወደ ኪሳራም ሊያስገባቸው ይችላል። ምክንያቱም አሁን ባለው ልምድ መሠረት የሚገዙት ጥናቱን ሰርተውና እሱን አስልተው ነው። ምናልባት ውሳኔያቸው ደግሞ ሊጎዳቸው ይችላል ማለት ነው።

ሌላው ደግሞ ቁጥጥሩ የሚፈተንበት (Regula­tory challenge) ጊዜ አለ፤ እንደ እኛ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች ያለው አስተዳደሩ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር (management inefficient) የሚፈተንበት ጊዜ ይኖራል። እንዲህም ሲባል ለምሳሌ ተቆጣጣሪው አካል ራሱ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር ማለት ነው። አንድ አካል ሲመጣ ሌላ ሕግ ያወጣል፤ በዚህ ውስጥ ደግሞ ሙስናው አለ። እነዚህ የሚያሳድሩት ማርኬት የተሳለጠ እንዳይሆን ያደርጋሉ። ማርኬት የተሳለጠ ካልሆነ ደግሞ ኢንቨስተሩ በራስ መተማመን አይኖረውም። ይህ እንግዲህ ሶስተኛው ችግር ሲሆን፣ ሬጉላቶሪ ቻሌንጅ በመባል ይታወቃል።

አዲስ ዘመን፡- የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው ምንድን ነው ይላሉ? እርስዎ እንዳሉት ወደ እኛ ሀገር ስቶክ ማርኬት ዘግይቶ የመጣ እንደመሆኑ ከሌሎች የወስድነው ልምድ ይኖር ይሆን?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ሌሎች ሀገሮች ስማቸው የገነነውን ብንጠቀስ እንደ ለንደንና ኒዮዎርክ ስቶክ ማርኬት እንዲሁም የጃፓኑም ሆኑ የሕንዶቹ ስቶክ ማርኬትን በብዛት ይሠሩበታል። በኢትዮጵያ አንድ ተረት አለ፤ ይኸውም ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ነው፤ ለሃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው የሚለው ሲሆን፣ ይህን አባባል በአግባቡ አልተጠቀምንበትም። ስቶክ ማርኬት እንደዚህ ዓይነት አባባል ነው ማለት ይቻላል። አንድ ሰው አንድ ኢንቨስትመንት ወይም ፕሮጀክት አሊያም ፋብሪካም ሊሆን ይችላል እከፍታለሁ ብሎ ካሰበ ለአንድ ሰው በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል፤ የማይቻልም ነው። ነገር ግን ከብዙዎች ገንዘቡ በስቶክ ማርኬት አማካይነት ተሰብስቦ ሊሠራ ይችላል፤ ይህ እንደ ኢንሹራንስ ማለት ነው፤ ኢንሹራንስ አንድ ሰው አደጋ ከደረሰበት ኢንሹራንስ ከሌለው ምን ያህል ሊከብደው እንደሚችል ይታወቃል። ስቶክ ማርኬትም ከብዙዎች የተሰበሰበውን በመጠቀም አንድ ሰው ሊቋቋምበት ይችላል።

በርካታ ሀገራት የአክስዮን ገበያን መጠቀም ከፍተኛ እድገት ላይ ደርሰዋል። አሜሪካ፣ አውሮፓ፤ ህንድ፤ ሜክሲኮ የመሳሰሉ ሀገሮች በስቶክ ማርኬት በመጠቀም እድገታቸውን አፋጥነዋል። ስለሆነም ስቶክ ማርኬት ለአንድ ሀገር እድገትን የሚያጣ ነው።

እኔ ለምሳሌ በሕንድ ሀገር ሁለተኛ ዲግሪዬን በምማርበት ወቅት ማይነሬ መርቻንት ባንኪንግ ነበር። ሁሉም በስቶክ ማርኬት የተገኘውን ገንዘብ በማሰባሰብ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት ማለት ይቻላል። የእኛን ሀገር መለስ ብለን ስናስተውል በጣም መዘግየታችን ይገባናል።

ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚባል የኮሪደር ልማት እየተካሄደ እንዳለ የሚታወቅ ነው፤ የኮሪደር ልማቱን ለመሥራት እየተንቀሳቀስን ያለነው ተበድረን ነው። ይህ ዓይነት ብድር ደግሞ በጣም ውድ ብድር እንደሚሆን ይታመናል።

በስቶክ ማርኬት በተገኘ ገንዘብ ከሆነ ግን የሚከፈለው ወለድ ጥቂት ነው አምስት በመቶ አሊያም አስር በመቶ ሊሆን ይችላል እንጂ እንደዛኛው ውድ አይሆንም። ስለሆነም ስቶክ ማርኬት ከጠቀሜታው አንጻር ፋይዳ ያለው ነውና በሀገራችን መለመድ አለበት እላለሁ። ምክንያቱም ሌሎች ሀገሮች ያደጉት በዚህ ነው የሚል አተያይ አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ኢትዮ ቴሌኮም አስር በመቶ የሚሆነውን የአክሲዮን ድርሻውን ሸጧል፤ ይህን እርስዎ የሚያዩት እንዴት ነው

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- በርግጥም የአክሲዮን ሽያጩ የተሸጠው አስር በመቶው ነው። አስር በመቶ ብቻ መሆኑ በተወሰነ መልኩ ገዥዎቹ መተማመን እንዳይኖራቸው የሚያደርጋቸው ነው። ብዙ ጊዜ አክሲዮን ሲሸጥ 51 በመቶ ለ49 በመቶ ድረስ ነው። ሻጩ ድርጅት 51 በመቶውን ሲይዝ፣ ገዥው አካል ደግሞ 49 በመቶውን ይይዛል። በዚህ ጊዜ ሻጩ አካል ብልጫ ስላለው ለውሳኔ ያመቸዋል። ሻጩ አካል 49ኙን በሚሸጥበት ጊዜ አላስፈላጊ ነገር ቢፈጠር እንኳ የገዛው 49 በመቶ በመሆኑ ሻጩን አካል ሊገዳደረው ይችላል ማለት ነው። ምናልባትም ደግሞ ከ51 በመቶው ውስጥ ገዥውን አካል ሊደግፍ የሚችል አካል ሊኖር ይችላል። በዚህ ጊዜ ሻጩ አካል ፈተና ውስጥ ሊገባ ይችላል። ስለዚህ ሁልጊዜ ትክክለኛ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው አክሲዮኖች በዚህ መልኩ ሲሸጡ ነው።

አስር በመቶ ሲሆን ግን ውሳኔ ላይ ሲመጣ እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ አንድ ውሳኔ በሚቀርብበት ጊዜ እጅ ወጣ አልወጣ ትርጉም የሚሰጥ አይሆንም ማለት ነው። ነገር ግን መጀመሩ በራሱ በጣም ጥሩ ነው የሚባል ነው። እንዲያም ሆኖ አክሲዮን ተሸጦ የሚገኘው ገንዘብ ለምን ዓይነት ኢንቨስትመንት ይውላል የሚለው መታወቅ አለበት እንጂ ጅማሬ ጥሩ የሚባል ነው። ምክንያቱም አክስዮን የመሸጡ ዋና ዓላማ ገንዘብን በማሰባሰብ እና ሌላ ኢንቨስትመንት ለመገንባት ነው። ነገር ግን ኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮን ሸጦ ራሱን ለማስፋፋት ነው ወይስ ለሌላ ነው የሚለው ግልጽ ባይሆንም መጀመሩ በራሱ በጣም የሚደገፍና የሚበረታታ ነው።

ለሕዝብ ማስተላለፈ የምፈልገው መልዕክት አክሲዮን መግዛት ማለት ገንዘብን በባንክ እንደ ማስቀመጥ ማለት ነው። እንደዚያ ሲባል ገንዘብን በባንክ ስናስቀምጥ ማንም የማይወስድብን መሆኑንና ተዓማኒነት ያለው ስለመሆኑ አሳምረን እናውቃለን፤ አክሲዮንም ልክ እንደዚያ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ስቶክ ኤክስቼንጅ ማርኬት ውስጥ የተመዘገቡት ኩባንያዎች ናቸው ይህንን የሚሸጡት። ስለዚህም ተዓማኒነት ያለው ነው። ስለዚህ ተዓማኒ ስለሆነ ገንዘባችንን በባንክ ብቻ ተወስነን ከማስቀመጥ የዚህ ዓይነቶችንም በመግዛት ገበያችንን ከፍ ማድረግ እንችላለን። እነዚህን ስቶኮች በምንሸጥበት ጊዜ ገበያችን ከፍ እያለ ይሄዳል፤ የውጭዎችንም ኢንቨስተሮችን መሳብ ይችላል። የውጭ ኢንቨስተሮች ደግሞ የውጭ ምንዛሬም ይዘው ስለሚመጡ የውጭ ምንዛሪ እጥረታችንን እንቀርፋለን ማለት ነው። ስለዚህ በብዙ መንገድ የሚጠቅመን ስለሆነ ሁሉም ሊሳተፍበት ይገባል ለማለት እወዳለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ ከልብ አመሰግናለሁ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 

አስቴር ኤልያስ

 

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You