![](https://press.et/wp-content/uploads/2024/12/fri2-1.jpg)
የግብርናው ዘርፍ የአስር ዓመት መሪ እቅድ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ በምርምር የሚገኙ ውጤቶችን ተግባራዊ ማድረግን ከተቀዳሚ ዓላማዎቹ መካከል አድርጓል። መሪ እቅዱ የምርምር ውጤቶች የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ የሚያሳድጉ፣ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሊሆኑ እንደሚገባም ያስቀምጣል።
በገበያ ተፈላጊ የጥራት ደረጃን ለማሟላት እንዲችሉ ተስማሚ የቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴ አማራጮችን ማቅረብ ይፈልጋል፡፡ ብሎም በተጠቃሚው ዘንድ ተቀባይነት ኖሯቸው በአግባቡ ተተግብረው ተጠባቂውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይጠበቃል። በጥቅሉ ሀገሪቷ የግብርና ዘርፍ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው እድገት የግብርና ምርምር የመሪነት ሚና አለው። በዚህ ረገድ እንደ ሀገር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ምን ያህል እየተተገበሩ ነው ስንል የመስኩን ተመራማሪዎች አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አለማየሁ፤ የወረር ግብርና ምርምር ማአከል ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ እስከ ቅርብ ጊዜ የምርምር ወጤቶች ወደ ማህበረሰቡ ሳይደርሱ የሚቀሩበት አጋጣሚ ነበር። ለምሳሌ በጥጥ ረገድ በርካታ ሥራዎች ተከናውነው ጥራት ያለው ዝርያ ተገኝቷል። እነዛ ሁሉ አምራች ጋር አሉ ወይ? የሚለውን ስንፈትሽ ላይገኙ ይችላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት አንደኛው የትኩረት ጉዳይ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት ንቅናቄ ሳይሰራበት ሲቀር የመተግበሩ ነገር የተቀዛቀዘ ይሆናል። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ መጥቷል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግሥት እንደ አቅጣጫ ያስቀመጠው መመሪያ በመኖሩ ሊተገበሩ የማይችሉ የምርምር ሥራዎች እንዳይጀመሩ ተደርጓል። ተተግባሪነታቸው የሚፈተሸው ደግሞ ምርምሩ ከመጀመሩ በፊት ነው።
አሁን ባለው አካሄድ ፕሮጀክቶች የሚቀረጹት በየሦስት ዓመቱ ነው። በመሀል የሚጀመር ሥራ አይኖርም። ምርምሮች ሊጀመሩ ሲሉ ከክፍል ጀምሮ በዘርፍ፤ በሥራ ሂደት ብሎም በማእከል ደረጃ ይገመገማሉ። ቀጥሎም በሀገሪቱ ያሉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች ተጋብዘው ያዩዋቸዋል። ከዚህ በኋላም በብሔራዊ ደረጃ እንደ ሀገር የሌሎች ማእከላት እንቅስቃሴዎችን ከግምት በማስገባት ይገመገማል።
ይህ የሚደረገው ሀገሪቱ የምትፈልገውና ሊተገበር የሚችል መሆኑን ለማጣራት ነው። በማጣራት ሂደቱ ምርምሩ እንዲቀጥል ከተወሰነ እንዴት መሠራት እንዳለበትም በዝርዝር ተፈትሾ ውሳኔ ይሰጥበታል። በሌላ በኩል ራሳቸው የምርምር ውጤቶችን በሚጠበቀው ደረጃ ለተጠቃሚ እንዳይደርሱ ከፍተኛ የበጀት ውስንነት አለ።
የግብርና ዘርፍ ለልማቱ የተሰጠውን ያህል ትልቅ ትኩረት ለምርምሩም ተሰጥቷል ለማለት አያስደፍርም። አንድ የምርምር ውጤትን ወደተግባር ለማውረድ እንደ ሁኔታው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ለአርብቶ አደር አካባቢ ስለ ግብርና ለማስተማር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማላመድ ብዙ ሥራ ይጠበቃል።
ምክንያቱም እዛ አካባቢ ያለው ነዋሪ የመጣበት ልምድ ከእንስሳት እርባታ ጋር በቅርብ የተቆራኘና በቂ የእርሻ ልምምድ የሌለው በመሆኑ ነው። በንጽጽር በደጋማ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ለግብርናው ቅርብ ስለሆነ በፍጥነት የወጡ ምርምሮችን ለማላመድ የሚቻልበት እድል ይኖራል።
ቆላማው አካባቢ የሀገሪቱን 65 በመቶ መሬት የያዘ ሲሆን፤ የሕዝብ ብዛቱ ግን 15 በመቶ የዘለለ አይደለም። ለምሳሌ በአፋር መካከለኛው አዋሽ የሚባለው አካባቢ ብቻ ከ350ሺ ሄክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አለ። ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም እየለማ ያለው ግን ከአስር በመቶ ያልዘለለ ነው። በመሆኑም እንደ ሀገር ውጤታማ ለመሆን ደግሞ ሁሉም ቦታ ላይ በበቂ ሁኔታ መተግበር ይጠበቃል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ግብርና ምርምር የምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሰፋ ተአ በበኩላቸው፤ ዛሬ ላይ ምርምሮች መደርደሪያ ላይ ሊቀሩ የሚችሉበት እድል አለመኖሩን ይናገራሉ። ይህ ሊሆን የቻለውም በአንድ ወገን ቅድመ ምርምር የሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ጠንካራ በመሆናቸው። በሌላ በኩል በምርምር ወቅትና ድህረ ምርምር በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጠንካራ ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑን እንደሚከተለው ያብራራሉ።
ከዛሬ ሦስት ዓመት ጀምሮ የኦሮሚያ ክልልን ሰባት ቦታ በመክፈል ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ግብርናው የሚመለከታቸውን ክፍሎች በሙሉ ያካተተ ካውንስል ተቋቁሟል። ይህ ካውንስል በዓመት ሁለት ጊዜ ይገናኛል በዚህ ጊዜ የማእከሉ ተመራማሪዎች ግንኙነቶቻቸውንና የደረሱበትን ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን ጨምሮ ያቀርባሉ።
ከዚህ በኋላ በመስኩ ቀዳሚ መፍትሔ የሚፈልጉ ችግሮች ይለያሉ። እነዚህም ለሚመለከተው ክፍል ይሰጡና ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ዝርዝር እቅድ ተዘጋጅቶ በባለሙያዎች ይቀርባል። ይህም ባሉት ዘጠኝ ዳይሬክቶሬቶች በከፍተኛ ተመራማሪዎች ይገመገምና የሚቀረው ይቀራል፤ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ይሻሻላል ቅድሚያ የሚሰጠውም ይለይና የውሳኔው ምክንያቱ ተገልጾ ወደ ተመራማሪው እንደሚመለስ ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላ የዚህ ዓመት አዲስ ምርምር ይህ ነው ተብሎ ለማእከሉ ይላካል። ዋናው የምርምር ማእከል የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ አካቶ ለዓመቱ የቀረቡትን የምርምር እቅዶች ይገመግማል። በውሳኔውም ሊሠራ የሚችል በጀት ያለው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባና በመላው ክልል ወይንም በአብዛኛው ቦታ ሊተገበር የሚገባውን ይለያል። ምርምሩ ከተጀመረም በኋላ በየሩብ ዓመቱ እየተገመገሙና ቁጥጥር እየተካሄደባቸው ይቆያሉ። በዓመቱ መጨረሻም የወጡት ቴክኖሎጂዎች ለተጠቃሚ፤ ለሚመለከተው አካል ይሰራጫሉ ጥናታቸውን ሊቀጥሉ የሚገባቸው ካሉም እንዲቀጥሉ ይደረጋል።
ቴክኖሎጂ ለተጠቃሚው ከደረሰ በኋላም በጥብቅ ክትትል እንደ ሁኔታው በተለያየ ጊዜ ግብረ መልስ ይሰበሰባል። በዚህ ረገድ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች በየሁሉም ማእከላት አሉ። እንደ የሁኔታው በሁለት በሦስትም አንዳንድ ጊዜ በአራት ዓመትም ጥናት ይካሄዳል። በዚህ ጊዜ ተቀባይነት አግኝቷል አላገኘም፤ ውጤታማ ሆኗል አልሆነም የሚለው ከተጠቃሚም ከግብርና ቢሮም ምላሽ እንደሚሰበሰብበት አመልክተዋል።
በዚህም ካልተተገበረ ለምን ጥቅም ላይ አልዋለም፤ ወይንም ለምን ተቀባይነት አላገኘም፤ መሻሻል ያለበትስ ምንድነው? እንዴት ነው ሊሻሻልስ የሚችለው ይፈተሻል። የእነዚህ ሂደቶች ሙሉ ውጤት ጨፌ ኦሮሚያን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና በሌሎችም በሚመለከታቸው አካላት ይገመገማል ቁጥጥርም ይካሄድበታል። ይህም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ተጠንቶ ሳይተገበር የሚቀር ምርምር እንደማይኖር ገልጸዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም