-የንግድ ፈቃዳቸውን ላላደሱ የንግድ ተቋማት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል
ያደጉት ሀገራት እና የአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች የንግድ ተቋማት ግብይት ቀን ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በምሽት ጭምር ይገበያያሉ:: በዚህም የንግድ ተቋማቱንና በምሽት ጭምር መገበያየት የሚፈልገው የህብረተሰብ ክፍል የሚገበያዩበትን እድል በማስፋት ሁለቱም ወገኖች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በአጠቃላይ ግብይቱ እንዲጎለብት የከተሞችም የሀገሮችም ኢኮኖሚ ይበልጥ እንዲነቃቃ ለማድረግ ያስችላል::
በአዲስ አበባ ይህ ግብይት አለ በሚባል ደረጃ ላይ አይገኝም:: በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ከሚስተዋል የምሽት ግብይት ውጭ፣ ትልቁን የአፍሪካ ገበያ መርካቶን ጨምሮ የአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ነጋዴዎች ገና ጀንበር ስታዘቀዝቅ መደብሮቻቸውን ዘግተው ወደየቤታቸው ያቀናሉ።
በከተማዋ መሀል አካባቢዎች እስከ ምሸት በመገበያየቱ ልምድ ያካበቱ የንግድ ተቋማት የግብይቱን ፋይዳ ተገንዝበው ተጠቃሚ ሲሆኑ ቢቆዩም፣ ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ግን የንግድ ተቋማቱም ሆኑ በምሽት የሚገበያየው ማህበረሰብ በጊዜ ወደቤቱ ሲገባ ይስተዋላል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሲቀርቡ ይደመጣል። የመንገድ መብራት አለመኖር፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ የምሽት ዋጋ ከፍተኛ መሆን፣ በዚህ የተነሳም ተገቢውን አገልግሎት እንደልብ ማግኘት አለመቻል፣ የሸገር እና አንበሳ አውቶቡሶችም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ የማይሠሩ መሆናቸው ከምክንያቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
አሁን መዲናዋ የኮሪደር ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች ምሽቱ ቀን እስኪሚመስል ድረስ የንግድ ሥራዎችን ጨምሮ ለየትኛውም እንቅስቃሴ አመቺ ሆናለች። ከጸጥታም፣ ከመንገድ መብራትና ከመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች አኳያ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፤ ይሁንና ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ በርካታ የንግድ ተቋማት በመነሳታቸው በዚህ ምቹ በሆነው መሠረተ ልማት አካባቢ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ እምብዛም ሆኖ ይታያል።
የከተማ አስተዳደሩም በቅርቡ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር እና የመዲናዋን የንግድ እንቅስቃሴና ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ይረዳል ያለውን ውሳኔ አሳልፏል። የንግድ ተቋማት እስከ ምሽት ሶስት ሰዓት ተኩል እንዲሁም የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ጨምሮ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እስከ ምሽት አራት ሰዓት እንዲያገለግሉ ወስኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ እንደተናገሩት፤ ባለፈው ሳምንት የከተማዋ የንግድ ተቋማት እስከ ምሽት ድረስ መሥራት ባለባቸው ሁኔታ እንዲሁም በንግድ ፍቃድ ምዝገባና አሰጣጥ ላይ ያለውን አሠራር አስመልክተው ለብዙኃን መገናኛ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ከአፍሪካ ሀገራት እንደ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ የመሳሰሉት ሀገራት አብዛኛውን ግብይታቸውን በምሸት ያካሂዳሉ። ይህን ዓይነት የንግድ ግብይት በአዲስ አበባም ተግባራዊ ማድረግ ይገባል:: የብዙኃን መገናኛዎቹም በዚህ ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል መሥራት ይኖርባቸዋል::
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሁለት የትኩረት መስኮች ላይ ይሠራል ያሉት ኃላፊዋ፣ በአንደኛው የትኩረት መስኩ የከተማው ነዋሪ በኑሮ ውድነት የሚደርስበትን ጫና ለማቃለል የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር አቅርቦትንና ፍላጎትን በማጣጣም ጤናማ የሆነ የንግድ ሥርዓት መፍጠር ላይ የሚሠራው ነው ብለዋል።
በሁለተኛው የትኩረት መስኩ ደግሞ የንግድ ሕጎቹን ተግባራዊ ለማድረግ በቁጥጥር ዘርፉ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል። ማንኛውም የንግድ ተቋም እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ተኩል አገልግሎት እንዲሰጥ፣ በተመሳሳይም የትራንስፖርት ዘርፉ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት እንዲያገለግል በከተማ አስተዳደሩ መወሰኑን አስታውቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ያሳለፈው ውሳኔ የንግዱ ማህበረሰብ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን እንዲያሳድግ የሚያደርግ፣ የማህበረሰቡንም ሆነ ከተማውን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃ መሆኑን አብራርተው፣ የንግዱ ማህበረሰብም በዚህ ላይ ግንዛቤ ወስዶ የትኛውንም የንግድ ተቋም እስከ ምሽት ሶስት ሰዓት ተኩል ድርጅቱን ክፍት ሆኖ እንዲሠራ ጥሪ አስተላልፈዋል።
መዲናዋ የከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት በፈጠራቸው ምቹ ሁኔታዎች ሰላሟ የተጠበቀ ከተማ ሆናለች ሲሉም ጠቅሰው፣ ይሁንና እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ተከናውነው ከ12 ሰዓት ጀምሮ በርካታ የንግድ ተቋማት በከተማዋ ተዘግተው እንደሚታዩ አስታውቀዋል። ይህ ሁኔታ መቀየር እንዳለበት አስገንዝበው፣ የንግዱ ማህበረሰብ የንግድ ተቋማቱን ክፍት በማድረግ የግብይት ሥራው እንዲቀጥል ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል:: የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም በዚህ ላይ ክትትል በማድረግ፣ ለተፈጻሚነቱ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የቢሮ ኃላፊዋ የንግድ ፈቃዳቸው ያላሳደሱ የንግድ ማህበረሰቡ አባላት እስከ ታኅሣሥ 30 ድረስ የንግድ ፍቃዳቸውን እንዲያሳድሱም ጥሪ አቅርበዋል:: በከተማዋ የንግድ ፍቃድ ምዝገባና አሰጣጥ በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ ይሰጥ እንደነበረ ጠቅሰው፣ ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አመልክተዋል:: የንግድ ፈቃድ በኦንላይን እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ጀምሮ በቢሮ ደረጃ አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ይህ አገልግሎት ሲሰጥም በአምስት ወር የተገኘው ውጤት እና ማሻሻል በሚገባው ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል:: እንደ ወይዘሮ ሀቢባ ገለጻ፤ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ወደ 47 ሺህ 707 ያህል ነጋዴዎች አዲስ የንግድ ፍቃድ አውጥተዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አገልግሎቱ በማዕከል መስጠት ከጀመረ ወዲህ የ10 በመቶ ብልጫ አሳይቷል። በተመሳሳይ ወደ 15 ሺህ 99 የሚሆኑ ነጋዴዎች ከንግድ ሥርዓቱ ወጥተዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከንግድ ፍቃድ የወጡት 17 በመቶ ያህል ቅናሸ ያሳየ ነው። ከንግድ ሥርዓቱ የሚወጣው ነጋዴ እየቀነሰ ወደ ንግድ ሥርዓቱ የሚመጣው መጨመሩን የአምስት ወር ዳታ ያመላክታል።
ኃላፊዋ እንደተናገሩት፤ ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የንግድ ፍቃድ የሚታደስበት ወቅት ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ወራት 211 ሺህ 720 ያህል ነጋዴዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው ንግድ ፍቃዳቸውን አድሰዋል። የንግድ ፍቃድ የማደሻው ቀን ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንት ብቻ ይቀሩታል:: እስከ አሁን የንግድ ፍቃዳቸውን ያላደሱ 184 ሺህ ያህል ነጋዴዎች አሉ:: እነዚህ ነጋዴዎች በተቀሩት ቀናት ማደስ ይጠበቅባቸዋል::
ቢሮው የንግዱ ማህበረሰብ ለቅጣት እንዳይዳረግ እድሳቱ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ እየጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም አንዱ የሥራ ሰዓቱን ማራዘም መሆኑን ጠቁመዋል:: ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ የንግዱ ማህበረሰብ ፈቃዱን እንዲያድስ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል::
መገናኛ ብዙኃን ለኃላፊዋ ጥያቄዎችን አንስተዋል:: ከጥያቄዎቹ መካከል የንግድ ፍቃድ እድሳቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት እስኪቀረው ድረስ ለምን ተጠበቀ? አስቀድሞ ማሳሰብ አይቻልም ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል:: ኃላፊዋ ለጥያቄዎቹ ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁትም፤ የንግዱ ማህበረሰብ ንግድ ፍቃዱን በወቅቱ እንዲያድስ በክፍለ ከተማ ደረጃ ቅስቀሳ ሲደረግ ቆይቷል። በዘርፉ በቢሮው የማህበራዊ መገናኛ ገፁ ላይም በየጊዜው መልዕክት ተላልፏል። እነዚህ 184 ሺህ የሚሆኑት ቀንም ማታም በየትኛውም ሰዓት በኦንላይን ማመልከቻ ቢያቀርቡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ ነው።
የቢሮ ኃላፊዋ የንግድ ተቋማት የሥራ ሰዓት ማራዘምን በተመለከተ ከፀጥታ፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከብዙኃን መገናኛ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በምላሻቸውም የንግድ ተቋማት የሥራ ሰዓት በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ሲወሰን ደንቦች፣ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ባሉበት መሆኑን ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህም የሥራ ድርሻ ክፍፍል ተደርጓል። በዋናነትም የኮሪደር ልማቱ በለማባቸው ዋና ዋና ጎዳናዎች እነዚህ የንግድ ተቋማት እስከ ምሽት ሶስት ሰዓት ከሰላሳ ክፍት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑን አስገንዝበዋል። የንግድ ተቋማቱ በተባሉት ሰዓቶች ክፍት ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ በዚህም ላይ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረጉ አመላክተዋል።
ወይዘሮ ሀቢባ እንዳስገነዘቡት፤ የንግድ ተቋማቱም ይሄንን እንደሚፈልጉት ቢሮው ይገነዘበዋል። ውሳኔው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሳድግ፣ የንግድ እንቅስቃሴውንም የሚጨመር ነው።
በታክሲ አገልግሎት ሰዓት ላይ ለተነሳው ጥያቄም አያይዘው በሰጡት ምላሽ አጠቃላይ የከተማ አውቶቡስን የሚመራው አካል እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥ መወሰኑን አመልክተው፣ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ማንኛቸውም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም እንዲሁ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
እነዚህን የትራንስፖርት አገልግሎቶች በእነዚህ ሰዓቶች እንዲሠሩ ማድረግ ካልተቻለ ይህ ሁሉ መሠረተ ልማት ተዘርግቶ፣ ከተማውም ውብ ሆና፣ ማህበረሰባችን ከምሽቱ 12 ሰዓት ወደቤቱ የሚገባ ከሆነ ከተሜነቱም አጠያያቂ ይሆናል ሲሉም አስታውቀዋል:: የብዙኃን መገናኛውም በዚህ ላይ ግንዛቤ እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ነጋዴው አምሽቶ ሲሠራ፣ ነዋሪውም በዚያ ምሽት ሰዓት ወጥቶ ሲገበያይ የከተማዋንም ውበት እንዲያይ፣ እንዲንሸራሸር ኢኮኖሚውንም እንዲያሳድግ ይፈለጋል። መንግሥት በበኩሉ ለከተማዋ ደህንነት እና ሰላም መጠበቅ ኃላፊነቱን ወስዶ እየሠራ ይገኛል፤ ሕዝቡን ለመጠበቅ፣ ነጋዴውን ማህበረሰብ ለመጠበቅ ኃላፊነቱን ይወስዳል።
በኮሪደር ልማቱ የንግድ ተቋማት የሚሠሩባቸው ህንጻዎችና መደብሮች ሲፈርሱ ምርጫቸው ተጠብቋል ያሉት ኃላፊዋ፣ በተለይ የመንግሥት ቤት ወይም የቀበሌ ቤት ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች አማራጭ እንደተጠበቀላቸው አስታውቀዋል። ከተማ ውስጥ መሥራት የሚፈልጉ በሚፈልጉት መንገድ ተደራጅተው ቦታ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ገልጸው፣ ከካዛንቺስ የተነሱ የንግድ ተቋማት ወደ ገላን ጉራ ሄደው እንዲሠሩ የተደረገበት ሁኔታ እንዳለም አመልክተዋል።
ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ 15 ሺህ 99 ሰዎች ከንግድ ሥርዓቱ መውጣታቸውንም ጠቅሰው፣ ይሄንንም ኦንላይን ላይ በሚደረገው ምዝገባ ያመለከቱ፣ ከንግድ ፍቃድ የወጡ፣ አዲስ የንግድ ፍቃድ ያወጡ እንደሚታዩ ተናግረዋል፤ ይህን ለማወቅ ተጨማሪ ጥናት ማድረግ እንደማይፈልግ ጠቁመዋል።
መደበኛ ያልሆነ ንግድን በተመለከተ ሲያብራሩ እንደገለፁት፤ በመዲናዋ እንደ ሌባና ፖሊስ ጨዋታ ከደንብ ማስከበር ጋር ሲሯሯጡ የሚውሉ ዜጎች አሉ። ይህንን ሥርዓት ለማስያዝ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የኢመደበኛ ንግድ ደንብ ወጥቷል።
ደንቡ በቅርብ ቀን ለካቢኔ ቀርቦ ይጸድቃል። ከፀደቀ በኋላም ሥርዓት ባለው መንገድ የንግድ እንቅስቃሴው እንዲከናወን ይደረጋል።
እስካሁን ቢሮው ባለው ዳታ በኢመደበኛ ተመዝግ በው ያሉት ወደ 4ሺ800 አካባቢ ናቸው:: ከዚያም ውጭ ነጋዴዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ሁሉንም መልክ በማስያዝ እንደ ማንኛውም ዜጋ ሰዓታቸው ተገድቦ፣ የሚሠሩበት የሥራ ቦታ ተወስኖ የንግድ ፍቃድና መታወቂያ ተሰጥቷቸው፣ የሚሠሩበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል:: በዚህ ላይ የሚሠራ የሥራ ክፍል መዋቀሩንም ጠቁመዋል።
በኮሪደር ልማቱ ከፈረሱ የነዳጅ ማደያዎች ጋር ተያይዞም በብዙኃን መገናኛዎቹ ጥያቄ ተነስቷል፤ የቢሮ ኃላፊዋ ለእዚህ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ በመዲናዋ ካሉት ጠቅላላ 126 አካባቢ ማደያዎች ሰባት ያህሉ በኮሪደር ምክንያት ተነስተዋል። እነዚህን ለመተካት እየተሠራ ነው። ባለሀብቶቹ በጠየቁት ልክ ሚዲያዎችን ለመተካት ይሠራል።
በሌላ በኩልም የንግድ ቢሮውም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ ነዳጅ ማደያ ማስፋፋት ላይ ሳይሆን ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ማበረታታት ላይ መሥራት መሆኑን አስታውቀዋል:: በከተማዋ በጥናት በተረጋገጠው መሠረት 260 አካባቢ ነዳጅ ማደያዎች ያስፈልጋሉ ሲሉም ገልጸው፣ አሁን በመንግሥት ፖሊሲ በብዛት ለማስገባት እየታሰበ ያለው የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መሆኑን ገልጸዋል:: ለዚህም ከተማዋ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎችን በብዛት ማመቻቸት ላይ አተኩራ እንደምትሠራ አመልክተዋል::
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም