የግብርና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት – በሐረሪ ክልል

በሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲሁም ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ያለውን ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። ለእዚህም እንደማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን በስፋት በማቅረብ፣ ለሜካናይዜሽን እርሻ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የታመነበትን ኩታ ገጠም እርሻን እንዲሁም ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት፣ ግብርናውን ከመኸርና በልግ በተጨማሪ በመስኖ ልማትም በመደገፍ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

ይህን ሁሉ ተከትሎም የዘርፉ ምርትና ምርታማነት በየዓመቱ እየጨመረ ይገኛል። ይህን ምርታማነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ ልማት ሁሉም ክልሎች በስፋት እየሠሩ ይገኛሉ።

በዛሬው የግብርና ዓምዳችን የሐረሪ ክልል በግብርናው ዘርፍ በተለይ በተያዘው የመኸር ወቅትና መስኖ ልማት ላይ እያከናወነ ያለው ሥራ ዳሰናል። ክልሉ በተለይ ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የክልሉን የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ ነው።

የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት እና የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር እንዳብራሩት፤ በክልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን 11,774 ሄክታር ለማረስ ታቅዶ ሙሉ 100% ታርሷል። ከዚህም 800 ሄክታር ማሽላ 450ሄክታር ሰንዴ ኢኒሺየቲቭ ነው። በዚህም በክልሉ ሁለት ክላስተር የሚገኝ ሲሆን፤ አንደኛው 450 ሄክታር የስንዴ ክላስተር ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ 350 ሄክታር የማሽላ ክላስተር እርሻ ነው። በክልሉ በስፋት የሚታወቁት የግብርና ምርቶች ማሽላ፣ በቆሎ፣ ለውዝ እና ስንዴ ናቸው።

ከዚህ 11,774 ሄክታር መሬት ውስጥ በኢኒሺየቲቭ የታረሰውን በተለየ መንገድ እንዲለማ ተደርጓል። ይህም የግብርና ቢሮ ባደረገው እገዛ የተሠራ ነው። አንዱ ኢኒሺየቲቭ የማሽላ ኢኒሺየቲቭ ሲሆን፣ ይህም በሀረማያ ዩኒቨርስቲ የተደረገውን ጥናት በመውሰድ የተዘራ ነው። ይህ የማሽላ ዝርያ ምርት በሦስት ወር ይደርሳል፤ ይህ አዝመራ ደርሶ ተሰብስቧል።

በክልሉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እየለማ ያለው ነባሩ የማሽላ ዝርያ ምርት ለመስጠት ከሰባት ወር እስከ ዘጠኝ ወር እንደሚወስድበት አስታውቀው፣ በሄክታር የሚያስገኘውም 13 ኩንታል ብቻ ነበር ብለዋል። በምርምር ተገኝቶ እንዲለማ የተደረገው የማሽላ ዝርያ በሦስት ወር ምርት የሚሰጥ እንደሆነ አመልክተው፣ በሄክታር ከ42 እስከ 45 ኩንታል እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የዚህ ማሽላ ዝርያ ጠቀሜታው ብዙ ነው፤ አንዱ ጠቀሜታው በፍጥነት መድረሱ ነው፤ ማሽላን በአነስተኛ መሬት ላይ ዝናብ በመጠበቅ ብቻ እንዲለማ የሚደረግ ከሆነ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አይቻልም። በክልሉ ያለው መሬት አነስተኛ ነው። አዲሱ የማሽላ ዝርያ በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረት እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ይህን የማሽላ ዝርያ ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲላመድ እና በክላስተርም እንዲለማ እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ ሮዛ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ጊዜም በዘር ከተሸፈነው 800 ሄክታር መሬት ላይ 36 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል። በተወሰኑ ወረዳዎች በተለመደው የማሽላ ዝርያ በዘር የተሸፈነው ማሳ ምርት ገና እንዳልደረሰ አስታውቀዋል። የቢሮ ኃላፊዋ ምርት በተሰበሰበበት መሬት ላይ የበጋ መስኖ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል፤ አራት ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ለማምረት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ የደረሰ ሰብልን በወቅቱ ለመሰብሰብ ማሽነሪዎችን ለመጠቀም ምን ያህል ተሠርቷል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣ ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል። የማሽላና የስንዴ ማሽነሪ ለየብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ጥቅም ላይ እንዲውል የተደረገው ምርት ለመሰብሰብ ሳይሆን ለመውቃት ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል በቴክኖሎጂ ምርምር ላይ ይሠራል፤ ክልሉ ማሽላን የሚወቁ ማሽነሪዎችን ለሦስት ወረዳዎች ከምርምር ማዕከሉ ገዝቶ አቅርቧል። ይህም ሰብሉን በተሻለ መንገድ ለመውቃት ያስችላል። ቴክኖሎጂው ሥራ ላይ መዋሉ አርሶ አደሩ ድካም ሳያጋጠመው በማሽነሪው በመውቃት ምርቱን እንዲሰበስብ አስችሎታል። ስድስት ማሽነሪዎች ተገዝተው ሦስቱን ማስተላለፍ ተችሏል። መግዛት ለሚችሉት ወረዳዎችም ስለቴክኖሎጂው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የቢሮ ኃላፊዋ እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን በማወያየት፣ የመንግሥት ሠራተኛውን፣ የፀጥታ አካሉን /በአካባቢው የሚገኘውን የምሥራቅ ዕዝ./ በማስተባበር ምርት በጊዜ እንዲሰበሰብ ተደርጓል። በዚህም በአካባቢው ተከስቶ የነበረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በአዝመራ ላይ ጉዳት ሳያስከትል በፍጥነት መሰብሰብ ተችሏል።

በክላስተር የተገኘው ምርት በመጀመሪያ ደረጃ ለምርጥ ዘርነት እንደሚፈለግ ተናግረው፣ በዚህም ምርጥ ዘር ወደ አልተደረሰባቸው አርሶ አደሮች ለማዳረስ እየተሠራ ነው ይላሉ። የክልሉ ግብርና ቢሮ ይህንን ምርት ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ከፍተኛ ግዢ አድርጓል ሲሉም ጠቅሰው፣ ክልሉ የገዛውን የማሽላ ምርጥ ዘር አንድ ቦታ በማሰባሰብ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ምርት ከአርሶ አደሩ ሲገዛ በቁጠባ እንዲጠቀም እየተደረገ ነው ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ለዘር እና ይህን ዘር ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች ለማስፋፋት ምርቱን ሲገዛ ምርቱን የሸጠው አርሶ አደር ገንዘቡን እንዳያባክን ለማድረግም በባንክ እንዲቆጥብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ለምግብ የሚያዘጋጀው እንዲሁም ለማኅበረሰቡ በቀጣይ በዚህ መሬት የሚዘራውን ምርጥ ዘር በተመሳሳይ እንዲቆጥብ በሚያስችለው ላይ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል።

በልማታዊ ሴፍቲኔት የሚጠቀሙ አርሶ አደሮችን በተመለከተም ሲያብራሩ፣ በዚህም በሴፍቲኔት እገዛ ውስጥ የቆዩ አንድ ሺህ 200 አርሶ አደሮች በዚህ ዓመት ማብቃት የተቻለ መሆኑን አስታውቀዋል። ለሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በተመለከተም ሲያብራሩ እንደገለጹት፤ በመጀመሪያ ደረጃ ውሃ እንዲያቁሩ በማድረግ የታቆረውን ውሃ በፓምፕ በመጠቀም እና ሦስት ጊዜ በላይ እንዲያመርቱ ለማስቻል እየተሠራ ነው።

ለእዚህም በድጋፍ እና በግዢ የቀረቡ ወደ 150 ፓምፖች ለሴፍቲኔት አርሶ አደሮች እንዲሰራጩ መደረጋቸውን አመላክተዋል። ውሃ የሚጠራቀምበት ሸራ እንዲሰራጭ በማድረግ 1200 አርሶ አደሮች በዚህ ዓመት ከሴፍቲኔት ድጋፍ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸው። በሶላር እና በመብራት የሚሠራውንም ፓምፕ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በመሆን እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደተቻለም ጠቅሰው፣ በዚህ መልኩ ራሳቸውን እንዲችሉ የተደረጉ ቤተሰቦች ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ሥራ ላይ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ይላሉ።

በሌላ በኩል በክልሉ በሌማት ትሩፋት የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክተው ወይዘሮ ሮዛ ዑመር እንዳብራሩት፤ የክልሉ ግብርና ቢሮ በእንስሳት እርባታ በተለይ የተዳቀሉ የተሻሻሉ እንስሳትን ዝርያ ቴከኖሎጂን በማስደገፍ በማዳቀል ዘዴ የወተት እንስሳት ምን ያህል ምርት መስጠት ይገባቸዋል በሚለው ላይ ተሠርቷል። በዚህም የወተት መንደር በሚል 17 ቀበሌዎችን በመለየት እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ ከሁለት እስከ አምስት የወተት እንስሳት ሊኖረው ይገባል በሚል እየተሠራ ይገኛል። እስካሁን ከ17 ቀበሌዎች በ15 ቀበሌዎች ላይ ሙሉ ፓኬጅ ማከናወን ተችሏል።

በእንስሳት ማርባት ሥራ ላይም ትልቅ የናይትሮጅን ማሽን መኖሩን ጠቁመው፣ በማዳቀል ሥራ ጊደሮችን በማዳቀል ለእርድ ብቻ ሳይሆን ጥጃ መስጠት በምትችል ደረጃ ከሀረማያ ዩኒቨርስቲ ጋር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል። ለእዚህም የእንስሳት ሐኪሞች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በዚህ ሥራ በልዩ ትኩረት ትልቅ በጀት ተመድቦ እየተሠራ ነው ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የዶሮ እርባታን በተመለከተም ለሁሉም አርሶአደር እናቶች በየቤቱ 25 ዶሮዎች ይሰጣሉ። እነዚህ እናቶች 25 ዶሮዎችን ሲወስዱም እኛ የምናረባቸው ዶሮዎች እና የግል ዶሮ አርቢዎች የሚያረቡዋቸው ልዩነት አላቸው። ልዩነታቸውም የግል አርቢዎች እንቁላል መጣል ብቻ እንጂ እንቁላላቸው መልሶ ጫጩት መሆን አይችልም።

በክልሉ ግብርና ቢሮ በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም የሚረቡት ዶሮዎች ግን እንቁላላቸው መልሶ ጫጩት መሆን የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚታገዝ ነው። እንቁላላቸው መልሶ ጫጩት መስጠት የሚያስችሉ 25 ዶሮዎችን በክልሉ ካሉት ዘጠኝ ወረዳዎች ለሁለቱ ወረዳዎች ማዳረስ ተችሏል። መግዛት የሚችሉ ቤተሰቦች ደግሞ መግዛት እንደሚችሉ ሙሉ ተስፋ በመስጠት እየተሠራ ነው።

በሌላ በኩል የተጠራቀመ ውሃ በተዘጋጀባቸው ቦታዎች ከሀረማያ ሐይቅ ላይ የዓሣ ጫጩት በማምጣት በየቀበሌው በምን መልኩ ውሃ በማጠራቀም አልያም የተጠራቀመ ውሃ ካለበት ስፍራ በሞተር ውሃ በማውጣት በተጠራቀመ ውሃ ዓሣን ማራባት እንደሚቻል ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል። በዚህ መልኩም ዓሣን የማርባት ሥራ እየተሠራ ነው።

በተመሳሳይ በክልሉ የማር መንደር እንዳለም ገልጸዋል። ሁለት ሄክታር መሬት ክላስተር በማድረግ ቀፎዎችን አንድ ቦታ ላይ በማሰባሰብ ወጣቶችን በዚህ ላይ በማደራጀት እየተሠራ ነው ብለዋል። በተለይም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለወጡ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጋር በተያያዘ ለወጣቶቹ የተወሰነ መነሻ ገንዘብ በመስጠት፣ የመሥሪያ ሼድ በመሥራት በዚህ ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል ሲሉ አብራርተዋል። በእነዚህ ሼዶች ያመረቱትን የማር ምርት መሸጥ እንዲችሉና ራሳቸውም እየተጠቀሙ የማኅበረሰቡንም ገበያ ለማረጋጋት እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የገበያ ትስስር በማድረግም የቅዳሜ እና እሁድ የሰንበት ገበያ በሚል የማር ምርታቸውን የሚሸጡባቸው የገበያ መዳረሻዎች ተዘጋጅተዋል ሲሉም ጠቁመው፣ በዚህም የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ላይ እየተሠራ መሆኑን ወይዘሮ ሮዛ አስረድተዋል።

ከሌማት ትሩፋት ሥራው ጋር በተያያዘ እንደ ችግር ያጋጠመው እና ከእንስሳት መኖ፣ ከዶሮ መኖ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ የዶሮ መኖ ችግር በዚህ ዓመት መፍታት መቻሉንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን በመግዛት በዶሮ ማርቢያው አካባቢ ተተክሏል። መኖውም እዛው ይመረታል፤ በግል ዶሮ የሚያረቡ ወጣቶችንም በቢሮው በኩል ያለው የዶሮ ማርባት አሠራር ላይ እየተሠራ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የዶሮ መኖ ከቢሾፍቱ ተጭኖ ይመጣ ነበር። ይህ ሲሆን ዋጋውና የትራንስፖርት ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ እንቁላሉንና ዶሮውን በተፈለገው ፍትሐዊ ዋጋ መሸጥ አልተቻለም ነበር። በመሆኑም የዶሮ መኖን እዚሁ ማምረት ይገባል በሚል የማቀነባበሪያ ማሽኑን በመግዛት ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

አሁን ላይ የሐረሪ ግብርና ቢሮ ከሱሉልታ ከሚመጣው የእንስሳት መኖ ጋር በተያያዘ ችግር ያጋጠመው መሆኑን አመላክተዋል። ዋጋውም ከትራንስፖርት ወጪ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ለእዚህ በመፍትሔነት የተወሰደው ከሐረር ቢራ ፋብሪካ ጋር የእንስሳት መኖውን ማገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስምምነት በመፈራረም እየተሠራ ነው።

የረጅም ጊዜው መፍትሔ ደግሞ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ እዚህ ማቋቋም መሆኑን ጠቁመው፣ ለእዚህም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። በእንስሳት መኖ እና በዶሮ መኖ ላይ ችግር ከማጋጠሙ በስተቀር በክልሉ የሌማት ትሩፋት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ወይዘሮ ሮዛ ዑመር አስታውቀዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You