የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን – በሀገር ልጅ

ካህሳይ ኃይለኪሮስ (ዶ/ር) ይባላሉ፡፡ በግብርናው መስክ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት ሰባት ዓመታትን ያህል አሳልፈዋል፡፡ በተለይ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ሀገር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ግብዓቶች ለማምረት አስበው ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ለዓመታት የደከሙበት ይህ የምርምር ሥራ ውጤታማ ሆኖም አራት ዓይነት የምርምር ውጤቶችን ማግኘት ችለዋል፡፡

የምርምር ሥራቸውን በመቀሌ ሲያደርጉ የቆዩት ዶክተር ካህሳይ፣ በተለይ የአፈር ለምነት ከመጠበቅ አንጻር ትኩረት ሰጥተው መመራመራቸውን ይገልጻሉ፡፡ የአፈር ለምነት ሊጠበቁ የሚችሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችንና ሌሎች ምርቶችን በምርምር አግኝተዋል፡፡

እነዚህ የምርምር ሥራዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ፋይናንስ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለማግኘትም ለሁለት ዓመታት ያህል ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው የምርምር ሥራዎቻቸውን ለእይታ ካቀረቡ በኋላ ግን በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስርና ባገኙት የሥራ አጋር በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸው እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አልትራ ኦርጋኒክ ፈርቲላይዘር እና ፔስቲሳይድ ፒኤልሲ(Ultra Organic Fertilizer and pesticides manufacturing plc) የተሰኘ ድርጅት መስርተዋል ፤ አራት ዓይነት ምርቶች ለማምረት የሚያስችል ሥራ አጠናቀዋል፡፡ እነዚህም አንደኛውና ጠጣር ማዳበሪያ(ሶሊድ ፈርቲላይዘር) የሚባለው ነው፡፡ ሁለተኛው ፈሳሽ ማዳበሪያ (ሊክዊድ ፈርቲላይዘር) ነው። እነዚህ የምርምር ውጤቶች በጠጣርና ፈሳሽ መልኩ የተዘጋጁ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ናቸው፡፡

ሦስተኛው አርትራ ቴን ኮምፖስት ፋስሊቴተር (Ul­tra ten compost facilitator) የተሰኘውን የተፈጥሮ ማዳበሪያን/ኮምፖስትን/ በአስር ቀን ማምረት ይቻላል። አራተኛው ጸረ ተባይ /ፔስቲሳይድ/ ከተፈጥሮ የአፈር ማዕድናትና እጽዋት ተዋጽኦ የሚዘጋጅ ነው፡፡ አራቱም ምርቶች በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ግብዓቶች ይመረታሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ሁሉም ምርቶች የራሳቸው አገልግሎቶች አላቸው፡፡ ፔስቲሳይድ (pesticides) የተሰኘው ምርት፣ ከአፈር ማዕድናትና እጽዋት ተዋጽኦ የሚዘጋጅ የጸረ ተባይ መከላከያ ነው፡፡ ጠጣርና ፈሳሽ ማዳበሪያ (ሶሊድና ሊኩዩድ ፈርቲላይዘር) ከጠጣር ወይም ደረቅና ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚሠራና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። አርትራ ቴን ኮምፖስት ፋስሊቴተር (Ultra ten com­post facilitator )የተሰኘው ደግሞ ከእንስሳትና ከእጽዋት የሚገኙ ተረፈ ምርቶች ወደ ጥቅም የሚቀየሩበትን ሁኔታ የሚያፋጥን በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

ምርቶቹ ለአርሶ አደሩ እንዲቀርቡ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ደረቅ/ጠጣር/ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በሁለት ወራት ውስጥ ለማምረት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡ ማዳበሪያውን ለማምረት የሚያስችለው ፋብሪካ ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ ማምረት ሥራ ለመግባት እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

እንደ ዶክተር ካህሳይ ማብራሪያ፤ የማዳበሪያ ዓይነቶቹ በምርምር የተገኙ እንደመሆናቸው ብዙ ነገሮች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ተዘጋጅተዋል፡፡ ሁለቱንም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዓይነቶች ብንመለከት በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች እና የአፈር ሁኔታ ላይ ምርምር ተካሄዶ የተዘጋጁ ናቸው። ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ለመጠቀም ስንፈልግ አፈሩ አሲዳማ ከሆነ አፈሩ ላይ ሕክምና ማድረግ ይገባል፤ ማዳበሪያው ተገቢ የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን እንዲይዝ ተደርጎ በሚገባ ታስቦበት የተሠራ ነው፡፡

እንደ ዶክተር ካህሳይ ገለጻ፤ የምርምር ሥራዎቹ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤትና በትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በኩል ምርምር ላይ እያሉ ተፈትሸው ውጤታማነታቸው ተረጋግጧል፡፡ ወደ ማምረት ሲገባ ደግሞ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና የግብርና ሚኒስቴር በሚያዘጋጇቸው የሙከራ ቦታዎች ላይ ተሞክረው ትክክለኛነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ጥቅም እንዲውሉና ለገበያ ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡

‹‹ምርቶቹ ላይ ችግር እንዳይገጥምን በማሰብ ትክክለኛነታቸው በደንብ እስኪረጋገጥ ድረስ እስካሁን ምርቶቻችን ወደ ገበያ አልገቡም፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተብሎ ብዙ ድርጅቶች ምርቶችን እያመረቱ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር መቀላቀል የለበትም፡፡ እኛም መንግሥት የሚያውቀው ማረጋገጫ ካገኘን በኋላ ወደ ገበያ እንገባለን በሚል እስካሁን ቆይቷል›› ይላሉ፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች በሀገር ውስጥ ማምረት መቻል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው የሚሉት ዶክተሩ፤ አሁን ላይ በሀገሪቱ እንደሚታየው ሰፊ የሆነ የማዳበሪያ የአቅርቦት እጥረት አለ፡፡ ይህ ምርት ወደ ገበያ ሲገባ እጥረት በመቅረፍ ረገድ ደጋፊ ይሆናል፡፡ ወደፊት ደግሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ጥቅም አርሶ አደሩም ሆነ ህብረተሰቡ እያጎለበተውና ሙሉ ተጠቃሚ እየሆነ ይመጣል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የአፈር ለምነት እየጨመረ አሲዳማነት እየቀነሰ ይመጣል፡፡ በመሆኑ ምርቶቹ ከአፈር ጋር ተያይዞ ለሚመጡ ብዙ ችግሮች መፍትሔ ሊሆን የሚችል እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡

አራቱም ዓይነት ማዳበሪያዎች ለአፈር ለምነት በእጅጉ ተፈላጊና ጠቃሚ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ቢሆንም ለሀገሪቱም ሆነ ለአርሶ አደሩ በእጅጉ ጠቃሚና ተመራጩ ደረቁ/ጠጣሩ/ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይህን ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስፈልገውን ፋብሪካ ከውጭ ለማስመጣት ግን ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል። በዚህ ላይ ብዙ ባለሀብቶች ኢንቪስት ለማድረግ ደፍረው እንደማይገቡም አመልክተው፣ ይህ ድርጅት ግን ፋብሪካ ለመገንባት ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ፋብሪካው በአዲስ አበባ እየተገነባ ነው፡፡ ለፋብሪካ የሚያገለግሉ ማሽኖች ከቻይና የመጡ ሲሆን፣ ግንባታውም በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባም በሰዓት አራት ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ያመርታል፡፡ ሥራው በደንብ ከጀመረ በኋላ የማምረት አቅሙን በመጨመር 30ሺ ኩንታል በሰዓት እንዲያመርት ያደርጋል፡፡ በቋሚነት ለ30 ለሚሆኑ፣ በጊዜያዊነት ደግሞ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

ከጠጣር (ከደረቅ) የተፈጥሮ ማዳበሪያ ውጭ ያሉት ሌሎቹ ምርቶች እንደ ደጋፊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ለአብነት አርትራ ቴን ማዳበሪያ ፋስሊቴተር ለደረቅ ተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚውለው ተፈጥሯዊ የሆኑ የእጽዋት ውጤቶችን በአስር ቀናት ውስጥ ኮምፖስት እየሠራ ለማስገባት ይረዳል፡፡ ሁሉም ምርቶች ለሚቋቋመው የደረቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በግብዓትነት እንዲውሉ ተደርገው ከፋብሪካ ጥቅም አንጻር የተዘጋጁ ናቸው፡፡

‹‹አሁን በገበያ ላይ ያሉ ከውጭ ሀገር የሚገቡ እንዲሁም ሀገር ውስጥ የሚመረቱ በርካታ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች አሉ፡፡ በተለይ ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በብዛት በገበያ ላይ ይገኛል፡፡ በሀገር ውስጥ ብዙ ድርጅቶች ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ያመርታሉ፡፡

እነዚህ ምርቶች ግን በሚጠቀሟቸው ነጥረ ነገሮችና ጥራት ይለያሉ፡፡ ብዙ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚያመርቱ ድርጅቶች በሥራ አጋጣሚ አይተናቸዋል፤ ጥናቶችንም አድርገናል ሲሉ ዶክተር ካህሳይ፣ ‹‹የእኛን ምርት ከእነርሱ ለየት የሚያደርገው ምርቶቻቸው በኛ ልክ ተፈጥሯዊ ነጥረ ነገሮች የሌላቸው መሆኑ ላይ ነው፤ በጥራትም ቢሆን ከእኛ ሊወዳደሩ የሚችሉ አይደሉም›› ይላሉ፡፡፡

አሁን በሀገር ውስጥ የተዘጋጁት አራቱም ዓይነት ምርቶች በዋጋም ቢሆን ከሌሎች በገበያ ላይ ካሉት ተመሳሳይ ምርቶች አንጻር በግማሽ ያህል እንደሚቀንሱም ጠቁመዋል፡፡ ለወደፊት የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ጠቀሜታ እየታወቀ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሲመጣ ተፈጥሯዊ የሆኑ ምርቶች ዋጋ እየተወደደ እንደሚሄድ ካህሳይ (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡ ‹‹አሁን ገበያውን ሰብሮ ለመግባትና ህብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ ለመሆን የምርቶቹን ዋጋ በ50 በመቶ ያህል በመቀነስ ወደ ገበያው ለመግባት እናስባለን ብለዋል፡፡

‹‹ወደ ማምረት ሂደቱና ገበያው ሳንገባ ከአሁኑ ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ ነው፤ የምርት እጥረት እንዳይገጥመን እየሰጋንም እንገኛለን፤ በገበያ ላይ ምንም ዓይነት ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምርቶቹ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተሞክረው ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ አርሶ አደሮቹ ባዩት በእጅጉ መደሰታቸውን ካህሳይ (ዶ/ር) ገልጸዋል። የፋብሪካው ግንባታ እንደተጠናቀቀ ወደ ማምረቱ ሥራ በመግባት ምርቶቹን ለገበያ በማቅረብ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል ሲሉ አስታውቀዋል፤ ይህ ሥራ ለሀገር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፣ መንግሥት ለምርቶቹ ትኩረት እንዲሰጥ፣ ማህበረሰቡም ማዳበሪያዎቹን ተረድቶ ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከምርቱም በላይ ዋነኛ ዓላማችን የሀገሪቱ አፈር ለምነትና ጤናማነት እንዲስተካከል እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም ሁሉም የግብርና፣ የሳይንስና ምርምር አካላትና የሚመለከታቸው ሁሉ ትኩረት ሰጥተው አብረውን ሊሠሩ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረት እንችላለን›› ብለዋል፡፡

የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃየሎም ገብረጨርቆስ በበኩላቸው እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎችን ለማምረት እንቅስቃሴ ሲጀመር ብዙ ነገሮች ታሳቢ ተደርገዋል፤ የመጀመሪያ ትኩረት የተፈጥሮ /ኦርጋኒክ/ የሚለው ነው፡፡ ኦርጋኒክ ስንል ስለ ሰውና ስለአፈር መናገራችን ነው፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ /የአፈር ማዳበሪያ/ የአፈር ጤንነት ለመጠበቅ ይጠቅማል፡፡ የአፈር ጤንነት ለመጠበቅ ተፈጥሯዊ ምርቶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በተጨማሪም ድርጅቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት በሚወስደው ረጅም ጊዜ ላይ ለውጥ ማምጣት ችሏል። ይህንንም ለአብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ‹፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ስድስት ወራት ይፈጅ የነበረበትን ሁኔታ ወደ አሥር ቀን ማውረድ ያስቻለ አርትራ ቴን ኮምፖስትን ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህም ማንኛውም አርሶ አደር ሆነ ህብረተሰብ በየቤቱ ያለውን ተረፈ ምርት ጥቅም ላይ መዋል ያስችላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹መሬት ልክ እንደ ሰው እንክብካቤ ይፈልጋል፤ ስለመሬት እንክብካቤ ካነሳን ደግሞ ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ትልቁ ለመሬት በግብዓትነት የሚያገለግል በመሆኑ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው›› የሚለው ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ይህንን ለማድረግ የግንዛቤና የትኩረት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየጓሮው ሊሠራው እንደሚችልም አስገንዘበዋል፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ የዶክተር ካህሳይ የምርምር ውጤት የሆነ ከተፈጥሮ የአፈር ማዕድናትና እጽዋት ተዋጽኦ የሚሠራው ጸረ ተባይ /አርተራ ቤስት ሳይድ/ 14 ዓይነት የጸረ ተባይ ምርምር ውጤት ይዟል። ይህ ጸረ ተባይ እንደ ሀገር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛው በመሆኑ ወደ ማህበረሰቡ ማስፋት ይገባል፡፡ በተለይ ለአርሶ አደሩ ወይም ለአምራቹ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ግብዓት ሊሆን ይችላል፡፡

አሁን አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ የታገዝ ባይሆንም እንደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኮምፖስት/ ያሉትን እየሠራ ሲጠቀም ኖሯል የሚሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ይሄ ግን በምርምርና ፈጠራ የተደገፈ የአርሶ አደሩን ድካም ማቅለል ጊዜንና ወጪን መቀነስ የተቻለበት ነው ብለዋል፡፡

ይህም አርሶ አደሩ ብዙ ድካም ውስጥ ሳይገባ ጊዜውን ቆጥቦ እንዲሠራ እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ይሄን የምርምር ውጤት መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You