ባንኮች ራሳቸውን ለውድድር ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል!

እ.አ.አ በ2024 የባንኩ ዘርፍ ከሌሎች የፋይናንስ ዘርፎች የበለጠ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። የባንኩ ዘርፍ ከፋይናንስ ዘርፍ ጠቅላላ ሀብት ያለው ድርሻ 96.1 በመቶ ደርሷል። ይህም ማለት የኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት በባንክ ዘርፍ መረጋጋት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 32 የግል ባንኮች ተቋቁመውና በርካታ ቅርንጫፎችን ከፍተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተቀማጭ ገንዘብ፣ በብድር እና በካፒታል ያደጉት ባንኮች እስካሁን ሲሰጡ የቆዩት አገልግሎት ተመሳሳይነት ያለውና የተደራሽነትም ችግር የሚታይበት ነበር። ውድድሩም ርስ በርሳቸው ስለነበር ልቀው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም ነው።

ባንኮች እስካሁን የሰጡት አገልግሎት ሀገርን የጠቀመ ጤናማ የሚባል የፋይናንስ ስርዓትን የተከተለ ነበር። ሆኖም አሁን የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን የሚገዳደር የውጪ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅድ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ወጥቷል። እንደ ሀገር ሲታይ ይሄ ትልቅ ዕድል ነው። ይሄንን ወርቃማ ዕድል ለመጠቀም ታዲያ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸውን ማጠናከርና አቅማቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። ከተለመደው አሠራርና አካሄድ ወጥተው መወዳደር አለባቸው። ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ካፒታላቸውን ማሳደግና አቅማቸውን እየገነቡ መሄድ አለባቸው። ለዚህም ዋነኛው መንገድ ሰብሰብ ብለው መጠናከር እና ለዓለም አቀፍ ውድድር ራሳቸውን ማዘጋጀት ነው።

ባንኮች በተለያየ የስም መጠሪያ ቢደራጁም ዞሮ ዞሮ ሀብቱ የግለሰቦች ወይም የጥቂት ቡድኖች ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ነው። ይሄን የሕዝብ ሀብት ስትራቴጂክ ሆኖ መምራት ይገባል። ከተለመደው አገልግሎት ወጣ ብሎ አገልግሎቱን ማስፋት፣ ተደራሽ ማድረግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ማዘመን ከባንኮች ይጠበቃል።

በመንግስት በኩል ላለፉት ዓመታት የግል ባንኮችን የመደገፍና የማስታመም ሁኔታ ነበር። አቅማቸውን እንዲያጎለብቱም በተደጋጋሚ ጊዜ ጉትጎታ ተደርጓል። ምክክር ተካሂዷል። ከውጪ ባንኮች የሚመጣውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ለመወዳደር የሚቻለው በሁሉም መልኩ ብቁ ሆኖ መገኘት ሲቻል መሆኑ ተገልጿል። ሆኖም እስካሁን በባንኮች በኩል አንድም እርምጃ አልታየም። አሁን ግን ሁሉንም ነገር ጆሮ ዳባ ብሎ መቀጠል አይቻልም።

ይህን በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን አዋጅ ተከትሎም በቅርቡ የውጪ ባንኮች ወደሀገር ቤት እንደሚገቡ ይጠበቃል። ያኔ ቅሌን ጨርቄን ማለት ያዳግታል። እናም ብቁ ሆኖ መገኘት ተወዳድሮ ማሸነፍን ይጠይቃል። ለዚህ ራስን ዝግጁ ማድረጊያው ጊዜም አሁን ነው።

ርስ በርስ ከመፎካከር ባለፈ ኅብረት መፍጠር፤ ከመፈራራት ይልቅ መቀራረብና መመካከር ብሎም መዋሃድን ይጠይቃል። ይሄ ሲሆን ነው ለዓለም አቀፍ ውድድር በፋይናንስ አቅም፣ በአገልግሎት ቅልጥፍና በተደራሽነት እና በሌሎችም አገልግሎት አሰጣጥ ብቁና ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው።

የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ተከፈተ ማለት የውጭ ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ ይሠራሉ፤ የባንክን ዘርፍ ያጥለቀልቃሉ ማለት ባይሆንም የዳበረ ልምድ ያላቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ ብሎ ማሰብ ደግሞ ይገባል። ስለዚህ በፉክክሩ ከገበያው ላለመውጣት ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል።

የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረጉ ጉዳይ ከሦስት ዓመት በፊት ለውይይት ቀርቦ ውሳኔ የተሰጠውና በፖሊሲ የተደገፈም ነው። አሁን የአዋጁ መጽደቅ ለሀገር ውስጥ ባንኮች በጎ አስተዋጽኦ እንጂ ተጽዕኖ እንደማይኖረው፤ ይልቁንም ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና የመሥራት፣ የእንደራሴ ቢሮ እና ቅርንጫፎችን የመክፈት ሥራዎችን በማከናወን የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

የውጭ ባንኮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የብድር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማስፋት ማክሮ ኢኮኖሚውን የሚያረጋጉ ናቸው። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ባንኮች የበለጠ የመጠንከር፣ የመጎልበት እና የመፈጸም አቅም ያገኛሉ። የሀገር ውስጥ ባንኮች ዕድገትም አስተዋጽኦም ከምንጊዜውም በላይ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያስመዘገበ ያለውን ዕድገት ለማስቀጠል፤ በባንኮች ላይ ቀውስ ሲፈጠር እልባት ለመስጠት፤ የባንክ ዘርፍ የፈቃድ አሰጣጥና የቁጥጥር ማሕቀፍ ከዓለም አቀፍ አሠራር ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማስቻል የሚያግዝ ነው፡፡ በመሆኑም ይሄንን ወርቃማ ዕድል ተጠቅሞ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ራስን ማዘጋጀት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ከሀገራችን ባንኮች ይጠበቃል!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You