ከእድሜ ዘለላ ቅጥያ ከነፍስ ህላዌ ምስያ የሃቅ ስሜት ያፋፋት ሰሞነኛ የብእር ቱርፋት መቆያ እንዲሆነን ከወግ ሰበዝ ይህን ልምዘዝ::
አው አለ ጅብ … ሰማኸው? ትናንት አማኸው? ኧረ ቆይ… ጅብ ሲጮህ አፉን ከመሬት የሚተክለው ለምንድነው? የእግዜር ዙፋን እንዳይነቃነቅ፣ ጨረቃ እንዳትጠልቅ፣ ፀሐይ እንዳትወድቅ መሰለኝ፤ ለነገሩ በፈጣሪ የተገባለትን ቃል ማስታወሱም ሊሆን ይችላል:: የምን ቃል አትሉኝም? በእኔ መጀን መልሱ ይሄውላችሁ::
ለዳግም ምጽአት ምልክት ከሆኑት ውስጥ የጅብ በቀን መውጣት አንዱ እንደሆነ መቼም አይጠፋችሁም:: ሁለት ፀጉር ያበቀሉ ሰዎች ሲያስረዱ “በስምንተኛው ሺ የጅብ መፍራት፣ ይሉንታ ማጣት ነውርነቱ ይቀራል” ይላሉ::
በድሮ ጊዜ “ከአይጥ ቤት ብቅል ከድመት ቤት ቋንጣ” ሳይታጣ በፊት ጅብ አህያን ይፈራት ነበር አሉ:: ኋላ አንድ ቀን የጅብ ልጅ ይሞትና አህይት ወገኖቿን ሰብስባ ለቅሶ እንደመጣች ለእዝን ከያዙት ድርቆሽ ያቀርብላቸውና አያ ጅቦ ከፊታቸው ተገመረ:: የአህያን አበላል አይቶ ጎመጀና ምራቁን ሲውጥ ገርገጭ የሚለው ድምጽ ጆሮዋን ከጣለችበት ቅርጫት አህያን ቀና አደረጋት:: “ምነው አያ ጅቦ” አለች በድንጋጤ የጎረሰችውን እንኳን ሳትውጥ::
“አበላልሽ አስቀንቶኝ ረሃቤን ቀሰቀሰውና ምግብ አሰኝቶኝ አብሬሽ ልበላ ነበር ግን…” ብሎ ሃሳቡን በእንጥልጥል ተወው:: “ግን ምን?” አለች አህያ እንደመሽኮርመም እየቃጣት:: አያ ጅቦ ቀንዷ እንዳይወጋው መስጋቱን ቢነግራት አህያ በሳቅ እየተንፈራፈረች ቀንዷ ሳይሆን ጆሮዋ መሆኑን ገለጠችለት:: ከዚያን እለት ጀምሮ “ላታመልጪኝ አታሩጪኝ” በሚለው የተፈጥሮ ሕግ አያ ጅቦ መፍራቱን አህያ ለቅሶ መድረሱንም በይፋ ሻሩት:: ፍርሃት ብትሉትስ እንድ ነገር ትዝ አለኝ::
የአባትሽን አጥር ጅብ የፈራውን፣
ሲዞረው አደረ ልቤ ብቻውን::
ስል የዘፈንኩላት ሥልጣኔን ያሻረችኝ፣ ትጥቄን ያስፈታችኝ ስፍራሽ የምትባል ጎረቤቴ ነበረችና ከመንደራችን ድድ ማስጫ ተቀምጬ አላፊ አግዳሚው በአይኔ ስመዝን ሰቀቀን የሆነችብኝ ደማም ብቅ አለች:: እርግማኗ ምርቃት ስድቧ ሙገሳ ስለሚመስለኝ ምነው ቆንጂት በቀን ጅብ ይወጣል እንዴ? ብላት “አዎ አንዳንተ አይነቱን አህያ ሊበላ ይወጣል” አለችና ረግጣኝ አለፈች:: እነተረት አያልቅበት …
“የመውደድ ነገር ቢሰማ ጅብ፣
ልጆቹን ይዞ አጀብ አጀብ::”
ብለው የገጠሙት እሷን አይተው መሆን አለበት::
የጅብ መውደድ ከተነሳ አይቀር የእድራችን ጥሩንባ ነፊ አያ ሸንቁጤን የጉለሌው ሰካራምን ያነበቡ ሰዎች “አክትፍ አበጀን ነው” ይሉታል:: በጎመጁ ጠጅ ቤት የሚያውቁትና የብርሌ አንገት የሚያጫብጡት ወዳጆቹ የሰዓቱን መግፋት አይተው “ቤትህ ጅብ ዋሻን አልፎ አይደለም? መሽቷልኮ” ሲሉት በሶስት ብር የፍየል ጭንቅላት ገዝቶ በመጋበዝ ያላመደውን ጅብ እየተመካበት “ሸኚ አለኝ” ይላቸዋል በኩራት::
ግሪኮችም እንደ አያ ሸንቁጤ ሀተታ ተፈጥሯቸውን (ሚቶሎጂያቸውን) ሁሉ ለጅብ በመስጠት መልካም እሴቶቻቸውን ለመገንባት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። እኛ ግን በተቃራኒው ለልጆቻችን ማስፈራሪያና ለእኩይ ድርጊት ምሳሌ አድርገነዋል:: በሥራ ላይ የማይለግምን ሰው ሲሠራ አቅሙ የጅብ ነው ብለን ያደነቅነውን ያህል “የሠራ ይብላ” የሚለውን ቅዱስ ቃል ሽረን አበላሉ እንደ ጅብ ነው በማለት የሆዳምነት መልክ ኳልነው::
ለዚህ ሃሳብ ማሳያ ይሆነኝ ዘንድ አንድ ጽሁፍ ዋቢ መጥቀሱ ነገሬን ያደምቀዋል:: ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም “አዳፍኔ” መጽሐፋቸው ላይ “ጅብን መጥራት” በሚል ርእስ ያሰፈሩት ትዝብት ይህን ይመስላል:: ሸዋ በሄዱበት አጋጣሚ የበሬን ግንባር የምታክል የአንድን አርሶአደር ማሳ ሲጎበኙ አንጀታቸው ተላውሶ “ሌላ የለህም?” ሲሉ ጠየቁት:: “አለኝ ግን ጅብ ስለሚጠራብኝ አላርሰውም” አላቸው ፊቱን በኀዘን ቅጭም አድርጎ:: ማን ያውቃል … አውደ ነገሥትን ሲገልጡ በገውዝ ንፋስ ኮከብ ስር የሰፈረውን “እንደ ጅብ ሳይበላ አያድርም” የሚለውን አንብበው ይሆናል:: ትርጉሙን አንሻፈውት እንጂ በየደረሰበት ሥራ ይሳካለታል ማለቱ ነበር::
ግን ጅብ ለምን ፈሪ ሆነ? አንድ ቀን ብርሃን ለጭለማ ቦታውን ሲለቅ እቁባቱ ናፍቃው ወደ ከተማ ከሚገሰግስ ሽፍታ ጋር ተገጣጠመና ሴት ዘንድ እንደሚሄድ ልቦናው ነግሮት አያ ጅቦ በቅናት እምሽክ አደረገው:: ይመጣል ብላ ተሰናድታ ስትጠብቅ ውሽማዋ ቀርቶ እርር ኩምትር ያለችው ወ/ሮ ስትበጥስና ስትቀጥል ያደረችውን እንዝርት አሽቀንጥራ ንጋቱ የአህያ ሆድ ሲመስል እንስራዋን አንጠልጥላ ወንዝ ስትወርድ ገላዋ የተራበው ወንድ እንዳይሆኑት ሆኗል። ምንም እንኳን ኀዘኗ ከብዶ ብታነባም የቀረ አካሉን ከማንሳት ይልቅ የጅብ አስራ ማሪያምን ታሪክ ታውቃለችና ለበቀል ጥርሷን ነክሳ ተመለሰች::
ከበሮው የተሠራበት ቆዳ ያልደረቀ በመሆኑ ይሸተውና ርሃቡን ለማስታገስ እየጎተተ ሲወጣ በሩን ማለፍ አልቻለም፤ ይህን ያዩ ካህናትም “ጅብ አስራ ማሪያም” ሲሉ ደብሩን ሰየሙት::
ለአስተርዮ ማሪያም ያኖረችውን ብቅል ከተሰቀለበት አውርዳ ከሥፍራው ስትደርስ በተቀዳደደ ልብሱ ግራ እጁንና ግራ እግሩን ከፍና ብቅሉን ሰባት ጊዜ ብታዞርበት አያ ጅቦን ለተጨማሪ ግዝት ዳረገችው:: ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጅብ በሕይወት ያለን ሰው ይቅርና አስከሬን ቢሆንም ሰባት ጊዜ ዞሮ (አሽትቶ) ካላረጋገጠ በቀር ለመብላት አይደፍርም::
ሊሆን ይችላል ብዬ በማሰብ ጅብ አውድማ ውስጥ ለምን እንደማይገባ ምክንያቱን እንድትነግረኝ አያቴን ጠየኳት:: ያሲያዘችኝን የዶሮ አይን የመሰለ ጠላ እየኮመኮምኩና ያቀረበችልኝን ሰነፍ ቆሎ እያንቀራጨሁ ያስለመድችኝን የእሳት ዳር ወግ ከስሩ ስታስጨብጠኝ ለመቅለብ እዝነ ልቦናዬን አሰላሁ:: “አጉማስ ሲጣል ድግሱ ማለፍያ ነውና ጠላ እስከ ተሾመ ድረስ የማሪያም ብቅል ግዝት አያ ጅቦን “ማህረቤን ያያችሁን” ያዙረዋል እንጂ አውድማው ውስጥ ለመግባት አያሰናዝረውም” አለች ከያዘችው ዋንጫ ጠላ ጎሮሮዋን ለማርጠብ እየተጎነጨች::
ቀጠለችና “አባሲኖዳን ታውቃቸዋለህ? ስትል ጠየቀችኝ:: ፍቅር እስከ መቃብርን ማንበቤን ገልጨ በዛብህ ያስተማረበት ደብር መሆኑን ነገርኳት ከጨዋታችን ጋር ምን እንደሚያገናኘው ለመስማት ጓጉቼ:: አያቴ ሙሉ ጎጀም ፍቅር እስከ መቃብርን አንብባዋለች ሳይሆን ኖራዋለች ነው የሚባለው:: “ልክ ብለሃል” አለችና የደብተራ ቀለመ ወርቅንና የበዛብህን ዳና ተከትላ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል”፣ “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” የሚሉት ተረትና ምሳሌዎች የበቀሉበትን የአባሲኖዳን ደብር ልታስጎበኘኝ የብራና መዛግብትን ገለጠች::
“አንዲት መነኩሴ የአባሲኖዳን ጸበል የያዙበት ቅል ከእጃቸው አፈትልኮ ድንጋይ ላይ በወደቀ ጊዜ ቅሉ ሳይሆን ድንጋዩ ለሁለት ተከፈለ፤ ይህን ታምር ያዩ ሁሉ “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” ሲሉ ተረቱ:: አንድ ቀን እንደዚሁ ለአባሲኖዳ በስለት የገባውን ሙክት አንድ የተራበ ጅብ ሲከመርበት የሾለ ቀንዱ በጎሮሮው ተሰነቀረና ሞተ፤ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” የሚለው አባባልም መነሻው ይህ ሁነት ነው ይላሉ” ብላ ትንፋሽ ለመውሰድ ወሬዋን ገታች:: “በድሮ ጊዜ” እያለች ያየችውንም የሰማችውንም ስታወጋኝ የቃምኩትን ቆሎ ሳልውጥና ቆሎ ያቀረበችበትን ገበታ እንደያስኩ ከምድጃው ስር እንቅልፍ ይጥለኛል::
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም