አባቶች ሲመርቁ “ደሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ የሚል ልጅ ይስጣችሁ።” ይሉ ነበር። ለዚህ ትክክለኛው ሰው ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ መሆናቸውን ታላላቅ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸው፣ የቅርብም የሩቅም የሥራ ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ፤ እንዲሁም ታሪካቸውን ያነበበ ሁሉ የሚረዳው ነው።
የክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ታሪክ እጅግ ሰፊ እና ትልቅ በመሆኑ በዚህ ተርከን የምንጨርሰው አይደለም። ነገር ግን ታላላቆች የሄዱበት፣ የሰሩት ሥራ፣ ትዕግሥት፣ ሙያ፣ ሀገርን መውደድ እና ለእውነት መቆምን ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት እና አርአያ በመሆኑ ዛሬ ልናነሳቸው ወደድን።
አቶ ከተማ ይፍሩ በአጼ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ስመ ጥር ፖለቲከኛና ዲፕሎማት ነበሩ። በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሂደት ላይ ያሳዩት የአደራዳሪነትና የዲፕሎማሲ ጥበብ ምናልባትም በአፍሪካ ምድር እስከዛሬ ከታዩ ጉምቱ ዲፕሎማቶች አንዱ ናቸው ብንል ታሪክ የሚመሰክረው ሃቅ ነውና ማጋነን አይሆንም።
አቶ ከተማ ይፍሩ ታህሳስ 3 ቀን 1921 ዓ.ም በቀድሞው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ጋራ ሙለታ በተባለ አካባቢ ነበር የተወለዱት። አባታቸው አቶ ይፍሩ ደጀን እናታቸው ወ/ሮ ይመኙሻል ጎበና ይባላሉ። በልጅነታቸው በቄስ ትምህርት ቤት ከፊደል መተዋወቅ ጀምረው የነበሩት ከተማ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ገና በሰባት ዓመት እድሜያቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሀገር ጥለው መጀመሪያ ወደ እንግሊዝ ሶማሊላንድ ከዛም ወደ ኬኒያ ለመሰደድ ተገደዱ።
በኬኒያ ስደተኞች ከአገሬው ተወላጅ ጋር በአንድነት ተቀምጠው መማር ስለማይፈቀድ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተብሎ በተከፈተውና በቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ኃላፊነት በሚመራው ትምህርት ቤት መማር ጀመሩ።
ነጻነት ሲመለስ ከተማና ቤተሰቡ ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው ኑሯቸውን ጋራ ሙለታ አደረጉ። በአንድ ወቅት ቀዳማዊ አጼ ኃ/ሥላሴ ጋራ ሙለታን ሲጎበኙ የከተማን የወደፊት ሕይወት የቀየረ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ። የአካባቢው ሰዎች “እዚህ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ልጆች አሉ ምን ተሻለ ሲሉ አቤት አሉ” ንጉሱም ወደ አዲስ አበባ መጥተው መማር ይችላሉ ሲሉ ምላሻቸውን ሰጡ።
በንጉሱ ፍቃደኝነት ወደ አዲስ አበባ ቢሄዱም የገበሬ ልጅ ለነበሩት ከተማ የመኳንንት ልጆች በሞሉበት ትምህርት ቤት ገብቶ መማር እንዲህ በቀላሉ የሚሆን አልነበረም። ከተማ ትምህርት ቤት የመግባት እድል ተነፍጓቸው ወገን ዘመድ በሌለበት ከወታደሮች ዘንድ ተጠግተው ሲኖሩ ጉዳያቸው ከወቅቱ የጦር ኃላፊ ጀነራል መርዕድ ንጉሴ ደረሰና በሳቸው ኃይል ትምህርታቸውን ለመጀመር በቁ።
አቶ ከተማ በትምህርት ክፍላቸው ውስጥ የነበረውን የማኅበራዊ ደረጃ ልዩነት ለልጃቸው መኮንን ከተማ እንዲህ ሲሉ ነግረውታል “ንጉሱ በየጊዜው እየመጡ ተማሪዎቹን ይጎበኛሉ። መምህሩም ስም በሚጠራበት ወቅት ከስማቸው ፊት ደጃዝማች፣ ልዑል እንዲሁም ሌሎች ሹመቶች ነበሩ። ጃንሆይም ልጆቹ በእኩልነትና ያለምንም ተፅእኖ ትምህርታቸውን እንዲማሩ ቅጥያው እንዲሰረዝ አዘዙ።
አቶ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮተቤ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት ከተከታተሉ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ሚቺጋን ሆፕ ኮሌጅ ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማጥናት ያቀኑ ሲሆን፤ የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በቦስተን ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ትምህርት ተከታትለው አጠናቀዋል።
አሜሪካን አገር ሳሉ ያጋጥሟቸው የነበሩ የዘረኝነት ጥቃቶች በኋላ ላይ ላሳዩት የፓን-አፍሪካኒስት ስሜት መነሻ እንደሆነ ይነገራል። በአሜሪካን አገር ሳሉ የሶስተኛ ደረጃ ትምህርት እድል ቢያገኙም ከትምህርቱ ይልቅ ቤተሰብና ሀገራቸውን በማስቀደማቸው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ምንም እንኳን ሥራ ቢጀምሩም በተማሩት እና በእውቀታቸው ልክ የሚገባቸው ቦታና ደረጃ ሳይሰጣቸው ብዙ ጊዜ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት አቶ ከተማ ትልቅ ቅሬታን አሳድረው እንደነበር ልጃቸው መኮንን ከተማ በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
ቢዘገይም ዳሩ ሥልጣንና ደረጃው አልቀረም። የገበሬው ልጅ ከተማ ይፍሩ ከስንት የመኳንንት እና የመሳፍንት ዘር ካላቸው ሰዎች መካከል ተመርጠው የውጭ-ጉዳይ ሚኒስትር እስከመሆን ደረሱ። ከተማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥራቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ጋር እንድትቀራረብ ለማድረግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ነው።
ስለዚህ ጉዳይ አምባሳደር ከተማ በአንድ ወቀት ሲናገሩ …«… እ.አ.አ 1961 ዓ.ም ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደገባሁ የመጀመሪያ አጀንዳዬ አድርጌ የያዝኩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጋር የበለጠ የምትቀራረብበትንና የምትተባበርበትን መንገድ መፈለግ ነበር።
ይህንን ጉዳይ ለጃንሆይ ነገርኳቸው። ‹ … ፋሺስት ኢጣሊያ በወረረን ጊዜ ወደ ዓለም መንግሥታት ማኅበር ሄደው የጮሁት ብቻዎን ነበር። ያ ጊዜ መደገም የለበትም። ከአረቦች ጋር ልንሆን አንችልም፤ ከአውሮፓውያንም ጋር መሆን አንችልም። የእኛ ተፈጥሯዊ ምንጫችን አፍሪካ ስለሆነ ከአፍሪካውያን ጋር ነው መተባበር ያለብን። በዚህ ጉዳይ መግፋት አለብን። ይህን ጉዳይ ያምኑበታል ወይ?› ብዬ ስጠይቃቸው <ዋናው የእኔ ማመን አይደለም። አንተ ታምንበታለህ?› ሲሉኝ <እኔማ አምኜበታለሁ› አልኳቸው። ‹እንግዲያውስ ካመንክበት ቀጥልበት› አሉኝ … » ብለዋል።
የአቶ ከተማ ሹመት በጊዜው በወግ አጥባቂዎቹ በኩል ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሹመት ነበር። አቶ ከተማ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በመጀመሪያ የተመደቡት የጣሊያንን ጉዳይ በሚከታተለው ዲፓርትመንት ሲሆን ቀጥለውም በአሜሪካና ኤዢያ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው አገልግለዋል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሃሳብ ሲነሳ የአፍሪካ አገራት ካዛብላንካና ሞኖሮቪያ በሚል በሁለት ጎራ ተከፈሉ። የካዛብላንካው ቡድን የአፍሪካ አገራት በፍጥነት ፖለቲካዊ ውህደት ፈጽመው አፍሪካ አንድ አገር መሆን ይገባታል የሚል አቋም ሲያራምዱ፣ ሞኖሮቪያዎች ግን አንድ ከመሆናችን በፊት ለሎች ውህደቶች መቅደም አለባቸው የሚል መከራከሪያ ሃሳብ ይዘው ተነሱ።
ይህ የሁለቱ ቡድን የሃሳብ ልዩነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በፍጥነት እንዳይመሰረት እንቅፋት ፈጠረ። ኢትዮጵያ በወቅቱ የሞኖሮቪያውን ቡድን ሃሳብ ትደግፍ የነበረ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ግን ሁለቱን ቡድኖች አደራድሮ ወደ አንድ የጋራ አቋም የማምጣቱ ታሪካዊ ኃላፊነት ኢትዮጵያ ላይ ወደቀ። የዚህ ሃሳብ አመንጪ ታዲያ ጉምቱው ዲፕሎማት ከተማ ይፍሩ ነበሩ። ጃንሆይም ይህን ጉዳይ የማስፈጸሙን ኃላፊነት ለከተማ ሰጧቸው።
አቶ ከተማ ይፍሩ ይህን ከባድ እና ታሪካዊ ተልዕኮ አንግበው የአፍሪካ አገራትን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አካለሉ ተወያዩ፣ተከራከሩ፣በመጨረሻም አሳመኑና እነዛ ጎራ ለይተው ጽንፍና ጽንፍ ቆመው የነበሩ ሁለት ቡድኖች አዲስ አበባ ላይ የጋራ ጉባኤ ለማድረግ ተስማሙ። በዚህ የአቶ ከተማ ይፍሩ ከፍተኛ የመደራደር ብቃትና የዲፕሎማሲ ጥበብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዲስ አበባ ላይ ተመሰረተ።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ በኋላ ሌላ የአቶ ከተማን ሥራ የሚጠይቅ ጉዳይ ተከሰተ። የድርጅቱ መቀመጫ የት ይሁን የሚለው ሃሳብ ላይ አለመግባባት ተፈጠረ። ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ምስረታ ከነበራት ሚና አንጻር የድርጅቱን መቀመጫ ቦታ በቀላሉ ታገኛለች ተብሎ ቢጠበቅም እንደታሰበው ሳይሆን ቀረና ብዙ አገራት የይገባኛል ጥያቄ አነሱ።
በተለይም የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገራት የድርጅቱን መቀመጫ ሴኔጋል ዳካር ላይ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ። ናይጄሪያም ቦታው ይገባኛል ስትል ጠየቀች። ኢትዮጵያ ለድርጅቱ መቀመጫነት እንዳትመረጥ ዘመቻ ተከፈተባት። ይህን ሁሉ ፈተና አልፎ ኢትዮጵያ የድርጅቱ መቀመጫ አገር የማድረግ ኃላፊነት የአቶ ከተማ ይፍሩ ነበር። ይህ አይነቱ ሥራ ወትሮም የሚዋጣላቸው አቶ ከተማ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገው ኢትዮጵያን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መዲና ለመሆን አብቅተዋታል።
በአፍሪካ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶች እንዲበርዱና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረዋል። የኮንጎ ግጭት ያለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲፈታ ለፍተዋል። በመጨረሻም በኢትዮጵያዊው ሌተናል ጀኔራል ከበደ ገብሬ የተመራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ኮንጎ እንዲሰማራ ተደርጓል።
የአልጀሪያና የሞሮኮ ግጭት እንዲፈታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉትም የአልጀሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (በኋላ ፕሬዚዳንት) አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ እና የሞሮኮው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ሬዳ ጉየዲራ የጋራ ወዳጅ የነበሩት፣ ከአልጀርስ-ራባት-አዲስ አበባ የተመላለሱትና ጥረታቸው በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ፊዝጌራልድ ኬኔዲ ጭምር የተደቀነላቸው ኢትዮጵያዊው አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ናቸው።
ከደቡባዊ ሱዳን ተፋላሚዎች ጋር በር ዘግተው መክረው በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙም አድርገዋል። የናይጀሪያ መንግሥትና የቢያፍራ ተገንጣዮች ጦርነት ውስጥ በገቡበት ወቅት አምባሳደር ከተማ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ጀኔራል ያኩቡ ጎዋን እና የቢያፍራው መሪ ኮሎኔል ኦድሜንጉ ኦጁኩ ወዳጅ ስለነበሩ መሪዎቹ አዲስ አበባ መጥተው እንዲወያዩና የግጭቱ ተጎጂዎች እርዳታ እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት የድንበር ግጭት ለጊዜውም ቢሆን እንዲፈታም ትልቅ ሚና ነበራቸው።
አምባሳደር ከተማ ለአፍሪካ መሪዎች ይሰጡት የነበረው ምክር የሚዘነጋ አይደለም። ተተኪ መሪዎችን በማፍራት ረገድ ስላለባቸው ድክመት አጥብቀው ይናገሩ ነበር። በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሲዘዋወሩ የመንግሥታቱን ሁኔታ ስለተገነዘቡ በወቅቱ በብዙ የአፍሪካ አገራት ዘንድ ሲስተዋል የነበረው ሥልጣንን በኃይል (በመፈንቅለ መንግሥት) የመንጠቅ ድርጊቶች ወደ ኢትዮጵያም መምጣታቸው ስለማይቀር ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ደብዳቤ ጽፈውላቸው ነበር።
ለልጃቸው እንዲያጋሩ፤ ሕገ መንግሥታዊ የዘውዳዊ ስርዓት እንዲመሰረት የሚሉና ሌሎች ኃሳቦችን አካተው ምክር አዘል ደብዳቤ ነበር ለንጉሡ የፃፉት፤ ይህ ድፍረታቸው ግን በንጉሡ ዘንድ አልተወደደላቸውም ነበር። በዚህም ምክንያት አቶ ከተማ ለንጉሡ ይህን ደብዳቤ በጻፉ ማግስት ከውጭ ጉዳይ ተነስተው ወደ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ሚኒስትር እንዲዛወሩ ተደረገ።
እኝህ የአገር ባለውለታ ያቀረቡት ሃሳብ በንጉሡ ሳይሰማ ቀርቶ አብዮት ፈንድቶ ዘውዳዊ ስርዓቱ ላይመለስ ሲያከትም እሳቸውንም ደርግ ለዘጠኝ ዓመታት በእስር አንገላቷቸዋል። አቶ ከተማ በእስር ላይ እያሉ ጊዜያቸውን በንባብ ያሳልፉ ነበር። ከእስር ከተፈቱ በኋላም በዓላም የምግብ ድርጅ (world food program) ተቀጥረው አገልግለዋል።
ጥር 6 ቀን 1986 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቶ ከተማ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ራሄል ሥነጊዮርጊስ ሙሉጌታ፣ ዮሐንስ፣ ሚካኤል እና መኮንን የተባሉ አራት ልጆችን ማፍራት ችለዋል።
እኛም እኚህን ጉምቱ ዲፕሎማት ነፍስ ይመር እያልን፤ የአፍረካ ሕብረት መደበኛ ጉባኤውን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ለሕብረቱ መመስረት ብሎም የሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት አመሰገንን ሰላም!
ለዚህ ፅሑፍ በምንጭነት የተለያዩ ድህረገጾችን ተጠቅመናል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም