የመዘመን፤የማዘመን ዘመን

ኢትዮጵያ ሶስት ሺ ዘመን ያስቆጠረች የረጅም ታሪክ ባለቤት ናት። ዓለምን ቀድማ የተዋሀደች የስልጣኔ በር ከፋችም እንደነበረች አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አስደናቂ የኪነሕንጻ ሥራዎች ዓለም እስካሁን ያልደረሰባቸው የጥበብ ውጤቶች ናቸው።

አውሮፓውያንንም ተከትላ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ የቴሌኮም፣ የባቡር እና የዘመናዊ ትምህርት አራማጅ ሀገርም ነበረች። ይሄ ሁሉ ታሪክ እንጂ በነበራት ፍጥነት በነበረችበት የዕድገት መሰላል ወደፊት አልተራመደም፤ ወደላይ አልወጣችም።

አገዝናቸው፣ ደገፍናቸው ካልናቸው ሀገራት እኩል እንኳን መጓዝ አልተቻለም። በእድገትም ሆነ በስልጣኔ ዛሬ ያለነው ከአደጉት ሀገራት ተርታ ሳይሆን ጭራ ሆነን ነው። ይሄ በጣም የሚያስቆጭ፣ ለመናገርም የሚያሳፍር ታሪካችን ነው።

ኢትዮጵያ ትታወቅበት ከነበረበት እድገት ወጥታ ከነበረችበት ደረጃ ወርዳ ዜጎቿ ስደተኞች፣ሀገሪቱ ተረጂ፣ በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመስ ሀገር መሆኗ ዛሬም ድረስ መለያችን እንዲሆነ ነው። አሁን ጥያቄው እስከመቼ በነዚህ በምንታወቅባቸው የስም ታርጋ ታውቀን እንቀጥላለን ? እስከመቼ የአደጉት ሀገራት እጅ እያየን በድህነት እንቀጥላለን ?

ኢትዮጵያን ማዘመን፣ ኢትዮጵያን ማሳደግ፣የነበረ መለያችንን የትልቅነት መለያችንን መመለስ፣ ሰርተንና ተለውጠን ማደግ ያለብንስ በማን ነው። ለዚህም ሁላችንም መልስ መስጠት ይጠበቅብናል፤ የጋራ ምላሽ ለመስጠት መነሳሳት አለብን፤ሁላችንም ከተኛንበት መንቃት፤ ሁላችንም እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ አእምሮ አሳቢ ሆነን መቆም ያስፈልገናል።

ቂምና ቁርሾ እኔ እበልጥ፤ አንተ አትበልጥ አይነት ተራ ፉክክርን አቁመን ለመለመወጥ አእምሯችንን ክፍት ማድረግ፤ ይሄ ካልሆነ አሁንም ኢትዮጵያ ወደፊት ሳይሆን ወደ ቁልቁል ትጓዛለች፤ ተረጂ ሆና ትቀጥላለች።

ሀገር የሚገነባው በጥቂት ጠንካራ መሪዎች እና በሁሉም ዜጎቿ ትብብር እንጂ በአንድና በሁለት ሰዎች ጥረት አይደለም። በአንድና በሁለት ሰዎች ምኞትና ፍላጎት አይደለም። ይሄንን መረዳት አለብን፤ ለዚህም መስራትና መለወጥ ይጠበቅብናል።

ይህን ለማድረግ በቅድሚያ ራሳችንን ለለውጥ ማነሳሳት አለብን። እስካሁን ወደኋላ የሚጎትተንን ኋላ ቀርነታችንን ማወቅና ማመን ይኖርብናል። ከዛ ለመወጣት መዘጋጀት። አንድ ሕመምተኛ ለሕመሙ መድሀኒት የሚያገኘውና የሚፈወሰው ወደ ትክክለኛው የጤና ተቋምና ባለሙያ ሲቀርብ፣ሕመሙንም በትክክል መግለጽ ሲችል እና አስፈላጊውን ምርመራ ሲያደርግ እና ሀኪሙም ተገቢውን መድሀኒት ሲያዝለት ነው።

በግምት የሚድን በሽታ የለም። ላልታወቀ በሽታ መድሃኒት የሚያዝ ሀኪም የለም። ሀገርን መለወጥም ዝም ብሎ በምኞትና በግምት የሚሆን አይደለም። ችግሮችን በአግባቡ ማወቅና ተጋቢውን መፍትሄ ማፈላለግን ይጠይቃል። ሁኔታዎችን በደንብ መገንዘብ፤ ተገንዝቦ ለመፍትሄ በቁርጠኝነት መስራትን ይጠይቃል።

የሀገራችን የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆነኝም፤ የእድሜውን ያህል የዘመነና እና የጸና አይደለም። ለዚህም ያልተሻገርናቸው ኋላቀር አስተሳሰቦች ምክንያት ናቸው። እነዚህ ኋላ ቀር አስተሳሰቦች ከራሳችን አእምሮ ጠራርገን ማውጣት ይጠበቅብናል።

አሁን በሀገራችን የሚታዩ በርካታ ለውጦች አሉ። የምንኮራባቸው ይበል የምንላቸው አንድ ሁለት ብለን የምንቆጥራቸው ውጤቶችም እየተስተዋሉ ነው። በሀገራችን የፖለቲካ ለውጡ እንዲመጣ ገፊ ምክንያቶች ከሆነባቸው አንዱም ይሄው የኋላ ቀርነት ስብራት ነው። ከለውጡ በኋላ ቀር አስተሳሰቦችን ለመሻገር ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለውጥም አምጥተዋል። ይህንን በአይናችን እያየን፤ በአፋችን እየመሰከርን ደግሞም እየኖርነው እንገኛለን።

ለምሳሌ ያህል በምግብ ዋስትና ራሳችንን ለመቻል የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል። ተረጂ የሚለው የሀገራችንን ቅጥል ስም ለመፋቅ በተሰራው ሥራ ብዙ አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል። ዝናብ ጠብቆ የሚደረግን ባህላዊ እርሻ መስኖ ጨምሮ በበጋ እርሻ በዓመት ሁለቴና ሶስት ጊዜ ማምረት ተችሏል። አርሶ አደሩ ከድህነት ወጥቶ ልጆቹን ማስተማር፣ በኢንቨስትመንት መሰማራት ጀምሯል። ከራሱ አትርፎ መሸጥና መግዛት ደረጃ ላይ ደርሷል፤አብዛኛው አርሶ አደር ሕይወቱን ቀይሯል።

እንደ ሀገር በግብርናው ላይ በተሰራው ስንዴን ከውጪ ከማስመጣት ስንዴን ወደ ውጪ እስከመላክ የደረሰ ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴዎችን በማከል ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ከጎተራ የተረፈ ምርት ወደመሰብሰቡ ተገብቷል። እነ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ገብስ፣ በቆሎና የፍራፍሬ ምርቶች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው። በገበያ ሞልተው በየጓዳው ገብተዋል።

ኢትዮጵያም ከአፍሪካ ስንዴ አምራች ሀገሮች ቀዳሚው ተርታ ላይ ተሰልፋለች። ይሄ ከየትም የመጣ አይደለም። ማንም የሰጠን ማንም የሚነሳን አይደለም። ስለተሰራ የተገኘ ነው፤ የሥራችን ውጤት ነው፤ የመሪዎቻችን የመምራት ብቃት ውጤት ነው። ነገም በዚሁ መልኩ ከሰራን፤ በዚሁ መልኩ ከተግባባን እና በዚሁ መልኩ ካመረትን ልምድ ቀሳሚ ሳንሆን ተመክሮ አካፋይ ወደመሆን እንሸጋገራለን።

በምግብ ራስን የመቻያው መንገድ አብዝቶ ማምረት ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም። ጎን ለጎንም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የራስን ጤና በምግብ መጠበቅ፣ ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ማድረግን ጭምር ነው። የቀነጨረ ማኅበረሰብ መገለጫው የቀነጨረ አስተሳሰብ ነው። ይሄ ደግሞ መልካም ሥራን ለመስራት ቀና አስተሳሰብን ለማዳበር አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማውጣት ጭምር እንቅፋት እንደሚሆን ይታመናል። ለዚህ በተመጣጠነ ምግብ የዳበረ ሰውነትና አእምሮ ያለውን ማኅበረሰብ ማፍራት ያስፈልጋል።

ለዚህም አንዱ አማራጭ የሌማት ትሩፋት ነው። በእያንዳንዱ ቤተሰብ ገበታ ላይ መጥፋት የሌላባቸው ምግቦችን ሁሉም ከእርሻ ወደ ጉርሻ፤ ከእርሻ ወደ ገበያ እንዲያደርግ በተሰራው ሥራ የተገኘው ውጤት ይበል የሚያሰኝ ነው።

የወተት፣ የዶሮ፣ የእንቁላልና የማር ምርቶች በቤተሰብ ሌማት ላይ እንዲገኙ ኅብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ተሰርቷል።

የዶሮ ሥጋን ምርት ከነበረበት 70 ሺህ ቶን ወደ 208 ሺ ቶን፤ የወተት ምርት ከነበረበት 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሊትር ወደ 10 ቢሊዮን ሊትር ማድረስ ተችሏል። የማር ምርትን ደግሞ ከ129 ሺህ ቶን ወደ 272 ሺህ ቶን ለማድረስ ተችሏል። ዛሬ በዚህ ልክ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ነገ በመላው ሀገሪቱ ተስፋፍቶ ሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ የሚሆን ይሆናል።

እንዲሁም ሀገሪቱ ለአረንጓዴ አሻራ በሰጠችው ትኩረት ከራሷም አልፋ ለዓለም አየር ንብረት የራሷን አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች። ኢትዮጵያን የማዘመን መንገድ አንዱም ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማድረግ ተግባር ነው።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተሰሩት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ካላቸው ሥራዎች መካከል 40 ቢሊዮን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን መትከል ነው።

ከእነዚህ ውስጥ 50.4 በመቶ የደን ዛፍ ችግኞች፣ 48.6 በመቶ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ፣ የፍራፍሬ፣ የመኖና የማገዶ የእንጨት ዛፎች ናቸው።

ኢትዮጵያን ለማዘመን በተሠራው የኢንዱስትሪ ምርታማነት ሥራ አያሌ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተቻለ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከዚህ በፊት ከውጪ የሚገቡትን የቢራ ብቅል፣ የምግብ ዘይት፣ ፓስታና አልሚ ምግቦች፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የፀጥታ አባላት የደንብ ልብስ፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች (ፖል፣ ገመድና ትራንስፎርመር) በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሥራ ውጤት እያሳየ ይገኛል።

በዚህ ዘመን የሚደረግ ሀገርን የማዘመን ተግባር ያለ ዲጂታላይዜሽን ሊሳካ የሚችል አይደለም። በዚህም የተነሣ መንግሥት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚያደርገው ምርምር እና የሚያፈሰው ምዋለ ንዋይ እየጨመረ መጥቷል። ለምሳሌ የዲጂታል አካውንት ብዛት ከነበረበት 52.1 ሚሊዮን ዛሬ ወደ 205.4 ሚሊዮን ደርሷል። በዘመናዊ የክፍያ ዘዴ የተላለፈው የገንዘብ መጠን ደግሞ 9.6 ትሪሊዮን ብር በመሆን ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።

ሌላው የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ የተሠራው የዲጂታል ብድርና ቁጠባ አገልግሎት ነው። በአጠቃላይ 7.7 ቢሊዮን ብር በዲጂታል ቁጠባ ሂሳብ ተሰብስቧል። 8.4 ቢሊዮን ብር የሚያህሉ ጥቃቅን ብድሮች ደግሞ በተለመደው የባንክ ሥርዓት ብድር ሊያገኙ ለማይችሉ ዜጎች ተሰጥቷል። ኢትዮጵያን ለማዘመን በአንድ በኩል ነባር አቅሞቿን አውጥቶ የመጠቀም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለዘመናዊነት በር የሚከፍቱ ተግባራትን የማከናወን ሥራ ተሠርቷል።

በገበታ ለሸገር በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡት የቱሪስት መዳረሻዎች በተጨማሪ፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በጎርጎራ፣ በወንጪ፣ በሐላላ ኬላና በኮይሻ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተው ጥቅም ላይ ውለዋል። በገበታ ለትውልድ ደግሞ በሌሎች ሰባት የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ናቸው።

የቱሪስት መስህብ የሆኑ ነባር ቅርሶችን የማደስ የማስዋብና አገልግሎታቸውን የማሳደግ ሥራዎችም ጎን ለጎን በመሥራት ላይ ያሉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ጅማ አባጅፋር፤ የአጼ ፋሲል ሀውልት፣ የላሊበላ እና ሌሎችም ትኩረት የተሰጣቸው የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው። ይሄም ነባር አቅማችን በማውጣት ተጨማሪ ገቢዎችንና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር አስችሏል።

የኢትዮጵያን ከተሞች ለዜጎች ምቹ፣ ጤናማና አካታች ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተዛምቷል። በቅርቡ የተመረቀው የሃዋሳ የኮሪደር ልማት እዚህ ላይ የሚጠቀስ ነው። በአማራ ክልል ባህርዳርን ጨምሮ በሌሎች የክልል ከተሞችም የልማት ኮሪደር እየተሰራ ያለ ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊነት የምታደርገውን ግስጋሴ አመላካቾች ናቸው።

በልማት ኮሪደር ፕሮጀክት አማካኝነት መሠረተ ልማቶችን የማሟላት፣ ከተሞችን ፅዱና አረንጓዴ የማድረግ፣ በድህነት አኗኗር ውስጥ ላሉ ዜጎች ኢትዮጵያን የሚመጥን የመኖሪያ አካባቢዎችን የመስጠት፣ ሕጻናትና ወጣቶች ከሱስና ከአጉል ሕይወት እንዲርቁ የሚያስችሉ መዋያዎችን የማዘጋጀት፣ ማኅበረሰባዊ ትሥሥርን የሚፈጥሩ አደባባዮችንና መስኮችን የመፍጠር ሥራዎች ተሠርተዋል።

ለውጡ ካዘመናቸው ነገሮች አንዱ የፕሮጀክቶችን የሥራ ባሕል መቀየር መሆኑ ግልጽ ነው። በቀናት እና በወራት የሚጠናቀቁ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ናቸው። ለ100 ቀናት የታቀዱ ሥራዎች በቀናቸው ሰርቶ የማጠናቀቅ ባህሉ እየዳበረ መጥቷል።

ጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸው የተጀመሩ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በመጠናቀቅ አገልግሎት መስጠት ችለው አይተናቸዋል። ይሄ የሀገሪቱን በጀት ከብክነት የሚያድን የሥራ መጓተት መጥፎ ባህልን የሚሰብር ሁሉንም ሰው የሚያበረታ ነው። በዚህም ከለውጡ በፊት ቆመው እና ተበላሽተው የነበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችም በልዩ ክትትል እየተጠናቀቁና ሊጠናቀቁ ጫፍ ደርሰው ተመልክተናል።

ይሄ ሁሉ ለውጡን ተከትሎ በተሰሩ ሥራዎች በተሰጡ አመራሮች የተገኘ ውጤት ነው። ኋላ ቀር የሆኑ ልምዶቻችንን ወደ ኋላ ጥለን ከወቅቱና ዘመኑ ከሚፈልገው ቴክኖሎጂ ጋር ወደፊት መራመድን መልመድ አለብን። የመዘመኛችን ዘመን አሁን ነው፤ ለመዘመን ደግሞ ቀድመን በሀሳብ መዘመን ይጠበቅብናል። ከዘመኑት እኩል ለመዘመን አስቀድሞ ራስን ማዘመን ይገባል።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You