ዓለማዊ ስሙን እርግፍ አድርጎ 50 ስሞች ተሸክሞ ወደ ማህበራዊ ድረ ገጽ የወረደ መናኝ ነው፡፡ እንደ ገበሬ ማልዶ ተነስቶ ጥርጣ ሬን፣ ጥላቻንና በቀልን ይዘራል፡፡ የተከታዮቹን ስነልቦና ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰባኪ ነው፡፡ በአስር ማንነት ውስጥ ተሸጉጦ ምርኮኛውን ይቀርጻል፡፡እንደ አናጺ ሲያሰምር፣ ሲቆርጥ ሲቀጥልና ሲያፈርስ ይውላል፡፡ ሲቋጥር ፣ ሲተበትብና ሲያሴር ይነጋበታል፡፡ መለያየትን ፣ ማፈናቀልንና መበተንን የተካነ መሃንዲስ ነው። ምላሱ ሟርት ፣ ስድብና እርግማን ያዘንባል፡፡ ሚዛን ጠባቂ የአእምሮ ክፍሉ አብቅቶለት ሰዎች እንዲያበቃላቸው የሚታትር ብርቱ ነው። “ሶፋ ላይ ተቀምጦ መደብ ላይ የተቀመጠውን ህዝብ ተነስ ግደል የሚል ጀግና “ ነው።
እርግማን ጥርሱን ነቅሎ ያደገበት ቋንቋው ነው፡፡ ዛሬ ዕድል ፊቷን አዙራለት እንደ እርሱ ተራጋሚ አለቃ ገጥሞታል፡፡ “እኔ አንተን ምንም ማድረግ ስለማልችል የእውነት አምላክ ይፍረድብህ” ተብሎ መረገሙን እንደ ስኬት ይቆጥረው እንደሆን እንጂ ፈጽሞ አያፍርበትም። እንዲያውም ይህችን የምርቃት ጎረቤት የሆነች ለስላሳ እርግማን የሰማ ዕለት “ምጥ ለእናቷ” ብሎ ሳይተርት አይቀርም፡፡
በእነዚህ ሁሉ ብቃቶቹና በተከታዮቹ ድክመት ታግዞ ወጣቱን ከያለበት ቀስቅሶ ለሰይፍ ማግዶ ሲያበቃ የበእውቀቱ ስዩምን ግጥም በቃሉ ይወጣል፡፡
ዘማች በሌት ገሰገሰ
ዘ ሟች ሆኖ ተመለሰ
ርቃን የኖረ ሜዳ ፣ ያስክሬን ግምጃ ለበሰ
ለጀግናው ሐውልት ስሩ ፣ ጀብደኛውን ሸልሙት
እኔን ተውኝ ፣ አንሶላዬ ውስጥ ልሙት፡፡
እርሱ ያነሳሳል ፤ ይገፋፋል ፤ ያሳምጻል ፤ ያፋጃል እንጂ ሜዳው ላይ መገኘት የማይፈልግ አንሶላ ውስጥ ሟች ነው፡፡
በተለይ አገር ጥቁር ቀን ሲገጥማት አንሶላ ውስጥ ሟች ብዙ የዕድል በሮች ይከፈቱለታል። አያሌ የፈጠራ ድርሰቶችን ከጨለማው ቀን ጋር በማያያዝ ተጨማሪ ጥፋቶችን ለማከል ደፋ ቀና ይላል፡፡ ‹‹የተሳሳተ መረጃ ከሚደርሰው ማህበረሰብ መረጃ የሌለው ማህበረሰብ ይሻላል›› በሚለው ብሂል ካየነው እንዲህ ባለ የሽግግር ወቅት አገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ የማህበራዊ ሚዲያው መቋረጥ የአንሶላ ውስጥ ሟችን ክንፍ ስለሚሰብር ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ የሚያመዝን ይመስለኛል፡፡
አንሶላ ውስጥ ሟች የሚያገኘውን ጥቅም በማስላት ያሻውን አካል በጠላትነት በመፈረጅ በተከታዮቹ አዕምሮ ውስጥ ጥልቅ ጥላቻን ይዘራል፡፡ ታዲያ የዘራውን ዘር መለስ ብሎ የማያይ ሰነፍ ገበሬ አይደለም ፤ ከስር ከስር እየኮተኮተ ያሳድገዋል፡፡ አንድን ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ለማሸማቀቅ ፣ ለማግለልና ለማጥቃት ዘርን፣ ማንነትን፣ የቆዳ ቀለምንና ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን የሚሰብክ ንግግር፣ ተንቀሳቃሽ ምስል ፣ ፅሁፍና ካርቱን ማሰራጨት መደበኛ ስራው ነው፡፡
ዜጎችን ከማፈናቀል፣ የጅምላ ጥቃትን ከማድረስና ከዘር ማጥፋት እኩይ ተግባራት ጀርባ አንሶላ ውስጥ ሟች አለ፡፡ ነገር ግን እዚህ ደረጃ የደረሰ ጥፋት ማድረስ የሚችለው የኛን ትብብር ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ እኛ ካልፈለግነው፤ ካልተከተልነውና ካልታዘዝነው ህልሙ ይጨነ ግፋል … ምኞቱ ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል። እዚህች ጋር አንድ ተረት ብተርት ሸጋ ነው፡፡
በመጥረቢያ እየደረሰባቸው ያለው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በአንድ ወቅት ዛፎች ሁሉ ስብሰባ አድርገው ነበር። ዋርካ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፎ መድረኩን ለውይይት ክፍት ከማድረጉ አንድ ጎልማሳ ጥድ “ችግር ላይ ነን” ሲል ንግግር ማድረግ ጀመረ፡፡ “የኛ የዛፎች ቁጥር እየተመናመነ መጥቷል፡፡ መጥረቢያዎች ቆራርጠው እየጣሉን ነው፡፡ የሰው ልጆች ህይወት ቀላል እንዲሆን ጠላታችን መጥረቢያ ተባባሪ በመሆኑ መኖር ከባድ እየሆነብን ነው። መጥረቢያን ሁላችንም ማጥፋት አለብን !” አለ፡፡ ግራር ግራ በመጋባት ውስጥ ሆኖ “ጥድ ያቀረበው ሃሳብ ጥሩ ነው ነገር ግን እንዴት አድርገን ነው መጥረቢያን የምናጠፋው?” ሲል ጠየቀ፡፡
ባህርዛፍ መጥረቢያን በተመለከተ በቀረበው ሃሳብ አለመስማማቱን ለመግለጽ ቅርንጫፎቹን ካወዛወዘ በኋላ “መጥረቢያ የኛ ጠላት አይደለም” ሲል በስብሰባው የተገኙት አብዛኞቹ ዛፎች አጉረመረሙ። ባህርዛፍ ንግግሩን በመቀጠል “መጥረቢያ የተሰራው ከብረት ነው፡፡ እጀታው ግን ከእኛ የተገኘ እንጨት ነው፡፡ ተጣሞ ያደገ ዛፍ ነው ለመጥረቢያ እጀታ የሚሆነው፡ ፡ ሁላችንም ቀጥ ብለን ብናድግ መጥረቢያዎች ለእጀታ የሚሆን ጠማማ እንጨት አያገኙም፡፡ ቀጥ ብለን ስናድግ ነው በመጥረቢያ ከመቆረጥ የምንተርፈው ፤ እኔ በበኩሌ ከዚህ በኋላ ቀጥ ብዬ አድጋለሁ” አለ፡፡ ባህርዛፍ ይህን ቃሉን ጠብቆ ፣ ቀጥ ብሎ ማደጉን ቀጠለ፡፡ ሌሎች ዛፎች ግን የባህርዛፍን ፈለግ ሳይከተሉ ጠማማ ግንድና ቅርንጫፍ ሆነው አደጉ፡፡ መጥረቢያም ዛፎችን መቁረጡን ቀጠለ፡፡ በሌሎች ዛፎች ተጣሞ ማደግ ምክንያት ምስኪኑ ባህርዛፍም ከመጥረቢያ ማምለጥ ሳይችል ቀረ፡፡
እኛም ልጆቻችንን ፍቅርን መተሳሳብንና አብሮነትን እያስተማርን በኖሩ ባህላዊ እሴቶቻችን ታንጸው እንዲያድጉ ስናደርግ ነው ለዘለቄታው ከአንሶላ ውስጥ ሟች ሰይፍ የምንድነው፡፡ አሁን የተደቀነብንን አደጋም መቀልበስ የምንችለው የአንሶላ ውስጥ ሟችን ገጽና ፕሮግራም እየተከታ ተልን የሚያሰራጨውን በጥላቻ የተሞላ የፈጠራ ወሬ ከመቀባበል ስነቆጠብ ነው፡፡ ማንኛውንም መረጃ ትክክለኛነቱን ሳናጣራ ለሌሎች ካጋራን ግን ለመጥረቢያው እጀታ በመሆን ራሳችን ሰለባ መሆናችን ሳይበቃ ለአያሌ ንጹሃን አካል መጉደልና ህይወት መጥፋት ምክንያት እንሆናለን፡፡
መንግስትም የእርግማንን ልምጭ አስቀምጦ ግብፅንና አውስትራሊያን ከመሰሉ አገራት ተሞክሮ በመውሰድ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ለመቆጣጠር ጠንካራ ህግ ማውጣትና ከአገራት ጋር ስምምነት በማድረግ አንሶላ ውስጥ ሟችን ተጠያቂ ለማድረግ መስራት አለበት፡፡
የተቃዋሚዎችን ድምፅ ለማፈን ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን ሲገድብ የኖረ መንግስት “የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የጥላቻ ንግግር ህግ አወጣሁ” ሲል ህጉ ለፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሳሪያነት ሊውል ይችላል የሚል ጥርጣሬ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን የጥላቻ ንግግር ህግ የመናገር መብትን ከመገደብ ይልቅ ሰዎች የሚያሰራጩትን መልዕክት እንዲያጤኑት የሚያደርግ ነውና ጥርጣሬውን ወደጎን ብሎ ለተፈጻሚነቱ መስራት ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ያደርጋል እላለሁ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011
የትናየት ፈሩ