ጅማ፡- አሁን ላይ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያን የማይቻለው ዳገት ወደኋላ መመለስ ብቻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለማልማት የሚመጡ ባለሀብቶች ሰላምን በማረጋገጥና ምርታማነትን በማጠናከር ከጎናቸው መሰለፍ እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ፣ ከእንግዲህ በኋላ ወደኋላ መመለስን፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝን፣ ከልማት ውጪ በድህነት መኖርን የሚሸከም ጫንቃ የላትም፡፡ በመሆኑም የጦርነት ወሬ፣ የስድብና የጭቅጭቅ ወሬ በእጅጉ የሚያሰንፍ ስለሆነ፤ ከዚህ ተግባር መቆጠብና ፍቅርን እየዘሩና መደመርን እያስተማሩ ኢትዮጵያን ማላቅና ከፍ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ለውጡ የብቻ ሩጫ ሳይሆን የጋራ ማራቶን እንደመሆኑ፤ ፈጥኖ ለመቅደም ሳይሆን ረጅም ርቀትን አብሮ በመሮጥ ብዙ ሰዎችን ይዞ ወደ ተሻለ ደረጃ የማድረስ ሩጫ መሆኑን ተገንዝቦ መራመድን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም ከሥራና ከሙያ ባልደረባው ጋር መደመር ይጠበቅበታል፤ አለፍ ሲልም በአገራችንና ከዛም ባሻገር ከሚከናወኑ በጎ ነገሮች ጋር ሁሉ በመደመር የላቀ ነገር ለመስራት ራስን ማዘጋጀት ይገባል፡፡ «ስንደመር ለብቻችን የማንችላቸውንና የሚቻል የማይመስሉን ነገሮች ማድረግ ያስችለናል፡፡ በመደመር የዛሬ ችግሮቻችንን ለነገ ስኬታችን ዕድል ይሆንልናል፡፡ ዕድል ደግሞ የስኬት በርና ድልድይ ነው›› ሲሉም ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ወጣቶችና አገር ተረካቢዎች አዲስ የጉዞ ምዕራፍ የሚጀምሩ እንደመሆኑ፤ በቀጣዩ ምዕራፍ ህዝቡ የሚመርቃቸው፣ አገር የሚኮራባቸው፣ ወላጅ የሚመካባቸው፣ መንግሥት የሚተማመንባቸው መሆን እንደ ሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀላሉን ሳይሆን ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ፤ በምቹው ሳይሆን በፈታኙ ጎዳና ላይ ቀና ብሎ መሄድ፤ የቅርቡን ብቻ ሳይሆን የሩቁን መመልከት፤ ወደኋላ ሳይሆን ወደፊት መራመድ፤ መበጣጠስ ሳይሆን መደመርን በውስጣቸው ማኖር፤ ማነስ ሳይሆን መስፋት፣ መፍረስ ሳይሆን ማደግ ለኢትዮጵያውያን የሚገባን መሆኑን በጽኑ ማመንም ይገባል፡፡ የማይቻለውን በማብሰልሰል ሀሞትን ማፍሰስም አይገባም፡፡ ይህ ሲሆን በኢትዮጵያ አሁን የማይቻለው ዳገት ከእንግዲህ ወደኋላ መመለስ ብቻ ነው፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ አገሩና ጊዜው ለለውጥ ዝግጁ ነው፤ ህዝቡና ምድሩ ለመደመርና በእምርታ ከችግር፣ ከጉስቁልና፣ ከግርፋት፣ ከስድብ፣ ከመናናቅ በመውጣት በእኩልነት የሚኖርባት በእኩልነት የሚጠቀምባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በማኮብኮብ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ምን እንደምናደርግ ዓለም በሞላ ወደ እኛ እያየ ነው፡፡ እናም ይሄንን ተገንዝቦ በጋራ ተደምሮ ለውጡም መምራትና ለዓለም ፈርጥ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ እናም የዛሬው ችግር የነገው ህልማችን እውነተኛነት ማረጋገጫና መፈናጠጫ ነው፡፡ እዚህም እዚያም የሚሰሙ ጩኸቶች፣ ረብሻዎች፣ ፀቦችና መፈናቀሎች፤ ጃፓን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አመድ ሆና ደግማ ለመነሳት ስንቅና ጉልበት እንደሆናት ሁሉ ኢትዮጵያም ዳግም ታላቅ ለመሆን መነሻ እንጂ መቀበሪያችን አይሆንም፡፡
ኢትዮጵያውያን በድህነትና በችግር መኖር፣ በራሳቸው መንግሥት መገረፍና መበደል አዲሳቸው አይደለም፤ ለእኛ አዲስ የሆነው ነገር ችግርና ድህነትን ንቆ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መርቶ በዱላ ሳይሆን በምርጫ የሚያምን ማህበረሰብ ፈጥሮ ካሸነፍክ በቅንነት ማገልገል፤ ከተሸነፍክ በታማኝነት ማስረከብ የሚችል ጀግና ማህበረሰብ ያስፈልገናል፡፡ በምርጫ ለማሸነፍና ለመሸነፍ፣ ህዝቡን ለማልማትና ለማሳደግ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በእኩል ዓይን ለማየትና ለማገልገል፣ መገንጠል መገነጣጠል ሳይሆን፤ መስፋት፣ መግዘፍ፣ ማደግ ያስፈልገናል ነው ያሉት፡፡
በመድረኩ የሱዳንና የጂቡቲ ፕሬዚዳንቶች የተገኙ ሲሆን፤ አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ዘላለማዊ ይሆን ዘንድ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ እና ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር በመሆን የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው ሲከፍቱ እንደገለጹት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ለማልማት የሚመጡ ባለሀብቶች ሰላምን በማረጋገጥና ምርታማነትን በማሳደግ ከባለሃብቶች ጎን መሰለፍ ይገባል፡፡
መንግሥት ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት የሚያደ ርገው ጥረት እንዲሳካ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ወሳኝነት እንዳለው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ የአካባቢው ወጣቶች ቀንና ሌሊት በመስራት ቴክኖሎጂዎች መቅሰምም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፤ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአገሪቱና ለክልሉ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ተጠቃሚ ለመሆን ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የፓርኩን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ ለሥራ ወደ አካባቢው የመጡ ባለሙያዎችንና ባለሀብቶችን ተንከባክቦ መያዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ለአገር ዕድገት ሰላም ትልቅ ዋጋ እንዳለው የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለህግ የበላይነትና ለሰላም መረባረብ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ለሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርና ለጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ የአካባቢው ነዋሪዎች ሽልማት አበርክተዋል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተጠናቀቀው ኢንዱስትሪ ፓርኩ 150 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ይቀረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ወንድወሰን ሽመልስና ጌትነት ምህረቴ